Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየገቢዎችና ጉምሩክ አዋጅ የተሻሻለው የተከሰሱና የተቀጡ ሰዎችን ለመጥቀም ታስቦ አለመሆኑ ተገለጸ

የገቢዎችና ጉምሩክ አዋጅ የተሻሻለው የተከሰሱና የተቀጡ ሰዎችን ለመጥቀም ታስቦ አለመሆኑ ተገለጸ

ቀን:

–  የእነ አቶ መላኩ ፈንታ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ውድቅ ተደረገ

ከየካቲት 12 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ኅዳር 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ለአምስት ዓመታት በሥራ ላይ የነበረውን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 622/2001ን የተካው አዋጅ ቁጥር 859/2006 የተሻሻለው፣ አዋጅ ቁጥር 622/2001 ላይ የተቀመጡ ጉዳዮችን በትኩረት ለማየት እንጂ፣ ተከሳሾችን ወይም የተቀጡ ሰዎችን ለመጥቀም ታሳቢ የተደረገ አለመሆኑን የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አስታወቀ፡፡

አዲሱ የተሻሻለው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ አዋጅ ተከሳሾችን ወይም የተቀጡ ሰዎችን ለመጥቀም ታሳቢ ተደርጎ አለመሻሻሉን ጉባዔው የገለጸው፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታን ጨምሮ፣ 13 በከባድ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የተከሰሱ ኃላፊዎች፣ ነጋዴዎችና ድርጅቶች አዲሱን አዋጅ በመጥቀስ አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡ ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥ ላዘዘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት በሰጠው ምላሽ አጣሪ ጉባዔው አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ በአቶ መላኩ ፈንታ፣ አቶ ገብረዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ፣ አቶ በላቸው በየነ፣ አቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር፣ አቶ ከተማ ከበደ፣ አቶ ስማቸው ከበደ፣ ዶ/ር ፍቅሬ ማሩ፣ አቶ ገብረ ሥላሴ ገብረ ማርያም፣ ኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ጄኤች ሲሜክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ነፃ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ጌታስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ኮሜት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አዋጅ ቁጥር 60/89፣ 368/95፣ 622/2001ን እና የወንጀል ሕጎችን ተላልፈዋል በሚል ክስ አቅርቦባቸዋል፡፡

ተከሳሾቹ የተጠቀሱትን አዋጆች በመተላለፍ፣ በሥልጣን አላግባብ በመገልገልና በጥቅም በመተሳሰር፣ ከቀረጥ ነፃ መብትን አላግባብ በመገልገል፣ እንዲፈተሽ ባለማድረግ ገደብና ቁጥጥር የሚደረግባቸውን ዕቃዎችና መድኃኒቶች አስገብተዋል በማለት የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ሰፋ ያለ የክስ ትንታኔ አቅርቦባቸው፣ ከግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ ሆነው በክርክር ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ተከሳሾቹ በክርክር ላይ እያሉ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አዲስ አዋጅ በመውጣቱ፣ ከላይ የተጠቀሱትን አዋጆች ሙሉ በሙሉ መሻሩን በአዲሱ አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 181 በመደንገጉ ምክንያት፣ የተጠቀሱት ተከሳሾች ክሳቸው እንዲቋረጥ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡

ከቀረጥ ነፃ የገቡ ዕቃዎች ለታለመላቸው ዓላማ አለማዋላቸው፣ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ያልተፈጸመባቸው የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች መግባታቸው፣ በወንጀልና በዲስፒሊን መጠየቅ ያለባቸውን ሠራተኞች በዝምታ ማለፍ፣ የቀረጥ ነፃ መብትን ያላግባብ እንዲገለገሉ ማድረግ፣ ዕቃዎችን ሕገወጥ በሆነ መንገድ በየብስ ትራንስፖርት በማጓጓዝ ላይ የሚፈጸም ድርጊት፣ በፍራንኮ ቫሉታ ከቀረጥ ነፃ የገባን ሲሚንቶ ወደብ ላይ ሳይደርስ ለሦስተኛ ወገን ማስተላለፍና ሌሎች ዘርዘር ብለው በኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክሶች ቀርበዋል፡፡ ቀደም ብለው በነበሩ የገቢዎችና ጉምሩክ አዋጆች፣ የወንጀል ድርጊት መሆናቸውንና በወንጀል የሚያስጠይቁ የነበሩ ቢሆንም፣ በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 181 ወንጀል መሆናቸው ተሰርዞ፣ በተሻሻለው አዋጅ አንቀጽ 30(2ለ)፣ 156፣ 163 መሠረት በአስተዳደራዊ ዕርምጃ የሚታለፉ መሆናቸው በመደንገጉ፣ ተከሳሾችም ይኸንኑ በመጥቀስ ክሱ እንዲቋረጥላቸው አመልክተው ነበር፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ በሰጠው የመቃወሚያ መልስ፣ ተጠርጣሪዎቹ በሙስና ስለተከሰሱና በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 182 መሠረት፣ አዋጁ ከፀናበት ቀን በፊት የተጀመሩ ጉዳዮች በነበረው ሕግ ፍፃሜ እንደሚያገኙ መደንገጉን በማስታወስ፣ የተከሳሾቹ ማመልከቻ ውድቅ እንዲደረግለት ተከራክሮ ነበር፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የተሻሻለውን አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 182 በመጥቀስ የተከራከረ ቢሆንም፣ ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 5(3)ን የተሻረ ሕግ ይሠራ በነበረበት ጊዜ የተፈጸመ ወንጀል እንደ ወንጀል እንደማይቆጠርና ሊያስከስስም ሆነ ሊያስቀጣ እንደማይችል መደንገጉን በመጥቀስ ተከራክረዋል፡፡ በተጨማሪም የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 22(2) ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ የወጣ ሕግ ለተከሳሹ ወይም ለተቀጣው ሰው ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ፣ አዲሱ ሕግ ተፈጻሚነት እንደሚኖረው መደንገጉን በመጥቀስ፣ የባለሥልጣኑ አዋጅ ቁጥር 182 ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንደሚጣረስ በመግለጽ ተከራክረዋል፡፡

የሁለቱን ወገኖች ክርክር የሰማው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት፣ ሰኔ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚያስፈልገው በመግለጽ፣ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ልኮት ነበር፡፡ ጉባዔው የሰጠውን ውሳኔ ፍርድ ቤቱ ሐምሌ 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ለችሎቱ በንባብ አሰምቷል፡፡

ጉባዔው አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 182፣ ከወንጀል ሕግ አንቀጽ 5 (3) እና ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22 (2) ጋር ይጋጫል? ወይስ አይጋጭም? የሚለውን መመርመሩን ገልጿል፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22 እና የወንጀል ሕግ አንቀጽ 5 ላይ የተደነገጉት ድንጋጌዎች ግልጽ መሆናቸውን የጠቆመው ጉባዔው፣ በማንኛውም መልክ ወንጀልን የሚደነግጉ ልዩ ድንጋጌዎች በሚኖሩበት ጊዜ፣ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 3 (ሌሎች የሚያስቀጡ ሕጎች፣ ቅጣት የሚደነግጉ ደንቦችና ልዩ ሕጎች የተጠበቁ ናቸው፡፡ በደንቦቹና ሕጎቹ ላይ በተለያየ አኳኋን ካልተደነገገ በስተቀር የዚህ ሕግ መርሆዎች ለእነርሱም ተፈጻሚ ይሆናሉ) መሠረት የተጠበቁ መሆናቸውን አብራርቷል፡፡ ወንጀልን የሚደነግጉ የአዋጅ ቁጥር 859/2006 ድንጋጌዎችም የተጠበቁና የወንጀል ሕጉን መርሆዎች ተከትለው ተፈጻሚ እንደሚሆኑ ግልጽ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

የተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 182 “በሌሎች ሕጎች የተደነገጉት እንደተጠበቁ ሆኖ…” የሚለው ሐረግ፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) እና በወንጀል ሕግ አንቀጽ 5(3) ሥር የተደነገጉትን የሚመለከት ነው? ወይስ አይደለም? ይጋጫል? ወይስ አይጋጭም? የሚለውን ከማየትና ውሳኔ ከመስጠት በፊት፣ ሕጎች በራሳቸው ግልጽነት ከሌላቸውና በትርጉም ደረጃ አሻሚ ከሆኑ ለሕግ ትርጉም መሰጠት ያለበት፣ ከአዋጁ አጠቃላይ ዓላማና ከሕጉ አቀራረፅ ሥርዓት አንፃር መሆን እንዳለበት ጉባዔው ገልጿል፡፡

የተሻሻለው አዋጅ ዓላማ በአገሪቱ እያደገ የመጣውን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት የሚደግፍ፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታና ዘመናዊ የጉምሩክ የሕግ ማዕቀፍ በሥራ ላይ ማዋል መሆኑን ጉባዔው አስታውቋል፡፡ ኢትዮጵያ አባል የሆነችባቸው ዓለም አቀፋዊ፣ አኅጉራዊና አካባቢያዊ የንግድ ስምምነቶች፣ ወቅታዊ የጉምሩክ ሕግና የአሠራር ሥርዓት እንዲኖር የሚያስገድዱ መሆናቸውንም አክሏል፡፡ ኮንትሮባንድና ሌሎች የንግድ ማጭበርበር ወንጀሎች በሕጋዊ የንግድ እንቅስቃሴ፣ በሕዝብ ደኅንነት፣ በመንግሥት ገቢና በሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቶች ላይ የሚያስከትሉትን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል፣ የጠነከረ የሕግ ማስከበሪያ ሥርዓት በማስፈለጉ፣ የቀድሞ አዋጅ ቁጥር 622/2001 ላይ የተቀመጡ ጉዳዮችን በትኩረት በማየት በአዋጅ 859/2006 መቀየሩን የጉባዔው ውሳኔ ያብራራል፡፡ በመሆኑም አዲሱ የተሻሻለው የባለሥልጣኑ አወዋጅ ቁጥር 859/2006 ለአዋጁ አጠቃላይ ዓላማ እንጂ፣ ተከሳሾችን ወይም የተቀጡ ሰዎችን ለመጥቀም ታሳቢ ተደርጎ አለመውጣቱን ማሳወቁን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

የተሻሻለው አዋጅ በዋናነት መተርጎም ያለበት ከአዋጁ አጠቃላይ ዓላማ አንፃር መሆን እንደሚገባው በውሳኔው ተጠቅሷል፡፡ መታየት ያለበትም በፍትሐዊነት፣ በርትዕ መርህና በአዋጁ ውስጥ የተቀመጡ መሠረታዊ ዓላማዎችን በማስከበር “ጠንካራ ሕግ ማስከበሪያ ሥርዓት ተዘርግቷል?›› ተብሎ እንጂ፣ በቀድሞ ሕግ ለተከሰሱ ወይም ለተቀጡ ሰዎች  “ይጠቅማል? ወይስ አይጠቅምም?” በሚለው ቀጥተኛ መነሻ መሆን እንደሌለበት ፍርድ ቤቱ በንባብ ያሰማው የጉባዔው ውሳኔ ያስረዳል፡፡ አዋጅ ቁጥር 859 አንቀጽ 182 ውስጥ የተቀመጠው ጉዳይ በግልጽ ሌሎች ጉዳዮችን፣ ማለትም ከወንጀል ሕግ ጠቅላላ መርሆዎች ውጪ ያሉ ሌሎች ሕጎችን ተፈጻሚነት በመጠበቅ፣ በአዋጁ መግቢያ ላይ የተቀመጠውን ዓላማ ለማሳካት መሆኑን ገልጿል፡፡ ሕግ አውጪውም ታሳቢ ያደረገው፣ ቀደም ሲል የተጀመሩ ክሶችን ባሉበት እንዲቀጥሉ በግልጽ ለማስቀመጥ መሆኑን የጉባዔው ውሳኔ እንደሚያስረዳ ፍርድ ቤቱ ጠቁሟል፡፡

አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 182 ተከሳሾች በዚህ አዋጅ እንዳይጠቀሙ ማድረጉን ጉባዔው በውሳኔው ገልጾ፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22(2) የሚሠራው የተሻሻለው አዲሱ አዋጅ ተከሳሾችን እንዲጠቀሙ ሲያደርግ ብቻ መሆኑን ጉባዔው ማሳወቁን ገልጿል፡፡ አዲሱ አዋጅ ተከሳሾች እንዲጠቀሙ ባለማድረጉ የአዋጁ አንቀጽ 182 ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 22 (2) ጋር እንደማይጋጭ በውሳኔው ማሳወቁን ፍርድ ቤቱ ለተከሳሾች በንባብ አሰምቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ከሴራ ፖለቲካ በስተጀርባ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁ ኃይሎች

በመኮንን ሻውል ወልደ ጊዮርጊስ የአፄ ቴዎድሮስ መንግሥት የወደቀው ከመቅደላ በፊት...

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...

አማርኛ ተናጋሪዋ ሮቦት

በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የሳይንስ ሙዚየም፣ ሚያዝያ 2 ቀን...

ወዘተ

ገና! ከእናቴ ሆድ ሳለሁ፤ ጠላት ሲዝትብኝ ሰምቻለሁ። በዳዴ ዘመኔም፣ በ'ወፌ ቆመችም!'፤ አውዴ ክፉ ነበር...