ጁሴፔ ሚስትሬታ፣ በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር
ሐምሌ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. የጣሊያን መንግሥት ለምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ድርጅት [ኢጋድ] ሽብርተኝነትን ለመዋጋትና ተያያዥ ጉዳዮች የሚውል የ500 ሺሕ ዩሮ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ተገኝተው ስምምነቱን የፈረሙት የኢጋድ ዋና ጸሐፊ አምባሳደር (ኢንጂነር) ማሕቡብ ማዕሊም፣ ጣሊያን እስካሁን ለድርጅቱ የምታደርገው ድጋፍ በጣም ትልቅ መሆኑን ገልጸው አመስግነዋል፡፡ ጣሊያን ኢጋድን ለመደገፍ የተቋቋመውን የዓለም አቀፍ አጋሮች ቡድን በሊቀመንበርነት ትመራለች፡፡ ጣሊያን ለድርጅቱ በምታደርገው ድጋፍ፣ የደቡብ ሱዳን ቀውስን ጨምሮ የአካባቢውን ችግሮች ለመፍታት ኢጋድ እያደረገ ስላለው ጥረት የማነ ናግሽ በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ጁሴፔ ሚስትሬታን አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የተፈረመው ስምምነት ምንን የተመለከተ ነው?
አምባሳደር ጁሴፔ ሚስትሬታ፡- ከኢጋድ ዋና ጸሐፊ ከኢንጂነር ማህቡብ ማእሊም ጋር የተፈራረምነው 500 ሺሕ ዩሮ ለኢጋድ በዕርዳታ መልክ ለመስጠት ነው፡፡ ዓላማው ደግሞ ኢጋድ በተለይ በአካባቢው የሚያከናውናቸውን የደኅንነት ሥራዎች በአግባቡ እንዲያካሂድ በገንዘብ ለማገዝ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የደኅንነት ጉዳዮች በዝርዝር የሚያካትቱን ማወቅ ይቻላል?
አምባሳደር ጁሴፔ ሚስትሬታ፡- ገንዘቡ እንዲውል የታቀደው በሦስት ዋና ዋና ፕሮጀክቶች ላይ ነው፡፡ አንደኛው ኢጋድ በዋና ጽሕፈት ቤቱ ለሚያካሂዳቸው የሥራ እንቅስቃሴዎች ይውላል፡፡ ሁለተኛ በዋናነት ኢጋድ በቀጣናው ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ለሚያደርገው ጥረት ይውላል፡፡ ሦስተኛ ድርጅቱ በሶማሊያ የተረጋጋ ፖለቲካ እንዲፈጠር በሚያደርገው እንቅስቃሴ በአካባቢው ቢሮ ከፍቶ እየሠራ ስለሆነ ይህንን ቢሮ ለማጠናከር የሚውል ነው የሚሆነው፡፡ በአጠቃላይ ዛሬ ያደረግነው ኢጋድ እንደ ድርጅት በሁለት እግሩ ቆሞ በአካባቢው በተለይ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የሚያከናውናቸው ተግባራት በገንዘብ እጥረት ምክንያት እንዳይስተጓጎሉ በሚል እሳቤ ነው፡፡ ዓላማውም አካባቢው የተረጋጋ እንዲሆንና ለዚህም የሚያደርጋቸውን ጥረቶች ለማገዝ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ በፊት ጣሊያን ለኢጋድ ተመሳሳይ ዕርዳታ አድርጋ ታውቃለች? ወይስ የመጀመሪያዋ ነው?
አምባሳደር ጁሴፔ ሚስትሬታ፡- አይደለም፡፡ የዛሬው ዕርዳታ የመጀመርያችን አይደለም፡፡ ኢጋድን ማገዝ እንደ ኃላፊነት ይዘነዋል፡፡ ከዚህ በፊት ሁለትና ሦስት ጊዜ ለድርጅቱ ተመሳሳይ ዕርዳታ አድርገናል፡፡ ለምሳሌ ከስምንት ወራት በፊት ኢጋድ በደቡብ ሱዳን የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት ለሚያደርገው ጥረት የ250 ሺሕ ዩሮ ዕርዳታ ሰጥተናል፡፡ ከስድስት ወራት በፊትም በኢጋድ ተነሳሽነት በሶማሊያ ለተከፈተው አንድ ትምህርት ቤት ዕርዳታ ሰጥተናል፡፡ በመሆኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ ኢጋድ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የተቻለንን ዕርዳታ ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ያንን በማድረጋችንም የአገራችን ሕዝብና መንግሥት ደስተኞች ናቸው፡፡
በቀጣዩም ድርጅቱን ዓላማውን እንዲያሳካ አስፈላጊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን፡፡ ምክንያቱም በዚህ በርካታ የሆኑ የደኀንነትና የሰላም ችግሮች ፈተና በሆኑበት ቀጣና የማይተካ ሚና እየተጫወተ ያለው አካል ኢጋድ እንደሆን ግልጽ ነው፡፡ ሶማሊያ ውስጥ ለነበረው የፖለቲካ ቀውስ መፍትሔ ያስገኘው ኢጋድ ነው፡፡ አሁንም በደቡብ ሱዳን ለተከሰተው አሳዛኝ የእርስ በርስ ጦርነት መፍትሔ እያፈላለገ ያለው በዋናነት ይኼው ድርጅት ነው፡፡ በሶማሊያና በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ኢጋድ የያዘው የጋራ የልማት ዕቅድ አለ፡፡ እነዚህንና የመሳሰሉ የልማት እንቅስቃሴዎች የጣሊያን መንግሥት ማገዝ ይፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- የጣሊያን መንግሥት ኢጋድን በገንዘብ ብቻ ወይስ በፖለቲካም ድጋፍ ያደርጋል?
አምባሳደር ጁሴፔ ሚስትሬታ፡- በገንዘብ ብቻ አይደለም፡፡ ለኢጋድ የምናደርገው ድጋፍ ይዞት ከተነሳው ዓላማ አንፃር ነው፡፡ ስለዚህ የፖለቲካም ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ኢጋድ በማናቸውም እንቅስቃሴዎቹ ዓለም አቀፍ ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው ታምኖበት፣ ዕርዳታ የሚያደርጉ አገሮች በሙሉ አንድ የጋራ ቡድን ፈጥረው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የኢጋድ አገሮች ፎረም (IGAD Partners Forum) እንለዋለን፡፡ ጣሊያን የቡድኑ አባል ብቻ ሳትሆን ከኢጋድ ጋር የጋራ ፎረሙን በሊቀመንበርነት ትመራለች፡፡ ለድርጅቱ አስፈላጊ የፖለቲካና የገንዘብ ድጋፍም ታፈላልጋለች፡፡ በእርግጥ የፎረሙ አባላት በሙሉ ጥሩ ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ጣሊያን እንደ የኢጋድ አጋሮች ፎረም ሊቀመንበርነቷ በተለይ የደቡብ ሱዳንን ቀውስ ለመፍታት ድርጅቱ በሚያደርገው እንቅስቃሴ በተግባር ምን አበርክቷል?
አምባሳደር ጁሴፔ ሚስትሬታ፡- ኢጋድ ቀደም ሲል ቀውሱን ለማረጋጋትና በዘላቂነት ለመፍታት ያስቀመጠው መንገድ ግልጽ ነው፡፡ የአጋሮቹም ፎረም እሱን ሙሉ በሙሉ ሲደግፍ ቆይቷል፡፡ አቋሙ የኢጋድ መንገድ ነው፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ እስካሁን የተደረገው ጥረት ውጤት አላስገኘም፡፡ አሁንም ኢጋድ ፕላስ [IGAD+] ተብሎ አዲስ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ የአውሮፓ ኅብረት፣ የአፍሪካ ኅብረትና ሌሎች አካላት ተጨምረውበታል፡፡ አንድ የመፍትሔ ሐሳብም አዘጋጅቷል፡፡ እሱን በተመለከተ ለመነጋገር ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በሚገኙበት በቅርቡ በአዲስ አበባ አንድ ጉባዔ ተጠርቷል፡፡ አንድ እልባት ላይ ይደረሳል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ አሁንም ከኢጋድ ጎን ሆነን ለጉባዔው መሳካት በጋራ እየሠራን ነው፡፡ ተስፋችንም ከፍ ያለ ነው፡፡
በእርግጥ እስካሁን አልተደመጥንም፡፡ ሐሳባችንም አልተከበረም፡፡ ጥረታችንም አልተሳካም፡፡ እሱ አሳዛኝ ነገር ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ያለበት ጭንቀት ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ሐሳባችን አልተከበረም ብለን እጃችንና እግራችንን አጣጥፈን አንቀመጥም፡፡ ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥላለን፡፡ ማናቸውም ለደቡብ ሱዳን የሚቆረቆር አካልም ድጋፍ ማድረግ ካለበት በኢጋድ በኩል መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ከዚያ ውጪ መፍትሔ ያለ አይመስለኝም፡፡ እስከ መጨረሻ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በደቡብ ሱዳን ያለውን ቀውስ ለመፍታት ኢጋድ ያደረገው ጥረትም መመስገን አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን ለውይይት የሚቀርበው አዲስ መፍትሔ ተቀባይነት ያገኛል ብለው ያምናሉ?
አምባሳደር ጁሴፔ ሚስትሬታ፡- አዎ፡፡ ይኼ የመጨረሻ መፍትሔ ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ሁለቱንም ተፋላሚ ወገኖች የሚያስታረቅ ሐሳብ የያዘ ነው፡፡ እስካሁን የሁለቱም ወገኖች ምላሽ አወንታዊ ይመስላል፡፡ እኔ ራሴ በጉዳዩ ላይ እስካሁን በተካሄዱት ስድስት ስብሰባዎች ተሳትፌያለሁ፡፡ አሁን በኢጋድ ፕላስ የቀረበው አስታራቂ የመፍትሔ ሐሳብ (Compromise Agreement) አዲስ አይደለም፡፡ እስካሁን ውይይት እየተደረገባቸው የቆዩ ናቸው፡፡ አቀራረቡ ግን የተሻለ ይመስለኛል፡፡ እኔም ውጤት ያመጣል የሚል ግምት አለኝ፡፡
ሪፖርተር፡- ኢጋድ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ይዟቸው የተነሳቸውን ዓላማዎች ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር የተሳካ ሥራ ሠርቷል ብለው ያምናሉ?
አምባሳደር ጁሴፔ ሚስትሬታ፡- ኢጋድ መጀመርያ ሲቋቋም ድርቅንና ልማትን መሠረት አድርጎ ነበር፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አካባቢውን ለማዋሀድ፣ ልማትን ለማምጣትና የአካባቢውን ደኅንነት ለማስፈን ዓላማ ይዞ ተነስቷል፡፡ እንግዲህ አካባቢው እንደሚታወቀው አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለያዩ የፖለቲካ ቀውሶች የሚታመስ ነው፡፡ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ኤርትራ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ተመልከት፡፡ ከዚህ አንፃር ድርጅቱ የያዘውን ዓላማ እያሳካ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢጋድ ባይኖር ምን ይሆን ነበር ብለህ ስታስብ ብዙ ነገር እንዳሳካ ትገነዘባለህ፡፡
ኢጋድ ሲመሠረት የኢኮኖሚ ዓላማ ይዞ ነበር የተነሳው፡፡ እምብዛም የፖለቲካ ድርጅት አልነበረም፡፡ መዋቅሩም እንዲህ አልነበረም፡፡ አሁን ግን የአካባቢው ዋና ችግር የሆነውን የፖለቲካ ቀውስና የደኅንነት ችግር መፍትሔ ለማምጣትና አገሮቹ በአንድ ጠረጴዛ ተቀምጠው እንዲወያዩ ትልቅ የፖለቲካ መሣርያ ሆኗል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሪፖርተር፡- እስቲ ከቀጣናው ፖለቲካ እንውጣ፡፡ የሁለትዮሽ ጉዳይ ላንሳልዎት፡፡ ጣሊያን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያላት ግንኙነት ምን ይመስላል?
አምባሳደር ጁሴፔ ሚስትሬታ፡- መልካም ነው፡፡ ጣሊያን በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለውን ልማት ታውቃለች፡፡ ትረዳለችም፡፡ ከአፍጋኒስታን ቀጥሎ ጣሊያን ትልቁን ዕርዳታ የምትሰጠው ለኢትዮጵያ ነው፡፡ የአፍጋኒስታን ሁኔታ የተለየ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ልማት በተለይ ደግሞ ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር የምታደርገው ጥረት እንደግፋለን፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2013 ጀምሮ ለሦስት ዓመታት ያደረግነው ዕርዳታ አንድ መቶ ሚሊዮን ዩሮ ይደርሳል፡፡ አሁን ደግሞ ለሚቀጥሉት ዓመታት ዕርዳታዋ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ይህንን ስምምነት በተመለከተ በቅርቡ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር እዚህ በመጡ ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር መክረዋል፡፡ በተለያዩ ዘርፎች እንሳተፋለን፡፡ በዋናነት ግን የኢንዱስትሪ ዕድገት ላይ ነው ትኩረት የምናደርገው፡፡
ሪፖርተር፡- የተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ለኢትዮጵያ ዕርዳታ ሲያደርጉ የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ጣሊያን ምን ዓይነት አቋም ነው ያላት?
አምባሳደር ጁሴፔ ሚስትሬታ፡- ከተቀሩት የአውሮፓ አገሮች የተለየ አቋም የለንም፡፡ የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ ጉዳዮችን በተመለከተ በትልቁ በአውሮፓ ኅብረት የተያዘው አቋም የእኛም አቋም ነው፡፡ የተለየ ምልከታ የለንም፡፡ የአገሪቱ የዴሞክራሲ ጉዳይ አከራካሪ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ የአገሪቱ ዴሞክራሲ የሚበለፅገው በውይይትና በጋራ ምክክር ነው ብለን እናምናለን፡፡