Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትኢትዮጵያ ኦባማን “ሕመሜ በሰው ፊት እንዳታዋርደኝ” ማለት ቻለች

ኢትዮጵያ ኦባማን “ሕመሜ በሰው ፊት እንዳታዋርደኝ” ማለት ቻለች

ቀን:

በበሪሁን ተሻለ

ኦባማ ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ ከተባለ ጊዜ ጀምሮ መላው ኦፊሴል ኢትዮጵያ በጥፍሩ ቆመ፡፡ (ዓርብ ዓርብ ይሆናል እንደሚባለው) እንደ እየሩሳሌም ተሸበረ፡፡ እጅ ባለመጠምዘዝ ድልና ሪከርድ የሚኮራው “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ሳይቀር ትናንት ግንቦት 17 ምርጫ መዳረሻ ላይ በግንባሩ ሊቀመንበርና በጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት ለአልጄዚራ ቴሌቪዥን ስለብሎገሮች የአሸባሪነት ወንጀል ማስረጃ፣ ስለነፃ ፍርድ ቤት የተባለው ተረስቶ፣ “ወንጀለኞቹ አሸባሪዎቹ” በኦባማ ጉብኝነት ዋዜማ ላይ በቀጠሮ ላይ ያሉበት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ አዲስ አበባ ላይ ተለቀቁ፡፡ በአመክሮ የመፈታት ሕግ ተፈጻሚነት እንኳን የኦባማን ጉብኝት ግፊትና ግለት በሰበብ ተጠቀመ፡፡ መላው ኢትዮጵያ በተለይም አዲስ አበባ ላይ የ“Potemkin Villlage” ተመሠረተ፡፡ (ፖተምኪን ሠፈር ማለት መልኩን አሳምሮ “ቢከፍቱት ተልባ”  ማለት ዓይነት ነው፡፡ የሩሲያ ንግሥተ ነገሥታት የነበረችው ታላቋ ካትሪን ክሪሚያን ስትጎበኝ እግሯ በሚረግጠው መንገድና በምትጎበኘው አካባቢ ሁሉ የፊት ለፊት ገጽታ ብቻ ያለውና የሚታይ ቤቶች የተገጠገጡበት መንደር መሠረተ፡፡ በዚህ ምክንያት ስያሜው ብዙ ቋንቋዎች ውስጥ የገባ ማታለያ ማጭበርበሪያ “ቱሪስት መብያ” ማለት ሆኗል)፡፡ ይህን ሁሉ ሕዝቡ በሹክሹክታና አሁን ደግሞ ከዚያ በላይ በሰፊው በሚደመጥና በሚሠራጨው በሶሻል ሚዲያ አገለማው፣ አሳጣው፡፡ “ለማያውቅሽ ታጠኝ” አለው፡፡ ሌላው ቀርቶ ማዘጋጃ ቤታዊ ሥራ እንኳን አልይዝልህና አልዋጣልህ ያለው፣ የገዛ ራሱን መንገድና የመንገዱን ስያሜ በቅጡ የማያውቀው፣ የአዲስ አበባ መንግሥት አፍሪካ ጎዳና ላይ ክረምት መጣና በማዘጋጃ ቤት ስም በመንገድ ስም የሚጠራ ሁሉ፣ ሁሉም ማዘጋጃ ቤት፣ ሁሉም መንገድ አይደለም አለው፡፡ ለዚያውም አፍሪካ ጎዳና ላይ፡፡ አፍሪካ ጎዳና ደግሞ ከጥቂት ጎዳናዎች መካከል አንዱ ነው፡፡

ማዘጋጃ ቤቱ ያለአመሉና ያለባህሪይው፣ ለወረት ሌላ ባለሙያ እስኪመስሉ ድረስ የሥራ ልብስ ሳይሆን የክትና የአውደ ዓመት ልብስ አድርጎ ያለበሳቸው ሰዎች አስገራሚ የሠራተኛ ቅነሳና ድልድል ታሪክ ያላቸው፣ ሥራቸውን እንደ ሥራ የማይቆጥሩ “ተደብቀው” የሚሠሩ ሁለት የተለያየ ሕይወት ያላቸው ናቸው፡፡

የማንኛውም አገር መሪ ጉብኝት፣ የእኛም አገር መሪዎች የውጭ ጉብኝነት መታየት ያለበት ከአገር የውጭ ጉዳይና ግንኙነት አኳያ ነው፡፡ አገር የተጻፈ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኖራትም አልኖራትም ጉዳዩ የሚታየው በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ከአሜሪካ ጋር ያለንን የግንኙነት ማዕቀፍ ይዘረዝራል፡፡ ከሌሎች አገሮች በተለይም ከአውሮፓ አገሮች ጋር ከሚኖሩን ግንኙነት የተለየ የሚያደርገውን አምሳያ የለሽ ባህሪይም ይናገራል፡፡

አውሮፓ ሰፊ ገበያ መሆኑን፣ በስፋቱና በብልፅግናው ከአሜሪካ ጋር የሚመጣጠን በሒደትም ሊበልጥ የሚችል ገበያ መሆኑን፣ የግሎባላይዜሽንንና የኢኮኖሚ ሕግጋቱን በመወሰን ረገድ ከአሜሪካ ቀጥሎ ወሳኝ አስተዋጽኦ ያለው ገበያ መሆኑን፣ ይኸው ገበያ ዋናው ገበያችን መሆኑን፣ የአገራችን የዕርዳታ ዋነኛው ምንጭ እሱው እንደሆነ፣ ኢንቨስትመንት በመሳብ ረገድ በጣም ቁልፍ የኢንቨስትመንት ምንጭ እንደሆነ የሚገልጸው የአገራችን የውጭ ጉዳይና የአገራዊ ደኅንነት ፖሊሲ አሜሪካ ከአውሮፓ ለየት የሚያደርጋትን ጉዳይ ይገልጻል፡-

“… ዋናው ለየት ያለው ጉዳይ አሜሪካ በዓለም ያላት ሚና ነው፡፡ የግሎባላይዜሽን መሠረታዊ ኢኮኖሚያዊ ሕግጋትን የምትወስን ዋነኛዋ አገር አሜሪካ ነች፡፡ ከዓለም ሰላምና መረጋጋት አኳያም ወሳኝዋ አሜሪካ ናት፡፡ ይልቁንም ወደ አሜሪካ ገበያ ሰብረው ያልገቡ የኢንዱስትሪ ልማት ፈጣን ለውጥ ያመጡ አገሮች የሉም ማለት ይቻላል፡፡

“በመሆኑም የአሜሪካን ድጋፍና ይሁንታ ማግኘት ለልማታችንም ሆነ ለአገራዊ ደኅንነታችን እጅግ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ሊሰመርበት ይገባል፡፡

“ኢትዮጵያ ሁሉን ነገር ወደ ጎን በማለት በልማትና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ማተኮር መወሰንዋ፣ በአካባቢያችን ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆንዋ፣ አሜሪካ በአካባቢው ከምትከተለው ፖሊሲ ጋር የተጣጣመና ለግንኙነታችን መዳበር አንድ ምክንያት ሊሆን የሚችል ነው…

“የአካባቢያችንን ሰላምና ደኅንነት በተመለከተ ያስቀመጥነው አቅጣጫ ከአሜሪካ ፖሊሲ ጋር የሚጣጣም እንደሆነ ተቀምጧል፡፡ አሜሪካ በአሁኑ ወቅት በዓለም የፖለቲካ ሒደት ላይ ወሳኝ ሚና የምትጫወት አገር እንደሆነች በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ ከፍተኛ ቦታ ያላት እንደሆነም ይታወቃል፡፡ በሰላምና መረጋጋት አጀንዳችን ላይ የአሜሪካንን የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ማግኘት ለዓለማችን መሳካት የላቀ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ስለሆነም በዚህ ጉዳይ ላይ ከአሜሪካ ጋር እየተመካከሩ መሥራት ጠቃሚና አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ አልፎ አልፎ የአመለካከት ልዩነቶች እንደሚከሰቱና ሊከሰቱም እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡ እነዚህን ልዩነቶች በግንኙነቱ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ማዕቀፍ ውስጥ አስገብተን ማየትና ለማጣጣምም መሞከር ይኖርብናል፡፡ በአካባቢያችን ግጭቶችን ለመግታት መቻልና በዚህ ረገድ አሜሪካ ልትጫወተው የምትችለው ሚናና አልፎ አልፎ ሊከሰቱ የሚችሉ ልዩነቶችን በማገናዘብ ማየትና መፍታት ወሳኝ ነገሮችን ከመለስተኛ ነገሮች ለይቶ የማየት አሠራር በጥብቅ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል፤” ይላል፡፡

ከፍ ሲል እንደተገለጸው የአንድ አገር መሪ ወይም ወኪል በሌላው አገር የሚያደርገው ጉብኝት በሁለቱ አገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነት ውስጥ የሚታቀፍና የሚታይ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ጉዳይ ነው፡፡ የእኛ አገር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲም ይህን አሳምሮ ያውቀዋል፡፡ ከአውሮፓ ጋር በጋራ ከየአገሮቹ ጋር በተናጠል እንዲሁም ከአሜሪካ ጋር ጭምር ያለን ግንኙነት መመሥረት ያለበትን ጉዳይ በሚገባ ይናገራል፡፡

ከአውሮፓም ሆነ ከአሜሪካ ጋር ባለን ግንኙነት ዋናው ችግር ግንኙነቱ ሊፈጥርልን የሚችለውን ዕድል በሚገባ አሟጠን መጠቀም አለመቻላችን ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ የልማት ብድርና ዕርዳታ የማፈላለግና እሱኑ ጥቅም ላይ ማዋል ብቻ አይደለም፡፡ ዋነኛው ኢንቨስትመንትና ንግድን የማስፋፋት ጉዳይ ነው ይለናል፡፡

ለዚህ ተወዝፎ ለኖረ አሁንም ላልተቀየረ ችግር ዋነኛው ምክንያት በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና የደኅንነት ፖሊሲ በራሱ እንደተገለጸው፣ “የኢትዮጵያ ገጽታ እጅግ የተበላሸ፣ የኢትዮጵያን የማያባራ ጦርነትና የአስከፊ ድህነት አገር እንጂ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት መዳረሻ አድርጎ የማይመለከት አስተሳሰብ ስላለና ይህን ገጽታ ለመቀየር ብቃት ያለው ሥራ ስላልተሠራ ነው፡፡ በተጨማሪም ኢንቨስትመንት ለመሳብ የሚያስችል የተመቻቸ ሁኔታና በዕቅድ የሚመራ የተጠናከረ ሥራ አልተሠራም” (ሰረዝ የተጨመረ)

ዋነኛው ምክንያት የገጽታ ግንባታ ችግር ሆኖ መቅረቡ ትናንት ፖሊሲው በተጻፈበት ጊዜ ጭምር የተሳሳተ ምክንያት ነው፡፡ ዋነኛው ችግር በተጨማሪ የተባለው ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የተመቻቸ ሁኔታ አለመኖሩ ነው፡፡ መጀመሪያ ድኅረ ደርግ ዘመን ላይ የፖለቲካ ሰላም እጦት፣ የመዋዕለ ንዋይና የሥራ እንቅስቃሴዎች አሸማቃቂ ሆነው ተነሱ፡፡ ሕዝብ፣ ምሁራንና የግል ባለሀብቱ ከገዥዎች ጋር ያለው የጥርጣሬና የጥላቻ ግንኙነት ዛሬም እየባሰ እንጂ እየተቃለለ አልመጣም፡፡ የሹመት፣ የአወቃቀር፣ የሕግና የደንብ መለዋወጥ ሌላ በጥባጭና አደናቃፊ ነው፡፡ አዲሱ ተሿሚ ያለፈውን ጠርጣሪ፣ አበጣሪና ያለቀለትን ነገር ሁሉ መልሶ አጥኚ ይሆናል፡፡ አዲስ ተሿሚ ከሥራው ጋር ትውውቅ እስከሚያበጅ “ጥናትና ምርመራ” እስኪያካሂድ በሒደት ላይ ያሉ ሥራዎች የሚቆሙበት፣ አዲስ መጥ ጉዳዮች የሚያድሩበት፣ ያለፈው ሹም ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮች እንደገና የሚከለሱበት፣ የተፈቀዱ የሚከለከሉበት፣ የተከለከሉ የሚፈቀዱበት አገር ሆኖ ከመመዝገብ የበለጠ የገጽታ ችግር የለም፡፡

ኦባማ ናይሮቢ ኬንያም ሆነ አዲስ አበባ ማንዴላ አዳራሽ ውስጥ ያነሱት የሙስና ነገር ኢትዮጵያም ውስጥ የፀረ ሙስና ኮሚሽንን በአዋጅ መቋቋሙን በማሳየት ብቻ የሚገላገሉት “የገጽታ” ችግር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በይፋና በሕጋዊ መንገድ ብቻ እሄዳለሁ/እሠራለሁ ያለ ባለሀብት ለመክሰር የቆረጠ ሞኝ ተደርጎ የሚወሰድባት አገር ናት፡፡ ጨረታ ለማሸነፍ፣ ተደራድሮ ሥራ ለመሥራት፣ መንግሥታዊ ትብብር ለማግኘት፣ ቀረጥ፣ ግብር ቅጣት ለማስቀነስ ሁሉ ገንዘብ አለበት፡፡ አንድ ባለሀብት የሕዝብ ፍቅርን የተጎናፀፈ፣ የሥራ ስኬቱን ለመፍጠር ሲል ወድዶ ከሚያደርገው ይልቅ ላለመጠመድና የአሻጥር ሰለባ ላለመሆን ሲል የሚከፍለው ሌላም ዓይነት “ግብር” አለ፡፡ በተለይ በገጠር አካባቢዎች ቢወዱም ቢጠሉም፣ ሥራውን ለማዝለቅ ከፈለጉ በጥቅማ ጥቅም ቢሮክራሲውን መያዝ ከዚያም አልፎ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ልማት ነክ ጉርሻዎች (መንገድ፣ ክሊኒክ፣ ንፁህ የመጠጥ ውኃ ግንባታ፣ ወዘተ) ማበርከት፣ በአካባቢው በሚካሄዱ መዋጮዎች ጥሩ ነጥብ የሚያሰጥ ገንዘብ የመለገስ ግዴታ አፍጥጦ ይጠብቀዋል፡፡

የውጭ ባለሀብት ዝር አለማለቱ አለዚያም አሰልሎና አየት አድርጎ መሸሹ፣ የውስጥ ባለሀብቱም በከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ ውስጥ ከመልከስከሰ አለዚያም “ከመርመስመስ” አለመወጣቱ፣ እነዚህን የመሳሰሉ ችግሮች ቀጥተኛና ኢቀጥተኛ ገጠመኝ ጥቅል ውጤት ነው፡፡

የኦባማን የሙስና ንግግር ልብ አድርጎ ለተከታተለ ብዙ ጊዜ እንደሚደረገው ጉቦ ሰጪውን ከጉቦ ተቀባዩ እኩል አላሳጡትም፣ አላብጠለጠሉትም፡፡ አለ የሚባለው ባለሀብት ሁሉ በሙስና መንገዶች የሚሹለከለክ መሆኑ በአልጠግብ ባይነት ብቻ የሚብራራ አይደለም፡፡ በየአቅጣጫው የሚኖርበትን ማለቂያ የለሽ ወጪ ሸፍኖ ለማትረፍ ቀላሉና ርካሹ መንገድ ሕገወጡ ነው፡፡ ፈልጎም ሆነ ሳይፈልግ ጉቦና ኮሚሽን እያበላ (በተጋነነ አገልግሎት፣ የግንባታ ወጪና የቁሳቁስ ሽያጭ አማካይነት በተለያየ ደረጃ ግብርና ቀረጥን በመሸወድ፣ ወዘተ) ከመንግሥትና ከኅብረተሰቡ ሀብት ላይ ሒሳብን የማወራረድ ዑደት ውስጥ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ እኔ ነኝ ያለ ንፁህ በትክክለኛ ሰነድና ሒሳብ በሕጋዊ መንገድ የሚሠራ ባለሀብት እንኳ የተጋነነ ግብር እንዳይጫንበት ወይም ሌላ ዓይነት የበቀል ወጪ እንዳይመጣበት ማላሻ ይከፍላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ሕጋዊ ለመሆንና ሕጋዊው ነገር እንዲከበር ለማድረግ የሚችለው ጉቦ ከፍሎ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ የተሻለ መንግሥታዊ አያያዝንና መልካም አስተዳደርን ይጠይቃሉ፡፡ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ይዣለሁ ማለት በትክክለኛ ስሙ በኢትዮጵያ ውስጥ ካፒታሊዝምን እገነባለሁ ማለት ነው፡፡ ለዚህ ሥርዓት ግንባታ ደግሞ ባለሀብቱ በሙሉ፣ ከበርቴው በጥቅሉ አጋር ነው፣ ባለቤት እሱ ነው፡፡ የሚገነባው ሥርዓትም የራሱ የከበርቴው ነው፡፡ ዋናው ትግልም በማኅበራዊ ቀውሶችና በካፒታል ድርቀት ካፒታሊዝም ጭንጋፍ ሆኖ እንዳይቀር፣ የአጠቃላይ የኅብረተሰቡን ኑሮ በሚያነሳ አኳኋን ወደ ኢንዱስትሪ እንዲሸጋገር ማስቻል ነው፡፡ ይህ የገባው መንግሥት ልማታዊ ነኝ ቢል ያምርበታል፡፡

የአገሪቱን ባለሀብት መንከባከብ፣ መግራትና የባህል ደረጃውን ማሳደግም ይጠበቅበታል፡፡ የአገሩን ባለሀብት ንቆና ረስቶ የውጭ ባለሀብትን አስባለሁ ማለት የማይሆን ነው፡፡ የውጭው ባለሀብት ከመንግሥት የማባበያ ጉብኝትና “የገጽታ ግንባታ” መግለጫ ይልቅ፣ ይበልጥ የሚያምነው ከብጤው (ከባለሀብቱ) የሚያገኘውን መረጃ ነው፡፡ የውጭ ባለሀብትን የመሳብ ስኬት ለአገር ልጆች ከመመቸት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡

የኦባማ ጉብኝት በዚህ ማዕቀፍ፣ በዚህ ዓላማና ግብ ውስጥ መታየት ለዚህም አገልግሎት መዋል ሲገባው፣ ፕሮፓጋንዳው ሁሉንም ነገር ካልደመሰስኩ እኔ ብቻ ካልተደመጥኩ ብሎ ደነፋ፡፡ ኢንቨስትመንትን የሚስብ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር ዋናው ሥራው መሆኑ ቀርቶ ገጽታ ግንባታ የዚህ ቅድመ ሁኔታ ሆነ፡፡ በዚህ ምክንያት የኦባማ ጉብኝት የመጀመሪያው (እና ብቸኛው) ሥልጣን ላይ ያለ መሪ ኢትዮጵያን ሲጎበኝ በማለት በድል ተመዘገበ፡፡

ኦባማ ኢትዮጵያን መጎብኝታቸው፣ ይህም ሥልጣን ላይ ላለ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የመጀመሪያው መሆኑ በራሱ ትርጉም የለውም፡፡ በኢትዮጵያ የብዙ ሺሕ ዘመን ታሪክ ውስጥ በአሜሪካም የ239 ዓመት ታሪክ ጭምር ይኼ የሆነው ዛሬ መሆኑም (አሜሪካ ውስጥ በዴሞክራቶች ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ በኢሕአዴግ መንግሥት መሆኑም) ብቻውን የአንዱ መንግሥት ድል ተደርጎ የሚታይ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሶማሊያን አንድ ሥልጣን ላይ ያለ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የጎበኛት በጆርጅ (ኸርበርት ወከር) ቡሽ (አባትየው) ዘመን እ.ኤ.አ. በ1992 መጨረሻ ነው፡፡ ቡሽ ከዲሴምበር 31 እስከ ጀንዋሪ  2 ድረስ ሞቃዲሾ፣ ባይደዋ፣ ባሌዶግሌ ደርሰው ዓለም አቀፋዊ የዕርዳታ ሠራተኞችንና የአሜሪካ ወታደራዊ ፐርሰኔሎችን ጎበኙ ማለት ለዚያኔዋም ሆነ ለዛሬዋ ሶማሊያ በጭራሽ የክብር ምልክት አይደለም፡፡ እንዲህ ያለ ጉብኝት ያስመዘገበ አገርም አለ፡፡

የፕሬዚዳንት ኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝነት ከፍ ያለ ፋይዳ ያለው መሆኑ የማይካድ ነው፡፡ ይህ ግን ብቸኛ ሥራቸውና ግባቸው “ገጽታ ግንባታ” የሆነው አዳናቂዎች እንደሚሉት የኢሕአዴግ ከሌሎች የላቀነት ማሳያና ማስረጃ አይደለም፡፡

ኢሕአዴግ ይህን ማስረዳትና ማሳየት ከፈለገ፣ ዋናው የአገር ጉዳይ ይህ ከሆነ፣ በገጽታ ግንባታ ውስጥ ከመሸፋፈንና ራሱንና ገጽታ ገንቢዎቹን ጭምር ከማታለል ተላቆ፣ ቁም ነገር ውስጥ ገብቶ ራሱን መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ቀደምም ተደጋግሞ እንደተገለጸው በዚህ ረገድ የተሳካ ነገር መሥራቱን መመዘን የፈለገ መንግሥት፣ ከቀድሞዎቹ በስንት በለጥኩ እያለ ቁጥር ከማስላት ወጥቶ፣ ኢንቨስትመንት የሚስብ ለሥራ የሚያነሳሳ ምን ያህልና ምን ዓይነት ምቹ ሁኔታ ፈጠርኩ? የሥራ አጥነትን ለማዳከምና የሥራ መከፈትን በማበራከት ረገድ ምን ያህል ርምጃ ታየ? ኅብረተሰቡን አስተባብሬ ለልማትና ለለውጥ አነቀንቄያለሁ? ለልማት የቆረጡ በውስጥና በውጭ ያሉ የአገሪቱን ውድ ልጆች በዙሪያዬ አሰባስቤያለሁ? ምሁራኑ ከዝምታና ከሐሜት፣ ለይምሰል በአቋም መግለጫ ከማጨብጨብ፣ አሁን ደግሞ ከየዩኒቨርሲቲው “እየተወከሉ” የየዕለቱ ዜና የኢሕአዴግ “የምሁራን ድምፅ” ከመሆን ወጥተው በልማት አነቃናቂነት እየተዋደቁ ነው? ነቀዞችና አንቃዦች ሽፋን እያጡ ሕዝብ፣ ጋዜጠኛው፣ ሠራተኛውና ባለሀብቱ ሁሉ መደበቂያ እያሳጣቸው ነወይ?

አድራጊ ፈጣሪነት፣ አምባገነንነት፣ ሕዝብን መፍራት ጀመረ? በፖሊስና በፍርድ ቤት ላይ ሕዝብ ዕምነት መጣል ቻለ? ወይስ አሁንም ሥርዓት እንደለቀቀ፣ ሕጋዊና ቀጥተኛ መንገዶች እንደተደፋፈኑ ዘወርዋራ መንገዶች እንደተንሰራፉ ናቸው?

የሕዝብን ነፃ የልማት እንቅስቃሴዎች የማያያዝና የማስተናገድ ሥራ መንግሥትን እያዋከበው ነው? ወይስ ሕዝብን ማነቃነቅ መከራ ሆኖበታል? መንግሥት እነዚህን ጥያቄዎች “አዎ!”  ብሎ መመለስና ማስረዳት አልቻለም፡፡

ሌላው ቀርቶ በአሁኑ ጊዜ ቅድመ 97 እንኳን የነበረው ሁኔታ ቀርቷል፡፡ የሐሳብ ነፃነት ያለ ማስመሰያ የነበረው የጋዜጦች ድምፅ፣ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪነት፣ የአገር ውስጥ ጩኸት፣ የሠልፍና የአደባባይ ስብሰባ ግርግር እንኳን የሌለበት አጠቃላይ ረጭታ ሰፍኗል፡፡

ለጥቂት ጊዜ ተናግቶ የነበረው የአደባባይ አንገት መድፋት ተመልሶ በሕዝብ ላይ ወድቋል፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ወደ አሜሪካ ገበያ ሰብረው የሚገቡ ባለሀብቶችን ማፍራት ዴሊሳ ዴሲሳን እጅ ከፍንጅ አስሮና ቀፍድዶ ቦስተን ማራቶን ላይ ማሠለፍ ማለት ነው፡፡

የኦባማን የኢትዮጵያ ጉብኝት ይፋና አደባባይ ያወጣው ሌላው ጉዳይ አሜሪካና የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ በፕሬዚዳንት ኦባማ የቤተ መንግሥት ንግግርና ጥያቄና መልስ ያልተደሰቱት፣ ከዚያም በኋላ ፕሬዚዳንቱ በአፍሪካ ኅብረት በማንዴላ አዳራሽ ያሉት ሁሉ ያላረካቸው ዜጎች አሜሪካና ሰብዓዊ መብት ምንና ምን ናቸው የሚለው ጥያቄ  ከዱሮው የበለጠ ሳያደናግራቸው አልቀረም፡፡

ለነገሩ ይህ ጉዳይ የተነሳው ገና ዛሬ አይደለም፡፡ ከ1997 ዓ.ም. የምርጫ ውጤትና ከተከተለው ግርግር ጋር በተያይዘ ምክንያት አሜሪካ ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት ያላትን ተቆርቋሪነት ትታዋለች፡፡ ዋና ጉዳይዋ በራሷ ጥቅም (በፀረ ሽብር ትግል) ላይ ሆኗል ማለትን የመሰለ ሮሮ በተደጋጋሚ ተሰምቷል፡፡

አሜሪካ ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት ያላት ጥብቅና ለሰው ልጆች ካሏት ተቆርቋሪነት የመጣ ሳይሆን፣ ከምትመራው ዓለማዊ (ግሎባል) ኢኮኖሚና ከፖለቲካው የመጣ ነው፡፡

ለምሳሌ የባርነትን ጉዳይ በአገራችን ስንመለከት ንጉሥ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መሳፍንቱንና የአካባቢ ገዥዎችን የፍፁማዊ ሥልጣናቸው ሙሉ ክፍል የማድረግ፣ ሥልጣን የመገንባት ሒደቱን የቀጠሉት ጭሰኝነትንና ባርያ መፈንገልን ሳይነካኩ ነበር፡፡ ባሪያ መፈንገል በአዋጆችና በተግባራዊ ሙከራዎች ትንሽ ሊቆነጠጥ የቻለው፣ በኋላም በሕግ ይቅር የተባለው በአውሮፓውያኑ ጫና ምክንያት ነበር፡፡ አሁን ጥያቄው የአውሮፓውያኑ ጫና መነሻ ምንድነው የሚለው ነው፡፡

የአውሮፓውያኑ ጫና የሰብዓዊ መብት ልባስ ይኑረው እንጂ እውነተኛ ምክንያታቸው ድንበር እየተሻገረ በርካሽ ጉልበትና ጥሬ ዕቃ ሸቀጥ ማምረት ለጀመረው ካፒታላቸው ምቹ ሁኔታን የማደላደል ሥራ ነበር፡፡ ስለሰው ልጅ መብት የሚናገሩት እነዚህ “ሥልጡን” አውሮፓውያን ራሳቸው ከዚያን ጊዜ ቀደም ብሎ ከትንሽ ጊዜ በፊት፣ በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ ምድር ላይ ከባርነትና ከከፊል ባርነት ጋር ጡት የተጣቡ ነበሩ፡፡

አሜሪካም ዛሬ ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት ያላት ጥብቅናና ወገንተኛነት ከሁኔታዎች ጋር የሚገናዘብ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ይነሳ ከተባለ ከአገራቸው የተገፉት ፍልስጤማውያን በቁራጭ መሬት ለይ እንደ አገር የመቋቋም ትንሽዬ ፍትሕ እንኳ ያጡበት የዓለማችን ታላቁ የሰው ልጅ መብት ረገጣ የአሜሪካና የአውሮፓ ተጠያቂነት ያለበት ነው፡፡

በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅትም አሜሪካ ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብትን እየዘመረች ወደር ለሌላቸው መብት ረጋጭ መንግሥታት ተገን ሆና ኖራለች፡፡ የሥርዓት ፍጥጫ ከተወገደ በኋላም ደግሞ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ወገንተኝነቷ በአንፃራዊነት በተግባር ጎልቶ መውጣት ችሏል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ወገንተኝነቷ ከሁኔታዎች ጋር የሚገናዘብ ነው፡፡ ለምሳሌ የፀረ ሽብርተኝነት ትግሉዋ ልዕለ ኃያላዊ ማናለብኝነቷን አጋልጦባታል፡፡ በሰብዓዊ መብት ረገጣም አቆሽሿታል፡፡ ይህም በአፍጋኒስታን፣ በኢራቅና በጓንታናሞ እስር ቤቶች በተደረገው ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡

አፍሪካ ውስጥ የሩዋንዳው ጭፍጨፋ እንደ ዋዛ እንዳልታለፈ ሁሉ፣ በዚምባቡዌ የነጮች መሬት ተነካ ሲባል ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ ድረስ ዚምባብዌን ለመሰነግ የተካሄደው ፈጣን እንቅስቃሴ ከዘረኝነትም ጋር ይጣቀሳል፡፡ ነዳጅ ካላት ኢራቅ ውስጥ አልወጣ ብላ ወታደሮቿን በየቀኑ እያስገደለች ስትቆይ፣ ነዳጅ የሌላትን ሶማሊያን ግን የአንድ ሁለት ወታደሮቼ ሬሳ ተጎተተ ብላ ጥላ ወጥታ የሶማሊያ ሕዝብ መዋረድ የሶማሊያና የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን፣ የሠለጠነውም ዓለም መዋረድ መሆኑ ሳይሰማት ሶማሊያ እነሆ (እስካሁን ድረስ) ሰብዓዊ መብት የተረሳበት፣ የዘርፎ በሎችና የአሸባሪዎች አገር እንድትሆን በመፍቀድ ግፍ ሠርታለች፡፡

ወደ ጉዳያችን ስንመለስ የኢትዮጵያን የ97 ዓ.ም. የምርጫ ውጤት ውዝግብንና የመንግሥትን “የፀረ ሁከት” ዕርምጃ አወሳሰድ አስመልክቶ አሜሪካ ኢሕአዴግን አለማዋከቧም የጥቅሞቿን ተገናዛቢነት እንጂ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት “ጠበቃነቷን” መቅረት አያሳይም፡፡ ተቃዋሚዎች ወደ ሥልጣን ቢወጡ የአገሪቱን ሕዝቦች ያስማማና ያረጋጋ መንግሥት መምራት ስለመቻላቸው ውስጣዊ ሥጋት እንደነበረ ሁሉ (ኋላ እንደታየው ደግሞ ሥጋቱ አደገኛ ነበር)፣ ለአሜሪካኖችም ሥጋት የማይሆንበት ምክንያት አልነበረም፡፡ በድኅረ ምርጫ ግርግር ወቅት አሜሪካ የኢሕአዴግን መንግሥት የዕርምጃ አወሳሰድ ስትተች ተቃዋሚዎችንም ሕገወጥ እንቅስቃሴ በማነሳሳት ወቅሳ እንደነበር አይረሳም፡፡ ኢትዮጵያ በፖለቲካ ቀውስ መተራመሷ ከአሜሪካኖች ስትራቴጂካዊ ጥቅም ጋር አይስማማም፡፡ ተቃዋሚዎች ሥልጣን ቢጨብጡ ሽብርተኝነትን የመዋጋት ቁርጠኝነትና አቅሙ ይኖራቸው ይሆን የሚለውም ጉዳይ አብሮ ታሳቢ ነው፡፡ ስለዚህም ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ከሌሎች የአሜሪካ ጥቅሞች ጋር የሚተያዩና የሚገናዘቡ ከመሆናቸው “በስተቀር”፣ አሜሪካ ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት ደጋፊነቷ አልቀረም፡፡ ችግሩ ዋናው የትኛው ነው? “በስተቀሩ” ወይስ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቱ የሚለው ነው፡፡

ኢትዮጵያ ቀድሞም በአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ አሁን ደግሞ በአፍሪካ ኅብረት ውስጥ ያላት ታሪካዊና ወቅታዊ ሚና የታወቀ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያላት ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ ከዙሪያ ጎረቤቶች ጋር በውኃ ሀብትም ሆነ በሕዝብ ዝምድናና በሃይማኖት መተሳሰሯ፣ ሰላሟም ከእነሱ ጋር መያያዙ፣ ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች ተስማምተው የሚኖሩባት አገር መሆኗ ለቀንዱ አካባቢ ሚዛን መጠበቂያነት ምቹ ያደርጋታል፡፡ የቀንዱ ክልል ትርምስና የሽብርተኝነት ችግር የተመላለሰባት መሆኑ፣ በውጭ የፀረ ሽብርተኝነት ትግል ከክልሉ አገሮች ልቃ መውጣቷና በሰላም አስከባሪነትም ሆነ በውጊያ ብቃት ስም ያለው ጦር ማፍራቷ ቦታዋን ከፍ አድርጎታል፡፡ ይህም የማንም መሣሪያና ተቀጥላ መሆን ሳያስፈልጋት፣ ኢትዮጵያ አካባቢዋን በማረጋጋት እየጠቀመች ልትጠቅም የምትችልበት ዕድል የሚያጎናጽፋት ነው፡፡

ምሥራቅ አፍሪካ ተበጥብጦ ለአልቃይዳም ሆነ ለዳኢሽ (አይኤስ) እንቅስቃሴ መራቢያ እንዳይሆን አሜሪካ ኢትዮጵያን  በአጋርነት አጥብቃ መያዝ እንደሚያዋጣት አስተውላለች፡፡ ለአፍሪካ ስትራቴጂካዊ የጥናት ማዕከልዋን ከመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ኦባማ ጉብኝነት ድረስ ያለው እንቅስቃሴ ይህንን የሚያንፀባርቅ ነው፡፡

ይህን የአሜሪካና የኢትዮጵያን አጋርነት ወቅታዊ ክብደት በአሜሪካ ውስጥ የየትኛውም ፓርቲ ማሸነፍ የሚያናጋው አይመስልም፡፡ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ስለመድፈሩዋና ስለመርገጧ የአሜሪካ ምክር ቤቶች ሙሉ ስምምነት ላይ ሊደርሱ ቢችሉ እንኳን፣ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ይጣላል ብሎ ማሰብ በጭራሽ አይቻልም፡፡ ጉዳዩ ዛሬ የአሜሪካ አጋር የመሆን ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ አሜሪካ ዛሬም ኃያልና የዓለም ጠባቂ አድርጋ ራሷን እንዳነገሠች ብትሆንም፣ አገሮችን በማዕቀብና በኃይል አንበርክካ የፈቀደችውን ማስደረግ ስለመቻሏ በእርግጠኝነት መናገር የማይቻልበት ሁኔታ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ውስጥ እየታየ ነው፡፡ ለአሜሪካ ልዕለ ኃያልነት መስገድን ግድ ያደረገው (አጭር) ዘመን እያለቀ ሳይሆን አልቀረም፡፡ ለአሜሪካና ለአጋሮቿ ፍላጎት ተቃውሞ በማሳየትና ድምፅ በመንፈግ የምትታወቀው ቻይና በፈጣን ዕድገት ወደ ተፎካካሪነት ከወጣች ቆይታለች፡፡ ቻይና ለምዕራቡ ዓለም በሩዋን በከፈተች ጊዜ ቁጥር አንድ የሕዝብ ብዛት ያለው ሰፊ ገበያ በማግኘታቸው የፈነጠዙት አሜሪካና አውሮፓ ዛሬ ሲከስሩ እየታየ ነው፡፡ የቻይና ምርት የሚያሳየውን መስፋፋት የማይገድቡት ሆኗል፡፡ በአገር ውስት ገበያቸውም የቻይናን ሸቀጥ በዋጋ ለማሸነፍ አለመቻላቸው ውድቀታቸውን እያጣደፈ አስደንግጧቸዋል፡፡

በ1999 ዓ.ም. በተካሄደው የአፍሪካ ቻይና የአጋርነት ስብሰባ ላይ ቻይና የዕርዳታ፣ የኢንቨስትመንትና የንግድ ግንኝነቷን ከቀድሞው በጣም ከፍ ለማድረግ ከወሰነችበት ጊዜ ጀምሮ ግንኙነቱ እየታደሰ፣ እየተስፋፋ፣ እንደገና እያበራ መጥቷል፡፡ ያን ያህልም አስደንግጧል፡፡ እንደገና ማዋቀር፣ ወደ ግል ይዞታ ማዞር፣ ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት የሚባሉ ግዴታዎችና ትዕዛዞች ያሰመረሯቸው የአፍሪካ አገሮችና አምባገነነቾ ቻይናን ዋና መጠጊያና ተስፋቸው አድርገዋል፡፡ ቻይና በከፈተችው ከቀረጥ ነፃ ዕድል አማካይነት የማዕድንና የግብርና ምርቶች በእሽቅድድም ወደ ቻይና የሚጎርፉበትና የቻይና ሸቀጥና ካፒታልም ያለማነቆ ወደ አፍሪካ የሚፈልስበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

ኢትዮጵያም ከቻይና ጋር ያላት የዕርዳታና የንግድ ግንኙነት እየጠበቀና እየጨመረ ነው፡፡ እንደ ሁለቱ አገሮች የንግድ አስተዳደግ ከሆነ ቻይና ሌሎችን አገሮች አልፋ ዋና የኢኮኖሚ አጋራችን የምትሆንበት ጊዜ በጣም ቅርብ ነው፡፡ በዴሞክራሲ የወደፊት ዕድል ላይ አጠቃላይ የቻይና ሚና አወንታዊ መሆን አለመሆኑ ገና ከአሁኑ የለየለት ባይሆንም፣ ከአሁን በኋላ የአሜሪካ ጫና የት አባቴ ልግባ የሚያሰኝ አይደለም፡፡ በአንፃሩም አሜሪካ ከቻይና ጋር በገባችው ይህን የመሰለ ውድድር ምክንያት የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ወገንተኛነቷን ከሁኔታዎች ጋር የማገናዘብ መለኪያዋን በዚሁ መሠረት ማስተካከል ውስጥ ትገባለች፡፡

ይህም በመሆኑ ለምሳሌ ኦባማ አዲስ አበባ ከመግባታቸው በፊት ሳይቀር የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊነት መቶ ፐርሰንት ነው እስከማለት ድረስ ሆን ብለው ሲቀኙ እና ሲሸወዱ ሰምተናል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥትም “የግሎባላይዜሽን መሠረታዊ ኢኮኖሚያዊ ሕግጋትን የምትወስን ዋነኛዋን አገር” ‘ሕመሜ በሰው ፊት እንዳታዋርደኝ፣ እኔኑ ብቻየን ጎንተል ጎንተል አርገኝ’ ማለት የሚደርስ የመደራደሪያ አቅም ስታገኝ ማየት ችለናል፡፡

በሱዛን ራይስ ድብልቅልቁ የወጣና ከፊል ስላቅ ንግግር ውስጥ፣ በኦባማ የግል፣ የእርስ በእርስና በሌላ በኩል ደግሞ የቤተ መንግሥትና የአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ንግግር መካከል ያየነው “ድንብርብሮሽ” የሚያሳየው ይህንኑ “ሕመሜ በሰው ፊት” ችሎታችንን ነው፡፡ የ“ሕመሜ በሰው ፊት” ድል ግን፣ ከመዋረድ “ይታደግ” እንደሆነ እንጂ ከመሞት አያድንም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

  

 

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...