ከመጪው ሐምሌ 30 እስከ ነሐሴ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በሚዘልቀው የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች በአዲስ አበባ በሚያደርጉት ድርድር፣ አዲስ ነገር እንደሚፈጠርና ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሰደር ተወልደ ሙሉጌታ አስታወቁ፡፡
አምባሳደሩ ይህን ያስታወቁት ባለፈው ዓርብ ሐምሌ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ከደቡብ ሱዳን ድርድር በተጨማሪ ከፊታችን ነሐሴ 6 እስከ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ስለሚከበረው የመጀመርያው አገር አቀፍ የዳያስፖራ በዓል አከባበር፣ እንዲሁም ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ጉብኝት ስላደረጉት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራኮ ኦባማ ጉብኝት ውጤት አብራርተዋል፡፡
የደቡብ ሱዳን ግጭትን በተመለከተ በአገሪቱ በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት ግጭቶችን ለማስቆምና አገሪቱ ወደ ሰላም እንድትመለስ ለማድረግ፣ በኢጋድ አደራዳሪነት የተለያዩ ድርድሮች ሲካሄዱ መቆየታቸውን የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአገሪቱ እየተካሄደ ያለው ግጭት እስካሁን ምንም ውጤት እንዳላስገኘ አምባሳደር ተወልደ አስረድተዋል፡፡
በዚህም ምክንያት ቻይና፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ኖርዌይ፣ የአፍሪካ ኅብረትና የአውሮፓ ኅብረትን በአባላትነት ያካተተው ኢጋድ ፕላስ የሚባለው አደራዳሪ ቡድን ተግቶ ሲሠራ መቆየቱን፣ በቅርቡም የመቻቻል (Compromise) ሰነድ ማዘጋጀቱንና ተፋላሚ ወገኖቹ እንዲወያዩበት መላኩን አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡
‹‹ከሐምሌ 30 ቀን እስከ ነሐሴ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የጋራ መደበኛ ስብሰባ እዚህ አዲስ አበባ፣ በዚሁ ሰነድ ላይ ተወያይተው ወደ አንድ ስምምነት ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡
በመቀጠልም ከሁለቱ ወገኖች ውይይት በኋላ ‹‹ልዩነቶች ካሉ ነሐሴ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚደረገው የኢጋድ ፕላስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የበለጠ በቀሩት ጉዳዮች ላይ እንዲግባቡ ጥረት ይደረጋል፤›› ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ውይይት ላይ መፍትሔ ካልመጣ ደግሞ ወደ መሪዎቹ ደረጃ ውይይቱ እንደሚሻገር ገልጸው፣ ነሐሴ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚካሄደው የመሪዎች ውይይት ስምምነትና እርቅ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
በዚያ ቀን ስምምነት ላይ ካልደረሰሱ ምን ይደረጋል ለሚለው የሪፖርተር ጥያቄ፣ ‹‹ወደ ስምምነቱ ይመጣሉ የሚል ዕምነት አለ፡፡ ነገር ግን ወደ ስምምነቱ መምጣት አለባቸው የሚለው ላይ ማስመሩ ጥሩ ይመስለኛል፤›› በማለት መልሰዋል፡፡
የዳያስፖራ በዓልን በሚመለከት ‹‹ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በሚሳተፍበት ከነሐሴ 6 እስከ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ይከናወናል፤›› ብለዋል፡፡
በዚህ የዳያስፖራ በዓል ላይ ለመታደም ከተለያዩ የዓለማችን ከፍሎች ከ6,000 በላይ የእንግዶች እንደሚመጡ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ለበዓሉ ወደ አገር ቤት መግባት የጀመሩ እንግዶች መኖራቸውም እንዲሁ ተገልጿል፡፡
በዓሉ የሚከበረው ‹‹ሁሉም ለህዳሴ›› በሚል መሪ ቃል ነው፡፡ ኤግዚቢሽኖች፣ የፓናል ውይይቶችና ጉብኝቶች፣ እንዲሁም ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የሚደረጉ ውይይቶች የበዓሉ አካል መሆናቸውን አምባሳደር ተወልደ አስረድተዋል፡፡