Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርከሚያምረን ይልቅ የሚያምርብን ይመረጥ

ከሚያምረን ይልቅ የሚያምርብን ይመረጥ

ቀን:

በዮዲት ሸዋረጋ

በቅርቡ ከካናዳ (ሞንትሪያል) ከመጣ አብሮ አደጌ ጋር በመጣበት የኢንቨስትመንት ጉዳይ ምክንያት ከተማው ውስጥ ያላዳረስነው ቦታ የለም፡፡ ከሥራ ሰዓት ውጪ የተለያዩ መዝናኛ ሥፍራዎች ስንሄድ በዚህ ክረምት ወራት የሴቶቻችን አለባበስ በጣም ነበር ያስገረመው፡፡ ምንም እንኳ ክረምቱ ያዝ ለቀቅ ቢሆንም፣ ዝናብ መዝነቡና ቅዝቃዜው መሸንቆጡ አልቀረም፡፡ ሴቶቻችን ስስ አልባሳትና አብዛኞቹን የሰውነት ክፍሎቻቸውን የሚያጋልጡ እራፊ ጨርቆችን እየለበሱ መታየታቸው ለአብሮ አደጌ አልተመቸውም፡፡ በተለይ መሸት ሲል የሚያያቸው ‹‹ራቁት ቀረሽ›› የሚባሉት የቆነጃጅቱ አለባበሶች በጣም ስላስገረሙት አንድ አስገራሚ የውጭ አገር ትረካ ነገረኝ፡፡ እንዲህ ልንገራችሁ፡፡

ሁለት ወጣት ሴቶች ለዓይን በማይመች አለባበስ አብዛኛውን የሰውነታቸውን ክፍል አራቁተው በአንድ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ከአዳራሹ ይደርሳሉ፡፡ በአለባበሳቸው በጣም የተገረመውና የተበሳጨው የስብሰባው ሊቀመንበር በሚገባ ካጤናቸው በኋላ ‹አንዴ ላናግራችሁ› ብሎ ወንበር ስቦ ያስቀምጣቸዋል፡፡ ከዚያም ዓይናቸውን በቀጥታ እያየ በሕይወት ዘመናቸው የማይረሱትን ነገራቸው፡፡ ይህ ታሪካዊ ንግግር ይህንን ይመስላል፡፡

‹‹ወይዛዝርት! በዚህ ምድር እግዚአብሔር የመረጠው ውድ ነገር በሚገባ የተሸፈነ፣ ከአላስፈላጊ ነገር የተጠበቀ፣ በቀላሉ የማይታይና ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ እስቲ አንድ በአንድ ልዘርዝርላችሁ፡፡ አልማዝ የሚገኘው የት ነው? እጅግ ጥልቅ የሆነ ሥፍራ በደንብ ተሸፍኖና በሚገባ ተከልሎ ነው፡፡ ዕንቁ የት ይገኛል? ከጥልቁ ባህር ወለል ላይ ሲሆን፣ በሚገባ የተሸፈነ፣ የተጠበቀና ውብ በሆነ ሼል ውስጥ ነው፡፡ ወርቅ የት ይገኛል? ከጥልቁ የማዕድን ማውጫ ውስጥ በንብርብር አለቶች ውስጥ ተሸፍኖ ነው፡፡ እነዚህን ውድ ማዕድናት ለማግኘት ደግሞ በጣም መልፋት፣ በጥልቀት ማሰስና መቆፈር የግድ ይላል፤›› አላቸው፡፡

እንደገና ፊቱን ኮስተር አድርጎ በቁጣ ዓይኖች እየተመለከታቸው፣ ‹‹አያችሁ አካላችሁ የተቀደሰና ልዩ ነው፡፡ እናንተ ከአልማዝ፣ ከዕንቁና ከወርቅ እጅግ በጣም የበለጣችሁ ውድ ፍጥረቶች ናችሁ፡፡ በመሆኑም ሁሌም አካላችሁ መሸፈን አለበት፡፡ እናም ይህንን አካላችሁን (ሀብታችሁን) እንደ አልማዝ፣ ዕንቁና ወርቅ በሚገባ ከሸፈናችሁት በጣም ታዋቂና ዝነኛ የማዕድን ድርጅት ተገቢውን ማሽን ይዞ በመምጣት ለዓመታት የሚዘልቅ ፍለጋ ማድረግ ይጀምራል፤›› በማለት አሁንም ኮስተር ብሎ አያቸው፡፡

‹‹ይህ ታዋቂ ኩባንያ መጀመሪያ ከመንግሥታችሁ (ቤተሰብ) ጋር ይገናኛል፡፡ ከዚያም የኮንትራት ስምምነት ለማድረግ ድርድር (ሽማግሌ) አድርጎ ውል ያፀናል፡፡ በኋላም ፕሮፌሽናል የማዕድን ማውጣት ሥራ ለማድረግ የሚያስችለውን ሥነ ሥርዓት (ሕጋዊ ጋብቻ) ያደርጋል፡፡ ነገር ግን የራሳችሁን ውድ ማዕድን ሜዳ ላይ በግልጽ ከተዋችሁት ለሕገወጥ ማዕድን አውጪዎች በመጋለጥ ሀብታችሁን ታዘርፋላችሁ፡፡ እነዚህ ሕገወጦች ያልተገሩ መሣሪያዎቻቸውን በመጠቀም በነፃ በመቆፈር ያላግባብ ይጠቀሙባችኋል፡፡ ስለዚህ ክቡር የሆነውን ገላችሁን በተገቢው ሁኔታ በመሸፈን ራሳችሁን ከሕገወጦች (ደፋሪዎችና ሴሰኞች) ስትጠብቁ፣ ፕሮፌሽናል ማዕድን አውጪዎች (ለተከበረው ጋብቻ የሚፈልጉዋችሁ) በክብር ይቀርቡዋችኋል፤›› በማለት ይህ የተባረከ ሰው ነገራቸው ሲል አብሮ አደጌ የዘመኑን የምዕራቡ ዓለም ትርክት (Narration) ነገረኝ፡፡

እንግዲህ እህቶቼ ‹‹ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ››፣ ‹‹ባለቤት ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም፣›› ‹‹መከበር በከንፈር››፣ ወዘተ የሚባሉ ምርጥ ብሂሎች ባሉበት አገርና ኩራት በሚያስከብርበት ሕዝብ ውስጥ መዝረክረክ ጥሩ አይደለም፡፡ ያስንቃል፡፡ ከካናዳ የመጣው አብሮ አደጌ ሴቶቹን ብቻ አይደለም፣ የተዝረከረከ ሱሪ ለብሰው ከወገባቸው በታች አልረጋ ያላቸውን ሳይቀር ሲቆጣ ነበር የሰነበተው፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ይህች የተከበሩ ሕዝቦች አገር ኩሩ ባህሎችና ደስ የሚያሰኙ መሳጭ ታሪኮች ያላት በመሆኗ፣ በአጉል አለባበስ መዝረክረክ ተገቢ አይደለም ነው የሚለው፡፡ ወደ ወይዛዝርቶች ልመለስ፡፡

ከዓመታት በፊት ‹‹ሴቶች የሚያምራችሁን ሳይሆን የሚያምርባችሁን ብትለብሱስ?›› የሚል ጽሑፍ ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ በወቅቱ ጸሐፊው በአዲስ አበባ ውስጥ በልብስ ስፌትና ዲዛይን ታዋቂ ከሆኑ ወይዘሮ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ መሠረት አድርጎ ነበር ጽሑፉን ያቀረበው፡፡ ብዙዎቹ የልብስ ዲዛይነሮችም ከሚያምረን ይልቅ የሚያምርብንን ብንለብስ የተሻለ እንደሆነ ይመክሩናል፡፡ ብዙዎቻችን ይህንን ምክር ተቀብለን ተግባራዊ ብናደርግ ተጠቃሚዎቹ እኛ እንደሆንን ይሰማኛል፡፡

የዛሬ አሥር ዓመት ገደማ ፒያሳ የኤሌክትሪክ ሕንፃ አጠገብ ቆሜ ጓደኛዬን እጠብቃለሁ፡፡ አንዲት ለግላጋ ወጣት ከመሐረብ ብዙም ከፍ የማይል ቀሚስ ተብዬ (ሚኒስከርት) ለብሳና ረጂም ታኮ ጫማ ተጫምታ ስትውረገረግ፣ አንድ ከየት መጣ የማይባል ንክ (ዕብድም ሊሆን ይችላል) ዘሎ ላይዋ ላይ ይከመራል፡፡ ከዚያም አንዳች በሚያህሉ እጁ ይቺን ቀሚስ ተብዬ እራፊ ከላይዋ ላይ ገፎ ሲወረውር ልጅቷ ራቁቷን ቀረች፡፡ በጣም አስደንጋጭ ነበር፡፡ በአካባቢው የነበሩ ፖሊሶችና ተላላፊዎች ተረባርበው ከዚያ አስፈሪ ሰው እጅ ባያድኗት ኖሮ ዘግናኝ ነገር ነበር የምናየው፡፡

እንዲህ ዓይነቶቹ አጋጣሚዎች ብዙ ቢያነጋግሩንም፣ በተለይ በክረምት ወራት ለአለባበስ ተገቢውን ትኩረት ብንሰጥ ለጤናም ጠቃሚ ነው፡፡ በየክሊኒኩና በየሆስፒታሉ በቅዝቃዜ ምክንያት ከሚፈጠሩ ሕመሞች መካከል በዋናነት በአለባበስ ግድየለሽነት ምክንያት የሚከሰቱት ብልጫ አላቸው፡፡ አጉል ለማጌጥ ሲባል ራስ ላይ አደጋ መጋበዝ ትልቅ የጤና ጠንቅ ነው፡፡

እኔም ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ አብሮ አደጌ እንደተመረረበት በጣም አሳዛኝ ነገሮች በአገራችን ስለሚስተዋሉ ነው፡፡ የምዕራባውያን የባህል ወረራ ውጤት የሆነው አጉል አለባበስ የሥልጣኔ ምልክት እየሆነ ብዙዎችን እያሳሳተ ነው፡፡ በበጋና በክረምት፣ በቀንና በምሽት እንዴት እንደሚለበስ (ባለ አቅም) ማወቅ ካልቻልን ችግር ነው፡፡ ከሕዝባችን የጋራ መገለጫ ከሆኑት ኩሩነትና ደርባባነት አንፃር አሁን የሚታየው ሁኔታ አያስኬድምና እናስብበት፡፡   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...