Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየእያዩ ፈንገስ ‹‹ፌስታሌን››

የእያዩ ፈንገስ ‹‹ፌስታሌን››

ቀን:

‹‹…በነገራችን ላይ ጋሽ ቆፍጣናው ማለት የሠፈራችን ደረጃ አንድ ታጥቦ የተቀሸረ ሙጢ ማለት ነው፡፡ ፊት ለፊት ተናጋሪ እና ሐቀኛ፡፡ ለማንም የማይመለሱ ቆፍጣና፡፡ የነገር ጠጠር ውርወራና ምክራቸው፡፡ በሰከንድ በአሽሙር ቋጥኝ ይፈረካክሱኋል፡፡ ቆፍጣናው እንዲህ ናቸው፡፡ አንድ የፈረደበት ተከራይ ጋዜጠኛ አላቸው፡፡ እንዲሁ ፍዳውን የሚያሳዩት፡፡ አንድ ቀን የሆነ ባለሥልጣኖችና ባለሀብቶች ኳስ ጨዋታ አድርገው ነበር መሰለኝ፡፡ ይኼንን ዘገባ ሠርቷል ጋዜጠኛው ተከራይ ሲመጣ ምን ቢሉት ጥሩ ነው በምን ለየሃቸው ግን?…››

ንግግሩ የተቀነጨበው ‹‹ፌስታሌን›› ከተሰኘው ዋን ማን ሾው (አንድ ተዋናይ ብቻውን የሚተውንበት ቴአትር) ነው፡፡ ቴአትሩ የታየበት መድረክ ከተጨናነቁ የመዲናችን መንደሮች አንዱ ይመስላል፡፡

የደሳሳው ጭቃ ቤት ልስን ፈራርሶ የቤቱ ማገር ይታያል፡፡ ከቤቱ አጠገብ ያሉ ሌሎች መኖሪያዎች ግርግዳዎችም እንዲሁ ያረጁ ናቸው፡፡ የጭቃ ቤቱ መጠነኛ መስኮትና በር ላይ ‹‹ታሽጓል›› የሚል ጽሑፍ ተለጥፏል፡፡ እዛው አካባቢ የሚታዩ ማስታወቂያዎች የአብዛኛውን የአዲስ አበባ መንገዶች ገጽታ ያስታውሳሉ፡፡

‹‹ሠርግዎን በዲጄ››፣ ‹‹ዋ ትሸናና፤ ከሸናህ ትሸነሸናለህ››፣ ‹‹አርቲስት መሆን ይፈልጋሉ?›› እና ‹‹እፀነፍስ የባህል መድሐኒት ቤት›› የሚሉ የኮምፒዩተር ጽሑፎች ይጠቀሳሉ፡፡

ካረጁ ቆርቆሮዎች እንደነገሩ የተሠራው መጠለያ ባደፉ ጨርቆች ተሸፋፍኗል፡፡ መጠለያው ውስጥ ጋደም ብሎ የነበረው እያዩ ፈንገስ ወደ መንገድ ዳር ይወጣል፡፡ ፊቱን በንዴት ቅጭም አድርጓል፤ በቁጭትም ይንዘፈዘፋል፡፡ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ፌስታሉን ሌቦች ሰርቀውታል፡፡ ይገኝበታል ብሎ በገመተው ሥፍራ ሁሉ ተዘዋውሮም ሊያገኘው አልቻለም፡፡ በፍለጋ ላይ ሳለ ይባስ ብሎ ዘለፋ ይደርስበታል፡፡ እንዲህ ሲልም እያዩ ምሬቱን ይገልጻል፡፡

‹‹… የእትዬ ምልጃን ምክር ሰምቼ እኮነው ጉድ የሆንኩት፡፡ የሰፈሩን ቆሻሻ የሚያነሱት እነሱ ስለሆኑ ጠይቃቸው ያገኙልሃል ብለውኝ ሄጄ እኮ ነው በጠዋት ያገኙኝ፡፡ የቆሻሻ ገንዳቸውን እየገፉ ቁልቁል ሲወርዱ አየዋኋቸውና ሮጥ ሮጥ ብዬ ደረስኩባቸው፡፡ ያለ የሌለ ትህትናዬን አጠራቅሜ እባካችሁ ወንድሞቼ ትናንትና አሮጌ ልብሶች የያዘ ፌስታል ጠፍቶብኝ ነበረ፤ ምናልባት ካገኛችሁት ብዬ ነው አልኩኝ፡፡ አንደኛው እስኪ ምልክቱን ተናገር አለኝ፡፡ ሁሉም ፌስታሉ ውስጥ ያለውን ልናገር አልኩ፡፡ ታዲያስ ምልክት አይደለም እንዴ ሁሉንም ነው እንጂ መናገር አለኝ፡፡

ድምፄን ከፍ አድርጌ አራት የሽንት ጨርቆች ከነመዓዛቸው፣ አንድ እግር ጫፍ አይጥ የበላው የሕፃን ልጅ የዳንቴል ካልሲ፣ ጡጦ ክዳኑ የተሰነጠቀ፣ ሁለት የሴት ፓንቶች፣ ድርያ ከድሬዳዋ ፊልድ ስመለስ የተገዛና እንዲሁም ተረከዛቸው የሳሱ ነጠላ ጫማዎችና ቀዩ አጀንዳዬ፡፡ የእኔና የብዙ ሰዎች ሐሳብ የሰፈረበት ቀዩ አጀንዳዬ፡፡ ይኼ ሁሉ ውድ ንብረት ፌስታሌ ውስጥ ነበር አልኳቸው፡፡ ዘውድዬ ትሙት እርስ በርስ ሲተያዩ ልቤ ቀጥ ነበር ያለው፡፡ አግኝተውታል ብዬ ጠርጥሬ እኮ ነው፡፡ ከዛ በአንክሮ ካዩኝ በኋላ አንደኛው ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? 904 ደውለህ አዘጋው፡፡ እየሳቁ ሄዱ፤››

እያዩ ፈንገስ የተባለው ገፀ ባህሪ የአዕምሮ ሕመምተኛ ነው፡፡ በገጠመው መሪር ሐዘን ሕይወቱ እንዳይሆን ሆኗል፡፡ ቴአትርሩም እያዩ የጠፋበትን ፌስታል መነሻ ያደረገ ነው፡፡

ብዙዎች የእያዩ ፈንገስን ገፀ ባህሪ የሚያውቁት በጦቢያ ግጥምን በጃዝ መርሐ ግብር ላይ ነው፡፡ በየወሩ በሚካሄደው ዝግጅት ላይ በዋነኛነት ግጥሞች የሚደመጡ ሲሆን፣ ወግ፣ መነባንብ፣ ዲስኩርና ሌሎችም ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎች ይስተናገዳሉ፡፡ ታዳሚዎች የየወሩን የመጀመሪያ ረቡዕ በጉጉት እንዲጠባበቁ ከሚያደርጉ አንዱ ደግሞ የእያዩ ፈንገስ ትዕይንት ነው፡፡

ለአንድ ዓመት ያህል ወደ 13 የሚደርሱ ክፍሎች ታይተዋል፡፡ የእያዩ ፈንገስ አንደኛ ዓመት የመድረክ ቆይታ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ተከብሮ ነበር፡፡ በየክፍሎቹ የተወሰኑ ደቂቃዎች ይወስድ የነበረው ትዕይንቱ አሁን የሙሉ ጊዜ ቴአትር ሆኗል፡፡ ሰኞ ሐምሌ 27፣ 2007 ዓ.ም. በአዶት ሲኒማና ቴአትር ተመርቋል፡፡

አስቂኝ በሆነ ዘዬ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትችቶችን በመሠንዘር የሚታወቀው እያዩ፣ በ‹‹ፌስታሌን›› ላይም በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ያነሳል፡፡ የኅብረተሰቡን አኗኗርና የወቅቱን ሥርዓት ያጠይቃል፡፡ መጨካከን፣ መታበይ፣ ሸፍጥና ሌሎችም ሕፀፆችን ይተቻል፡፡ የመሠረተ ልማት አለመስፋፋት፣ ኢኮኖሚያዊ ችግርና መሰል ጉዳዮችን ይዳስሳል፡፡

በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ታዳሚዎች እየሳቁ፣ በጭብጨባ ድጋፋቸውን እየገለጹም ተውኔቱን ይከታተሉ ነበር፡፡ ሲገባደድም ከመቀመጫቸው ተነስተው ለደቂቃዎች በማጨብጨብ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡ እያዩ ፈንገስን ሆኖ የሚተውነው እንዲሁም የቴአትሩ አዘጋጅ ግሩም ዘነበ ሲሆን፣ ደራሲው በረከት በላይነህ ነው፡፡

እያዩ የሚነቅሳቸውን ችግሮች ‹‹ፈንገሱ ነው›› በማለት ይገልጻል፡፡ በተለያየ ዘርፍ አግባብ ያልሆኑ አካሄዶች ሥር መስደዳቸውንና በፍጥነት መስፋፋታቸውን ያመላክታል፡፡ ‹‹ፈንገስ›› የሚለው ቃል በማኅበረሰቡ ውስጥ የተንሰራፉ ችግሮችን እንደሚያሳይ በረከት ይናገራል፡፡ እያዩ አንድም የባዬሎጂ መምህር ስለነበር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፈንገስ በፍጥነት የመራባት ባህሪ ስላለው ለገፀ ባህሪው መጠሪያ እንዲሆን መመረጡን ይገልጻል፡፡

እሱ እንደሚለው፣ ገፀ ባህሪው የተጠነሰሰው ግሩም ከአውግቸው ተረፈ ‹‹ያስመዘገብኩት›› ላይ በጥቂቱ ቀንጭቦ በጦቢያ ግጥምን በጃዝ መድረክ ላይ ባቀረበበት ወቅት ነበር፡፡ ግሩም መኩሪያ የሚባል ገፀ ባህሪን ተላብሶ ነበር የሚጫወተው፡፡ ከተመልካቾች ያገኘውን በጎ ምላሽ በመመልከትም ቴአትሩ ተጀምሯል፡፡

እያዩ በነጻነት እንዲናገር ሲባል የአዕምሮ በሽተኛ ገፀ ባህሪ እንደተሰጠው በረከት ይናገራል፡፡ ‹‹ብዙ ነገሮችን መናገር የምችለው በእያዩ ነው፤›› ይላል፡፡ በአንድ ጉዳይ ዙሪያ ሐሳብ ይሰጣሉ ተብለው ከሚጠበቁ ግለሰቦች ውጪ ያልተገመቱ ሰዎች ሲናገሩ የበለጠ ተሰሚነት እንደሚኖራቸውም ያምናል፡፡

የአዕምሮ ሕመምተኛው እያዩ የተቀዳደደ ልብስ ለብሶ በደሳሳ መጠለያ ይኖራል፡፡ ፌስታሉን ፍለጋ ከቆሻሻ መጣያ ገንዳ ውስጥም ሳይቀር ይገባል፡፡ ‹‹ይህን ዓይነት ሰው ተመልካች የማይገምተውን ነገር ሲናገር ተደማጭነት ይኖረዋል፤›› ይላል በረከት፡፡

እንደ ደራሲው ገለጻ፣ የአዕምሮ ሕመምተኞች ወይም በልዩ ልዩ ምክንያት ማኅበረሰቡ የገፋቸው ሰዎች በምሬት የተሞሉና ቁጡ የሚሆኑበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡ ተውኔቱም ይህን እውነታ ተመርኩዞ ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል፡፡ ‹‹ቴአትሩ በዋነኛነት ማኅበራዊ ትችት አዘል ነው፤ ፖለቲካዊ ሽሙጥ (ፖለቲካል ሳታየር)ና ፍልስፍናዎችም አሉት፤›› በማለት ይዘቱን ያብራራል፡፡

እያዩ በገጠመው መሪር ሐዘንና የሕይወት ውጣ ውረድ አዕምሮውን ቢስትም ንግግሮቹ ፍልስፍናውን እንደሚያንፀባርቁ ይናገራል፡፡ የታዳሚዎችን ቀልብ ለመግዛትና መሰላቸት እንዳይኖርም አስቂኝ ሁነቶች ይካተታሉ፡፡

በደራሲው እምነት፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ የግለሰቦች መብት በሚገባ አልተተነተነም፡፡ የየራሳቸው ስሜትና ምልከታ ያላቸው ግለሰቦች ማንነት በተናጠል መፈተሽ ሲገባው በቡድን መፈረጅ እንደሚያመዝን ይገልጻል፡፡ እያዩን ሰዎች እንደገፉት በመጥቀስ፣ ‹‹እያዩ ጨርቁን ስለጣለ አገር ጨርቁን አይጥልም፤ ሰው በሕይወቱ አሳዛኝ ነገር ይገጥመዋል፤ ዋናው ጥያቄ ሌሎች ሰዎች እንዴት ይቀበሉታል የሚለው ነው፤›› ሲል ይናገራል፡፡

ቴአትሩ መገፋፋትና ጭቆና ተቀርፎ አጠገባችን ያለውን ሰው ትኩረት እንስጠው የሚል መልዕክት ያስተላልፋል ይላል፡፡ የአንድ ማኅበረሰብ ጥንካሬና ትስስር የሚታየው ለግለሰቦች በሚሰው ቦታ መሆኑን በአጽንኦት ይናገራል፡፡

በየወሩ ይቀርብ የነበረው የእያዩ ትዕይንት በየመድረኩ የተለያዩ ጉዳዮች አንስቷል፡፡ በአንፃሩ ‹‹ፌስታሌን›› ወጥና የቴአትር ግብዓቶችን ያሟላ ነው፡፡ ባለቤቱ ዘውድዬን የመሰሉና ከእያዩ ጋር የሚታወቁ ገፀ ባህሪያት በአዲሱ ተውኔትም ይገኛሉ፡፡ ቴአትሩ የራሱ ማጀቢያ ሙዚቃ አለው፡፡ ተውኔቱ የሚያጠነጥንባቸውን ጉዳዮች የሚያጎሉት ሙዚቃዎች ከአንድ ትዕይንት ወደ ሌላው እንደመሸጋገሪያ የሚለቀቁ ሲሆኑ፣ የሚያዜሙት በዛወርቅ አስፋውና ግዛቸው ተሾመ ናቸው፡፡

ቴአትሩ የፌስታሉን ፍለጋ ተከትሎ በሚያስቁ በሚያሳዝኑም ሁነቶች የተሞላ ነው፡፡ በረከት እንደሚናገረው፣ ተመልካች ትዝብትና ስላቁን እንዲሁም አዝናኝነቱን ፈልጎ ይሄዳል፡፡ አንዳንዴ በትዕይንቱ መሳቅ ብቻ ሊያመዝን ቢችልም እያንዳንዱ ሰው የሚወስደው መልዕክት እንዳለ ያምናል፡፡

‹‹የእያዩ ሥራ ሌላ አይን የመትከል ያህል ነው፤ ታዳሚው ወደየቤቱ ሲገባ ራሱን እንዲመለከት እንፈልጋለን፤›› ይላል፡፡ የተመልካቾችን ቀልብ ለመሳብ ሲባል የሚያስቁ ሁነቶች ቢኖሩም ጠቃሚ መልዕክቶችም ተሳስረው እንደሚቀርቡ ያክላል፡፡ እያዩ እያዝናና መልዕክቱን ማስተላለፉ እንደ ገፀባህሪ እውቅና እንዲያገኝ እንዳደረገውም ያምናል፡፡

ደራሲው ከመድረክ ቆይታቸው የማይዘነጉ ከሚላቸው የእያዩ ፈንገስ መድረኮች አንደኛ ዓመት ክብረ በዓሉ ላይ የቀረበውን ይጠቅሳል፡፡ በዝግጅቱ ላይ ግሩም የ40 ደቂቃ ትዕይንት አቅርቦ ነበር፡፡ ትዕይንቱ ‹‹ፌስታሌን›› ወደሚለው የሙሉ ጊዜ ቴአትር ለመሸጋገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ይናገራል፡፡ ሰዎች ለረዥም ደቂቃ ያለ ምንም ቴአትራዊ ግብዓት መመልከታቸው፣ ግብዓቶች ተካተውና ተራዝሞ ቢቀርብ ተመልካች እንደሚያገኝ እንዳመለከታቸው ይገልጻል፡፡

የዋን ማን ሾው አለመለመድ ቴአትሩ ተመልካች ያገኝ ይሆን የሚል ጥያቄ እንዳጫረባቸው ይናገራል፡፡ በአንድ ተዋናይ የሰውን ስሜት መንካትና ቀልብ ገዝቶ ለረዥም ጊዜ መመልከት እንዲቻል ለማድረግ ፈታኝ እንደነበረም ይገልጻል፡፡

እሱ እንደሚለው፣ አንዳንዶች እያዩን የሚረዱበት መንገድም ሌላው ችግር ነው፡፡ ‹‹እያዩን የፖለቲካ መሣሪያ አድርገው የሚወስዱ አሉ፡፡ እውነታው ግን እንደዛ አይደለም፡፡ ስለ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሲያነሳ ፖለቲካውን ይዳስሳል፡፡ ይህ ደግሞ የተቃውሞ ጽምፅ አይደለም፤›› ይላል፡፡

እያዩ በጦቢያ ግጥምን በጃዝ መድረክ ሲቀርብ ካገኛቸው ምላሾች መካከል ጥቂቱን ይጠቅሳል፡፡ እያዩ ላይ ያተኮረ ጥናት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መሠራቱን፣ ከአዲስ አበባ ውጪ ጎንደርና ሻሸመኔ በሄደበት ወቅት የተገኘውን ምላሽና በእያዩ ስም በማኅበረሰብ ድረ ገጽ የተከፈተውን ገጽ ማንሳት ይቻላል፡፡ ቴአትሩ ስኬታማ መሆኑ ሌሎች ባለሙያዎችንም ወደ ዘርፉ የሚስብ እንደሆነ ተስፋ ያደርጋል፡፡

ቴአትሩን ፕሮዲውስ ያደረገው አበባው መላኩ ሲሆን፣ ማጀቢያ ሙዚቃው ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች አበጋዝ ክብረወርቅ ሺኦታ፣ ግሩም መዝሙር፣ ጆርጋ መስፍንና አለማየሁ ደመቀ ናቸው፡፡ ተውኔቱን ከአዲስ አበባና ከኢትዮጵያ ውጪ የማሳየት እቅድ እንዳለ በረከት ይናገራል፡፡ ቴአትሩ አንድ ተዋናይ ያለው መሆኑ ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር እንደሚያመች ያክላል፡፡

 ‹‹ፌስታሌን›› ለጥቂት ጊዜ ከታየ በኋላ ‹‹አጀንዳዬን›› የሚል ቀጣይ ክፍል ይኖራል፡፡ ቴአትሩን በቪሲዲ የማሳተም እቅድም አለ፡፡ የእያዩ ትዕይንት በጦቢያ ግጥምን በጃዝ መድረክም ይቀጥላል፡፡ በያዝነው ሳምንት ምርቃቱን ምክንያት በማድረግ አርብና ቅዳሜ በ12 ሰዓት በአዶት ሲኒማና ቴአትር ይታያል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...