Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ለሁለት ለመክፈል ታስቧል

የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ለሁለት ለመክፈል ታስቧል

ቀን:

መንግሥት ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ለሁለት ከፍሎ በሚኒስትር መሥሪያ ቤት ደረጃ ሊያዋቅር ማሰቡ ተሰማ፡፡

የመንግሥት አዲስ ሐሳብ ውኃና መስኖ ለብቻ፣ ኢነርጂን ደግሞ እንዲሁ ለብቻው በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ ማዋቀር ነው፡፡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደገለጹት፣ ሁለቱም ዘርፎች እጅግ ሰፋፊ ሥራዎች የሚካሄድባቸውና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ከሁለቱም ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት የሚጠበቅ በመሆኑ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ጉዳዩ በከፍተኛ ባለሙያዎች እየታየ ሲሆን፣ በቅርቡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች አመልክተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ‹‹ማንም ሰው ሐሳብ ሊያነሳ ይችላል፡፡ ጊዜው ገና ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት አልሰጥም፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ነግረዋል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚቀርቡለትን ሁለት መዋቅሮች የሚያፀድቅ ከሆነ፣ የውኃና መስኖ ሚኒስቴር ትኩረቱን ሙሉ ለሙሉ ንፁህ የመጠጥ ውኃ ሽፋንን ለማሳደግ የአገሪቱን ግብርና ከዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅ ላይ ያደርጋል ተብሏል፡፡

በተጠናቀቀው የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ሚኒስቴሩ ለ29 ሚሊዮን ሕዝብ ንፁህ የመጠጥ ውኃ ማቅረብ መቻሉ ተገልጿል፡፡ በ2006 ዓ.ም. ንፁህ የመጠጥ ውኃ ሽፋን በገጠር 75.5 በመቶ፣ በከተማ ደግሞ 84.1 በመቶ፣ በአገር አቀፍ ደረጃም አጠቃላይ ንፁህ የመጠጥ ውኃ ሽፋን 76.7 በመቶ መድረሱን ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ባወጣው ሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ሰነድ ላይ ተገልጿል፡፡

በመስኖ በኩልም በአገር አቀፍ ደረጃ 679,352 ሔክታር መሬት በመካከለኛና በሰፊ መስኖ ለማልማት የሚያስችል ጥናትና ዲዛይን ተሠርቷል፡፡ በዕቅድ ዘመኑ አራተኛ ዓመት በሆነው በ2006 ዓ.ም. 199,304 ሔክታር መሬት በመካከለኛና በሰፊ መስኖ ፕሮጀክቶች መልማቱን ሰነዱ አረጋግጧል፡፡

እንደ አዲስ ይቋቋማል ተብሎ የታሰበው የውኃና መስኖ ሚኒስቴር በዚህ መስክ ብዙ ሥራ የሚጠብቀው መሆኑን፣ አገሪቱን ከዝናብ ጥገኝነት ወደ መስኖ ግብርና ልማት ማሸጋገር እንደሚጠበቅበት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ለኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ ደግሞ የኢነርጂ ሚኒስቴር እንደሚቋቋም ይጠበቃል፡፡ በዚህ ዘርፍ በመጀመርያው ዕቅድ ዘመን በርካታ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ሆነዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ፊንጫ አመርቲነሽ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ አሸጎዳ፣ አዳማ ቁጥር አንድና ቁጥር ሁለት የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች ተጠናቀው ኃይል ማመንጨት ጀምረዋል፡፡

ወደ ሁለተኛው ዕቅድ ዘመን የተሸጋገረውና በ2008 ዓ.ም. የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚጀምረው ጊቤ ሦስትና ታላቁ የህዳሴ ግድብም ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ኃይል ማመንጨት ይጀምራል ተብሏል፡፡

በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን ብቻ ሰባት ሺሕ ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት ዕቅድ ተይዟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በገጠሩ የአገሪቱ ክፍል ከታዳሽ የኃይል ምንጮች ማለትም ከፀሐይ ኃይል፣ ከባዮጋዝ፣ ከአነስተኛ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን በመጠቀም የገጠሩን የኤሌክትሪክ ሽፋን ከፍ ማድረግ ታቅዷል፡፡

እነዚህን ግቦች አንግቶ በርካታ ሥራዎችን ይሠራል ተብሎ የሚጠበቀው ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአማራጭ የኃይል ምንጮችና (ከውኃ ከንፋስ ከጂኦተርማል) በተጨማሪ የተፈጥሮ ነዳጅ ፔትሮሊየም ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚጠበቅበት ተመልክቷል፡፡

የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በድጋሚ የተዋቀረው በመጀመርያው የዕድገት ዘመን መጀመርያ በ2003 ዓ.ም. ነበር፡፡ በወቅቱ የውኃ ሀብት ልማት ሚኒስቴር ከማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፉን በመውሰድ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተብሎ ተቋቁሞ እንደነበር ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...