Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየኢትዮ አሜሪካ ታሪካዊ የግንኙነት ሒደትና የደረሰበት ከፍታ

የኢትዮ አሜሪካ ታሪካዊ የግንኙነት ሒደትና የደረሰበት ከፍታ

ቀን:

በጥሩነህ ዜና (አምባሳደር)

የሁለት አገሮች ግንኙነት በመንግሥታት ደረጃ የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ1903 በአፄ ምንሊክና በፕሬዚዳንት ቴኦዶር ሩዝቬልት መልዕክተኛ በሆኑት በሚስተር ሮበርት እስኪነር መካከል በተደረገው የንግድ ስምምነት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ፈር ቀዳጅ የሆነው ስምምነት ለሁለቱ አገሮች ይህ ነው የሚባል ፋይዳ ያለው ጠቀሜታ ሳያስገኝ እስከ ጣሊያን ወረራ ድረስ ዘልቋል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያ የጣሊያን ቅኝ ግዛት መሆኗን ላለመቀበል ከወሰኑ አምስት አገሮች አንዱ ቢሆንም፣ በአምስት ዓመታት የጣሊያን ወረራ ወቅት የኢትዮጵያን አርበኞች (ሕዝቦች) በሞራልም ሆነ በፖለቲካ ለመርዳት ያደረገው የሚታይ እንቅስቃሴም ሆነ ጥረት አልነበረም፡፡

በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት በመንግሥት ደረጃ ጠንከር ብሎ የወጣው በ1940ዎች መጀመሪያ ኢትዮጵያ እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ወቅት ነው፡፡ በወቅቱ የእንግሊዝ መንግሥት ጣሊያንን ከኢትዮጵያና ከአካባቢው ለማስወጣት የአፄ ኃይለ ሥላሴ በቦታው መገኘት ያለውን ጠቀሜታ በመገመት፣ ንጉሡ ከለንደን ተነስተው በሱዳን በኩል ከእንግሊዝ ወታደሮች ጋር ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ወስኖ ነበር፡፡  በዚህ መሠረት ንጉሡ በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ቢገቡም ከኬንያ ወደ አዲስ አበባ የተንቀሳቀሰው የደቡብ አፍሪካ፣ የህንድ፣ የናይጄሪያ፣ የጋና፣ የቤልጂግና የፈረንሣይ ወታደሮችን ያቀፈው የኮመንዌልዝ ሠራዊት ከኢትዮጵያ አርበኞች ጋር በአጭር ጊዜ ውስጥ የጣሊያንን ሠራዊት በማሸነፍ አዲስ አበባ የገባው ከንጉሡ አንድ ወር ቀደም ብሎ ነበር፡፡

- Advertisement -

ንጉሠ ነገሥቱ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስተር በነበሩት በዊንስተን ቸርችልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩት አንቶኒ ኤደን በተሰጣቸው ቃል መሠረት ነፃይቱን ኢትዮጵያ ለመገንባት አዲስ አበባ ቢገቡም፣ ቀደም ብለው የገቡ የእንግሊዝ የቅኝ ግዛት አስተዳደር ኃላፊዎች ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች እንግሊዝ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ እንድትቆጣጠር ያስገድዳሉ የሚለውን አቋም በመያዝ፣ ንጉሡ ሥልጣን እንደሌላቸው በመግለጽ አገሪቱን ማስተዳደር ጀመሩ፡፡ በእነዚህ ባለሥልጣናት አስተሳሰብ ሊቢያ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያና የጣሊያን ሶማሊያ የጠላት ግዛቶች ስለሆኑ፣ የሰላም ንግግር በእንግሊዝና በጣሊያን መካከል ተደርጎ ዕጣ ፈንታቸው እስኪወሰን ድረስ በእንግሊዝ ቁጥጥር ሥር መቆየት እንዳለባቸው ተደረገ፡፡

ከዚህ በላይ በተጠቀሰው ምክንያት በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መንግሥታት መካከል የ1942 ስምምነት እስኪፈርም ድረስ ንጉሡን ሥልጣን አሳጥቷቸው ቆይቷል፡፡ ይህ ስምምነት በመግቢያው ኢትዮጵያ ነፃ አገር መሆኗን የሚጠቅስ ቢሆንም፣ የእንግሊዝ ዜጎች ለኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካና የሕግ አማካሪዎች፣ የፖሊስ አዛዦች፣ የፍርድ ቤት ዳኞች፣ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ የእንግሊዝ ጦር አዛዥ ሳይፈቅድ የኢትዮጵያ መንግሥት በወታደራዊ ጉዳይ ከሌላ የውጭ አገር መንግሥት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ማድረግ እንደማይችል የሚዘረዝሩ አንቀጾች ነበሩት፡፡ በኢኮኖሚ ረገድም የእንግሊዝ የምሥራቅ አፍሪካ ሽልንግ የአገሪቱ ኦፊሴላዊ ገንዘብ ሆኖ እንደያገለግል ይፈቅዳል፡፡ ይህንን ስምምነት ለመቀየር ኢትዮጵያ ብቻዋን ከእንግሊዝ ጋር ለመጋፋትም ሆነ፣ ኢኮኖሚዋን በተለይም የመከላከያ ኃይሏን ለብቻዋ ለመንገባት በወቅቱ የነበሩ ነባራዊ  ሁኔታዎች የሚፈቅዱ አልነበሩም፡፡

ስለሆነም እየተካሄደ ባለው ጦርነት ኢኮኖሚዋ ያልደቀቀባትና የአፍሪካን አገሮች እንደቅርጫ ከፋፍሎ የመግዛት ልምድና ዓላማ ካልነበራት ከአሜሪካ ጋር ወዳጅነት በመፍጠር፣ ለችግራቸው መፍትሔ ለማግኘት ንጉሡ መንቀሳቀስ የጀመሩት በዚህ ወቅት ነበር፡፡ በአሜሪካ በኩልም ኢትዮጵያን በአውሮፓና በመካከለኛው ምሥራቅ ላለው የጦር ኃይል የምግብ አቅርቦት ምንጭ ለማድረግ እንደሚቻል ግምት ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ሩዝቬልት ከአፄ ምንሊክ ዘመን ጀምሮ ከኢትዮጵያ ወገን በከንቲባ ገብሩ ደስታ፣ በሐኪም ወርቅነህ በተለይም  በጦርነት ወቅት በዶ/ር መላኩ በያን፣ በአሜሪካ በኩል ደግሞ በእነ ዊልያም ኤች ኤልስ (ታዋቂ ነጋዴ) ደበሊዉ ኢ ድቦዋ (ተቀዳሚ የጥቁር አንድነት ሊቅ) ኮሎኔል ጆን ሮቢንሰን (በማይጨው ከኢትዮጵያ ጎን ሆነው የተዋጉ) በመሳሰሉ ግለሰቦች ጥረት በከፍተኛ ደረጃ የደረሰውን የአሜሪካ ጥቁሮች ከኢትዮጰያ ሕዝብ ጋር ያላቸውን የትግል አንድነት (ሶሊዳሪቲ) በውል ተረድተው ነበር፡፡ የአሜሪካ ጥቁሮች በዚያ መጥፎ ጊዜ የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆም ባይሳካላቸውም ከፍተኛ የሚባል እንቅስቃሴ አድርገዋል፡፡ ተከለከሉ እንጂ ብዙዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ለመዋጋት ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህች አንጋፋ ጥቁር አገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ከነፃነት በኋላ ከእነዚህ ወገኖች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ለመፍጠር የሞከረችበት ወቅት የለም፡፡

በወቅቱ አሜሪካ በአዲስ አበባ በውል ያልተወከለች በመሆኗ በኢትዮጵያ በኩል ያለው ፍላጎት ለአሜሪካ ሊገለጽ የቻለው በአቶ ይልማ ዴሬሳ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ፣ በዓለም የምግብ ድርጅት ስብሰባ ለመካፈል ወደ አሜሪካ በሄደበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ልዑኩ ከስብሰባ ውጪ በሚካሄዱት የሁለትዮሽ ጉዳዮችን በተመለከቱ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ እነዚህም ኢትዮጵያ ብር ለማሳተም  እንዲቻላትና ብድር እንዲሰጣት፣ ከእንግሊዝ ጋር የተደረገው የ1942 ስምምነት እንዲለወጥ በእንግሊዝ ላይ ግፊት እንዲደረግ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ የንግድና የገንዘብ እንቅስቃሴዎች ከእንግሊዝ ተፅዕኖ ለማላቀቅ እንዲቻል የቴክኒክ ዕርዳታ እንዲሰጥ የሚጠይቁ ነበር፡፡

ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ንጉሠ ነገሠቱ በ1944 ዓ.ም. ከፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት ጋር በግብፅ በተነጋገሩበት ወቅት የወታደራዊ ዕርዳታ፣ የኤርትራና የባህር በር ጉዳይ፣ እንዲሁም የአሜሪካ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ማበረታታት የሚሉት ነጥቦች ተነስተው እንደነበር ይታወሳል፡፡ እነዚህና የመሳሰሉት ጥያቄዎች በየጊዜው ከአሜሪካ አወንታዊ መልስ በማግኘታቸው ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ ጋር ልዑላዊነቷን የሚያረጋግጥ የ1944 ዓ.ም. ስምምነት በመፈራረም ከእንግሊዝ ጥገኝነት ለመላቀቅ ችላለች፡፡ በመሆኑም ለአሜሪካና ለኢትዮጵያ ግንኙነት ጠንካራ መሠረት የጣለውና ለኢትዮጵያም ከፍተኛ ጥቅም ያስገኘው የአሜሪካ መንግሥት ከ1940ዎች አጋማሽ እስከ 1960ዎች መጨረሻ ድረስ ያደረገው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ዕርዳታ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለኤርትራና ለኦጋዴን ችግሮች መፍትሔ በማግኘት ለረጅም ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የባህር በርና በቅኝ ገዥዎች ተወስደውባት የነበሩትን ግዛቶች በማስመለስ ረገድ የአሜሪካ ዕርዳታ ወሳኝ ነበር፡፡ ከዚህ ወቅት ጀምሮ እ.ኤ.አ እስከ 1978 ባለው ጊዜ ውስጥ ከአሜሪካ መንግሥት 282 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ወታደራዊ ዕርዳታ፣ 366 ሚሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ዕርዳታ እንደተገኘ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በኢትዮጵያ በተለይ እ.ኤ.አ. ከ1972 ጀምሮ እያየለ ባካሄደው ድርቅና ረሃብ የብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ሕይወት ለማዳን አሜሪካኖች ያደረጉት ሰብዓዊ ዕርዳታ እጅግ  ከፍተኛና ሊረሳ የማይችል  ነው፡፡

ይህ መልካም የሚባል የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በወቅቱ ለኢትዮጵያ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ጉዳትም አስከትሎ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በመቀላቀልዋ የተበሳጩ የዓረብ አገሮችና ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር የመከላከያና የኢኮኖሚ ተራድኦ ስምምነት በ1963 በመፈራረሟ ያልተደሰተችው ሶቭየት ኅብረት (ሩሲያ) በማበር የኤርትራ ነፃ አዋጪዎችንና የሶማሊያን መንግሥት በወታደራዊ ኃይል በማጠንከር በኢትዮጵያ ላይ እንዲዘምቱ የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በአካባቢው ያለው የኃይል ሚዛን በእጅጉ መዛባቱን ንጉሠ ነገሥቱ እ.ኤ.አ. በ1973 አሜሪካን በጎበኙበት ጊዜ ለፕሬዚዳንት ኒክሰን አበክረው ቢገልጹም፣ ከፕሬዚዳንቱ ያገኙት መልስ ተሰፋ የሚሰጥ እንዳልነበረ በወቅቱ የተዘጋጁ ቃለ ጉባዔዎች ያረጋግጣሉ፡፡ አሜሪካ ወዳጅነቷን በመጠቀም ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር የሚያጋጩ ዕርምጃዎችን እንዳትወስድ ትጎተጉት ነበር፡፡

ለምሳሌ ያህል ፕሬዚዳንት ናስር የስዊዝ ቦይን እንደወረሱ በጉዳዩ ላይ ተነጋግሮ አቋም እንዲወሰድ የምዕራብ አገሮች በለንደን በጠሩት ስብሰባ ላይ፣ ከምዕራባውያን በተጨማሪ ኢትዮጵያ እንድትገኝ ተደርጋ ነበር፡፡ ይህን ስብሰባ ግብፅ በእሷ ላይ ያነጣጠረ ደባ እንደሆነ በመረዳት በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን የጠላትነት ዕርምጃ አጠናክራለች፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መድረክ በአሜሪካ ግፊት የሚወሰዱ አንዳንድ አቋሞችም ከአካባቢው አገሮች ጋር የሚያጣሉ ነበር፡፡

ከዚህ በላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች በኢትዮጵያ ላይ የአካባቢው አገሮች ጫና ባየለበትና የአሜሪካ የመሣሪያ ዕርዳታ በቀዘቀዘበት አደገኛ ወቅት ነበር በኢትዮጵያ አብዮት የፈነዳው፡፡ አሜሪካኖች በወቅቱ ንጉሡ ፈላጭ ቆራጭ በመሆናቸው ከለውጡ በኋላ የሚመጣው መንግሥት ምቹ እንደሚሆን በመገመት ለመተባበር ዝግጅት እንደሆኑ በጉዳዩ ላይ የቀረቡ የውስጥ ማስታወሻዎች ያሳያሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ንጉሡ ጠይቀዋቸው የከለከሉዋቸውን መሣሪያ ጭምር ለደርግ ለመስጠት አስበው ነበር፡፡ የኢኮኖሚ ዕርዳታም በንጉሡ ጊዜ ከነበረው እንደሚጨምር አስታወቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ደርግ በ60ዎች ከፍተኛ የቀድሞ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ላይ ያለፍርድ ዕርምጃ በመወሰዱና የአካባቢውና የዓረብ አገሮች (ግብፅ፣ ሱዳንና ሳዑዲ ዓረቢያ) በሚያደርጉት ግፊት ምክንያት ዕርዳታውን መቀነስና በወቅቱ ያለመልቀቅ አዝማሚያ ያሳዩ ጀመር፡፡ ደርግም በበኩሉ የጀመረውን የፀረ አሜሪካ ፖሊሲ በማጠናከሩ በአገሮቹ መካከል የነበረው ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ሊለወጥ ችሏል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት በተለይም ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ በደርግ ጊዜ ከሰብዓዊ ዕርዳታ በስተቀር ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድርጅቶች ጭምር ምንም ዓይነት ዕርዳታ እንዳታገኝ በርካታ ውሳኔዎችን አሳልፎ ስለነበር፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ  በኋላም እንኳ ብዙ መሰናክሎችን ሲፈጥሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በደርግ  ጊዜ ተላልፈው የነበሩት እነዚህ ውሳኔዎች በተለይም ‘የዓለም አቀፍ ፀጥታና የልማት አክት’ መንግሥት ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት በመነሳቱ፣ ዕርዳታው ከዓለም ባንክና ከአሜሪካ መንግሥት መምጣት ጀመረ፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ዕርዳታ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ቢሆንም፣ በመጀመሪያዎቹ የኢሕአዴግ ዘመን ከሞላ ጎደል የምግብ ዕርዳታ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ በምግብ ራስዋን ለመቻል ባደረገችው ጥረት የድርቁና የረሃቡ ችግር እየተወገደ በመምጣቱ የአሜሪካ ዕርዳታ በጤና፣ በእርሻ፣ በትምህርትና በመሳሰሉት መስኮች ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡

በሁለቱ አገሮች መካከል እያደገ የመጣው ባለ ብዙ ፈርጅ ግንኙነት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት መወሳሰብና ገባ ወጣ ማለት ጀምሮ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በዚህ ወቅትና ከጦርነቱ በኋላ በነበሩ ጥቂት ዓመታት  የተፈጠረውን ሁኔታ ለመመልከት ጉዳዩ ገና እልባት ያላገኝ በመሆኑ ለጊዜው ማለፉ የተሻለ ይሆናል፡፡ ከኤርትራ ጦርነት በኋላ ለሁለቱ አገሮች ግንኙነት መቀዛቀዝ ምክንያት ሆኖ የነበረው እ.ኤ.አ. በ2005 የተካሄደው ምርጫ (ምርጫ 97) ነበረ፡፡ ከምርጫው በኋላ በተለይም የአሜሪካ ኮንግረስ የሰብዓዊ መብቶችን መጣስ ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ዕርዳታዎችን ለማገድና ለመቀነስ ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች፣ በአገሮቹ መካከል እያደገ በመሄድ ላይ በነበረው መልካም ግንኙነት ላይ ጫና ፈጥሮ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የአገሮቹ ግንኙነት ያጋጠሙትን ችግሮች ቀስ በቀስ በመቅረፍ ወደላቀ ደረጃ ደርሷል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለበት ምክንያቶች አንዱ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ መስክ እያሳየች ያለችው ፈጣን ዕድገት ነው፡፡ ይህ ዕድገት ከቅርብ ዓመታት በፊት ኢኮኖሚውን ቀስፎ ይዞ የነበረውን ግሽበት በሚታይ ሁኔታ ቀንሶ፣ ከአምስት ዓመታት በፊት አምስት በመቶ  የነበረውን የአገር ውስጥ ቁጠባ ወደ 18 በመቶ ከፍ አድርጓል፡፡ ይህ ዕድገት ከነዳጅ ዘይት ወይም ከአልማዝና ከወርቅ የመነጨ ሳይሆን፣ ከሕዝቡ ሰማንያ በመቶ የሚሆነውን የገጠር ነዋሪ ያሳተፈና እሱን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ፣ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ከሚታያው ለየት ይላል፡፡ ሌላው በአክራሪዎችና እርስ በርስ በሚካሄድ ግጭት በሚናጠው ቀጣና ኢትዮጵያ የሰላም ደሴት ከመሆንዋ በተጨማሪ፣ የቀጣናውን ሰላም በማረጋጋት ረገድ የመሪነት ሚና በመጫወትዋ በአኅጉሩና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያገኘችው አክብሮት እንደሆነ ለመገመት የሚያስቸግር አይደለም፡፡ አገሪቱ ከላይ የተጠቀሱ በዓለም ደረጃ የተደነቁ ውጤቶችን ያስመዘገበችው በጠንካራ ተቋምና በተቀናጀ አመራር መሆኑ እንዲሁ ሌላ አድናቆት ያተረፈ ጉዳይ ነው፡፡

 ለዚህ ነው ከ112 ዓመታት የዲፕሎማሲ ግንኙነት በኋላ የአሜሪካ በሥልጣን ላይ ያሉ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የመጡት፡፡ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በጣም ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ነበር በተባለበት በ1950ዎች መጨረሻ ቢሆንም፣ አገሪቱን ለመጎብኘት አዲስ አበባ ድረስ የመጡት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ በተረፈ የኢትዮጵያ መሪዎች እስከ ዋሽንግተን በመሄድ ከአሜሪካ መሪዎች ጋር የተገናኙባቸው ጊዜያት በርካታ እንደሆኑም ይታወቃል፡፡ ያም ቢሆን በእኛ ጥያቄና ጉትጎታ እንጂ ከወዲያ ፍላጎትና ጥሪ ቀርቦ የተፈጸመ እንዳልነበር ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ሁሉ የሚያውቁት ነው፡፡ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ቀድማ እንደነበረችው ላጋጠማት ችግር የሌሎቹን አገር ዕርዳታ ለመሻት የምትሯሯጥ ሳትሆን፣ የዓለም አቀፍ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩሏን አስተዋፅኦ እንድታደርግ በኃያላን ጭምር የምትፈለግ ነች፡፡ ዛሬ የአካባቢውንም ሆነ የአኅጉሩን ችግር ለመፍታት የሚጥሩ ወገኖች ኢትዮጵያን ከጎናቸው ማሰለፍ እንዳለባቸው የሚያስገድዱ ሁኔታዎች በርካታ ናቸው፡፡

የዓለም የኃይል ሚዛን እንደገና መደላደል በጀመረበት በአሁኑ ወቅት እየተነሳች ያለችው አፍሪካ፣ በሁሉም መንግሥታት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ትንታኔ የጎላ ቦታ እያገኘች መምጣቷ የሚታወቅ ነው፡፡ ስለሆነም በአኅጉሩ በማያጠራጥር ሁኔታ የአውራነት ሚና የመጫወት ብቃት እያሳየች ካለችው ኢትዮጵያና መሪዎቿ ጋር  ግንኙነት ማጠናከርንና መቀራረብ ከማንኛውም ብልህ መሪ የሚጠበቅ ነው፡፡ የፕሬዚዳንት ኦባማ ጉብኝት መቃኘት ያለበት በዚህ ዕይታ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትና ለወደፊት በአኅጉሩና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊኖራት የሚችለውን ተፅዕኖ በመገመት አሜረካ ብቻ ሳትሆን፣ ሌሎች የአገሮችና የተቋማት መሪዎች አዲስ አበባን በተለያዩ ምክንያቶች በመጎብኘት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ወዳጅነት ለማጥበቅ እየተቀንሳቀሱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ነው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት 50ኛ ምሥረታ በዓል በአዲስ አበባ በተከበረበት ወቅት ከሁሉም አኅጉራት የታላላቅ አገሮች መሪዎች በአዲስ አበባ የተገኙት፡፡

እንዲሁም እየተጠናቀቀ ባለው የሐምሌ ወር ሦስተኛው የፋይናንስ ለልማት ዓለም አቀፍ ጉባዔን ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ ተመርጣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ፣ የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንትና ከ67 አገሮች የተወከሉ የገነንዘብ ሚኒስትሮች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ እንዲሁም የተለያዩ የአኅጉራትና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ የተካሄደው፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይህን ስብሰባ እንዲመሩ መደረጋቸው የራሱ አንድምታ አለው፡፡

የፕሬዚዳንት ኦባማ ጉብኝት ኢትዮጵያ የደረሰችበትን ከፍታ አጉልቶ ለዓለም የሚያሳይ መነጽር ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ስለኢትዮጵያ ሰላምና ብልፅግና የተናገሩዋቸው ቃላት ከማንኛውም ማስታወቂያ የበለጠ ኢንቨስተሮችን ወደ ኢትዮጵያ የሚስቡ ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ እንደ ኢትዮጵያ ያለ መንግሥት በኃይል ለመጣል የሚሞክሩትን አሜሪካ እንደምትቃወም የተናገሩትን፣ በአገሪቱ እያደገ በመሄድ ላይ ያለውን ዴሞክራሲ በመጣል ውዥንብር ለመፍጠር የሚፈልጉ ሁሉ ልብ ሊሉት የሚገባ ነው፡፡ እንዲሁም ተራ ግለሰብ በመንደር የሚያወራውንና የመንግሥት አቋም ሳይለዩ የፖለቲካ ተንተኝ መስለው በአገሮች መካከል አላስፈለጊ ውጥረት ለመፍጠር ለሚሹ ወገኖችም ጥሩ ትምህርት ነው፡፡ በአጠቃላይ የፕሬዚዳንት ኦባማ ጉብኝት ለኢትዮጵያና ለመሪዎችዋ “Vote of Confidence” ሲሆን፣ ይህ ጉብኝት በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን የጣሩ ወገኖችን በእጅጉ የሚያኮራ ነው፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተው በቅርቡ ኃላፊነታቸውን ማስረከባቸው ይታወሳል፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው   [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

                                                                             

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...