Tuesday, February 27, 2024

የገቢ ግብር አዋጅ ማሻሻያ በነሐሴ ወር ይጠናቀቃል

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

–  የደመወዝ ግብር ምጣኔ አንዱ ማሻሻያ ነው

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የጀመረው የገቢ ግብር አዋጅ ማሻሻያ ጥናት በነሐሴ ወር እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ በከር ሻሌ ማክሰኞ ሐምሌ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በተወያዩበት ወቅት ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል የገቢ ግብር አዋጁ ማሻሻያ ይገኝበታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የግብር ይግባኝ ለማቅረብ የሚመለከተው ግብር ከፋይ በመጀመሪያ የቀረበበትን ግብር ከነቅጣቱና ከነወለዱ 50 በመቶ እንዲከፍል መደረጉ አግባብ አለመሆኑን በመጥቀስ በ2005 ዓ.ም. ለቀረበ ቅሬታ፣ ጠቅላይ ማኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በዚህ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ መመርያ መስጠታቸውን ያስታወሱ የንግዱ ኅብረተሰብ ተወካይ ጉዳዩ ከምን እንደደረሰ ጠይቀዋል፡፡

የገቢ ግብሩ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ የጠየቁ አንዳንድ ተወካዮች አሁን ባለው አሠራር መሠረት የቅጥር ግብርና የትርፍ ግብር ምጣኔ ተመሳሳይ መሆን እንደሌለባቸው፣ ምክንያቱ ደግሞ የትርፍ ግብር የሚከፍሉ ነጋዴዎች ትርፍ ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረትና ተቀጣሪዎች የሚለፉት አይመጣጠንም ብለዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ በመጀመሪያ ምላሽ የሰጡት የባለሥልጣኑ የፌዴራል አገር ውስጥ ታክስ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ታፈሰ፣ ከነጋዴዎች ይልቅ ከፍተኛ ግብር ለመንግሥት እያስገቡ የሚገኙት ተቀጣሪዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም የአዲስ አበባን ሁኔታ በማንሳት በ2007 ዓ.ም. በከተማው ከተሰበሰበው ቀጥተኛ ታክስ ውስጥ 56 በመቶ የተገኘው ከተቀጣሪዎች መሆኑን፣ ከነጋዴዎች ትርፍ ግብር የተገኘው ደግሞ 36 በመቶ ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በገቢ ግብር ማሻሻያው ላይ ተጨማሪ አስተያየት የሰጡት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ በከር ሻሌ፣ በነሐሴ ወር ውስጥ የማሻሻያው ጥናት እንደሚገባደድ ገልጸዋል፡፡

ይህ ማለት ግን ማሻሻያው በአዋጅ መልኩ ተቀርፆና ፀድቆ በዚህ ዓመት ተግባራዊ ይሆናል ማለት አይደለም ብለዋል፡፡ ሕግ አውጪው አካል በ2008 ዓ.ም. ማሻሻያውን ተመልክቶ ውሳኔ እንደሚሰጥበትና በ2009 ዓ.ም. ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

ማሻሻያው ከሚይዛቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የግብር ይግባኝ አቀራረብ ላይ አቤቱታ አቅራቢ ግብር ከፋይ የተጣለበትን ግብር 50 በመቶ ከፍሎ ይከራከራል የሚለው አንዱ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት መመርያ ጥናት ይካሄድ እንጂ ማሻሻያ ይደረግ አለመሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በጥናቱ መሠረት የውሳኔ ሐሳብ ለሚመለከተው አካል እንደሚቀርብ ገልጸዋል፡፡

አቤቱታ ለማቅረብ ከሚያስፈልገው 50 በመቶ ክፍያ ውስጥ ቅጣትና ወለድ ይነሳ የሚለውን ውሳኔ ሰጪ አካላት የሚፈቱት ነው ብለዋል፡፡

የገቢ ግብር አዋጁን ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ባለሙያዎች ጋር በመሆን በመጪው ወር እንደሚያጠናቅቁ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከመስከረም 2008 ዓ.ም. በኋላ ለባለድርሻ አካላት ለውይይት እንደሚቀርብ ጠቁመዋል፡፡

የገቢ ግብር አዋጁ በተለይ በቅጥር ገቢ ላይ የተጣለው አነስተኛ ምጣኔና ከፍተኛ ምጣኔን ያስተካክላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ይህም ማለት በአሁኑ ወቅት ከ150 ብር ጀምሮ ታክስ የሚጣልበት ገቢ ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁም 35 በመቶ ታክስ ክፍያ የሚጣልበት ከ5,000 ብር በላይ ያለ ወርኃዊ ገቢም ከፍ እንዲል እንደሚደረግ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች በድፍኑ ጠቁመዋል፡፡

ዝርዝር የማሻሻያ ሐሳቡ የሚያተኩርባቸው የገቢ ዘርፎችን ከመግለጽም ኃላፊዎቹ ተቆጥበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -