Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክኦባማ ስለዴሞክራሲ አልተናገረምን?

ኦባማ ስለዴሞክራሲ አልተናገረምን?

ቀን:

ኦባማ ኬንያንና ኢትዮጵያን ጐብኝቶ ወደ አገሩ ተመልሷል፡፡ ጉብኝቱ ታሪካዊ ነበር፡፡ በሥልጣን ላይ እያሉ ኢትዮጵያን የጐበኙ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የአገራቱን ከ100 ዓመታት በላይ የቆየ ግንኙነት ላሰበ ጉብኝቱ የራሱ የሆነ አዎንታዊ አንድምታ አለው፡፡ ኦባማ ኬንያንና ኢትዮጵያን እንደሚጐበኙ ከተገለጸበት ጊዜ ጀምሮ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎች መነሳታቸውን አስተውለናል፡፡ በውጭ አገር ያሉ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ፕሬዚዳንቱ በዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት አከባበር በጐ መዝገብ የሌላቸውን አገሮች መጐብኘታቸው አገራቸው ለዴሞክራሲያዊ መሠረታዊ መርሆች ያላትን የላላ አቋም ያሳያል በሚል እንዳይጐበኙም የወተወቱ አልጠፉም፡፡ በዚህ ረገድ የሚቀርቡት ትንተናዎች አገሮች ከዴሞክራሲና ከሰብዓዊ መብት ያለፈ በሌላ ዘርፈ ብዙ መስኮች ግንኙነት የማይኖራቸው ወይም የሌላቸው ያስመስለዋል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት አቋምንም ብንመለከት እጅግ የባሰ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግር ያለባቸውንም አገሮች ፕሬዚዳንቱ ግንኙነታቸውንም ጉብኝታቸውንም አላቋረጡም፡፡ በርማ፣ ኢራን፣ ቻይና ለዓይነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አቅጣጫው እየጐበኙ እየተነጋገሩ መፍታት በርቀት ተቀምጦ ከማውገዝም የተሻለ ይሆናል እንደማለት ሳይሆን አይቀርም፡፡

ፕሬዚዳንቱ ሁለቱን አገሮች (ኢትዮጵያንና ኬንያን) በጐበኙበትም ወቅት ብዙዎች ዋናው አጀንዳ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎች ሊሆን እንደሚችል ጠብቀዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከአገሮቹ የሁለትዮሽ ምክክር በኋላ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተቃዋሚዎች ፕሬዚዳንቱ በአገሪቱ የሚታየውን የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ችግር ተቃዋሚዎችን ጨምሮ ከመምከር ይልቅ ለገዥው ፓርቲ በዴሞክራሲ ሒደት መመረጡን በማወጅ ምስክርነት ሰጥተዋል በሚል አለመርካታቸውን ገልጸዋል፡፡ በውጭ አገር ያሉ አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ፕሬዚዳንቱ ለዴሞክራሲያዊ መርሆች ተገቢውን ቦታ ባለመስጠት በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ እንዲቀጥል እውቅና የሰጠ ጉዞ ስለመሆኑ በተቃውሞ ጽፈዋል፡፡

የፕሬዚዳንት ኦባማ የኢትዮጵያ ጉዞ በሦስት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ያተኮረ እንደነበር በገለጻውም፣ በዝግጅቱም ወቅት ተረድተናል፡፡ የንግድና ኢንቨስትመንት፣ የደኅንነትና ሰላም ግንባታ እንዲሁም ዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት አያያዝ ናቸው፡፡ በቤተ መንግሥት ከተደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ለመረዳት እንደሚቻለው የሁለቱ አገሮች መሪዎች በሦስቱም ነጥቦች ላይ በዝርዝር መምከራቸውን ሲሆን፣ ስለዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት በግል በስፋት መነጋገራቸውን ከመግለጽ ባለፈ በይፋ የተገለጸ ምስጋና ወይም ውግዘት አልተመለከትንም፡፡

ኦባማ በቅኔ መልክ “I believe that when all voices are being heard, when people know that they are included in the political process that makes a country stronger and more successful and more innovative” በማለት መናገራቸው በሁለቱ መሪዎች ውይይት ጊዜ ስለዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት መነጋገራቸውን ግን ለመገናኛ ብዙኃን በዝርዝር የቀረበ ነገር አለመኖሩን ያመላከተ ነው፡፡ በጥያቄና መልስ ክፍለ ጊዜ ፕሬዚዳንቱ ከፎክስ ኒውስ ጋዜጠኛ ኬቨን ኮርክ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታና የኢኮኖሚና የደኅንነት የአሜሪካ ፍላጐትን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ማስተናገድ ይቻላል ወይ? ተብለው ተጠይቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱም ለጥያቄው ውስጠ ወይራ የሆነውን መልሳቸውን ሲሰጡ ‹‹ከአገሮቹ ጋር የጋራ በሆኑ ጉዳዮችና ፍላጎታችን ላይ አብረን እንሠራለን፡፡ ከቻይናና ከሌሎች አገሮች ጋር በመረጃ ነፃነትና በመሰብሰብ መብት ላይ ያለን አስተሳሰብ ባይመሳሰልም መነጋገሩን እንቀጥላለን፡፡ ይህ የውጭ ፖሊሲያችን አካል ነው፤›› በሚል አገራቸው በኢትዮጵያ ላይ በየዓመቱ የምታወጣው የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ቢኖርም በመነጋገር ወደፊት ማሻሻል እንደሚቻል የሚያምኑ እንደሆኑ መረዳት ይቻላል፡፡

ዴሞክራሲንና ሰብዓዊ መብትን በተመለከተ ፕሬዚዳንት ኦባማ በዝርዝር የተናገሩት ለአፍሪካ መሪዎች ባደረጉት ንግግር ነው፡፡ በቤተ መንግሥቱ ከተደረገው ውይይት በላይ በአፍሪካ ኅብረት ፕሬዚዳንቱ ያደረጉት ንግግር በቀጥታ ለሕዝብም የደረሰ፣ ለዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሰፊ ቦታ የሰጠ ነው፡፡ ሰሚ ካለ አገራችንን ጨምሮ ለሁሉም የአፍሪካ አገሮች የአኅጉሪቱን ችግሮች በግልጽና በማስረጃ በመግለጽ አብራርተዋል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ አንዳንዶች ፕሬዚዳንቱ ስለንግድና ደኅንነት ተናግረው ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብትን አጽንኦት ሳይሰጡ ሄደዋል ለሚለው ትችታቸው ተገቢ መልስ የሰጠ ይመስላል፡፡ እንደ ጸሐፊው እምነት በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ያደረጉት የፕሬዚዳንቱ ንግግር ለአፍሪካ መሪዎችና ለአፍሪካውያን የዴሞክራሲንና የሰብዓዊ መብትን መርሆችና አፈጻጸማቸውን ሀሁ ያስተማረ ትንተና ነበር፡፡ የንግግራቸውን የተወሰኑ ክፍሎች በማንሳት ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን ጨምረው በዴሞክራሲ ላይ የሰጡትን ትችት እንመልከት፡፡

የሙስና ነቀርሳ መስፋፋት

እንደሚታወቀው በማንኛውም ዴሞክራሲን እከተላለሁ በሚል አገር ኅብረተሰቡ ከልማት ተጠቃሚ እንዳይሆን የሚያደርገው ሙስና ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው አፍሪካውያን ሕፃናት ትምህርት እንዳያገኙና የሥራ ዕድል ለወጣቱ እንዳይደርስ የሚያደርገው ሙስናን ‹ነቀርሳ› በሚል የገለጹት ሲሆን፣ አፍሪካውያን ችግሩን ራሳቸው እንዲቀርፉ አሳስበዋል፡፡ አንድ አፍሪካዊ ንግድ ለመጀመር ወይም ትምህርት ለመማር ጉቦ የሚጠየቅ ከሆነ ይህ ‹አፍሪካዊ ዘይቤ›› አይደለም በማለት በሁሉም አገሮች ሙስና ቢኖርም በአፍሪካ ያለው የወጣቶች ሥራ እንዳይፈጠር፣ ትምህርት ቤትና ሆስፒታል እንዳይሠራ የሚከለክል በመሆኑ የከፋ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በኬንያ ባደረጉት ንግግር የችግሩን አስከፊነት በማስረጃ አቅርበዋል፡፡ በቅርቡ የተደረገ ጥናትን በመጥቀስ በኬንያ በየዓመቱ የሚፈጸመው ሙስና 250,000 ኬንያውያንን የሥራ ዕድል ያሳጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሙስና ለተዘፈቁት ብዙ የአፍሪካ መሪዎች ኦባማ ሙስና ዴሞክራሲን ያቀጨጨና ሕዝብን በልማት እንዳይጠቀም ያደረገ መሆኑን መግለጻቸው የጉብኝታቸው አንዱ አዎንታዊ ሥራ ነው፡፡

የዴሞክራሲ መርሆች እንዲከበሩ ጠይቀዋል

ፕሬዚዳንቱ የአፍሪካ ዕድገት በዴሞክራሲ ላይ ሊመሠረት እንደሚገባ በመግለጽ አፍሪካውያን እንደ ሌሎች ሕዝቦች ሁሉ በአገራቸውና በሕይወታቸው የሚፈጸሙትን ኩነቶች የመቆጣጠር የክብር መብት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ፣ የመናገር መብት፣ የመረጃ ነፃነት መብትና የመሰብሰብ መብት የዴሞክራሲያዊ መርሆች አካል በመሆናቸው በአፍሪካ እንዲከበሩ ጠይቀዋል፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች የዴሞክራሲን መሠረት መገንባት በመጀመራቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባ በመግለጽ ለብዙኃኑ አፍሪካውያን ግን መደበኛ ምርጫ ከመደረጉ ውጪ የእውነት ዴሞክራሲ የራቀ መሆኑን በንግግራቸው እንደሚከተለው ገልጸዋል፡፡ “I have to proclaim, democracy is not just formal elections. When journalists are put behind bars for doing their jobs or activists are threatened as governments are crack down on civil society then you may have democracy in name but not in substance” በማለት ጋዜጠኞችን ለሚያስሩ፣ የሲቪል ማኅበራትን በዴሞክራሲያዊ ሥራ እንዲሳተፉ ለሚከለክሉ መንግሥታት ልክ ልካቸውን ነግረዋል፡፡ ይህ ንግግር አገራችንን አይመለከትምን? እንደሚመለከት ለማስረዳት ከዚህ ሐሳብ ጋር አያይዘው ፕሬዚዳንቱ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት ንግግር ያለ ሁከት ምርጫ ማድረግ የዴሞክራሲ መጀመሪያ መሆኑን እንደገለጹ ጋዜጠኞች በነፃነት ካልሠሩና ተቃዋሚዎች በምርጫ ቅስቀሳ ካልተሳተፉ አገሪቷ የሕዝቧን አቅም በመጠቀም ዴሞክራሲዋን ማሳደግ እንደማትችል ገልጸዋል፡፡ ሰሚ ካለ ችግሩን በግልጽ ተናግረው ሄደዋል፡፡

ሰብዓዊ መብትና ሕገ መንግሥታዊነት

ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ሰብዓዊ መብት ሰው ከመሆን የሚገኝ ተፈጥሮአዊ መብት እንጂ የምዕራባውያን ሐሳብ አለመሆኑን በማስመር አፍሪካውያን በእኩልነት፣ በክብርና በነፃነት የመኖር መብታቸው ሊከበር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካውያን ዕድገት በሰብዓዊ መብት መከበር ላይም የሚመሠረት መሆኑን አውቃችሁ የዜጐቻችሁ በተለይም የሴቶችንና የሕፃናትን ሰብዓዊ መብት ለማክበር ሥሩ ሲሉ በአጽንኦት መሪዎቹን መክረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አንዳንድ አፍሪካዊ ባህሎች በጠንካራ ሞራል ላይ እንድንመሠረት የሚያደርጉ በመሆናቸው ይዘናቸው ልንቀጥል እንምንችል በመግለጽ ከዕድገት ወደኋላ የሚያስቀሩንን ልማዶች የሴት ልጅ ግርዛትና ያለዕድሜ ጋብቻን የመሰሉን ልማዶች ማስቀረት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ የጸሐፊው ፍርኃት ፕሬዚዳንቱ ሰብዓዊ መብትን መነሻ በማድረግ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን ዲስኩር ሊጀምሩ መስሎት ቢጨነቅም አፍሪካ መሆኑን በአግባቡ ተረድተው ዝምታን መርጠዋል፡፡ በቅርቡ በአገራቸው ፍርድ ቤት የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ እውቅና ሲያገኝ ደስታቸውን እንደገለጹ ሁሉ አፍሪካንም ለመበከል አለመነሳታቸው ያስመሰግናቸዋል፡፡ ድርጊቱ ወንጀል በሆነባት፣ ምንም የሞራል ውድቀት መነሻ በማይሆንባትና ባህሎቿና የተለያዩ ሃይማኖቶች የሚጸየፉትን ድርጊት የሰብዓዊ መብት አድርጎ ለማቅረብ የሚያስችል ከባቢ አየር አለማግኘታቸው ፕሬዚዳንቱን ተስፋ ሳያስቆርጣቸው አልቀረም፡፡ በኬንያ ባደረጉት ንግግር ጾታዊ አመለካከትን (Sexual orientation) መሠረት አድርጐ የሚደረግ መድልኦ እንዲቀር ለማሳሰብ ቢጥሩም ኡሁሩ ኬንያታ ‹‹ይህ እኛን የሚመለከተን፣ ኬንያውያንን የሚያሳስብ ችግር›› ባለመሆኑ እንዲተውት መክረዋቸዋል፡፡

ከሰብዓዊ መብት ጐን ለጐን ኦባማ ባነሱት የሕገ መንግሥታዊነት (Constitutionalism) መርህ አፍሪካውያን መሪዎች ለዘመናት በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል እንዲያቆሙና ብዙ ተስፋ ላላቸው ወጣት መሪዎች ሥልጣን እንዲለቅቁ መክረዋል፡፡ የራሳቸውን ተሞክሮ በማንሳት ‹እኔ ለሦስተኛ ጊዜ ብመረጥ አሸንፋለሁ፣ ሥራውንም እወደዋለሁ፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግሥቱ አይፈቅድልኝም፡፡ ሕግ ሕግ ነው፡፡ ፕሬዚዳንትም ቢሆን ከሕግ በላይ አይደለም፤›› በሚል ሥልጣን ሙጭጭ ለሚሉ የአፍሪካ መሪዎች ሥልጣን በሕግ መሠረት ከአንዱ ወደ ሌላው እንዲተላለፍ የብሩንዲን ምሳሌ በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላና ጆርጅ ዋሽንግተን በሥልጣን በነበሩበት ጊዜ በሠሩት ሥራ ሳይሆን ሥልጣናቸውን ለተተኪው በሰላም በማስተላለፋቸው ለዘመናት ሲወሱ እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡ የሥልጣን ጉዳይ የሕይወት መጨረሻ ለሚመስላቸው ብዙ የአፍሪካ መሪዎች የሚዋጥ ባይሆንም ኦባማ ግን መናገር ያለባቸውን እውነት ለአኅጉሪቱ መሪዎች ተናግረው ሄደዋል፡፡

ኦባማ ከሄዱ በኋላስ?

ኦባማ በአፍሪካ ኅብረት ያደረጉት ንግግር ታሪካዊና አሜሪካ በአፍሪካ ላይ ልትከተለው ያሰበችውን መርሐ ግብር የገለጠ ነው፡፡ ዴሞክራሲንና ሰብዓዊ መብትን በተመለከተ ፕሬዚዳንቱ አፍሪካውያን በክብር፣ በሕይወትና በነፃነት የመኖር መብታቸውን አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካ መሪዎችን ዴሞክራሲን በስም ብቻ እንዳይከተሉ፣ ከሥልጣን በሰላም እንዲወርዱና የራሳቸውን ሕገ መንግሥት እንዲያከብሩ፣ ከሙስና ርቀው ለወጣቶቻቸው ተስፋ እንዲሠሩ፣ የዜጐችን የመናገር፣ የመረጃ ነፃነት፣ የመሰብሰብና የሴቶችንና የሕፃናትን መብት እንዲያከብሩ በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡ በአፍሪካ ያሉትን ችግሮች በዝርዝር ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካ መሪዎችም በእያንዳንዱ ንግግራቸው አጨብጭበዋል፣ አሜን ይሁንልን ብለው ተቀብለዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የንግድና የደኅንነት ጉዳዮችን ያህል አይግነን እንጂ በሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ ላይም እንደሚገዳቸው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት አሳይተውናል፡፡

ኦባማ የወከሉት አሜሪካን እንደሆነ ሁሉ የየአገሮቹ መሪዎች የወከሉት የአገራቸውን ሕዝቦች ነውና በአደባባይ የገቡትን ቁርጠኝነት በቀጣዮቹ ወራት ሊያሳዩን ይገባል፡፡ የእኛው ጠቅላይ ሚኒስትርም ኬቨን ኮርክ ኢኮኖሚያችሁ ያደገውን ያህል አገሪቷ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ትታገሳለች የሚል አመለካከት አለ እርስዎ ምን ይላሉ? ብሎ ለጠየቃቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ ‹‹አገራቸው ለዴሞክራሲ ጀማሪ  መሆኗን በመግለጽና ያለብንን ገደቦች ስለምናውቅ ለሕዝባችን የተሻለ ለመሥራት እንተጋለን፤›› ብለዋል፡፡ ይህ መንግሥት ያለበትን ቀጣይ ሥራ ያወቀና የተገነዘበ መሆኑን አመላካች ነው፡፡

የአንዲትን አገር ዴሞክራሲያዊነት ማጠናከርና የሰብዓዊ መብትን ሁኔታ ማሻሻል በዋናነት የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ መንግሥት ጀማሪ ዴሞክራሲያዊነትን ሁልጊዜ እንደመከላከያ ሳይቆጥር በተጨባጭ ሁኔታዎች እንዲለወጡ መሥራት ይጠበቅባታል፡፡ የአሜሪካ ድርሻ ከዚህ አንፃር እንደ ጓደኛና አጋር በመሆኑ ክፍተቱን ለመሙላት ብቻ እንደሚሠራ መጠበቅ ተገቢ ነው፡፡ ኦባማ የአገሪቱ ዴሞክራሲ ለውጥ የለውምና አሻሽሉ፣ የበጐ አድራጐትና የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ የዜጐችን የሰብዓዊ መብት ስለሚገድብ ለውጡ፣ አፈጻጸሙንም ከሰብዓዊ መብት ጋር እንዳይጣረስ ሥሩ፣ የታሰሩት ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እንድትፈቱ፣ ወዘተ የሚል መግለጫ እንዲሰጡ የጠበቁ ወገኖች ትክክለኛ አቋም እንዳልነበራቸው   ጸሐፊው ያምናል፡፡ ቻይና ባለችበት ዓለም አንዳንዴ ለአሜሪካ ከዴሞክራሲ በላይ ንግድ ሊያሳስባት ይችላል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ሽብርተኛ ባለበት ዓለም ደግሞ ከዴሞክራሲ በላይ ደኅንነት ሊያሳስባት ይችላል፡፡ ያም ሆኖ ግን የአሜሪካ መንግሥት በየጊዜው ስለአገራችን የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ የሚያወጡት ሪፖርት ኦባማም የሚያውቀው፣ በጽሑፍም የሚገኝ በመሆኑ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ሁኔታው በአገራችን እንዲሻሻል በቀጣይነት ተፅዕኖ አያደርጉም ማለት ሞኝነት ነው፡፡ በአሁኑ ጉዞአቸውም ቢሆን ፕሬዚዳንቱ በግል ከተናገሩት በተጨማሪ በአደባባይ ምርጫ ማድረግ ብቻ ዴሞክራሲያዊነት ባለመሆኑ የተቃዋሚ ድምፆች እንዲሰሙ፣ ጋዜጦችና የሲቪል ማኅበራት ተሳትፎ እንዲጨምር አሳስበው ሄደዋል፡፡

አገራችን ይህን አጋጣሚ እንደ በጐ ዕድል በመጠቀም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ለማሻሻል የሚያስችሉ ዕርምጃዎች በቀጣይነት እንደምትወስድ ተስፋ ማድረግ የዋህነት አይሆንም፡፡ ምንም ተቃዋሚ ፓርቲ ባልተወከለበት መጪው ምክር ቤት የተቃዋሚዎችን በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ማረጋገጥ፣ ለፕሬስ ነፃነትና ለሕግ የበላይነት መሥራት በተለይም አገሪቱ ተቀብላ ያፀደቀችውን ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች የድርጊት መርሐ ግብር አፈጻጸምን መገምገም ፈጣን ዕርምጃ መውሰድ  በቀጣይ ከአገራችን የሚጠበቅ ሥራ ይመስለኛል፡፡ ይህንን ካደረግን የኢኮኖሚ ዕድገቱ ያለሰብዓዊ መብቶችና የዴሞክራሲያዊ መርሆች መስዋዕትነት እንዳልመጣ ለዓለም እንመሰክራለን፡፡ ገጽታችንንም እንቀይራለን፡፡ 

ከአዘጋጁ፡– ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...