Thursday, May 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፓልም ዘይት ነጋዴዎች ከአዲስ አበባ አስተዳደር የንግድ ቀጣናዎችን ተረከቡ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  ጉና ለወታደራዊ ተቋማት ፓልም ዘይት የማቅረብ ኃላፊነት ወስዷል

ንግድ ሚኒስቴር የመረጣቸው አምስት ኩባንያዎች በአዲስ አበባ ከተማ የፓልም ዘይት የሚከፋፈሉባቸውን የግብይት ቀጣናዎች ተረከቡ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወር የተሰጠውን 7.5 ሚሊዮን ሊትር ፓልም ዘይት ለማከፋፈል የተመረጡት የንግድ ተቋማት ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጋር ሐምሌ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ጋር የተፈራረሙት ጉና ንግድ ሥራዎች፣ አልሳም፣ አፋም (ሆራይዘን ፕላንቴሽን)፣ በላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪና መንግሥታዊ የንግድ ተቋም የሆነው አለ በጅምላ ናቸው፡፡ ሐማሬሳ የምግብ ዘይት አክሲዮን ማኅበር በንግድ ሚኒስቴር የተመረጠ የግል ኩባንያ ቢሆንም፣ የሚያስመጣውን የፓልም ዘይት ለሐረርና ለአካባቢው እንዲያቀርብ መወሰኑ ታውቋል፡፡

ጉና ትሬዲንግ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለፌዴራል ፖሊስ፣ ለአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ለዩኒቨርሲቲዎች፣ ለሆስፒታሎች፣ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶችና ለሕዝባዊ ተቋማት የማቅረብ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

መንግሥታዊው አለ በጅምላ ደግሞ ለቦሌ፣ ለቂርቆስና ለአራዳ ክፍላተ ከተሞች ያቀርባል፡፡ የግል ኩባንያ የሆኑት አልሳም ለጉለሌ፣ ለኮልፌና ለልደታ ሲያቀርብ፣ አፋም ንፋስ ስልክ ላፍቶና አቃቂ፣ በላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪ ደግሞ ለየካ ክፍለ ከተማ ፓልም ዘይት እንዲያቀርቡ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ከነሐሴ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ የፓልም ዘይት ማቅረብ እንደሚጀምሩ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

መንግሥት በአገሪቱ ያለውን የፓልም ዘይት አቅርቦት ችግር ለመፍታት ቀደም ሲል በመንግሥት ዕቃዎች ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አማካይነት የፓልም ዘይት ግዥ እየፈጸመ፣ በመንግሥታዊ የንግድ ተቋማትና በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ለተጠቃሚዎች እንዲከፋፈል ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ነገር ግን ግብይቱ መልካም አፈጻጸም ባለማሳየቱ ንግድ ሚኒስቴር ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጋር በመመካከር በዘይት ግብይቱ የተወሰኑ የግል ኩባንያዎችንና የኢንዶውመንት ኩባንያዎችን በማስገባት ቀደም ሲል የነበረውን የፓልም ዘይት ግብይት አሠራር አስቀርቷል፡፡

በዚህ መሠረትም የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ መሥሪያ ቤታቸው ከፓልም ዘይት ግዥ መውጣቱን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

በአዲስ አበባ ሥራው ከተሰጣቸው የግል ኩባንያዎች በተጨማሪ የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ እህት ኩባንያ የሆነው ሐማሬሳ የምግብ ዘይት አክሲዮን ማኅበር፣ የኢንዶውመንት ኩባንያ የሆኑት አምባሰል ንግድ ሥራዎች፣ ቢፍቱ አዱኛ ቢዝነስ፣ ወንዶ ንግድና ኢንቨስትመንት ከተመረጡት መካከል ይገኛሉ፡፡

እነዚህ የንግድ ተቋማት የፓልም ዘይት ግዥ ሲፈጽሙ የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች ትዕዛዝ ከመስጠቱም በላይ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በበኩሉ ነጋዴዎች የሚፈጽሙት ግዥ ከማንኛውም ቀረጥና ታክስ ነፃ እንዲሆን፣ የመድን ሽፋን ክፍያቸውም 50 በመቶ ብቻ እንዲሆን ትዕዛዝ መሰጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በዚህ መሠረት የንግድ ተቋማቱ የሚጠበቅባቸውን ዘይት በወቅቱ አስገብተው ያከፋፍላሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ በብዛት ዘይት ወደ አገር ውስጥ በማስገባት አቅርቦቱን ከማሻሻል በተጨማሪ፣ ለኅብረተሰቡ በጥሩ ዋጋ የፓልም ዘይት ማቅረብ ያስችላል በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በተለይ የንግድ ተቋማቱ የተመረጡት በአገር ውስጥ ዘይት ለማምረት ኢንቨስትመንት ውስጥ በመግባታቸው ነው በማለት አቶ ሺሰማ ተናግረዋል፡፡ የኢንዶውመንት ድርጅቶቹ ደግሞ ባሉበት አካባቢ በተገቢ መንገድ የሚያስገቡትን የፓልም ዘይት ማቅረብ ይችላሉ በሚል ምክንያት በመንግሥት መመረጣቸው ታውቋል፡፡

ነገር ግን ቀደም ብለው በዘይት ንግድ ውስጥ ተሰማርተው የነበሩ ኩባንያዎች የፓልም ዘይት ግብይት ክፍት አለመሆኑን በመቃወም ላይ ይገኛሉ፡፡ ቅሬታ አቅራቢ ነጋዴዎች በአሁኑ ጊዜ ለንግድ ሚኒስቴር ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ እየጠበቁ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

በአገሪቱ የፓልም ዘይት ፍላጎት እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከሁለት ወራት በፊት 7.1 ሚሊዮን ሊትር የነበረው ወርኃዊ ፍላጎት፣ አሁን ወደ 7.5 ሚሊዮን ሊትር መጨመሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃም 26 ሚሊዮን ሊትር የነበረው ወርኃዊ ፍላጎት፣ አሁን 40 ሚሊዮን ሊትር መድረሱን አቶ ሺሰማ ተናግረዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች