Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጁልፋር መድኃኒት ፋብሪካ ዓለም አቀፍ የጥራት ሠርተፊኬት አገኘ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጁልፋር መድኃኒት ፋብሪካ ዓለም አቀፍ ጨረታዎችን ለመወዳደርና የኤክስፖርት ገበያ ውስጥ ለመግባት የሚያስችለው የጥራት ደረጃ ሠርተፊኬት (GMP) አገኘ፡፡ ለአገሪቱ የፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪ ዕድገትና የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት አኳያ አወንታዊ ለውጥ እንደሚኖረው ተጠቅሷል፡፡

ጁልፋር ሠርተፊኬቱን ያገኘው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከጀርመን መንግሥት ጋር ባለው ስምምነት መሠረት ጂአይዜድ ለጁልፋር አስፈላጊውን ሥልጠና ከሰጠ በኋላ ገለልተኛ ኦዲተሮች መጥተው የፋብሪካው ምርቶች ዓለም አቀፍ የጤና ተቋም (WHO) ባወጣው መስፈርት መሠረት መመረታቸውን በማረጋገጣቸው ነው፡፡ አጋጣሚው የፋብሪካውን ተወዳዳሪነቱን እንደሚያሳድግ፣ የጥራት ማረጋገጫ ሠርተፊኬቱ ሐምሌ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. በፋብሪካው ቅጥር ግቢ በተሰጠበት ወቅት ተገልጿል፡፡

አቶ ሙከሚል አብደላ በጁልፋር መድኃኒት ፋብሪካ የኢትዮጵያ ተጠሪ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ሠርተፊኬቱ ሰፊ የገበያ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ከዚህ ቀደም የፋብሪካው ገበያ ውስን ነበር፡፡ ይኸውም መንግሥት ፋይናንስ የሚያደርገው ግዢና የግሉ ገበያ ብቻ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን በሠርተፊኬቱ አማካይነት ሰፊ በሆነው የዓለም ገበያ ላይ መሳተፍ ይቻላል ያሉት አቶ ሙከሚል፣ ‹‹ማምረትና ማቅረብ በቻልነው ልክ ኤክስፖርት ማድረግ እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡ የፋብሪካውን የጥራት ደረጃ ለማሟላት በተደረጉ ልዩ ልዩ ወጪዎች ሁለት ሚሊዮን ብር እንደወጣም ተናግረዋል፡፡ ‹‹መቀየር የነበረብን ማሽኖች ነበሩ፣ የመረጃ አያያዝ፣ የሕንፃ ጥራትና ጥሬ ዕቃ የሚያቀርቡ አቅራቢዎችን ለመቀየር ተገድደናል፤›› ይላሉ፡፡

ፋብሪካው ሲገነባ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃውን ታሳቢ አድርጎ ስለነበር ሠርተፊኬቱን ማግኘት ከባድ አልነበረም የሚሉት ተጠሪው፣ ጁልፋር የዓረብ ባለሀብቶችና የሜዲቴክ ኢትዮጵያ የጋራ ኢንቨስትመንት ሲሆን ሜዲቴክ 45 በመቶ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡ የዓረቡ ኩባንያ ቀደም ብሎ የጥራት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት የነበረው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሚገኘው የእሽሙር ኩባንያቸው ጁልፋር ሠርተፊኬቱን እንዲያገኝ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል ተብሏል፡፡

ጁልፋር የሙከራ ኢንቨስትመንት ነው ያሉት ተጠሪው፣ አገሪቱ ያላትን አመቺ የኢንቨስትመንት ዕድል በመጠቀም የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ሙከሚል ከሆነ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ አራት ፋብሪካዎችን ለማቋቋም ያለመ ሲሆን፣ 11 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ገርጂ መብራት ኃይል አካባቢ ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ ይሁን እንጂ ርክክቡ እስካሁን ባለመፈጸሙ ፕሮጀክቱ እየተጓንተተ ይገኛል፡፡ ርክክቡ ተጠናቆ ወደ ሥራው ሲገባም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገኝ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን አሁን ባለን አቅም ከሌሎች እኩል ለመፎካከር ያስቸግረናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ለመሳተፍ የጥራት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ በዋጋም ተፎካካሪ መሆን ግድ ይላል፡፡ ይህንንም ከወዲሁ አስበን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፤›› ብለዋል፡፡

በሌላው ዓለም እጅግ ተፈላጊ የሆነውን የሄፒታይትስ በሽታ መድኃኒት ለማምረት በዝግጅት ላይ ሲሆኑ፣ መድኃኒቱ በዓለም አቀፍ ገበያ ካለው ተፈላጊነት አንፃር ጠቀም ያለ የውጭ ምንዛሪ ማስገባት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የፋርማሲቲካል ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ በአምስት ዓመቱ መጨረሻ ላይ 20 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት የታቀደ ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ. በ2014 መጨረሻ ከሁለት ሚሊዮን ዶላር የበለጠ ማግኘት አልተቻለም፡፡ እንዲሁም የአገር ውስጥ አምራች ኩባንያዎች መቶ በመቶ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ በማስቻል ከውጭ የሚገዙ መድኃኒቶችን ለመቀነስ የታቀደ ቢሆንም፣ የታሰበውን ያህል ማድረግ አልተቻለም፡፡ በአሁኑ ወቅት 80 በመቶ የሚሆነው መድኃኒት ከውጭ የሚገባ ነው፡፡

መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ የጠቆሙት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ መሐሙድ አህመድ፣ ሠርተፊኬቱ አገሪቱ እያቀደች ላለችው ግብ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከጀርመን መንግሥት ጋር በመተባበር የመድኃኒት ፋብሪካዎች የጥራት ደረጃ ለማሳደግ እየሠራ ይገኛል፡፡ ‹‹ዓለም አቀፍ የጥራት ማረጋገጫ ለንግድ እንዲሁም ቴክኖሎጂን ከማስፋፋት አንፃር ትልቅ ሚና አለው፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች