Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግል ባንኮች ለቦንድ ግዥ ያወጡት ከ36 ቢሊዮን ብር በላይ ደረሰ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግል ባንኮች ከሚሰጡት ከእያንዳንዱ ብድር ላይ 27 በመቶ በማስላት ለቦንድ ግዢ እንዲያውሉ የሚያስገድደው መመርያ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት መጋቢት 2003 ዓ.ም. ወዲህ፣ አሥራ ስድስቱ የግል ባንኮች ለቦንድ ግዢ ያዋሉት ከ36.2 ቢሊዮን ብር በላይ ደረሰ፡፡ እስካሁን ለቦንድ ግዢው ያዋሉት ገንዘብም ከቀጣዩ በጀት ዓመት መጨረሻ ጀምሮ ሊመለስላቸው እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡

በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ከእያንዳንዱ ብድር 27 በመቶ የሚሆነውን ለቦንድ ግዥ ያዋሉት ገንዘብ የተጠቀሰውን ያህል የደረሰው፣ እስከ ሰኔ 2007 መጨረሻ ድረስ በተሠራው የመጀመሪያ ወይም ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት መሆኑ ታውቋል፡፡ ባንኮቹ ለቦንድ ግዥው ያዋሉት ገንዘብ በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ላይ 31 ቢሊዮን ብር አካባቢ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከአራት ዓመት በላይ የሆነው ይህ መመርያ የወጣው ለአምስት ዓመት እንዲያገለግል ሲሆን፣ ከአምስት ዓመት በኋላ ባንኮቹ ለቦንድ ግዥ ያወጡት ገንዘብ ሊመለስላቸው እንደሚችል ማረጋገጫ የተሰጠበት ነው፡፡ ይህ መመርያ ግን ወደፊትም ቀጣይ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት የብሔራዊ ባንክ ገዥው አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ እንደተናገሩት፣ የግል ባንኮች የቦንድ ግዥ የሚቀጥል ነው፡፡ ሦስት በመቶ ወለድ እየተከፈለበት እስካሁን የቦንድ ግዢ የተፈጸመበት ከ36.2 ቢሊዮን ብር በላይ እና በሚቀጥለው ዓመት የቦንድ ግዢ የሚፈጸምበት የባንኮቹ ገንዘብ ተደምሮ፣ ከመጋቢት 2008 ዓ.ም. በኋላ እንዲመለስላቸው ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አመላለሱም በአንዴ ሳይሆን የየአንዳንዱ ዓመት ቦንድ ግዢ በየዓመቱ እየተከፈለ በአምስት ዓመት እንደሚጠናቀቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኦዲት ያልተደረገውና የአሥራ ስድስቱም ባንኮች ዓመታዊ የሒሳብ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ከፍተኛውን የቦንድ ግዥ የፈጸመው ዳሸን ባንክ ነው፡፡ ባንኩ እስከ ሰኔ 2007 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ 5.81 ቢሊዮን ብር ያህል የቦንድ ግዥ ፈጽሟል፡፡ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ 5.36 ቢሊዮን ብር የቦንድ ግዥ በመፈጸም በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፣ ወጋገን ባንክ ደጋግሞ 4.16 ቢሊዮን ብር የቦንድ ግዥ መፈጸሙ ታውቋል፡፡ ኅብረት ባንክም ወደ አራት ቢሊዮን ብር ለቦንድ ግዥው አውሏል፡፡

ከአሥራ ስድስቱ የግል ባንኮች አራት ባንኮች ብቻ ከ900 ሚሊዮን ብር በታች የቦንድ ግዥ የፈጸሙ ናቸው፡፡ በተለይ እናት ባንክ፣ ደቡብ ግሎባል ባንክና አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ወደ ሥራ የገቡት ዘግየት ብለው በመሆኑ ለቦንድ ግዥው ያዋሉት ገንዘብ ከሌሎች ባንኮች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው፡፡

በመረጃው መሠረት አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ 320 ሚሊዮን ብር፣ እናት ባንክ 342 ሚሊዮን ብር፣ ደቡብ ግሎባል ባንክ ደግሞ 156 ሚሊዮን ብር ለቦንድ ግዥው አውለዋል፡፡ ከ900 ሚሊዮን ብር በታች የቦንድ ግዥ የፈጸመው ሌላው ባንክ ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ ደግሞ 814 ሚሊዮን ብር አካባቢ ለቦንድ ግዢ ማዋሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከአራቱ ባንኮች ውጪ ያሉት 12 የግል ባንኮች ግን እስካሁን የፈጸሙት የቦንድ ግዢ ከ1.01 ቢሊዮን ብር እስከ 5.81 ቢሊዮን ብር ይደርሳል፡፡

የብሔራዊ ባንክ መመርያ ተግባራዊ መሆን መጀመር የግል ባንኮችን ሊጐዳ እንደሚችልና እየጎዳ መሆኑ ከባንኮቹ አካባቢ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በተከታታይ አውጥቷቸው በነበሩ ሪፖርቶቹ ጭምር በግል ባንኮች ላይ የተጣለው 27 በመቶ የቦንድ ግዢን እስከመተቸት ደርሷል፡፡ በየዓመቱ በሚካሄደውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩት የግልና የንግዱ ኅብረተሰብ የጋራ ምክክር መድረክ ላይ ሳይቀር ይኼው ጉዳይ ሲነሳ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ከመንግሥት የተሰጠው ምላሽ መመርያው የማይቀለበስ መሆኑን የሚያመለክት ነበር፡፡ መመርያው ባንኮችን እየጎዳ ነው የሚለውን አስተያየትም ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

በአንፃሩ ባንኮቹ አሁንም በአትሪፊነታቸው እየዘለቁ ናቸው፡፡ በ2007 በጀት ዓመት ትርፋቸው ከታክስ በፊት ከ5.4 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ በ2007 ዓ.ም. አገኙት የተባለው ትርፋቸው ካለፈው በጀት ዓመት በጥቅል አግኝተውት ከነበረው ትርፍ ጋር ሲነፃፀር ወደ 800 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ብልጫ ያለው መሆኑን ያሳያል፡፡ እንዲህ ያሉት አኃዛዊ መረጃዎች መመርያው ባንኮቹን ጎድቷል የሚለውን አስተያየት አደብዝዘዋል የሚሉ ትችቶች እንዲሰጡባቸው እያደረጉ ነው፡፡

በከፍተኛ ፉክክርና ጥረት ባንኮች በአምስት በመቶ ወለድ እየከፈሉ የሰበሰቡትን  ገንዘብ በሦስት በመቶ ወለድ ብቻ ማስቀመጣቸው በራሱ ጉዳት መሆኑን የሚገልጹት ደግሞ፣ በብሔራዊ ባንክ ላለፉት አምስት ዓመታት ለቦንድ ግዢ ያዋላቸውን ገንዘባቸውን ቢያበድሩ ከፍተኛ ጥቅም ያገኙበት እንደነበርም ይጠቁማሉ፡፡

ለሀብታቸው ዕድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክትላቸው ይችል ስለነበር፣ ዓመታዊ ትርፋቸው እየጨመረ በመምጣቱ ብቻ 27 በመቶ የቦንድ ግዥ እንዲፈጽሙ የሚያስገድደው ሕግ አልጐዳቸውም ማለት እንደማይችል ይጠቁማሉ፡፡  

ከግል ባንኮቹ በቦንድ ግዢ የሚሰበሰበው ገንዘብ በቀጥታ ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፈሰስ የሚደረግ ሲሆን፣ ባንኩም ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባቸዋል ለተባሉ ኢንቨስትመንቶች እያበደረ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች