Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የአፍሪካ መሪዎች ለምን ሥልጣን ላይ እንደሚቆዩ አይገባኝም በተለይ ሀብት ካካበቱ በኋላ›› ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ

ሰሞኑን ኢትዮጵያን በመጎብኘት የመጀመሪያው በሥልጣን ላይ ያለ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሆኑት ባራክ ሁሴን ኦባማ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች፣ እንዲሁም በሚያሳስቧቸው የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ከመከሩ በኋላ፣ በአፍሪካ ኅብረት ማክሰኞ ሐምሌ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በመገኘት ንግግር አድርገዋል፡፡ በአፍሪካ ኅብረት በመገኘት ለአኅጉሪቱ መሪዎችና ሕዝቦች ያደረጉት ንግግር ዋና ዋና ሐሳቦች እንደሚከተለው ተሰናድቷል፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና የኢትዮጵያ ሕዝብ ስላደረጋችሁልኝ ደማቅ አቀባበል አመሰግናለሁ፡፡ የፓን አፍሪካ ተቋም የሆነው የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤትን በማስተናገዳችሁም በድጋሚ ልትመሰገኑ ይገባል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት አባላትና የተከበራችሁ እንግዶች ደማቅ አቀባበል ስላደረጋችሁልኝ አመሰግናለሁ፡፡ በአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት በመገኘት ለኅብረቱ ንግግር ያደረግኩኝ የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል፡፡

ከአንድ ቢሊዮን ሕዝብ በላይ የሆነውን የአፍሪካ አኅጉር በወከላችሁት በእናንተ ፊት ንግግር ማድረግ መቻሌ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ንግግር በማደርግበት በዛሬው ዕለት በመካከላችን የሲቪክ ማኅበረሰቡ ተወካዮችና የሃይማኖት መሪዎች ይገኛሉ፡፡ በተለይም የዛሬይቷን አፍሪካ ኃይልና ተስፋ የሰነቁ በርካታ ወጣቶችን በዚህ አዳራሽ በማየቴ በእጅጉ ተደስቻለሁ፡፡

ዛሬ ከፊታችሁ የቆምኩት እንደ ኩሩ አሜሪካዊና እንደ አንድ ኩሩ የአፍሪካ ልጅ ነው፡፡ አፍሪካና ሕዝቦቿ የዛሬ ማንነቴንና ዓለምን የማይበትን መንገድ እንድቀርፅ ረድተውኛል፡፡

አባቴ በተወለደበት የኬንያ መንደር ካሉ የዘር ሐረጐቼ ብዙ ተምሬያለሁ፡፡ ከወንድ አያቴ አኗኗር፣ ከአባቴ ሕልሞች ግንዛቤ አግኝቻለሁ፡፡ አሜሪካዊያንና አፍሪካውያንን ካገናኘው የቤተሰቦቼ ሐረግ ብዙ ተምሬያለሁ፡፡

እንደ ወላጆች እኔና ባለቤቴ ሚሼል ሁለቱ ሴት ልጆቻችን የቤተሰቦቻቸውን የማንነት ምንጭ የሆኑትን አውሮፓንና አፍሪካን ከነሙሉ ታሪካዊ መከራውና ጥንካሬው እንዲያውቁ እንፈልጋለን፡፡ እኔና ባለቤቴ ከሁለቱ ልጆቼ ጋር በምዕራብ አፍሪካ የባህር ዳርቻዎች በእነዚያ መመለሻ የሌላቸው የባርነት በሮች ተገኝተን እንዲጐበኙ አድርገናል፡፡ ስለዚህም ቅድመ አያቶቻቸው ባሪያና የባሪያ ጌታ እንደነበሩ እንዲገነዘቡ፡፡

በሮቢን ደሴት በመገኘት በዚያች ጠባብ እስር ቤት ታስሮ የነበረው ኔልሰን ማንዴላ ምንም እንኳን በአካል እስር ቤት ውስጥ ቢቆለፍበትም፣ የሕይወቱ ዕጣ ፈንታ ወሳኝ እሱና እሱ ብቻ መሆኑን ለዓለም ሕዝብ ማሳየቱን ልጆቻችን እንዲገነዘቡ አድርገናል፡፡ በሌላ አነጋገር አፍሪካና ሕዝቦቿ ትምህርት አስተምረውናል፡፡ የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ ያለው ክብር ሊጠበቅለት እንደሚገባ አስተምረውናል፡፡

ክብር ሰው በመሆናችን ብቻ ሊኖረንና ሊሰጠን የሚገባ ነው፡፡ ከየትም እንምጣ፣ ማንም እንሁን፣ ምንም እንምሰል ሁላችንም በእኩልነት ነው የተፈጠርነው፣ የፈጣሪ ግርማ ሁላችንንም እኩል ነው የሚዳስሰው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ጥሩና ጠቃሚ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ያስፈልጋል፡፡ እያንዳንዱን ሰው በክብርና በመልካም ሁኔታ ልናይና ልንንከባከብ ይገባል፡፡ ካለፉት ታሪኮች የምንረዳው የሰው ዘር የሚገባውን ክብር አለማግኘቱን ነው፡፡

ክብር ለኃያላን ወይም ለአለቆች፣ ወይም ለንጉሦችና ለአዛውንቶች ብቻ የሚሰጥ አድርገን እየኖርን ነው፡፡ ለሰው ዘር ክብር የሚለውን ሞራላዊ አስተሳሰብ ለመፍጠር ዘመናትን ያለፈ አብዮት ፈጅቷል፡፡ በዓለም ኅብረተሰብ ደረጃ ትውልዶች ትግል በማድረግ ይህንን ሞራላዊ ጽንሰ ሐሳብ ወደ ተግባርና ወደ ሕጐቻቸው ለማስረፅ ታግለዋል፡፡

በዚህም በአፍሪካ የሰው ዘር መገኛ በሆነችው፣ የታላላቅ ሥልጣኔ ላይብረሪዎችና ዩኒቨርሲቲዎችን የያዘችው የአፍሪካ መንግሥታት ለሰዎች ክብር ታግለዋል፡፡ ነገር ግን የባርነት ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ከአፍሪካ ውጭ ባሉ አኅጉሮች ብቻ ሳይሆን፣ በዚሁ በአፍሪካም ሥር ሰዷል፡፡ ቅኝ ግዛት የአፍሪካን የኢኮኖሚ መንገድ አስቷል፡፡ አፍሪካውያን የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ የመወሰን አቅማቸውን በቅኝ ግዛት ተዘርፈዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ነው የነፃነት እንቅስቃሴዎች የተቀጣጠሉት፡፡ ከ50 ዓመታት በፊትም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ፍላጐት ገነፈለ፡፡ የአፍሪካውያን ደስታ ሆነ፡፡ የውጭ ባንዲራዎች ወረዱ፡፡ የአፍሪካ ሰንደቆች ከፍ ብለው ተውለበለቡ፡፡ ደቡብ አፍሪካዊው አልበርት ላቱሊ (አፓርታይድን በሰላማዊ መንገድ የታገሉ የዓለም ሰላም ኖቬል ተሸላሚ ናቸው) በወቅቱ እንዳሉት፣ ‹‹የሰላምና የወንድማማችነት መሠረት በአፍሪካ መሬት መያዝ የጀመረው የአፍሪካ አገሮች ብሔራዊ ሉዓላዊነትና ነፃነት፣ እኩልነትና የሰው ልጆች ክብር ከተረጋገጠ በኋላ ነው፡፡››

ወደዚህ የነፃነት ዘመን ለመሻገር ግማሽ ምዕተ ዓመት ፈጅቷል፡፡ የጦርነትና የግጭት መገለጫነትን ፈጽሞ ቆርጦ ለመጣል ረጅም ጊዜን ወስዷል፡፡ አሁን የዓለም ማኅበረሰብ የአፍሪካን ልዩ የሆነ ዕድገት ዕውቅና ሊሰጥ ይገባል፡፡ መካከለኛ ገቢ ያለው አፍሪካዊ ማኅበረሰብ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሊያድግ እንደሚችል ይገመታል፡፡

በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሞባይል ተጠቃሚዎችንና የኢንተርኔት አቅርቦቶችን በመፍጠር አፍሪካዊያን ከቀድሞ ኋላቀር ቴክኖሎጂዎች ወደ አዲስ ብልፅግና እየተሸጋገሩ ነው፡፡ እናም አፍሪካ በጉዞ ላይ ነች፡፡ አዲስ አፍሪካ እየተፈጠረች ነው፡፡

በዚህ ዕድገት እየተገፉና በዓለም ኅብረተሰብ ድጋፍ እየተሳቡ አፍሪካዊያን በጤናው ዘርፍ ታሪካዊ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡

አዲስ የኤችአይቪ ኤድስ ኢንፌክሽኖች ምጣኔ በከፍተኛ ደረጃ አሽቆልቁሏል፡፡  የአፍሪካ እናቶች በወሊድ ወቅት ሕይወታቸውን ከማጣት ተርፈው ጤናማ ልጆችን ማሳደግ ጀምረዋል፡፡

በወባ በሽታ መሞትን በግማሽ በመቀነስ በርካታ ሚሊዮኖች ሕፃናትን ሕይወት ማትረፍ ተችሏል፡፡ በርካታ ሚሊዮኖችን ከዘቀጠ ድህነት ማውጣት ተችሏል፡፡ በርካታ ሕፃናትን ወደ ትምህርት ቤቶች በመላክ አፍሪካ ከዓለም ቀዳሚ ሆናለች፡፡ በቀላሉ ለማስቀመጥ አፍሪካውያን ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት በክብርና በተስፋ እየኖሩ ነው፡፡

አፍሪካ በለውጥ ላይ ባለችበት በዚህ ጊዜ የዓለም ኅብረተሰብ ከአፍሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲቃኝ እጠይቃለሁ፡፡ ምክንያቱም በርካታ አፍሪካውያን ዕርዳታ ሳይሆን ዕድገታቸውን የሚያቀጣጥል ንግድ እንደሚፈልጉ ነግረውኛል፡፡

ጠባቂዎችን ሳይሆን ለማደግ ያለንን አቅም የሚያጐለብቱ ወዳጆችን ነው የምንሻው ብለውኛል፡፡ ክብርን የሚነካ ጥገኝነትን ሳይሆን የራሳቸውን ምርጫና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸውን መወሰን እንደሚሹ ነግረውኛል፡፡

እንደ ፕሬዚዳንት የአሜሪካና የአፍሪካን ግንኙነት ለመለወጥ ሠርቻለሁ፡፡ ስለዚህም አፍሪካውያን ወዳጆቻችንን እያዳመጥን ነው፡፡ በዚህ ረገድ በፈጠርነው መሻሻልም እጅግ ኩራት ይሰማኛል፡፡

በእርግጥ አሜሪካ ብቻ አይደለችም የእናንተን አፍሪካውያንን ዕድገት እንደ ዕድል እያየች ያለችው፡፡ ይህ በራሱ መልካም ነው፡፡ በርካታ አገሮች በኃላፊነት ስሜት አፍሪካ ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ካፈሰሱ በርካታ የሥራ ዕድሎች መፍጠር ይቻላል፡፡ ብልፅግናውም ለሁላችንም ይሆናል፡፡ ነገር ግን የኢኮኖሚ ትብብር ማለት አንዳንድ አገሮች በቀላሉ በራሳቸው የሰው ኃይል በአፍሪካ እንደሚገነቡት የመሠረተ ልማት፣ ወይም እንደሚያወጡት የተፈጥሮ ሀብት አይደለም፡፡

እውነተኛ የኢኮኖሚ ትብብር ለአፍሪካ ጠቀሜታ ያለው ኢንቨስትመንት ነው፡፡ የኢኮኖሚ ትብብሩ በአፍሪካ የሥራ ዕድል መፍጠር አለበት፡፡ የአፍሪካን አቅም መገንባት አለበት፡፡ ይህንን ዓይነቱን የኢኮኖሚ ትብብር ነው አሜሪካ ለአፍሪካ እያቀረበች ያለችው፡፡

በሙስና ላይ

የአፍሪካን ዕምቅ የኢኮኖሚ አቅም ለመጠቀም የሙስና ካንሰርን መንቀልን ያህል ጠቃሚ መሣሪያ የለም፡፡ ሙስና በአፍሪካ ብቻ የሚታይ አይደለም፡፡ ሙስና በየትኛውም ዓለም በአሜሪካም ጭምር አለ፡፡ በአፍሪካ ሙስና በርካታ ቢሊዮን ዶላሮችን ከኢኮኖሚው ይነጥቃል፡፡ ይህ ገንዘብ የሥራ ዕድልን ለመፍጠር፣ ሆስፒታሎችንና ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ይጠቅማል፡፡

አንድ ሰው ንግድ ለመጀመር፣ ትምህርት ቤት ለመግባትም ይሁን ባለሥልጣናት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጉቦ መስጠት የለበትም፡፡ ይህ የአፍሪካዊያን ባህል አይደለም፡፡ ይህ የምትወክሉትን ማኅበረሰባችሁን ክብር መርገጥ ነው፡፡

ራሳችሁ አፍሪካዊያን ብቻ ናችሁ በየአገሮቻችሁ ያለውን ሙስና መግታት የምትችሉት፡፡ የአፍሪካ መንግሥታት ይህንን ማድረግ ከቻሉ አሜሪካ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት፣ መልካም አስተዳደርን፣ ግልጽነትና የሕግ የበላይነትን ለማበረታታት ከጐናችሁ ትቆማለች፡፡ በዚህ ላይ መጨመር የምፈልገው የወንጀል ቡድኖች መረብ ሙስና እንዲቀጣጠል ከማድረግ ባለፈ፣ የአፍሪካ ብርቅዬ የዱር እንስሳትን ሕይወት በመቅጠፍ እያመናመነ በአፍሪካ የቱሪዝም መሠረት ላይ ሥጋት እየጣለ ነው፡፡

ስለዚህም አሜሪካ ሕገወጥ የዱር እንስሳት ዝውውርን ለመግታት ከጐናችሁ ትቆማለች፡፡

በዴሞክራሲ ላይ

ለአፍሪካ ዕድገት ሌላው መሠረት የዴሞክራሲ ሥርዓት ነው፡፡ ምክንያቱም አፍሪካውያን እንደሌላው ዓለም ማኅበረሰብ የራሳቸው ሕይወት መሪ የመሆን ክብርን ሊያገኙ ይገባል፡፡ የእውነተኛ ዴሞክራሲ መዋቅሮች ምን እንደሆኑ ሁላችንም ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡

ከእነዚህ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው የዴሞክራሲ መዋቅሮች መካከል ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የመናገር ነፃነትና የመሰብሰብ ነፃነት ናቸው፡፡ እነዚህ ዓለም አቀፍ መብቶች በአፍሪካ መንግሥታት ሕገ መንግሥቶች ውስጥም ተጽፈዋል፡፡ የሰዎችና የሕዝቦች ነፃነትን የሚያውጀው የአፍሪካ ቻርተር ‹‹ሁሉምና እያንዳንዱ ሰው፣ ሰው በመሆኑ ብቻ ያለው ክብር እንዲጠበቅለት መብት አለው፤›› በማለት ያውጃል፡፡

ከሴራሊዮን፣ ጋናና ቤኒን እስከ ቦትስዋና፣ ናሚቢያና ደቡብ አፍሪካ ድረስ ዴሞክራሲ ሥር እየያዘ ነው፡፡ በናይጄሪያ ከ28 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በአገሪቱ ምርጫ ድምፁን ሰጥቷል፡፡ እናም በተገቢው መንገድ በሰላም የሥልጣን ሽግግር ተደርጓል፡፡

ይሁን እንጂ በዚህ ወቅት እነዚህን ተመሳሳይ መብቶች ሌሎች አፍሪካዊያን ተነፍገዋል፡፡ ዴሞክራሲ ዝም ብሎ ምርጫ ማካሄድ ብቻ አይደለም፡፡ ጋዜጠኞች ሥራቸውን ስለሠሩ እስር ቤት የሚወረወሩ ከሆነ፣ መንግሥት የሲቪክ ማኅበራት ላይ በሚወስደው የመበታተን ዕርምጃ የመብት አራማጆች ሥጋት ውስጥ የሚወድቁ ከሆነ፣ ዴሞክራሲን በስም እንጂ በይዘቱ አታውቁትም ማለት ነው፡፡

አገሮች የዜጐቻቸውን ምሉዕ መብት ካላከበሩ የነፃነትን ተስፋ ምሉዕ ማድረግ አልቻሉም ማለት ነው፡፡ ይህ ጥሩ የዴሞክራሲ ዕድገት በሚታይባቸው የአፍሪካ አገሮች ጭምር የሚታይ እውነት ነው፡፡

ኬንያን በጐበኘሁበት ወቅት እንደጠቆምኩት ይህች አገር ሕገ መንግሥቷን በማሻሻልና ሰላማዊ ምርጫ በማካሄድ ያስመዘገበቻቸው አስደናቂ ውጤቶች፣ የሲቪክ ማኅበራትን በመገደብ የመቀልበስ አደጋ ሊገጥመው አይገባም፡፡ በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያንም ብዙ የሚያኮሩ ነገሮች አሏቸው፡፡ በቅርቡ የተካሄደው ምርጫ ያለ ብጥብጥ ተጠናቋል፡፡

ነገር ግን ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር እንደተወያየነው ይህ የዴሞክራሲ የመጀመሪያ ጫፍ ነው፡፡ ጋዜጠኞችን በማሰር፣ ሕጋዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅስቀሳ እንዲያደርጉ በመገደብ፣ ኢትዮጵያ የሕዝቦቿን ዕምቅ አቅም ማምከን የለባትም፡፡ ይህ እንደማይሆንም አምናለሁ፡፡ ምሥጋና ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ይሁንና ከእርሳቸው ጋር በተወያየንበት ወቅትም ምሉዕና ዘላቂ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ለመፍጠር ብዙ ሥራዎች እንደሚቀሩ ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡

ይህ ውይይታችን በወዳጅነታችን ምክንያት የመጣ ነው እንጂ፣ የእኛ ዴሞክራሲ እንከን የማይወጣለት ስለሆነ አይደለም፡፡ ለበርካታ ዓመታት ዴሞክራሲያችንን ለማሻሻል ሠርተናል፡፡ አሁንም ግን ዴሞክራሲያችንን ለማሻሻል ሁሌም ጥናት እናደርጋለን፡፡ የእኛ ጥንካሬ ምንጭ ይህ ነው፡፡ በገዢ ሕጎቻችን ላይ የሠፈሩ ዴሞክራሲያዊ ድንጋጌዎችን በቅንነት ለማሟላት ሁሌ ዝግጁ መሆናችን ነው፡፡

ዋናው ጉዳይ ዜጐች መብታቸውን ማጣጣም ሳይችሉ ሲቀሩ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድምፁን የማሰማት ኃላፊነት አለበት፡፡

አሜሪካ ይህንን ታደርጋለች፡፡ አንዳንዴ የሚጐረብጥ ቢሆንም፣ አንዳንዴ ወዳጆቻችን ላይ ቢሆንም፣ አንዳንድ አገሮች መልስ አይሰጡንም፡፡ ምናልባት ለአንዳንድ መሪዎች እንናገራለን፡፡ ዝምታ ማምለጫ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን የምናደርገው የእኛ ዴሞክራሲ ንጥር ያለ ስለሆነ አይደለም፡፡ ንጥር ያለ አይደለም፡፡ አሜሪካ ነፃ ከወጣች ሁለት መቶ ዓመታት ቢያልፉም የተሳካ አንድነትን በመካከላችን ለመፍጠር ገና እየሠራን ነው፡፡ ከወቀሳስ መቼ ወጣን? ነገር ግን ባስቀመጥነው ደረጃ ልክ ለመሆን ዘወትር እንጥራለን፡፡

አያችሁ ስለእምነቶቻችን በአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ስንናገር ለእምነቶቻችን ታማኝ እንሆናለን፡፡ ስለዚህም ከአገራችን ውጪ ያሉ የተጨቆኑ ሕዝቦችንም እናወጣለን፡፡ መናገራችን ትክክልና ተገቢ ነው፡፡ በተለይ ለእኛ ከአፍሪካ ለወጣን ትርጉም አለው፡፡ ምክንያቱም ፍትሕ ማጣት ሕመሙን እናውቀዋለን፡፡ ምክንያቱም መገለል ማለት ምን እንደሆነ ይገባናል፡፡ የመታሰር ሕመሙን እናውቀዋለን፡፡ ታዲያ ይህ በሌላ ሰው ላይ ሲደርስ እንዴት ዝም ማለት ይቻለናል? ሌሎች አገሮች ከቅኝ ግዛት መውጣታችሁን እንደደገፉት ሁሉ ዓለም አቀፍ መብቶች ሲጣሱም ድምፃችንን በጋራ ማሰማት አለብን፡፡ አፍሪካዊያን እኩል ክብር ይገባቸዋል በሚለው ላይ የእውነት ካመነን ከዓለም አቀፍ የሰው ልጅ መብቶችም ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ሁላችንም ልንቆምለትና ልንጠብቀው የሚገባ ዓላማ መሆን አለበት፡፡

ዛሬ የአፍሪካ የዴሞክራሲ ዕድገት ሥጋት ውስጥ የወደቀው የሥልጣን ዘመናቸውን የጨረሱ መሪዎች ለመውረድ ባለመፈለጋቸው ነው፡፡ እውነት እላችኋለሁ ይህ ለምን እንደሚሆን አይገባኝም፡፡ እኔ አሁን ሁለተኛ የሥልጣን ዘመኔ ላይ ነኝ፡፡ የአሜካ ፕሬዚዳንት መሆን ለእኔ ትልቅና የተለየ ክብር ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሆነ ክብርና ደስ የሚያሰኝ ሥራ ማሰብ ያቅተኛል፡፡ ሥራዬን እወደዋለሁ፡፡ ብወዳደር እንኳ እንደማሸንፍም እገምታለሁ፡፡ ነገር ግን በእኛ ሕገ መንግሥት መሠረት ከሁለት የሥልጣን ዘመን በላይ መቆየት አይቻልም፡፡ ብመረጥና አሜሪካ ከፍ እንድትል እንዲፈጸሙ የምፈልጋቸውን ብከውን ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን ሕግ ሕግ ነው፡፡ ማንም ከሕግ በላይ መሆን አይችልም፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢኮንም፡፡ እውነት ለመናገር ከፕሬዚዳንትነት ውጪ ያለው ሕይወት ይናፍቃል፡፡ ምክንያቱም ከምታዩት ከዚህ ሁሉ የደኅንነት አጀብ እገላገላለሁ፡፡ ሰፋ ያለ የቤተሰብ ጊዜ እንዲኖረኝ፣ በአዲስ መንገድ የማገልግል፣ እናም ወደ አፍሪካ በተደጋጋሚ ጉብኝት ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡

የማይገባኝ ነገር የአፍሪካ ፕሬዚዳንቶች በሥልጣን ረዥም ጊዜ መቆየት እንደሚፈልጉ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ከፍተኛ ሀብት ካካበቱ በኋላ፡፡

አንድ መሪ በሥልጣን ዘመኑ መካከል ሕጐችን በማሻሻል የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም መሞከር አለመረጋጋትንና ብጥብጥን ነው የሚፈጥረው፡፡ ልክ በብሩንዲ እየሆነ እንዳለው፡፡ ይህ አስተሳሰብ የአደገኛ ቁልቁለት መጀመሪያ ነው፡፡ መሪዎች ካለነሱ አገራቸውን አንድ አድርጐ መያዝ የሚችል የለም ብለው ካሰቡ፣ ያኔ ነው አገራቸውን በእውነት መገንባት የማይችሉት፡፡ በአንፃሩ ግን ኔልሰን ማንዴላ እንደ ጆርጅ ዋሽንግተን በሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ከፈጸሙት ድንቅ ተግባር በተጨማሪ፣ ሥልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ በመሆናቸውና በሰላማዊ መንገድ የሥልጣን ሽግግር በማድረጋቸው ታሪካዊ አሻራቸውን ትተዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት መፈንቅለ መንግሥትንና ሕገወጥ የሥልጣን ሽግግርን እንደሚያወግዘው ሁሉ፣ የኅብረቱ ኃላፊነትና ጠንካራ ወቀሳ መሪዎች በሥልጣን ዘመን እንዲገዙ ጫና በማድረግ የአፍሪካ ሕዝብን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ ማንም ሰው እስከ ሕይወቱ መጨረሻ ድረስ ፕሬዚንት ሊሆን አይችልም፡፡

ለአዲስ ደምና ሐሳብ ቦታ ስትሰጡ ነው ነገ አገራችሁን የተሻለ ማድረግ የምትችሉት፡፡ እኔ ገና ወጣት ነኝ ለማት እችላለሁ፡፡ ነገር ግን አዲስ ኃይልና ዕይታ ያለው ሰው በተሻለ ለአገሬ እንደሚጠቅም አምናለሁ፡፡ ለእናንተም ጠቃሚ ነው ቢያንስ በአንዳንድ አጋጣሚ፡፡

በሰላምና በደኅንነት ላይ

የአፍሪካ ዕድገት በሰላምና በደኅንነት ላይ ጭምር የሚመሠረት ነው፡፡ ምክንያቱም ለሰው ልጅ ክብር ወሳኙ ክፍል ደኅንነቱ መጠበቁና ከፍርኃት ነፃ መሆኑ ነው፡፡ በአንጐላ፣ በሞዛምቢክ፣ በላይቤሪያ፣ በሴራሊዮን ግጭቶች መቆማቸውንና የአገር ግንባታ መጀመሩን እያየን ነው፡፡

በሶማሊያ፣ በናይጄሪያ፣ በማሊና በቱኒዚያ አሸባሪዎች ንፁኃን ላይ ጉዳት እያደረሱ ነው፡፡ አብዛኞቹ እነዚህ አሸባሪ ቡድኖች እምነትን ሽፋን ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩት አፍሪካዊያን ሙስሊሞች እስልምና ማለት ሰላም መሆኑን ያውቃሉ፡፡

እነዚህን አሸባሪ ቡድኖች እንደ አልቃይዳ፣ አልሸባብ፣ ቦኮ ሐራም ነን የሚሉትን በሚገልጻቸው ድርጊታቸው ጨፍጫፊዎች ብለን ልንጠራቸው ይገባል፡፡

በእንደዚህ ዓይነት የሽብር ጥቃቶች ወቅት የአፍሪካ መንግሥታትና የአፍሪካ ኅብረት አመራራቸውን አሳይተዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ጦር በሶማሊያ በመሰማራቱ አልሸባብ ጥቂት የሶማሊያ ቦታዎችን ብቻ ነው መያዝ የቻለው፡፡ በተጨማሪም የሶማሊያ መንግሥት እየጠነከረ መጥቷል፡፡ በመካከለኛው አፍሪካም እንደዚሁ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል በመሰማራቱ የሎርድስ ሬዚስታንስ አርሚ አማፂ ቡድንን ማቀጨጭ ተችሏል፡፡ በቻድ ሐይቅ ተፋሰስ የአፍሪካ ኅብረትን ድጋፍ ያገኙ የተለያዩ አገሮች ወታደሮች ተሰማርተው ቦኮ ሐራምን እየተፋለሙ ነው፡፡ እናም ዛሬ የንፁኃን አፍሪካውያንን ሕይወት ለመታደግ እየለፉ ያሉትን ሁሉንም ጀግኖች ሰላም አስከባሪዎችን ልናመሰግናቸው ይገባል፡፡

የዓለም ኅብረተሰብ ይህንን የሰላምና የደኅንነት ሥራ መደገፍ መቻል አለበት፡፡ የዚህ ኃላፊነት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ የወደቀ ነው፡፡ በተመድና በአፍሪካ ኅብረት መካከል ያለውን ግንኙነት ከዚህ አኳያ መቃኘት በድጋሚ ማደስ ያስፈልጋል፡፡ አስተማማኝ የሆነ ድጋፍ የአፍሪካ ኅብረት ማግኘት በሚችልበት ሁኔታ አዲስ ግንኙነት መፈጠር አለበት፡፡

በደኅንነት ሥራዎች ላይ እንደምንመካከረውና የጋራ አቋም እንደምንይዘው ሁሉ፣ መልካም አስተዳደርን ለማሻሻል በምናደርገው ጥረትም መመሳሰል አለብን፡፡ ምክንያቱም መልካም አስተዳደርና የደኅንነት ሥራ የተያያዙ ናቸው፡፡ አለመረጋጋትንና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ምርጡ መሣሪያ መልካም አስተዳደር ነው፡፡

ለምሳሌ እውነተኛ የሕዝብ ተቃውሞዎችን በአግባቡ መመለስ ካልቻልን፣ አሸባሪዎች እንዲጠቀሙበት የተመቻቸ ሁኔታ በመፍጠር በሽብር ላይ የጀመርነው ትግል ሊንኮታኮት ይችላል፡፡ መተማመንን በማኅበረሰባችን ላይ ካልፈጠርንና የሕግ የበላይነትን ካላሰፈንን አሸባሪ ቡድኖች ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡

በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በዜጐች መካከል የተጀመረው የመነጋገር መንፈስ ሊቀጥልና አመራሮችም የሚስማሙበትና የሚቀበሉት ሆኖ ወደ ምርጫና ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ማለፍ አለበት፡፡ በማሊ አጠቃላይ የሰላም ስምምነቱ መተግበር መቻል አለበት፡፡    

በሱዳን ያሉ መሪዎች በሕዝባቸው ላይ በከፈቱት ጦርነት አገራቸው እንደማትለውጥ ሊያውቁ ይገባል፡፡ የዓለም ሕዝብ በሱዳን ዳርፉር የሆነውን መቼም አይረሳውም፡፡

በደቡብ ሱዳን የነፃነት ዝማሬ ለብጥብጥ እጁን ሰጥቷል፡፡ የደቡብ ሱዳን የነፃነት ጅማሬ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ተስፋ ውስጥ በከተተበት ስብሰባ ላይ በወቅቱ ነበርኩ፡፡ ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርም ሆኑ ዶ/ር ማቻር ሕዝባቸውን ከመከራ ማውጣት የሚችሉበት የፖለቲካ መግባባት ላይ አሁንም መድረስ አልቻሉም፡፡

የአካባቢውን አገሮች መሪዎች አግኝቼ አነጋግሬያቸዋለሁ፡፡ በውይይታችንም አሁን በደቡብ ሱዳን ካለው ሁኔታ አሳሳቢነት የተነሳ ፕሬዚዳንት ኪር እና ዶ/ር ማቻር መግባባት ላይ እንዲደርሱ እ.ኤ.አ. እስከ ኦገስት 17 ቀን 2015 ድረስ ጊዜ ሰጥተናቸዋል፡፡                

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ሒጂራ ባንክ የ143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዘገበ

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የዘሪሁን አስፋው ስሙር ምርምሮች

‹‹…በአንድ ጥራዝ ታትመው እንዲወጡ ያደረግሁት ለሥነ ጽሑፍ ተማሪዎች ስለደራሲዎችና...

ኢንቨስተሮች አደጋ ሲገጥማቸው ድጋፍ ማድረግ የሚያስችለው መመርያ ተሻረ

በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አደጋዎች በኢንቨስተሮች ንብረት ላይ አደጋ ቢከሰት፣...