Sunday, December 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊመንግሥት ለጆሮ ሕክምና ችግር ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ

  መንግሥት ለጆሮ ሕክምና ችግር ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ

  ቀን:

  አለመስማትን ከሚያስከትሉ የጆሮ ሕመሞች 50 ከመቶ ያህሉ ታክመው መዳን የሚችሉ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ለሕክምናው ትኩረት ባለመሰጠቱ የተነሳ የጆሮ ሕመምና የመስማት ችግር ያለባቸው ሰዎች ለማኅበራዊ፣ ለኢኮኖሚያዊና ለሥነ ልቦናዊ ችግሮች እየተጋለጡ መሆኑ ተገለጸ፡፡ መንግሥትም ለሌሎች በሽታዎች ትኩረት እንደሰጠው ሁሉ አለመስማትን ሊያስከትሉ ለሚችሉ የጆሮ ሕመሞች ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ፡፡

  የአንገት በላይ ሐኪሞች የጆሮ፣ የአፍንጫ፣ የጉሮሮ የራስና የአንገት ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር፣ ከኢስት አፍሪካ ሂሪንግ ኤይድ ሴንተርና ከአጋሮች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የተከበረውን የኢትዮጵያ የመስማት ቀን አስመልክቶ በሸራተን አዲስ ሐምሌ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ባዘጋጀው መድረክ የተገኙት የአንገት በላይ ሕክምና ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ነጋ ኪሮስ እንደተናገሩት፣ የጆሮ የመስማትና ያለመስማት አቅም ሕጻን ሲወለድ ክትባት እንደሚሰጠው ሁሉ በተወለደበት ጊዜ መለካትና መታወቅ ያለበት ነው፡፡ ሆኖም ይህ በኢትዮጵያ እየተተገበረ አይደለም፡፡ በመሆኑም ችግሩ ከሥር ታውቆ ሊድን የሚችለው የጆሮ ሕመም በጊዜ ሒደት ሰዎችን ላለመስማት ብሎም ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች እያጋለጠ ይገኛል፡፡

  ዶ/ር ነጋ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ በዘርፉ ያሉት የሕክምና ባለሙያዎች 23 ብቻ ናቸው፡፡ ከባለሙያ እጥረት በተጨማሪ የግንዛቤ ችግር፣ የሕክምና መሣሪያዎች አለመሟላት፣ የመስሚያ መርጃ መሣሪያዎች አለመገኘትና ውድነት እንዲሁም በመንግሥት በኩል የተሰጠው አነስተኛ ትኩረት መስማት የማይችሉ ሰዎችን ለውስብስብ ችግር እያጋለጠና እንዲገለሉ እያደረገ ነው፡፡

  ከአሜሪካ በተመለሱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የተከፈተው ኢስት አፍሪካ ሂሪንግ ኤይድ ሴንተር የመስሚያ መርጃ መሣሪያዎችን ከዓመታት በፊት ማቅረብ ቢጀምርም፣ መንግሥት ከታክስ ጀምሮ ለዘርፉ እገዛ ባለማድረጉ በውድ ዋጋ ከውጭ ተገዝተው የሚገቡ መሣሪያዎችን ለመግዛት የኅብረተሰቡ አቅም አይፈቅድም፣ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ሊሰጥ ይገባልም ብለዋል፡፡

  ማኅበሩ በዘርፉ ያለውን ሙያዊ ችግር ለመቅረፍ ከመንግሥት ጋር ባደረገው ውይይት መሠረት፣ በአሁኑ ሰዓት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና በቅዱስ ጳውሎስ ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ተከፍቷል ብለዋል ዶ/ር ነጋ፡፡

  የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ከበደ ደምሴ፣ የመስማት ችግር እንዳያጋጥም ከጽንስ ጀምሮ የእናትና የጽንስ ጤና ተጠብቆ መቆየት እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ በእርግዝና ወቅት ከሚወሰዱ መድኃኒቶች ጋር ተያይዞ የመስማት ችግር ሊከሰት ይችላል፡፡ ከመጠን ያለፈ አልኮል መጠጥና አደንዛዥ እፆችም መንስኤዎቹ ናቸው፡፡ ጆሮን አላግባብ ማጽዳት፣ ኢንፌክሽንና ከበድ ያሉ በሽታዎች፣ ለከባድና ለረዥም ጊዜ ለማያቋርጥ ጫጫታ መጋለጥ ከምክንያቶቹ ይጠቀሳሉ፡፡ በዘር የሚተላለፍ የመስማት ችግር ቢኖርም ብዙ የሚታይ አይደለም፡፡  

  በመድረኩ የተገኙት የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ፣ የአካል ጉዳተኝነት ችግር እነሱን የሚያግዙ መሣሪያዎች ተሟልቶ አለመገኘት በዩኒቨርሲቲ ደረጃም ያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

  የመስማት ችግር ከቀዳሚዎቹ ገዳይና ተላላፊ በሽታዎች የማይመደብ በመሆኑ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል ትኩረት ተነፍጎት ሰንብቷል፡፡ በመሆኑም ታክመው ሊድኑ የሚችሉ ሰዎች ሕክምናው ተደራሽ ባለመሆኑ የተነሳ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ተጋላጭ ሆነዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም በጆሮ ውስጥ በሚፈጠር ኢንፌክሽን ምክንያት ለነርቭ መጎዳትና መሞት የተጋለጡም አሉ፡፡

  ፕሮግራሙን የከፈቱት የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር አዲስ ታምሬ፣ ሚኒስቴሩ ላለፉት 20 ዓመታት በሕፃናትና በእናቶች ጤና ዙሪያ በስፋት መሥራቱንና የእናቶችና የሕፃናት ሞትን መቀነስ መቻሉን አስታውሰው፣ የማኅበራዊ ችግር ለሚያስከትለው የመስማት ችግር ሕክምና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ትኩረት እንደሚሰጠው፣ በዘርፉ የስፔሻሊስቶች ሥልጠናና ሕክምና እንደሚስፋፋም ተናግረዋል፡፡

  በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስድስት ሰዎች አንዱ ከማድመጥ ችግር ጋር የሚኖር ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 35 በመቶ ያህሉ ከ64 ዓመት በላይ ናቸው፡፡

  በኢትዮጵያ ከችግሩ ጋር በተያያዘ በመረጃ የተደገፈ አኅዝ ባይኖርም፣ እ.ኤ.አ. በ2005 የተሠራው ‹‹ቤዝላይን ሰርቬይ ኦን ዲዝኤቢሊቲ ኢን ኢትዮጵያ›› የሚያሳየው 2.93 በመቶ አካል ጉዳተኞች መኖራቸውን ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ይህንኑ አኅዝ 10 በመቶ ያደርሰዋል፡፡ በጥመርታ ሲሰላ 14.3 በመቶ የመስማት፣ 13.4 በመቶ የማየት ችግር እንዲሁም 6.5 ከመቶ ጭራሹኑ የማይሰሙ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...

  ዘንድሮ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን በበይነ መረብ ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩ ተገለጸ

  በሁሉም መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሐ ግብሮች የሚመረቁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን...

  ሕፃናትን ለውትድርና የመለመሉ አካላትን ለሕግ ማቅረቡ እንዳልተተኮረበት ተገለጸ

  በኢትዮጵያ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናትን ለጦርነትና ለውትድርና የመለመሉ አካላትን...