የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጉዳይ በጣም አነጋጋሪ ከመሆኑ የተነሳ በየጊዜው ዋነኛ አጀንዳ ነው፡፡ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉዳይ ሲነሳ የፖለቲካ ምኅዳሩ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ የመደራጀት መብት፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ፣ ነፃና ተዓማኒነት ያለው ምርጫና የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ መብት መከበርን በተመለከተ በሚነሱ ክርክሮች ዙሪያ የተለመዱ አስተያየቶች ሲንፀባረቁ ይሰማል፡፡ መንግሥት ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ስለሆነ መቼም ቢሆን የሚተወው አለመሆኑን ሲናገር ይደመጣል፡፡ መንግሥትን የሚቃወሙ ወገኖች ደግሞ ለዴሞክራሲ ደንታ የለውም በማለት ይተቹታል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ግፊቱ ጫን ብሎ ሲመጣ፣ መንግሥት የአገሪቱን ታሪካዊ ዳራ በመጥቀስ በሁለት አሥርት ውስጥ ዴሞክራሲን ለማስፈን የሚሳካ ተግባር አለመሆኑን ያስረዳል፡፡ ለህልውና እጅግ ጠቃሚ ነው የተባለው ጉዳይ እንደገና ጥሬ ይሆናል፡፡ አንዳንድ መሠረታዊ ጉዳዮችን እናንሳ፡፡
- ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ይከበር
ዜጐች የመሰላቸውን አመለካከት የማራመድ መብት እንዳላቸው በሕገ መንግሥቱ ትልቅ ዋስትና ተሰጥቶታል፡፡ አንድ ዜጋ የፈለገውን ዓይነት ዕምነት የመከተል፣ የፖለቲካ አመለካከት መያዝ፣ መደገፍም ሆነ መቃወም መብቱ ነው፡፡ ይህ መብት በሕግ ዋስትና ሲያገኝ ዜጐች ደግሞ ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ መጠቀም ይችላሉ፡፡ ዜጐች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው ሲረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነት ሲከበር፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በነፃነት ሥራውን ሲያከናውን፣ የዴሞክራሲ ተቋማት (ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት) ሲጠናከሩና በነፃነት ሲንቀሳቀሱ፣ የሚዲያ ነፃነት ሲከበር፣ ወዘተ ዜጐች ነፃነት ይሰማቸዋል፡፡
ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሚገባ ሲከበር ለአገር ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የበሰሉ ዕውቀቶች፣ ከስህተት የሚመልሱ የሰሉ ትችቶችና ጠቃሚ ግብዓቶች ይገኛሉ፡፡ ሐሳብ በታፈነ ቁጥር ለአማራጭነት የሚጠቅሙ ዕውቀቶች ይታፈናሉ፡፡ ለአገር ዕድገት የሚበጁ ሐሳቦች ይጋሽባሉ፡፡ ሕዝባቸውን ለመጥቀም የሚፈልጉ ዜጐች ይሸማቀቃሉ፡፡ የመከኑ ሐሳቦችና ተቀናቃኝ የሌለባቸው ድፍረቶች አገሩን ይወሩታል፡፡ ስህተትን በስህተት የሚያርሙ አገር አጥፊ ፖሊሲዎች እየወጡ ጉዳት ያመጣሉ፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከሚያገለግሉ ጉዳዮች መካከል ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት መከበር አንዱ ነው፡፡
ባለፈው ሰሞን ከፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጉብኝት ጋር በተያያዘ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለማጐልበት ጥረቱ ቢኖርም ሁለት አሥርት በቂ አለመሆናቸው ተገልጿል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ በአሜሪካ አሁንም በተሟላ ሁኔታ ዴሞክራሲ አለ ለማለት እንደማይቻል፣ ነገር ግን ችግሮቹን በመከታተል ሁሌም አገራቸው መፍትሔ ከመፈለግ እንደማትቦዝን ተናግረዋል፡፡ ችግሮች አሉ ሲባል ጊዜ እንደሚወስዱ በተደጋጋሚ ከመናገር ይልቅ፣ የህልውና ጉዳይ ነው እንደተባለው ለተግባራዊነቱ መረባረብ ይጠቅማል፡፡ ሐሳቡን በነፃነት መግለጽ የማይችል ኅብረተሰብ አገር ያሳድጋል ወይም የልማት ተባባሪ ይሆናል ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው፡፡
- የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋት
በኢትዮጵያ ምርጫ በመጣ ቁጥር ሁሌም ጭቅጭቅ ይነሳል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሁሉም እኩል በሆነ ሜዳ ላይ ስለማይወዳደሩ ነው፡፡ ከምርጫ በፊት ባሉ ጊዜያት በገዥው ፓርቲ ከፍተኛ ጫና እንደሚደርስባቸው የሚናገሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፖለቲካው ምኅዳር እጅግ በጣም እየተጣበባቸው ሰላማዊው የፖለቲካ ሒደት እየተበላሸ ነው ይላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ የሚካሄዱት ምርጫዎች በሙሉ ነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒነት ያላቸው ናቸው ቢባሉም፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዳጡ ቀጥለዋል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ያለመስፋት ችግር እዚህ ጥግ ደርሷል፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ የኢትዮጵያ መንግሥት በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ነው ሲሉ፣ ነፃና ተዓማኒነት የነበረው ምርጫ ተካሂዷል አላሉም፡፡ በአፍሪካ ኅብረት ማንዴላ አዳራሽ ንግግር ሲያደርጉ ይህንኑ ጉዳይ አፅንኦት በመስጠት በአፍሪካ ነፃና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ እንዲከናወን ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪም ምርጫው በሰላም መጠናቀቁን ገልጸው፣ ነፃና ተዓማኒ ስለመሆኑ ግን እንደማያውቁ መናራቸው አይዘነጋም፡፡ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት የሚረዳ ጥሬ ዕቃ ቢሆንም፣ በሁሉም ወገኖች መግባባት ላይ ካልተደረሰበት አወዛጋቢነቱ ይቀጥላል፡፡ ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቷ ተከብሮ ሁሉም ወገኖች በእኩልነት የሚወዳደሩበት ምርጫ ለማምጣት ምን ያህል ርቀት መኬድ አለበት?
የአሜሪካ ዴሞክራሲ 240 ዓመታት የሞላው ቢሆንም፣ እየተፈተሸና እየታደሰ እንደሚሄድ ከበቂ በላይ ተነግሮናል፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲያድግና ለወግ ለማዕረግ እንዲበቃ ከልብ ከተፈለገ ከባዶ አይደለም መጀመር ያለበት፡፡ ልምድ የሚቀምርበት በርካታ የዓለም ተሞክሮዎች አሉት፡፡ የዘመኑ አስተምህሮም የሚለው ጠቃሚ ልምዶችን ቀስሞ ለአገር በሚጠቅም መንገድ ሥራ ላይ ማዋል ነው፡፡ ዴሞክራሲን ለማጐልበት እስከ መቼ መከራ ይታያል መባል አለበት፡፡ ከአገር ተጨባጭ ሁኔታና ከሕዝቡ የአኗኗር ዘይቤ ጋር የሚመጣጠን ዴሞክራሲ ማስፈን የግድ መሆን አለበት፡፡ የሌሎችን ጥብቆ እንዳለ ማጥለቅ ሳይሆን፣ ለሕዝብ ነፃነትና ክብር የሚመጥን ዴሞክራሲ ለማስፈን ሌት ተቀን ጥረት መደረግ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ሕዝቡ አማራጭ ሐሳቦችን የሚያገኝባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት ይንቀሳቀሱ፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ይስፋ፡፡ ምርጫም ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊ፣ ነፃና ተዓማኒነት ይኑረው፡፡ ሁሉንም ያግባባ፡፡
- ሰብዓዊ መብቶች ይከበሩ
ዜጐች ሰብዓዊ መብቶቻቸው ይከበሩ ሲባል በተፈጥሮ የተቀዳጁዋቸው መሠረታዊ መብቶች መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል፡፡ እነዚህ መብቶችም በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩና ዋስትና ያገኙ መሆናቸውም እንዲሁ፡፡ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ይከበሩ ሲባል ሰዎች በፖለቲካ አመለካከታቸው፣ በባህላቸው፣ በዘራቸው፣ በቋንቋቸው፣ በዕምነታቸውና በመሳሰሉት ሰበቦች ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስባቸው መደረግ አለበት ማለት ነው፡፡ እነዚህ መብቶች በሕገ መንግሥታችንም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኙ ናቸው፡፡ በአገራችን ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞች፣ ወዘተ ሲታሰሩ ወይም የተለያዩ እንግልቶች ሲደርሱባቸው ከአፅናፍ አፅናፍ ጩኸቶች ይስተጋባሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የአገሪቱ ዴሞክራሲ ወደኋላ እየተንከባለለ ይሄዳል፡፡ የባዕዳን መጠቋቆሚያ ይሆናል፡፡
የሕግ የበላይነት አለ በሚባልበት አገር ውስጥ ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱና ችግሩ ችላ ሲባል ለአገር ጥሩ አይደለም፡፡ በተለይ ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዘው የሚነሱ በርካታ ችግሮች ዜጐችን በሚያስመርሩበት አገር ውስጥ፣ በፖለቲካው ምክንያት የሚደርሱ የመብት ጥሰቶች ሲደመሩበት ተስፋ ያጨልማሉ፡፡ ሕግ ይከበር ሲባል መንግሥትን፣ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ከታች እስከ ላይ ያሉ ሹማምንትን፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ዜጐችን ይመለከታል፡፡ ሕግ የማስከበር ኃላፊነት ያለበት መንግሥት በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ስሙ ሲብጠለጠል ከማንም በላይ ሊያሳስበው ይገባል፡፡ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ የተጀመረው የዕድገት ጉዞ የሚቀጥለው ዜጐች በነፃነት ኮርተው ሲኖሩ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ እስከ መቼ ጥበቃ ይደረጋል?
በአጠቃላይ ዴሞክራሲው ሕክምና ይፈልጋል፡፡ ሕክምናው የሚገኘው ደግሞ በአገር ውስጥ ሁሉም ዜጐች በጋራ በሚደርሱበት መግባባት መሆን አለበት፡፡ በአንድ ቡድን የበላይነት ብቻ አገር ለምቶ አያውቅም፡፡ ሰላምም አይሰፍንም፡፡ የንግግር ነፃነት፣ ሁሉንም የሚያስማማ የፖለቲካ ምኅዳርና የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ዴሞክራሲን ለማስፈን ፍቱን መድኃኒት ናቸው፡፡ የዘመናችን ዓለም የተቀበላቸው ናቸው፡፡ የዴሞክራሲን ችግኝ ዘርቶ ፍሬውን ለማየት ለዓመታት ጥበቃ ማድረግ አያስፈልግም፡፡ የተሻለውን ልምድ በመቀመር የነገዋን ዴሞክራሲያዊት አገር በተግባር በሚደገፍ መርህ መገንባት ይቻላል፡፡ ሕዝቡ ዴሞክራሲ እንዲሰፍንለት እስከ መቼ ጥበቃ ማድረግ ይኖርበታል?