Saturday, May 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዳሚ ቱሉ አዲሱን ፀረ አረም ማምረቻውን ሥራ አስጀመረ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  ፀረ አረም መድኃኒቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አቅዷል

በፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ከሚያስተዳድራቸውና ለሽያጭ አቅርቧቸው ከነበሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ አንዱ የሆነው አዳሚ ቱሉ ፀረ ተባይ ማዘጋጃ አክሲዮን ማኅበር ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ያስገነባውን አዲስ ማምረቻ በማጠናቀቅ ሥራ ጀመረ፡፡

ከአዲስ አበባ በ165 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዝዋይ ከተማ የተገነባውና ሥራ የጀመረው ማምረቻ 2.4.D የተባለውን ፀረ አረም መድኃኒት የሚያመርትና በተለያዩ መጠን ባላቸው መያዥያዎች የሚያሽግ ፋብሪካ ነው፡፡

ባለፈው ቅዳሜ በይፋ የተመረቀው አዲሱ ፀረ አረም ማምረቻ አክሲዮን ማኅበሩ የተለያዩ ፀረ አረምና በሽታ ተከላካይ መድኃኒቶችን ከሚያመርትበት ፋብሪካ ጋር ተያይዞ የተሠራ ነው፡፡ እንደ አክሲዮን ማኅበሩ የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ አዲሱ ምርቱ በአክሲዮን ማኅበሩ የሚመረቱ ፀረ አረም መድኃኒቶችን ቁጥር ወደ 23 ያሳድግለታል፡፡ ከዚህም ሌላ አገሪቱ በዓመት እስከ 5.2 ሚሊዮን ብር በላይ የውጭ ምንዛሪ ታወጣበት ነበር የተባለውን 2.4.D ፀረ አረም በአገር ውስጥ መመረቱ ለፀረ አረም መድኃኒቱ ግዥ ይውል የነበረውን የውጭ ምንዛሪም በመቀነሱ ረገድ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ፀረ ተባይ መድኃኒቶችን በማምረት የሚታወቀው አዳሚ ቱሉ ፀረ ተባይ አክሲዮን ማኅበር የማስፋፊያ ሥራዎችን እያከናወነ ያለው በዘርፉ የተሠማራ የግል ባለሀብት ባለመኖሩ ጭምር ነው፡፡ የአክሲዮን ማኅበሩ መረጃ እንደሚገልጸው በኢኮኖሚው ዘርፍ የግል ባለሀብቱ በተሟላ መልኩ ባልተሳተፈባቸው እንዲህ ባሉ ምርቶች መንግሥታዊው አክሲዮን ማኅበር ድርሻውን እየተወጣ ነው፡፡

ከአክሲዮን ማኅበሩ የተገኘው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያስረዳው ከዚህም በኋላ  ፋብሪካውን የማስፋፋት ሥራ የሚቀጥል መሆኑን ነው፡፡ ለዚህም የአምስት ዓመት ዕቅድ ተነድፏል፡፡ በዕቅዱ መሠረት አሁን በመመረት ላይ ያሉትን 23 የተለያዩ ፀረ አረም ምርቶች ቁጥር ወደ 37 ለማሳደግ የሚለው ይገኝበታል፡፡

በቀጣዩ አምስት ዓመታት የፀረ አረም ምርቶችን ቁጥር ከማሳደግ ባሻገር አራት ፀረ አረም ምርቶችን በመለየት ለጎረቤት አገሮች ለመሸጥና ፋብሪካው የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ እንዲሆን ጭምር መታቀዱን ያመላክታል፡፡

የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁና ከተለያዩ አገሮች የመጡ የነበሩ ፀረ አረም መድኃኒቶችን በአገር ውስጥ የማምረት የሚያስችል ውጥን መያዙንና አሁን በአገር ውስጥ በሚመረቱ ፀረ አረም መድኃኒቶች የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ ለመተካት የሚሠራ መሆኑንም አስታውቋል፡፡ በ2008 በጀት ዓመትም የአንዳንድ የፀረ ተባይ ማምረቻ የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ የሚያዘጋጅ መሆኑን ጠቅሷል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን አክሲዮን ማኅበሩ አከናውናቸዋለሁ ካላቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል ከአራት የተለያዩ ኩባንያዎች ጋር በጥምረት ለመሥራት የሚያስችለው ዕቅድ አለው ተብሏል፡፡

ኩባንያው በ2007 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 39.4 ሚሊዮን ብር ያተረፈ ሲሆን፣ ይህን ትርፍ በ2012 በጀት ዓመት በ234 በመቶ በማሳደግ 92.4 ሚሊዮን ብር ለማትረፍ የሚያስችለውን ሥራ በመሥራት ላይ ነው ተብሏል፡፡ ወደዚህ ደረጃ ለመድረስም በጆይንት ቬንቸር ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር ለመሥራት ዕቅድ አለው፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ በ2007 በጀት ዓመት 1.3 ሚሊዮን ሊትር ፈሳሽ፣ 1.2 ሚሊዮን ኪሎ ግራም ጠጣር ፀረ ተባይ ምርቶችን በማምረት ከ176.8 ሚሊዮን ብር ሽያጭ አከናውኗል፡፡ በ2012 በጀት ዓመት ግን የሽያጭ መጠኑን ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ የሚያስችለውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ የአክሲዮን ማኅበሩ  ባለፉት አምስት ዓመታት ስላከናወናቸው ተግባራት የሚያመለክተው መረጃም ስድስት ሚሊዮን ሊትር ፈሳሽ፣ 5.7 ሚሊዮን ኪሎ ግራም ፀረ ተባይ መድኃኒቶችንና 253,953 የአልጋ አጎበር በማምረት ማሠራጨቱ ነው፡፡ አዳሚ ቱሉ የፀረ ተባይ ማዘጋጃ አክሲዮን ማኅበር በ1987 ዓ.ም. ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ በ2000 ዓ.ም. በ40.5 ሚሊዮን ብር ካፒታል በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ እንዲዋቀር ተደርጓል፡፡ በወቅቱ ያመርታቸው የነበሩ ፀረ ተባይ መድኃኒቶች አሥር ብቻ ነበሩ፤ አሁን ግን 23 ደርሷል፡፡ በአሁኑ ወቅት 435 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ 343ቱ ቋሚ ናቸው፡፡

በፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ሥር ከሚተዳደሩና በአትራፊነታቸው ከሚጠቀሱ ተቋማት መካከል አንዱ ነው፡፡ እንደሌሎች የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ለማዛወር ሁለት ጊዜ ጨረታ ወጥቶ በግዥ እጦት ሳይዛወር ቀርቷል፡፡ ሆኖም የማስፋፊያ ሥራ ያስፈልጋቸዋል ከተባሉ ተቋማት ውስጥ አንዱ በመሆን የማስፋፊያ ሥራውን እያከናወነም ነው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች