Wednesday, February 28, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ከባዕዳን ይልቅ ሕዝብን ማዳመጥ ያዋጣል!

በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጉብኝት ምክንያት የዓለም የዓይን ማረፊያ የነበረችው አገራችን፣ እንግዳዋን ሸኝታ ወደ መደበኛ ተግባርዋ ተመልሳለች፡፡ በፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ወቅት ባለድርሻ አካላት የነበሩ ወገኖችም እንደ ፍላጎታቸውና እርካታቸው መሳካት መጠን በጉብኝቱ የተገኘውን ውጤት እያሰሉ ወደ ወትሮው እንቅስቃሴያቸው ተመልሰዋል፡፡ የሕዝብ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ያለበት መንግሥትም እንደዚሁ፡፡ እንግዳው ከተሸኙና ግምገማው ሲካሄድ ግን መንግሥት በአንክሮ ማሰብ ያለበት፣ ከባዕዳን ይልቅ ሕዝብን ማዳመጥ አዋጭ መሆኑን ነው፡፡ ባዕዳን ሲያሞግሱም ሆነ ሲነቅፉ ከጊዜያዊው ወዳጅነት ባሻገር ያለውን ዘለቄታዊ ጥቅማቸውን እያሰሉ ነው፡፡ ጠቃሚ ነጥቦችን ማንሳት አለብን፡፡

  1. መንግሥት ሕዝቡን ያዳምጥ

የፕሬዚዳንት ኦባማ ጉብኝት ከታቀደበት እስከመጡበት ጊዜ ድረስ መታዘብ የተቻለው የሁለት ጎራዎችን ወግ ነው፡፡ በመንግሥት ወገን ያለው ኦባማን እያንደረደረ ወደ ኢትዮጵያ ያመጣቸው አገሪቱ ያስመዘገበችው ተከታታይ ፈጣን ዕድገትና ስኬት መሆኑን በተደጋጋሚ አስገንዝቧል፡፡ ለጊዜው ለይቶለት ጽንፍ ውስጥ የገባውን የተቃውሞ ጎራ “ወደ ኢትዮጵያ አይሂዱ” የሚለውን ጨለምተኛ አስተሳሰብ ትተን፣ ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ ሲሄዱ የመንግሥትን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ዴሞክራሲ መቀልበስ “አንድ ይበሉልን” ያለው ወገን ድምፅ በስፋት ተሰምቷል፡፡ የሁለቱን ጎራዎች ሙግት አንድ ላይ አጭቆ ሲተነትን የነበረው ዓለም አቀፍ ሚዲያ የአገሪቱን አስደማሚ ዕድገት በለፈፈበት አፉ፣ የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ ነገር “ተከድኖ ይብሰል” ሲል በተደጋጋሚ አስተጋብቷል፡፡

ፕሬዚዳንት ኦባማ ኢትዮጵያ ደርሰው በአደባባይ ባደረጉዋቸው ሁለት ንግግሮች እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ አስተያየቶች ሰጥተዋል፡፡ በመጀመሪያው ንግግር “በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግሥት”፣ “የማይታመን ዕድገት ያስመዘገበች አገር”፣ “የአካባቢውን ፀጥታ ለማስከበር ጠንካራና ብርቱ ተዋጊዎች…”፣ ወዘተ የሚሉ ውዳሴዎች አቅርበዋል፡፡ በሁለተኛው ቀን ለ54 የአፍሪካ መንግሥታት ተወካዮች፣ ለሲቪል ማኅበረሰብ አባላትና ለወጣቶች ባደረጉት ንግግር የአፍሪካ መሪዎችን ሸንቁጠዋል፡፡ የሥልጣን ጥመኞችና በሙስና የተዘፈቁ በማለትም ወርፈዋል፡፡ በግልጽ ኢትዮጵያንም አንስተዋል፡፡ ይኼ ሽንቆጣ ሁሉንም የሚመለከት በመሆኑ የትናንቱ ውዳሴና የማግሥቱ ውረፋ የተደበላለቁ ስሜቶችን ፈጥረዋል፡፡

መንግሥት ፕሬዚዳንቱን ተቀብሎ ካስተናገደ በኋላ ቆም ብሎ ማሰብ ያለበት ከሕዝብ በላይ ማንም አለቃ እንደሌለው ነው፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ማረጋገጥ አለበት፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ስለሰብዓዊ መብት፣ ስለዴሞክራሲና ስለሙስና ሲናገሩ በአንድ ጊዜ ሁሉንም ማስደሰት ወይም ማበሳጨት ባይችሉም፣ በአድማጮቻቸው ዘንድ (በተለይ በወጣቶች ላይ) ተፅዕኖ ፈጥረዋል፡፡ ይኼም በትክክል ታይቷል፡፡ መንግሥት ሰብዓዊ መብትንና ዴሞክራሲን በተመለከተ የአገሪቱን ታሪካዊ ዳራ እየጠቀሰ አሁንም ጊዜ የሚፈጅ ነው እያለ ከመጣው ከሄደው ጋር ከሚነታረክ፣ ከዚህ ጨዋና ኩሩ ሕዝብ ጋር በሀቅ ተቀምጦ ቢመክር ይሻለዋል፡፡ ኦባማ የተለመደውን የአሜሪካ ጥቅም ለማስከበር ቴአትር የመሰለ ዲስኩር ሲያደርጉ፣ መንግሥት ደግሞ በዓለም ፊት የሚያስከብረውን ድርጊት በመፈጸም አደባባይ መውጣት አለበት፡፡ ‘የተቃውሞ ፖለቲካን ታፍናላችሁ፣ ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን ታስራላችሁ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ትጥሳላችሁ፣’ ወዘተ እየተባለ የወሬ ማዳመቂያ ከመሆን ይልቅ፣ በሕዝብ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ሥርዓተ መንግሥት እንዲኖር ማድረግ ያዋጣል፡፡

ሕዝብ በነፃነት ካልኖረ፣ የመሰለውን ሐሳብ ካላራመደ፣ የሚፈልገውን በነፃነት ካልመረጠ፣ በአመለካከቱ ምክንያት የሚደበደብ፣ የሚታሰርና የሚንገላታ ከሆነ፣ ከሥራና ከመኖሪያ ቀዬው ከተፈናቀለ እሪታውና ጩኸቱ ይቀጥላል፡፡ ሕዝብ በመንግሥት ፖሊሲዎችና ሕጎች ዝግጅቶች ላይ በቀጥታም ሆነ በውክልና ተሳታፊ ካልሆነ፣ በሥልጣን የሚባልግ ሹማምንት የሚፈነጩበት ከሆነ፣ በየደረሰበት ጉቦ ካልሰጠ ጉዳዩ ካልተስተናገደ፣ የመደራጀት መብቱ ከተገደበ፣ በገዛ አገሩ የበይ ተመልካች ከሆነና ምሬቱ ጣሪያ ከነካ ጩኸቱ የትም ድረስ ይሰማል፡፡ ጩኸቶችን አልሰማ ያለው መንግሥት ብቻ ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች ፈር አስይዞ አገር ማስተዳደር የመንግሥት ዋነኛ ተግባር ሆኖ ሳለ፣ ሰብዓዊ መብትን ለማክበርና ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ አሁንም ብዙ ይቀራል ብሎ መናገር ያስተዛዝባል፡፡ ሕዝብ ሁሉንም ነገር ያውቃል፡፡ አገሩ ስትለማ እየራበውም ቢሆን ይታገሳል፡፡ ነገን ተስፋ ያደርጋል፡፡ በሙሰኞችና በደንታ ቢሶች ምክንያት ግን ሲራብና ሲጠማ ይጮሃል፡፡ መብቱ ሲረገጥና ሲንገላታ፣ እንዲሁም ሲታሰርና ሲሰደድ ጩኸት ወደ አመፅ ይለወጣል፡፡ መንግሥት ሕዝብን እንደ አለቃው መመልከት ትቶ ችላ ሲለውና ለክፉዎች አሳልፎ ሲሰጠው ችግር ይፈጠራል፡፡ ኦባማ የአገራቸውን ሕዝብ ጥቅም አስቀድመው ከዘለቄታው ጥቅም አንፃር ሁሉንም ነገር በሆዳቸው አምቀው መያዛቸውን መዘንጋት ሞኝነት ነው፡፡ ግብር ከፋዩ የአሜሪካ ሕዝብ ከኦባማ ጉብኝት ተጠቃሚ መሆኑን ማረጋገጥ ይፈልጋል፡፡ በእሳቸው ውዳሴና ፈገግታ የተዘናጉ ካሉ ራሳቸውን ደጋግመው ይፈትሹ፡፡ እዚህ አገር ሕዝብን ማዳመጥ ነውር የሆነ ይመስል ባዕዳንን መመልከት ይብቃ፡፡ የሕዝብ ጥቅም ይቅደም፡፡ ሕዝብ ይደመጥ፡፡

  1. ማንም ቢመጣ ጥቅሙን አነፍንፎ ነው

ከኢትዮጵያ አኩሪ ታሪኮች መካከል አንዱ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ በዓደዋ በኮሎኒያሊስቶች ላይ የተገኘው ታላቅ ድል ነው፡፡ በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦችን ለታላቅ የነፃነት ተጋድሎ ያነቃቃ አኩሪ ታሪክ ባለቤት የሆነች አገር፣ በውስጥ ሲካሄድ በነበረው የዘመናት የእርስ በርስ ሽኩቻ ምክንያት ወደኋላ ብትቀርም አሁን አንገቷ ቀና እያለ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ ድንበሯን ሳታስደፍር የቆየች አገር ለበርካታ ዘመናት ገጽታዋ ተበላሽቶ የረሃብ፣ የልመና፣ የበሽታና የኋላቀርነት ተምሳሌት ሆና ቆይታለች፡፡ አሁን ያ የጨፈገገ ገጽታ ማንፀባረቅ ሲጀማምረው ተመልካቿ በዝቷል፡፡ በአሁኑ ዘመን ቻይና፣ ቱርክ፣ ህንድ፣ አውሮፓና አሁን ደግሞ በስፋት አሜሪካ አነጣጥረውበታል፡፡ ከዓለም ጋር ተባብሮ መበልፀግ ጥሩ ነው፡፡ ይህች ታሪካዊት አገር እንደ ንስር አንሰራርታ ስትነሳ ጥቅማቸውን መነሻ ያደረጉ ሁሉ እየመጡባት ነው፡፡ ደስ ይላል፡፡ ይኼ ደስታ ግን ጥንቃቄ ያሻዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሀብቶቿ ሕዝቧና የተፈጥሮ ፀጋዎቿ ናቸው፡፡ ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂ ታግዘው የሚመጡ የውጭ ሸሪኮችን ማስተናገድ ተገቢ ነው፡፡ ጠቃሚም ነው፡፡ ነገር ግን ቅድሚያ ለአገሪቱ ልጆች ይሰጥ፡፡ የሀብት፣ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያ ጀርባ ያለውን ፍላጎት ያጤነና ሚዛናዊ የሆነ ፖሊሲ አስፈላጊ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ከፋፍቶ በኋላ ማጣፊያው ቢያጥር የምትጎዳው አገር ናት፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች፣ የተማሩ ወጣቶች፣ ለአገራቸው ዕድገት ድርሻ የሚያበረክቱ ዳያስፖራዎችና ሌሎች ወገኖች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ይስተናገዱ፡፡ “የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ” እንደሚባለው አገራችን ውስጥ ሊኖር የሚችለው ሥራ ፈጣሪነት፣ የቴክኖሎጂ አመንጪነትና ሌሎች ዕውቀቶች ዕድል ይሰጣቸው፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮችም በሕጉ መሠረት በአግባቡ ይስተናገዱ፡፡ በዓለም ላይ በተለያዩ ሥፍራዎች የታየው የውጭዎቹ ዋና ዓላማ የተገኘውን ትርፍ ይዞ መሄድ ሲሆን፣ ሌላ አዲስና የማያጓጓ አገር ሲገኝ ደግሞ ነቅሎ መንጎድ ነው፡፡ ቻይናም መጣ አውሮፓ፣ ህንድም መጣ አሜሪካ፣ የአገሪቱ ዕድገት መሠረትም ሆነ አዛላቂ ኢትዮጵያዊያን ይሁኑ፡፡ የአገሪቱ ልጆች ያፈሩት ሀብት የሚኮበልል ሳይሆን መልሶ ለዕድገት ነው የሚውለው፡፡ ይኼም ይታሰብበት፡፡ ለአገር እስከጠቀመና ጉዳት እስካላመጣ ድረስ የውጭ ኢንቨስትመንትም የልማቱ አጋር ይሁን፡፡ እውነተኛ ትብብር ይፈጠር፡፡ ከዘመኑ ጋር የሚሄድ የፖሊሲ ማዕቀፍ ይኑር፡፡

  1. ኢትዮጵያ የአካባቢውን ሰላም መጠበቅ ያለባት ለህልውናዋ ስትል ብቻ ነው

ፕሬዚዳንት ኦባማ ኢትዮጵያ በአካባቢው በፀረ ሽብርተኝነት ትግሉ ወሳኝ አገር መሆንዋን አምነዋል፡፡ እሳቸው ተናገሩትም አልተናገሩትም በዓለም ሰላም ማስከበርም ሆነ የእዚህን ነውጠኛ የአፍሪካ ቀንድ ሰላም በማስፈን ረገድ የተመሰከረላት ናት፡፡ “ኢትዮጵያውያን ብርቱ ተዋጊዎች ስለሆናችሁ አሜሪካ ወታደር ማሰማራት አያስፈልጋትም…” ቢሉም፣ ኢትዮጵያ ለህልውናዋ ስትል የምታደርገው ትግል እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ብዙ ጊዜ እንደሚባለው አሜሪካ በአካባቢው በተለይ በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን በሚደረጉ የሰላም ማስፈን ሥራዎች ዕርዳታዋ ባይዘነጋም፣ አፅንኦት ሊሰጠው የሚገባው ዋነኛ ጉዳይ ይህች የተከበረች አገር የማንም ተላላኪ አለመሆኗን ነው፡፡ የአካባቢውን ሰላም የሚያደፈርሱ ኃይሎችንም ሆነ አልሸባብን የመሳሰሉ ሽብርተኞችን ኢትዮጵያ የምትጋፈጠው ታሪኳ በጦርነት የተሞላ በመሆኑ ምክንያት ለህልውናዋ ስትል ነው፡፡ ድሮ ድንበሯ ውስጥ ሆና ሊወሯት ከመጡ ኃይሎች ጋር ነበር የምትፋለመው፡፡ አሁን ደግሞ ጉልበትዋ ሲጠነክር ችግሩ ያለበት ቦታ ድረስ መሄድ ችላለች፡፡ ጀግኖቻችን ለዚህ ዓላማ መስዋዕትነት የሚከፍሉት ለአገር ህልውና በመሆኑ፣ አገሪቱ የአሜሪካም ሆነ የማንንም ተላላኪ አለመሆኗ በሚገባ ይጤን፡፡ የአገሪቱም ፀረ አሸባሪነት ትግል ከአካባቢው አደገኛ ፖለቲካ ጋር እንዳይጠላለፍ ብርቱ ጥንቃቄ ይደረግ፡፡ ከማንኛውም በጥባጭ ኃይል ጋር በሚደረግ ፍልሚያ ተባባሪ ሲገኝ የጋራ ጥቅም የፈጠረው ቁርኝት ሆኖ ይታሰብ፡፡ የአሜሪካም በዚህ መንገድ ይስተናገድ፡፡ ኢትዮጵያ ህልውናዋ የሚረጋገጠው ጎረቤቶቿ ሰላም ሲሆኑ ስለሆነ፣ በዚህ መንፈስ ከጎረቤት አገሮች ጋርም ትብብሩ ይጠናከር፡፡

  1. የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጠንቀቁ

ገዥውም ሆነ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያደርጉበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ በቀደም ዕለት በመንግሥት በሽብርተኝነት ስለተፈረጀው ግንቦት ሰባት ጉዳይ ሲነሳላቸው፣ የአገራቸውን የስለላ ሪፖርት በመጥቀስ የሰጡት ማብራሪያ ተሰምቷል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ጉዳይ ያለው አገር ሁሉ መረጃን የሚያነፈንፈው በደኅንነት ተቋሙ አማካይነት ነው፡፡ ለዚህ የሚያገለግሉ የአገራችን ሰዎች በተለይ የመኖሪያ ፈቃድ (ዜግነት)፣ ክሬዲት ካርዶችና የተለያዩ ጥቅሞች ስለሚያገኙ ከፍተኛ የመረጃ ምንጮች ናቸው፡፡ የአገርን ጥቅም ከግላዊ ወይም ከቡድናዊ ጥቅም በላይ ማየት የተሳናቸው ግለሰቦችና ቡድኖች የአገሪቱን ሚስጥር ይሸጣሉ፡፡ ይኼንን አሳፋሪ ድርጊት የሚፈጽሙ ሊወገዙ ይገባል፡፡ በተለይ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታቸውን በሠለጠነ መንገድ መፍታት ተስኖዋቸው ለባዕዳን ገላጋይነትና ሸምጋይነት በመጋለጣቸው የአገሪቱ ሚስጥር ይዘከዘካል፡፡ የአገሪቱ ብሔራዊ ደኅነትና ሚስጥራዊ ጉዳዮች ለፖለቲካዊ ፍጆታ ሲባል ለባዕዳን ይጋለጣሉ፡፡

ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ዋና ግቡ ሥልጣን ቢሆንም፣ የአገርን ጥቅምና ሚስጥር አሳልፎ መሸጥ ግን ክህደት ነው፡፡ ሥልጣንና የሕዝብን ሉዓላዊነት ለያይቶ አለመመልከት በአገሪቱ ላይ የሚያመጣውን የወደፊት ሥጋትና አደጋ አለመገንዘብ ነው፡፡ ይህ ኩሩ ሕዝብ ይከበር፣ ይደመጥ ሲባል እናት አገሩን ለአደጋ የሚያጋልጥበት ችግር አይፈጠርበት ማለት ነው፡፡ የወደፊቱ ትውልድ የሚረከባት የተፈራችና የታፈረች አገር ትኑር ማለት ነው፡፡ የፖለቲካ ፍትጊያውን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍትሔ ሰጥቶ አገርን መገንባት ሲገባ፣ ያለጥንቃቄ ለባዕዳን የሚደርሰው የአገሪቱ ሚስጥር መዘዙ የከፋ ነው፡፡ መንግሥትም በአሸባሪነትና በመንግሥት ተቃዋሚነት መካከል ያለውን ልዩነት ያስምርበት፡፡ ስለዚህ ሁላችሁም ለአገር ክብርና ለሕዝብ ስትሉ ተጠንቀቁ፡፡ ተዋርዳችሁ አገር አታዋርዱ፡፡ ተወደደም ተጠላም ከባዕዳን ይልቅ ሕዝብን ማዳመጥ ያዋጣል!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...

የጋራ ድላችን!

ከፒያሳ ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። ለበርካታ ደቂቃዎች ሠልፍ ይዘን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...