Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሐሳብና ህልም ያልሰመረበት ዘመን

እነሆ መንገድ። “ሙጀሌ ለበላሽ ፎክች ፎክች ላለሽ፣ ሸፋፋው መንገድ ነው ገዳዳው ትያለሽ አሉ። እንዲያው እኮ…” ይላሉ ጠና ያሉ ወይዘሮ ከሾፌሩ ጀርባ ቦታ እየያዙ። “ሙጀሌ ደግሞ ምንድነው?” ይላል አጠገባቸው የተቀመጠ ልጅ እግር። “ምን ይሰራልሃል ካልበላህ? ዕድሜ ለቻይና ጫማና መንገድ እናንተ የዛሬ ልጆች እኮ በአስተሳሰብ እንጂ በሙጀሌ አካሄዳችሁ አይበላሽም፤” ይሉታል። “አይ እማማ ያው ያለፈው መጪውን በቀና መንፈስ የማየት ‘ፎቢያ’ ኖሮበት እንጂ እንደየዘመኑ ገዳዳነት የሚያጣው ትውልድ አለ?” ሲላቸው፣ “ነገር ሲሆንማ ለመልሱ አንደኞች ናችሁ። ምናለ ታዲያ በነካ እጃችሁ የዚህችን አገር ቋጠሮ መፍታት ብትሞክሩ? እ? ሞክሩ እስኪ! ቅዱስ ያሬድ አንዲት ትል ወድቃ ስትነሳ አተኩሮ እያየ ከሙከራና ከጥረት ብዛት ስኬት እንዳለ ገባው። እህ የእሱ ወገን ሆናችሁ ሳለ በሰው ወርቅና ዜማ ካልደመቅን እያላችሁ በእሳት መንኮራኩር ካልተነጠቅን ከምትሉ፣ ምናለበት ከትል አብዝቶ ከሚበልጠው የሰው ልጅ ታሪክ ተምራችሁ ለአገር ብትጠቅሙ?” ብለው እንደመማፀንም እንደመቆጣትም አሉ።

“መቼ እንቢ አልን ብለው ነው? ከብልሆችና ከጠቢባን ታሪክ ልንማር ስንታትር የአሸናፊዎች ሽለላ፣ የአርበኞች ቀረርቶ እየበጠበጠ አስክሮን እኮ ነው የተሳከረብን፤” ብላ መሀል መቀመጫ ላይ ከወንድ ጓደኛዋ ጋር የተሰየመች ደመግቡ እንደ ዘበት ጣልቃ ገባች። ወይዘሮዋ ዘወር ብለው አይተዋት ፊታቸውን ሳይመልሱ ሦስተኛው ረድፍ አጠገቤ የተሰየሙ አዛውንት፣ “ቢቀና ባይቀና ምን ገዶኝ ለመንገድ፣ ደግ አበጀሁ ብሎ ክፉ ሊረግጥበት፤” ብለው ገጠሙ። በዕድሜ በጥቂት እንደሚያንሱዋቸው የሚያስታውቁት ወይዘሮ፣ “ክፉማ ክፉ ነው ውለታ መቼ ያውቃል፣ መንገድ እየሄደ በደግ ይራመዳል፤” አሉና ታክሲያችንን የቅኔ ቤት ቢያስመስሉት የገባውም፣ ያልገባውም፣ ግራ የተጋባውም ጭምር አጨበጨበ። ሸፈፍ ሸፈፍ ከሚል ጨዋታ ደግሞ አንደኛውን ሙጀሌን ማከክ ይሻላል መሰል?

ወያላው ገብቶ በሩን ይከረችማል። ታክሲያችን ከቆመበት ተነስቶ በአራት እግሩ መጋለብ ጀመረ። “ወይ ጉድ! ስንት የንፋስ ቁስል፣ የሐሳብ እከክ እንደማያስቸግረው ሁሉ ሙጀሌ የማያውቅ ትውልድ ይምጣ?” ይላሉ ወይዘሮዋ። ዞረው ዞረው ወደመጡበት፣ ኖረው አልያም አኗኑረው ወደ አፈር አይቀሬ መሆኑ የሕይወት ጎዳና ያሳመናቸው ይመስላሉ። ታዲያ ከመጨረሻ ወንበር አንድ ተሳላቂ ወጣት ይነሳባቸዋል። “መንገዱ አስፋልት ባስፋልት ሳይሆን፣ ዲግሪና ኑሮ የተጫነው ሳይቀር ድንጋይ እያነጠፈ አቧራና ጭቃ ሳያራግፍ ነበራ ሙጀሌ። ዛሬ ልማት በልማት ሆነን፣ ቢጠበንም በቀለበት መንገድ  ተሳስረን እያዩ ሴትዮዋ ምን ፍጠሩ ነው የሚሉን?” ይላል። “እንዲያ በል አንተ! የሰው ፈንገስ አልጠረግ እንዳለን ቀረ እንጂ በመንገድማ አንታማም፤” አለች አጠገቡ የተቀመጠች ነገር ጠማኝ መሳይ። አተኩረን ስናያት ግን እንደገባን አዕምሮዋ ጤነኛ እንዳልሆነ ገብቶናል።

 “ኧ? ደግሞ የሰው ፈንገስ ማለት ምን ማለት ነው?” ሲሉኝ አዛውንቱ፣  “በሰው ሥጋና በሰው ቆዳ የሚጫወት ቫይረስ ማለት ነዋ። ምነው? አውቆ እንዳላወቀ እየሆኑ ካሳበዱን ትልቅ ነን ባዮች ወንዝ ተጠምቀዋል መሰል?” ብላ ከለበሰችው ጂንስ ሱሪ ኪስ ውስጥ ፌስታል አውጥታ። የተቀነጣጠሱ ቅጠሎች አፏ ውስጥ እየሞጀረች “በማርያም፣ አሁን እኔን የመሰለች ቆንጆ ንክ ነች ሲሉ አያፍሩም? ነክተውኝ፣ ሳልደርስባቸው፣ ሳልጋፋቸው ‘ንክ’ ሲሉኝ ትንሽ ‘ሼም’ አያውቁም? እኔ አላበድኩም። ተደብቄ እንደ ፍየል የፈውሴን ቅጠል ስለማላመነዥክ እኮ ነው። ምነው እነሱ በአደባባይ የሰው እንጀራ ይበሉ የለም? በሰው ወርቅ እየደመቁ ትልቅ ሰው ይባሉ የለም? በሸሸኋቸው? ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም በቅጠልም እንጂ ባልኩ? ርስቴን፣ ድርሻዬን፣ ላቤን ስነጠቅ ይሁን ባልኩ? ለነገሩ ወትሮም ፈንገስ ፈንገስ ነው፤” ብላ ስታበቃ ፌስታሏን አንስታ እንደ ቡና ቁርስ ከጫቱ ካልዘገናችሁለት ትለን ጀመር። አይ መንገድና መገናኛው!

ወያላችን ሒሳብ እየተቀበለ ነው። በሾፌሩ ትይዩ መስመር መጨረሻ ጥጉን ይዞ የተቀመጠ ጎልማሳ ስልክ ይዟል። “ይሰማሃል? እኔ ይሰማኛል። አንተ ይሰማሃል? ይሰማኛል፣ ይሰማኛል፤” ይላል እየደጋገመ። “ታዲያ ከተሰማው ‘ወደገደለው’ አይገባም? ለምን ጆሯችንን ያሳምመዋል?” ስትል ከሾፌሩ ጎን የተሰየመች ተሳፋሪ ደግሞ እኛ ድረስ ይሰማል። ሾፌሩ፣ “ምን ታደርጊዋለሽ? ባለመደማመጥ ያሳለፍነው ጊዜ ቀላል ስላልሆነ እኮ ነው። ድንገት ስትደማመጪና ኔትወርኩ ጥርት ሲል እንዴት ግራ አይገባሽ?” አላት። “ግን  እንኳን ሰው የሚናገረውን ራሳችን የምናወራውን ሳይቀር እናዳምጣለን ብለህ ነው?” ስትለው ወዲያው ተግባቡ። “እሱ ላይ መጣሽ አየሽ። የአራዳ ልጅ የሚመቸኝ ለዚህ ነው። ለምሳሌ ሩቅ ሳትሄጂ የአስተዳዳሪውንና የአመራሩን ‘ፑትለካ’ ረስተሽ ከእኔ ብትጀምሪ፣ የምናገረውን የማዳምጠው ቀን የሠራሁትን ገንዘብ ማታስቆጥር ብቻ ነው። አስገባው እስኪ፤” ብሎ ታክሲውን አስቆመ። ወያላው ከፍቶ ያስገባል። ጉዟችን ይቀጥላል።

አጠገቤ የተቀመጡት አዛውንት ተሳፋሪዎች በሙሉ እየሰሙዋቸው፣ “እኔ የምለው? ግን ሐምሌ በጤናው ነው?” ብለው ጠየቁ። ያ ፌዘኛ ወጣት ይህቺን ሰምቶ፣ “አድሟል ይላሉ፤” አላቸው። “ምን አደረግነው ልጄ?” ሲሉት አዛውንቱ፣ “ሰው በአገሩ እንደ ሰው በማይቆጠርበት፣ ማንም ጉልበተኛና ቀማኛ እየተነሳ ያሻውን በሚያግበሰብስበት፣ ለደካማ ተቆርቋሪ በታጣበት አልዘንብም ነው አሉ የሚለው፤” አለ ቧልተኛው የምሩን ለማስመሰል ተኮሰታትሮ። “ታዲያ እንዲያ ሲል ዝም አልከው? ወትሮም ከሰማይ እንጂ ከምድር ተመፅውተን እንደማናውቅ አትነግረውም?” ብለው አዛውንቱ ሳቁ። ‘አፄ ኃይለ ሥላሴ ካልመጡ እንዳመሌ አልጨልምም አለ’ አለማለቱም አንድ ነገር ነው ኧረ!

ተራቸውን ጥንዶቹ ይጫወታሉ። “እኔ የምለው” ትለዋለች። ቅልስልስ ቅብጥብጥ እያለች። “እ?” ይላል አመል ይሁን ፍቅሩ አልቆ ዞር ብሎ እንኳ ሳያያት። “በአውሮፕላን ሄጄ እንደማላውቅ እያወቅክ ለምድነው ግን ዝም የምትለው?” ተራዋን ዙሩን አከረረችው። “በታክሲ መሄድሽም ተመስገን ነው። ሰው አውሮፕላን ለመሥራት ይጣጣራል አንቺ በአውሮፕላን መሄድ ብርቅሽ ሆኖ ቀረ፤” ብሎ ሲዘረጥጣት ብቻቸውን መኝታ ቤት ያሉ እንጂ ሕዝብ መሀል እንዳሉ ረስቶታል። ልጅቷ ገነፈለባት። “አንተ ምን ታደርግ? ወረቀት በጋዝ ነክረን የሰው ሥዕል እየገለበጥን አድገን፣ በሰው አገር ተረት፣ ፍልስፍና፣ ራዕይ ስንቧጨቅ እያየህ ኖረህ፣ በእኔ አውሮፕላን ተሳፍሮ አለማወቅ ብታሾፍ አልፈርድብህም፤” ብላው አኮረፈች፡፡ “አቤት ይኼን ጊዜ አልጋ ላይ ቢሆኑ ታይቶ የማይታወቅ ጀርባ አሰጣጥ ነበር የምናየው፤” ብሎ ጎልማሳው ያንሾካሹካል። ነገሩ ሁሉ ቀልድ የሆነው ወጣት “አንተ ጀርባ ስለመስጠት ታወራህ? እንኳን ተኳርፈው ተፋቅረውስ በአንድ አልጋ በአንድ መንበር የዘለቁ አይተሃል?” ይለዋል።

 አዛውንቱ በበኩላቸው ጠጋ ብለውኝ፣ “ ‘የፊልም ስክሪፕት’ እያጠኑ ነው ወይስ የምራቸውን ነው?” ብለው ይጠይቁኛል። የምር መሆኑን ስነግራቸው “የለም። በአውሮፕላን ተሳፍሮ አለማወቅ ብቻማ እንዲህ አያደርግም። ወይ በደንብ አልሰማናቸውም ወይ ቅኔው አልገባንም፤” ብለው አንዳች ቋጠሮ ሊፈቱ ፊታቸውን አጨፈገጉ። “ደግሞ ልጅነት ውስጥ ምን ቅኔ አለ አባት?” ሲላቸው ጎልማሳው፣ “ምናልባት የአንዳንዱ ሰው የስደት ቴክኒክ ተቀይሮ ይሆናላ። በረሃ ማቋረጥና ባህር መክፈል አቃተንና እንደ አሞራ መብረርን አናስብ መሰለህ?” ብለው እስኪያስረዱን አልገባንም ነበር። ወይ እነአልበር እንዳሞራ! እናም በቅርቡ ደግሞ አንዱ የመልካሙ ተበጀን ‘ደህና ሁኝ ፍቅሬ’ አሻሽዬ ዘፈንኩት ብሎ ሊያነፍረን ነዋ?! ይኼ መንገድ የማያመጣብን የለም!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ወይዘሮዋና ታዳጊው እንዳጀማመራቸው ሳይሆን በጣም ተግባብተዋል። ጭራሽ ታዳጊው እየነቆረ ሲያሰቃየው ስላደረው ቁራ እየተረከ ህልም ማስፈታት ጀምሯል። “አይዞህ ብዙም የከፋ ነገር አይደለም። የቅርብ ሰው አለ የሚመቀኝህ። ምቀኛ ደግሞ ጥሩ ነው። ምቀኛ ከሌለህ አታድግም። አትነሳም፤” እያሉ ይመክሩታል። አዕምሮዋን ታማሚዋ በዝምታ ሰመመን ርቃ ከተጓዘችበት ብቅ በማለት፣ “ኤድያ! እንዲህ እያላችሁ አሳድጋችሁን ነው በቁም የሚቀብረንን እሹሹሩሩ ብለን ታዝለን ኖረን ጉድ የሆንነው። አሁን ማን ይሙት ምቀኛ ባያሳጣን ባያዳክምልን ኖሮ ዓባይ በሰላም ይገደባል? ገዥው ፓርቲስ ቢሆን ምቀኛና ተቀናቃኙን እግር በእግር ተከታትሎ ድል ባያደርግ ኖሮ ከቢጤዎቹ ጋር መቶ በመቶ ያሸንፋል? አፈታታችሁ ሳያንስ ህልማችንን አጓጉል እየፈታችሁ ምናለበት ህልም ቢስ ባታደርጉን?” ብላ ጮኸች። “ህልም ብትሉ ትዝ አለኝ፤” ብሎ ደግሞ ጎልማሳው ስልኩን ይጎረጉራል፡፡ ምን እንደሚፈልግ እሱ ብቻ ያውቃል። ሐሳብና ህልም በማይሰምርበት በዚህ ጎዳና ስንቱ ተመላለሰበት? ወያላው፣ “መጨረሻ!” ብሎ በሩን ሲከፍትልን ዱብ ዱብ ብለን ወረድን። ብዙዎቻችን አልመን የረሳነው፣ ራሳችን ከፍተን ራሳችን የምንዘጋው በር እየናፈቀን በየፊናችን ነጎድን። እስከ መቼ በተከፈተልን እየገባን፣ በተዘጋብን በር እንዘል ይሆን? ሐሳብና ህልም ያልሰመረበት ዘመን ማለት ይኼ አይደል? መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት