Monday, October 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለተለየ የግብይት ሥፍራነት የተገነባው ሕንፃ ተመረቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለንግድ ማዕከልነት ተገንብተው ወደ ሥራ ከገቡ ትላልቅ ሕንፃዎች በተለየ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ ከ360 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የዮቤክ ኮሜርሻል ሴንተር ተመረቀ፡፡ ኩባንያው ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ሁለት ባለኮከብ ሆቴሎች በመገንባት ላይ ነው፡፡

በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች በመሰማራት በሚታወቁት በአቶ ብርሃኔ ግደይና ቤተሰቦቻቸው፣ በተለምዶ ሰንጋ ተራ በሚባለውና የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት መንደር ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው አካባቢ በ2400 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነባው የዩቤክ ኮሜርሻል ሴንተር መንታ ሕንፃዎች ያሉት ሲሆን፣ አንደኛው 14፣ ሁለተኛው ሕንፃ ደግሞ አሥር ወለሎች አሉት፡፡

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ በተገኙበት የምርቃት ሥርዓት ላይ የዮቤክ ኮሜርሻል ሴንተር ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኔ ግደይ እንደገለጹት፣ መንትዮቹ ሕንፃዎች የተለየ አገልግሎት እንዲሰጡ ታስበው የተገነቡ ናቸው፡፡ ያልተለመደ ነው የተባለው የንግድ ማዕከሉ አገልግሎት የኤሌክትሪክና የሕንፃ መሣሪያዎች ዋነኛ መገበያያ እንዲሆኑ ታስበው መደብሮቹ መሠራታቸው ተገልጿል፡፡ ከ200 በላይ የሚሆኑት መደብሮች ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክና የሕንፃ መሣሪያ መሸጫ እንዲሆኑ ከማድረጉም በላይ፣ ቀሪዎቹም ከ180 በላይ የሚሆኑ ቢሮዎችም ከመደብሮቹ ሥራዎች ጋር የተያያዙ አገልግሎት የሚሰጡ ይሆናሉ ተብሏል፡፡ ኮሜርሻል ሴንተሩ በዋናነት የኤሌክትሪክና የሕንፃ መሣሪያዎች መገበያያነት እንዲውል ቢደረግም፣ ለፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት፣ ለሬስቶራንትና ተያያዥ ሥራዎች የዋሉ ክፍሎችም አሉት፡፡ እንደ አቶ ብርሃኔ ገለጻ የኤሌክትሪክና የሕንፃ መሣሪያዎችን በተደራጀና በተሰባሰበ ሁኔታ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር፡፡ በዘርፉ የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩና ተጠቃሚ ደንበኞች የሚፈልጉትን ዕቃ ለማግኘት ከፍተኛ ችግር እየገጠማቸው ሲጉላሉ ነበርም ብለዋል፡፡ ዮቤክ ይህንን ችግር በማየት የገነባውን ሕንፃ የኤሌክትሪክና የሕንፃ መሣሪያዎች ዋነኛ መገበያያ ማዕከል እንዲሆን ማድረግ በመቻሉ፣ ተመሳሳይ ምርቶችን በአንድ አካባቢ መገበያየት ዕድል መፈጠሩንና እንዲህ ዓይነቱን አሠራርም ከሌሎች አገሮች ልምድ በመቅሰም ጭምር የተተገበረ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የዮቤክ ኮሜርሻል ባለቤት በኤሌክትሪክና በሕንፃ መሣሪያዎች ሥራ ውስጥ በርካታ ዓመታትን አሳልፈዋል፡፡ በተለይ በ1991 ዓ.ም. በ500 ሺሕ ብር ካፒታል የተቋቋመው ኩባንያቸው ከኮንስትራክሽንና የቤቶች ልማት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚያስፈልገውን የግብዓት ፍላጎት ከግምት በማስገባት በዋናነት የኤሌክትሪክና የሕንፃ መሣሪያዎች በማቅረብ ሥራ ላይ ቆይቷል፡፡

በዚህ ሥራ ከፍተኛ የገበያ ድርሻ ይዞ የተጓዘና አሁንም በዚሁ ሥራ ላይ የተሰማራ ሲሆን፣ እንደ ኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ያሉ ምርቶችን በአገር ውስጥ የሚያመርት ፋብሪካም አቋቁመዋል፡፡ ብክሮሜ የፒፒ ከረጢትና ፕላስቲክ ማምረቻ የሚል ስያሜ ያለው ይህ ፋብሪካ፣ በ1996 ዓ.ም. ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን ለተለያዩ ምርቶች መገልገያ ማዳበሪያ፣ የውኃ ፓምፕ፣ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች፣ ኬብሎችና የተለያዩ የኤሌክትሪክ ገመዶች ያመርታል፡፡ ይህን ፋብሪካ ለማስፋፋት ውጥን እንዳላቸው አቶ ብርሃኔ ገልጸዋል፡፡ ለኮሜርሻል ሴንተሩም የሚሆን የፓርኪንግ ቦታ የሚፈልጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሕንፃው የተወሰኑ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችል ሥፍራ ያለው ቢሆንም፣ በሕንፃው ከሚገለገሉ ደንበኞችና ተከራዮች ብዛት አንፃር ተጨማሪ የተሽከርካሪ ማቆያ ሥፍራ የሚያስፈልገው በመሆኑ፣ ለዚሁ የሚሆን ቦታ ማግኘት የሚችሉበት መንገድ ይመቻችላቸው ዘንድ ጠይቀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዮቤክ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ ባለኮከብ ሆቴል በመገንባት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በኋላ ግንባታቸውን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

ኩባንያው አሁን ያለበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት አቶ ብርሃኔ በ40 ብር ባልሞላ ካፒታል ሥራ መጀመራቸውን ከዚያም ወደ ታክሲ ሥራ በመግባት ቀስ በቀስ እያደጉ መምጣታቸውና አሁን ያለበት ደረጃ መድረሳቸውን ኩባንያውንና የእሳቸውን የንግድ ጉዞ የሚያመላክተውና በምረቃ ሥርዓቱ ላይ የተሠራጨው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች