ጌታቸው አምሳሉ የታክሲ አገልግሎት በመስጠት የሚተዳደር የአዲስ አበባ ነዋሪ ነው፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጋራ በመሆን በብሔራዊ ቤተ መንግሥት የሰጡትን መግለጫ ተከታትሏል፡፡ እምብዛም አላስደሰተውም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትን በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ይወርፋሉ የሚል ግምት ነበረው፡፡ ከኦባማ ይልቅ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በሙሉ ራስ የመተማመን መንፈስ የሰጡዋቸው ምላሾች ቀልቡን ስበውት እንደነበር ይናገራል፡፡ ‹‹አባማ እየተቆጠቡ ነበር›› በማለት፡፡
የዴሞክራሲ ንግርት በቻይና ግንብ
የአፍሪካ ኅብረት አዲሱ ዋና መሥሪያ ቤትና የሚያሸበርቅ አዳራሽ በ200 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በቻይና ዕርዳታ የተገነባ ነው፡፡ ጌታቸው በአፍሪካ ኅብረት ኦባማ ያደረጉትን ንግግርም አድምጧል፡፡ ይኼው ንግግራቸው ይበልጥ ደስታን ፈጥሮለታል፡፡ ‹‹እንግዲህ የሚገባቸው ከሆነ ቀስ አድርጐ የአፍሪካ መሪዎችን ልክልካቸውን ነግሯቸዋል፤›› ይላል፡፡ ለኦባማ ካለው አድናቆትና አሜሪካ በዴሞክራሲ ላይ ካላት አቋም አንፃር ከጠበቀው በታች የሆነበት ጌታቸው፣ የኦባማ የቤተ መንግሥት ውሎ በአፍሪካ ኅብረት የተካሰ ይመስለዋል፡፡
በአፍሪካ እየተከናወነ ያለው ሁለንተናዊ ለውጥ ዴሞክራሲን ወደ ጐን ያደረገ መሆን እንደሌለበት ኦባማ አስምረውበታል፡፡ በንግግራቸው መጨረሻ ‹‹ይገባኛል አንዳንድ አገሮች በዚህ ጉዳይ ላይ ዝምታን ይመርጣሉ፡፡ እንደዚያ መሆኑ ለአንዳንድ መሪዎች ምቾት ይሰጥ ይሆናል፤›› በማለት ፈገግ ብለው የቋጩት ወቀሳቸው ዴሞክራሲ ላይ ማዕከል ያደረገ ነበር፡፡ ሥልጣን በተቆጣጠሩ ጥቂት ወራት ውስጥ ወደ ተለያዩ አገሮች ባደረጉት የመጀመሪያ ጉዞ የጐበኟት ጋናን ጨምረው አንዳንድ የአፍሪካ አገሮችን በዴሞክራሲያዊ ለውጥ ላይ በምሳሌነት አንስተው፣ ኢትዮጵያን ሳይጠቅሱ አለፉ፡፡ በቤተ መንግሥት ‹‹በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጠ መንግሥት›› በሚለው ንግግር የኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች ቢበሳጩም የልባቸውን ያገኙ ይመስላል፡፡ ‹‹ዴሞክራሲ ማለት ምርጫ ማካሄድ ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ጋዜጠኞች ወደ እስር ቤት ከተወረወሩ፣ የመብት ተሟጋቾች ጫና ከተደረገባቸው፣ ሲቪክ ማኅበራት ሚናቸውን እንዳይጫወቱ ከተደረገ ዴሞክራሲ የይስሙላ እንጂ እውነተኛ አይደለም፤›› የሚለው ንግግራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጨምሮ በአዳራሹ ታዳሚዎች ከፍተኛ ጭብጨባ የታጀበ ነበር፡፡
‹‹ጋዜጠኞች ላይ ዕቀባ ከተጣለ ሕጋዊ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅስቀሳ ማድረግ ካልቻሉ፣ ኢትዮጵያ የሕዝቦቿን እምቅ አቅም በሙሉ ኃይል መጠቀም አትችልም፤›› በማለት የኢትዮጵያን መንግሥት በተመለከተ በቀጥታ ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡ በኦባማ መምጣት ዋዜማ የተፈቱት አምስት ጋዜጠኞችን ጨምሮ፣ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት አንዳንድ ጋዜጠኞች ለእስር መዳረጋቸው፣ ምርጫውም በበቂ ሁኔታ ፉክክርና በሚፈቅድና ተዓማኒነት ባለው ሜዳ አለመካሄዱን በመጥቀስ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምን ሸንቆጥ አድርገዋቸዋል፡፡ በዘንድሮ ምርጫ የአጋሮችን ጨምሮ ሙሉ ለሙሉ የፓርላማ ወንበሮችን የተቆጣጠረው ኢሕአዴግ አካሄድ፣ ጤነኛ ሒደት ስለመሆኑ ጥያቄ የተፈጠረባቸው በርካታ ዜጐችን ያስደስተ ንግግር ነበር፡፡
የኦባማ አጀንዳ
ፕሬዚዳንት ኦባማ በሥልጣን ላይ እያሉ ይኼንን የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ አምስተኛው ዙር ምርጫ ማግሥት በማድረጋቸው የመንግሥትን ተቃዋሚዎች ያስቀየመ ቢሆንም፣ ከአጀንዳዎች መካከል በአካባቢው ያለው ሽብርተኝነትና የደኅንነት ጉዳይ ይገኝበታል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ፣ በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን ቀውሶች ላይ ከአሜሪካ መንግሥት ነባር አጋር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መክረዋል፡፡
ዋነኛ አጀንዳቸው ግን ይህ አይመስልም፡፡ እሳቸው ራሳቸው ጉብኝታቸውን በተመለከተ በሰጡዋቸው መግለጫዎች፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት የጉብኝቱ ዋና ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
የቢቢሲ የሰሜን አሜሪካ ጋዜጠኛ ጆን ሶፔል ጉብኝታቸውን አስመልክቶ ፕሬዚዳንት ኦባማን፣ ‹‹ከአዲስ አበባ ለአፍሪካ የሚያስተላልፉት መልዕክት ቻይና በገነባችው ሕንፃ ውስጥ ሆነው ነው?›› በማለት ጥያቄ ያቀረበላቸው፣ ‹‹የቻይናን እንቅስቃሴ ለመግታት አይደለም ወይ?›› የሚል ይዘት ያለው ነበር፡፡
የታክሲው ሾፌር ጌታቸውም ተመሳሳይ ጥያቄ አንስቶአል፡፡ ‹‹አሜሪካውያን ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች እያሉ ከጨዋታ ውጪ ሆነዋል፡፡ እኔ የምለው ኦባማ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ልማት አድንቀዋል፡፡ ታዲያ ቻይና በሠራልን ኤርፖርት አርፈው፣ ቻይና በሠራልን መንገድ ተጉዘው፣ ቻይና በሠራው ሕንፃ ላይ ተስተናግደው አይደል እንዴ የሄዱት?›› በማለት ጥያቄ ያነሳል፡፡ አሜሪካ የዴሞክራሲ ጥያቄ ታንሳ እንጂ፣ ‹‹ማን ላይ ሆነሽ ማንን ታሚያለሽ?›› ሆኖባታል፡፡
ጋዜጠኛው ላቀረበላቸው ጥያቄ የፕሬዚዳንት ኦባማ ምላሽ ቀላል ነበር፡፡ ‹‹ቻይናውያን ለዘመናት የተትረፈረፈ ሀብት አላቸው፡፡ ያለተጠያቂነት በአፍሪካ እያራገፉት ይገኛሉ፤›› በማለት እምብዛም ግን ተቃውሞ እንደሌላቸው፣ እንዲያው ለወደፊቱ በአፍሪካ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የጋራ ምክክር ለማድረግ እንደሆነ ሐሳብ እንዳላቸው ነበር የገለጹት፡፡
አዲስ ምዕራፍ ወይስ አዲስ ትግል?
112 ዓመታት ያስቆጠረውና በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ቁንጮ ላይ ደርሶ የነበረው የኢትዮ – አሜሪካ ግንኙነት በሶሻሊስቱ ደርግ ጭራሹኑ ተዳክሞ ነበር፡፡ በኢሕአዴግ ዘመንም በመጀመሪያ የሥልጣን ዓመታት መልካም የሚባል አቅጣጫ ይዞ የነበረ ቢሆንም፣ የኋላ ኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት የአሜሪካ መንግሥት ካስቀመጣቸው የዴሞክራሲ አቅጣጫ ውጪ በመጓዙ ንትርኩ ቀጥሎ ነበር፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአሜሪካ መንግሥት፣ የፋይናንስ ተቋማቱና መቀመጫቸውን እዚያው አሜሪካ ያደረጉ እንደ ሒውማን ራይትስ ዎች የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ላይ በከፈቱት የቃላት ጦርነት ግንኙነቱ ሻክሮ ነበር፡፡ እስከ 1997 ዓ.ም. ድረስ የአሜሪካ መንግሥት ተቃዋሚዎችን ይዞ የመንግሥት ለውጥ ለማድረግ ይታትር እንደነበር መንግሥት ይተቻል፡፡
ደርግን የጣለው የኢሕአዴግ ሥርዓትም ከሁሉም የዓለም መንግሥታት ጋር መልካም ግንኙነት የፈጠረ ቢመስልም፣ የኒዮ ሊብራሊዝም አራማጆች የሚላቸውን የምዕራባውያን ኃይሎች በጠላትነት በመፈረጅ ፊቱን ወደ ምሥራቁ ዓለም ያዘነበለ ነበር፡፡
የአፍሪካ ያልተነካ ሀብትን ለመጠቀምና የተትረፈረፈ ምርቷን ማራገፊያ ፍለጋ ላይ የነበረችው ቻይና ክፍተቱን በመጠቀም፣ ኢትዮጵያን ትልቅ አጋር አገኘች፡፡ በአፍሪካ ከሚገኙት ግንባር ቀደም ወዳጆች መካከል ኢትዮጵያን ዋነኛ ያደረገችው ቻይና፣ የልማት ዕርዳታና ቀጥታ ኢንቨስትመንቷን በኢትዮጵያ ማፍሰስ ተያያዘችው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹ልማታዊ መንግሥት›› በሚል የተከተለው የልማት አቅጣጫም በቻይናና መሰል አገሮች ደጋፊነት የተመሠረተ ሲሆን፣ ለተከታታይ አሥር ዓመታት የሁለት አኃዝ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማምጣት ፈጣን ልማት ማስመዝገብ ተያያዘው፡፡ የቻይና አጠቃላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት በአሁኑ ወቅት 17 ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን፣ ኦባማ በተናገሩበት በዚሁ የአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ባለፈው ዓመት ንግግር ያደረጉት የቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪኪንግ፣ እ.ኤ.አ. በ2020 በአፍሪካ የቻይና ጠቅላላ ኢንቨስትመንት 100 ቢሊዮን ዶላር በማድረስ በወቅቱ ከነበረው እጥፍ ለማድረግ አገራቸው ማቀዷን ተናግረው ነበር፡፡ ኦባማም ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብትን አስመልክተው ንግግር ያደረጉበት ይኼው የቻይና ሥሪት አዳራሽ በመሆኑ፣ ቻይና በአፍሪካ ያላትን ዕቅድ ሳያስተውሳቸው አይቀርም፡፡
በ2000 ዓ.ም. የተመሠረተውና በየሦስት ዓመቱ የሚካሄደው የቻይና አፍሪካ ትብብር መድረክ (ፎካክ)፣ ቻይና በአኅጉሪቱ ያላት የኢንቨስትመንትና የንግድ ግንኙነት የሚመከርበት ሲሆን በነዳጅ ፍለጋ፣ በኮንስትራክሽን፣ በቆዳና በቆዳ ውጤቶች፣ በጨርቃ ጨርቅና በሌሎች መስኮች ቻይና በስፋት እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡
የቡሽ አስተዳደርን ጨምሮ በቀደሙት የአሜሪካ አስተዳደሮች በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የሚያወጡዋቸው የሰብዓዊ መብት ሪፖርቶችና ወቀሳዎች፣ በኢትዮጵያና በአሜሪካ መንግሥት መካከል ይኼ ነው የሚባል የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት እንዳይኖር የዘጉ ይመስላሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአሜሪካን ኃያልነት እየተፎካከረች ያለችው ቻይና፣ ያለምንም ተቀናቃኝ ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረገ በአፍሪካ የምታደርገው እንቅስቃሴ ግን አሜሪካን እንቅልፍ የነሳት ይመስላል፡፡
በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው በኢትዮጵያ የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ዴቪድ ሺን ባለፈው ዓመት ባቀረቡት ትዝብት፣ ‹‹እጅግ ፈጣን በሆነ ጉዞ ቻይና በኢትዮጵያ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ ኢትዮጵያም በምዕራባውያን ምትክ ቻይናን እንደ ትልቅ አማራጭ ማየት ችላለች፤›› ብለው ነበር፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም ይህንን በማስመልከት ለዘ አይሪሽ ታይምስ፣ ‹‹ቻይና በኢትዮጵያ ያላት ፍላጐት እንደ ተዓምር የመጣ ነው፡፡ የእኛ የአያያዝ ጥያቄ ነው፡፡ በደንብ የያዛቸው ይጠቀማል፡፡ በአግባቡ መያዝ ያልቻለ አይጠቀምም፤›› ብለው ነበር፡፡ የቻይና ኢንቨስትመንት በዘላቂነት የሌሎች አገሮችን ኢንቨስትመንት እንደሚስብ በመተንበይ፡፡
ቀደም ሲል አፍሪካ ‹‹ተስፋ የሌላት›› አኅጉር እንዳልተባለች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ‹‹እየተስፈነጠረች ያለችው ኮከብ›› የሚሉ ቅጽል ስሞች እየተሰጣት ነው፡፡
ጌዲዮን ጃለታ በኢራስመስ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪውን በመሥራት ላይ ያለ ወጣት ነው፡፡ የአፍሪካና የቻይና እንዲሁም የኢትዮጵያ ግንኙነት ላይ ተደጋጋሚ ጥናት በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ‹‹አሜሪካም ቻይናም አፍሪካን የሚፈልጉት ለንግድ ልውውጥ ብቻ ሳይሆን፣ ኩባንያዎቻቸው ኢንቨስት የሚያደርጉበት ትክክለኛ ቦታ በመሆኑ ነው፤›› ይላል ለሪፖርተር ሲናገር፡፡
‹‹ቻይና አፍሪካ ውስጥ ያለውን መልካም ዕድል ቀድማ በመጠቀም ተወዳዳሪ የላትም፤›› ይላል ጌዲዮን፡፡ እ.ኤ.አ. በ1980 አንድ ቢሊዮን ዶላር የነበረው የቻይና አፍሪካ የንግድ ልውውጥ፣ በ2000 ወደ 11 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱን፣ እንዲሁም በ2013 ወደ 225 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱን በማስረጃነት በመጥቀስ፡፡
የገበያው ፉክክር
በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ የተጠመደችው አሜሪካ በአፍሪካ ያለውን ገበያ ለመጠቀም አስባ አልነበረም፡፡ ቻይና በመንገድ መሠረተ ልማት፣ በኢነርጂ፣ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሙሉ ለሙሉ ስትንቀሳቀስ የቆየች ሲሆን፣ ከአንድ ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት የቻይና ፕሬዚዳንትም ተጨማሪ 16 ስምምነቶችን አድርገው ነበር የተመሰሉት፡፡
በተመሳሳይ ወቅት አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ጆን ኬሪ ድንገተኛ በሚባል ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ የላከች ሲሆን፣ አሜሪካ በቻይና እንቅስቃሴ ጭንቀት ውስጥ ለመግባቷ አመላካች ነበር ይላሉ የፖለቲካ ተንታኞች፡፡
የፖለቲካል ሳይንስ ምሁርና ነባሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ‹‹ፉክክሩ ከተጀመረ ቆየ፡፡ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ባገኙን አጋጣሚ የቻይናን እንቅስቃሴ ያነሱልናል፡፡ አሁንም ኦባማ ቻይናን ለመግፋት እንደመጡ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን የአሜሪካን ዕቃዎች ኢትዮጵያ ውስጥ አጥለቅልቀው የቻይናን ከገበያ ውጪ ያደርጋሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፤›› ይላሉ፡፡
ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት በአሜሪካ መምጣት የሚያሰጋው እንዳልሆነ ሁለት ምክንያቶች ይጠቅሳሉ፡፡ የቻይና ኢንቨስትመንት በምንም ዓይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ ቅድመ ሁኔታ የማይጠይቅ በመሆኑና የምታመርታቸው ዕቃዎች ዋጋ የኢትዮጵያን ሕዝብ የመግዛት አቅም ያገናዘበ በመሆኑ ነው፡፡ ኦባማ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ መለሳለሳቸው ይህ የቻይናና የኢትዮጵያ ግንኙነት ጫና እንደፈጠረባቸው አመላካች ነው ይላሉ፡፡ ሆኖም የሁለቱም አገሮች የኢንቨስትመንት አቅጣጫ ለየቅል መሆኑን ያክላሉ፡፡
የቻይና የመንግሥት ኩባንያዎች ኢንቨስትመንት አደጋን (ሪስክ) ለመጋፈጥ ድፍረት ያላቸው ሲሆኑ፣ በተቃራኒው የአሜሪካ ኩባንያዎች የግል መሆናቸውና ይህንን አደጋ በቀላሉ ለመቀበል የሚቸገሩ መሆናቸውን በማስቀመጥ፣ ‹‹ኦባማ ቻይናን ለመግፋት እንደመጡ ይታወቃል፡፡ ውጤቱ ግን ቻይና የበለጠ እንድትገባ ያደርጋታል፤›› ብለዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለውጥ
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢሕአዴግ በዘንድሮ ምርጫ ከነአጋሮቹ የፓርላማ ወንበሮችን ጠቅልሎ በመውሰድ አምባገነንነቱ የለየለት ሆኗል ብለው ያምናሉ፡፡ የተወሰኑት የምርጫውን ውጤት ባለመቀበል አሁንም እየተቃወሙት ሲሆን፣ ለይቶላቸው ያሉት እንደ ግንቦት ሰባት የመሳሰሉም የትጥቅ ትግል መጀመራቸው እየተናገሩ ነው፡፡
ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የትጥቅ ትግሉ መሪ (በኢትዮጵያ የሞት ቅጣት የተወሰነባቸው) ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ወደ አስመራ በተጓዙበት ማግሥት ነው፡፡
በመሆኑም የኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝት ተቃዋሚዎችን እጅግ ያስደነገጠ ይመስላል፡፡ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት የኦባማ መለሳለስም ከዚሁ የባሰ ያበሳጫቸው መሆኑን ከሚሰጡ አስተያየቶች መገንዘብ ይቻላል፡፡ ዶ/ር መረራ ግን ኦባማ ይዘውት የመጡት አጀንዳ ከዚህ የተለየ በመሆኑ እምብዛም አያስጨንቃቸውም፡፡ አሜሪካውያን የራሳቸው ጥቅም እንደሚያስቀድሙ በማስገንዘብ፣ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ዓላማ ሽብርና ንግድ እንጂ ዴሞክራሲ አይደለም ይላሉ፡፡ ‹‹በዚሁ ምርጫ ማግሥት መምጣታቸው የሚጠበቅ አልነበረም፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ንግግራቸውን ግን ወድጄዋለሁ፡፡ እንደ መሪ ማለት ያለባቸውን ብለዋል፡፡ ጆሮ ካላቸው ነግረዋቸዋል፡፡ የእኛም ጠቅላይ ሚኒስትር እዛው ነበሩ፤›› ብለዋል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ለውጥ እንዳለ ተጠይቀው፣ ‹‹የቻይና ወደዚህ መምጣት ጫና እንደፈጠረባቸው ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ድሮም ፈረንጆች ራሳቸው የረዳቸውን ነው የሚረዱት፡፡ እንዲደግፉን እንጂ ዴሞክራሲ ከአሜሪካ ተጭኖ እንዲመጣልንም አንጠብቅም፡፡ እንደሱ የሚመኙ ሞኞች ናቸው፡፡ ኦባማ አሉም አላሉም ሰላማዊ ትግሉ ይቀጥላል፡፡ ተስፋ የሚያስቆርጥ ምንም ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡
በአሜሪካ በኩል የውጭ ግንኙነት ለውጥ ስለመኖሩ በተመለከተ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ታየ አፅቀሥላሴ በበኩላቸው፣ ምንም ዓይነት ለውጥ እንዳላዩ ይናገራሉ፡፡
‹‹ትኩረት በመስጠትና በቅደም ተከተል ላይ ልዩነት ቢኖርብንም፣ የመጨረሻ ግባችን አንድ ዓይነት ዴሞክራሲ መሆኑን የተገነዘቡ ይመስላል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁለንተናዊ ለውጥና እየገጠመን ያለውን ፈተናም በውል እንዲገነዘቡ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፤›› ብለዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግር በማመን፡፡
ኦማር መሐመድና ሊሊ ኮዩ በምሥራቅ አፍሪካ ከናይሮቢና ከዳሬሰላም በመሆን በተለይ ቻይናን በተመለከተ የሚዘግቡ ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ “In Ethiopia Obama and the US Stand in China’s Long Shadow” በሚለው ጽሑፋቸው፣ ‹‹ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በቻይና በተገነባው አዳራሽ ውስጥ ሆነው ነበር ንግግር ያደረጉት፡፡ ንፅፅሩ አሜሪካ በአፍሪካ የምታደርገው እንቅስቃሴ ምን ያህል ፈታኝ እንደሚሆንባት አመላካች ነው፡፡ ኦባማ በአኅጉሪቱ ተወዳጅ ቢሆኑም እሳቸውም ሆኑ አገራቸው ፉክክር እያደረጉ ያሉት ከቻይና ጋር ነው፤›› በማለት ሐሳባቸውን ይቋጫሉ፡፡