Saturday, June 22, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የሕዝብ ዲፕሎማሲው የአገር ውስጥ ገጽታ ሲፈተሽ

በአብደልቃድር መሐመድ

የሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዲፕሎማሲ በቀደመው ጊዜ የመንግሥታት የሥራ ድርሻ ብቻ ተደርጎ የሚቆጠረውን ዕይታ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ ቀይሮታል። በዚህ ወቅት የሲቪክ ማኅበራት፣ ስመጥር ግለሰቦች (Celebrities) ምሁራንና ሌሎችም ተደማጭነት ያላቸው አካላት ተሳታፊ ሆነዋል። አገሮች የራሳቸውን ተፈላጊነት ሊያሳድጉ በሚችሉ እንቅስቃሴዎች ከምንጊዜውም በላይ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ አብዛኛዎቹ ጥረቶች በውጭው ዓለም የሚገኘውን ኅብረተሰብ በባህል ትርዒቶች፣ በባለሙያ ልውውጥና በምሥልና በድምፅ መረብ መድረስ ላይ ብቻ ያተኮሩ ሆነው እናገኛቸዋለን።

የማይናቅ ቁጥር ያለው የኅብረተሰብ ክፍል የሕዝብ ዲፕሎማሲ ሲባል በተለምዶ ቀድሞ በአዕምሮው የሚያቃጭለው በውጭው ዓለም ከሚኖሩ የሕዝብ፣ የሙያ ማኅበራት እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጋር የሚደረግ ግንኙነት አድርጎ የመውሰድ ዝንባሌ ይስተዋላል። ነገር ግን የሕዝብ ዲፕሎማሲ በአገር ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ አካላት ጋር በሚደረጉ ግንኙነቶችም ሊገለጽ እንደሚችል የተዘነጋ ይመስላል። በዚህ ጽሑፍ የኢትዮጵያ የሕዝብ ዲፕሎማሲ አገራዊ ገጽታ (Domestic Dimension of the Ethiopian Public Diplomacy) ትኩረት ተሰጥቶ ይዳሰሳል። በተጨማሪም በዘርፉ ቢካተቱ የተሻለ እምርታን ያመጣሉ ተብለው የሚታሰቡ ምክረ ሐሳቦችን ለመጠቆም ይሞክራል።

  1. የዓለም ነባራዊ ሁኔታና የሕዝብ ዲፕሎማሲ ተግዳሮቶች

በአሁኑ ጊዜ የዓለም ማኅበረሰብ መስተጋብር ከምንጊዜውም በላይ ትስስር ውስጥ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ለውጥ ከሚገለጹ ፈርጀ ብዙ ምክንያቶች መካከል በመገናኛና መረጃ መስክ የቴክኖሎጂ መራቀቅ፣ ከዕለት ተዕለት እያደገ የመጣው ገደብ የለሽ የሰዎች ዝውውር፣ የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ሥርዓት መናኘት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችና የፀጥታ ሥጋቶች ከብዙ በጥቂቱ ይገኙበታል። እዚህ ላይ የተጠቀሱት ዓበይት ምክንያቶች በመንግሥት የሚከናወን የዲፕሎማሲ ሥራን ለኅብረተሰቡ ይበልጥ ግልጽ፣ በትብብር ላይ የተመሠረተና ቴክኖሎጂን ማዕከል ያደረገ እንዲሆን አስገድዷል።

ከላይ በተጠቀሱት መሠረታዊ ለውጦች ምክንያት በውጭ አገር ለሚደረግ የላቀ የገጽታ ግንባታ ስኬት በአገር ውስጥ የሚደረጉ የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች አስፈላጊነት መታመን ለሕዝብ ዲፕሎማሲ የአገር ውስጥ ገጽታ ኑባሬ መሠረታዊ መነሾ ሲሆን፣ ይህም በዓለም ላይ የሚገኙ የውጭ ጉዳይና የዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በዘርፉ የአገር ውስጥ ድጋፍና ማስተባበር ሒደት ከሥረ መሠረቱ እንዲዳብር የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ አስገድዷል። በዚህ መስክ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የአገር ውስጥ ተደራሽነት እንዲሰፋ የሚደረገው ተግባር የላቀ የሰው ሀብት ሥምሪት መጠየቁ፣ በቂ መዋዕለ ንዋይ፣ የተጠናከረና የተደራጀ መረጃና ግንኙነት ቴክኖሎጂ አጠቃቀም የሚያስፈልጋቸው መሆኑ የአገሮቹ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቶች ከገጠሟቸው ተግዳሮቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ በአገር ውስጥ የምታካሂዳቸው የሕዝብ ዲፕሎማሲ ተግባራት በምን ደረጃ ይገኛሉ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እንሞክራለን።

 

 

  1. በፖሊሲ ውይይት መስክ

መንግሥት የአገሪቱን ፍላጎቶች ለሟሟላት በሚያስፈልጉ አጠቃላይ የፖሊሲ ማዕቀፎች በመመራት፣ የወቅቱ ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ ተመሥርቶ ፕሮግራሞችን መቅረፅ ቁልፍ ተግባሩ ነው። በተለይ የኅብረተሰቡን የልብ ትርታ የሚያዳምጡ መንግሥታት ለሚነድፏቸው ፈርጀ ብዙ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ስኬት፣ የኅብረተሰቡን ዕይታ ለማካተት የሚያደርጉት ጥረት የማይተካ ሚና ይጫወታል። ከዲፕሎማሲው ጋር በተገናኘ ለዲፕሎማሲ ሥራው መሠረታዊ ግብዓት ሆኖ የሚያገለግለውን የውጭ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት የፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ በ1995 ዓ.ም ከመፅደቁ በፊት የሰነዱ ረቂቅ ለሕዝብ፣ ለሙያ ማኅበራትና ለሌሎች አደረጃጀቶች ለውይይት ቀርቦ በፖሊሲው ላይ በኅብረተሰቡ በኩል በጎ ጎኖቹ ጎልተው እንዲወጡ፣ አሉታዊ ጎኖችም ካሉት ኅብረተሰቡ ችግሮቹን ነቅሶ እንዲያወጣ መድረኮችን በማዘጋጀት፣ ኅብረተሰቡ የአገራችን የውጭ ጉዳይና አገራዊ ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ገና ከመሠረቱ ቅርፅ በመስጠት ረገድ የራሱን ሚና እንዲጫወት ሁኔታዎች ተመቻችተዋል።

በመሆኑም በዘመናዊው የሕዝብ ዲፕሎማሲ ጽንሰ ሐሳብ መሠረት የአገር ውስጡን ሕዝብ ተኮር የሕዝብ ዲፕሎማሲ ዕይታ ገና ፖሊሲው ሲረቀቅ ጀምሮ በአገራችን በሥራ ላይ ውሏል። እዚህ ላይ ምናልባት የፖሊሲ ሰነድ በሥልጣን ላይ ያለን የፖለቲካ ድርጅት አቋም የሚያመላክት በመሆኑ አጠቃላይ የሕዝቡን ዕይታ ሊወክለው አይችልም የሚል ክርክር ቢነሳ እንኳን፣ እንደ ኢትዮጵያ ባለ በዴሞክራሲውም ሆነ በኢኮኖሚው ታዳጊ አገር ውስጥ የዴሞክራሲ ባህልን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ላይ የሕዝብ ተሳትፎን መፍቀድ ሊጫወት የሚችለው ሚና የጎላ ነው። ከላይ የተነሳው የፖሊሲ ሰነድ የአንድ ፓርቲ ልሳን ይሆናል የሚለው ሥጋት ተገቢ ሊሆን ከሚችልባቸው አጋጣሚዎች አገርን ለመታደግና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር፣ ቀጣይነት ያለው በፖሊሲ ላይ የሚደረጉ አገር አቀፍ ምክክሮች አገሪቱ ሊገጥሟት ከሚችሉ ችግሮች መታደግም ብቻ ሳይሆን፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብትን በማስከበር፣ ኅብረተሰቡ በልዩነት ውስጥ የሚፈልቁ መልካም ሐሳቦችን ለአገሩ ዕድገት ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ ያለምንም ሥጋት እንዲያቀርብ ዕድል ይፈጥራል።

  1. የመገናኛ ብዙኃን ተደራሽነትን ማስፋት

በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን በማናቸውም ፈርጅ ለሚደረግ እንቅስቃሴ ወቅታዊና ተዓማኒነት ያለው መረጃ ይዞ መገኘት ለስኬት የሚደረገውን ጉዞ እንደሚያቃናው እሙን ነው። በመቀጠል የምንመለከተው በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንና በኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትብብር በየሁለት ሳምንቱ እየተዘጋጀ ለተመልካች የሚቀርበውን “ዲፕሎማሲያችን” የተሰኘ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ነው።  ይህ ፕሮግራም ለኅብረተሰቡ ወቅታዊ መረጃዎችን ከማቅረብ ባለፈ አገሪቱ በዘርፉ በክፍለ አኅጉር፣ በአኅጉር ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለችበትን ደረጃ፣ የገጠሟትን እንዲሁም ሊገጥሟት የሚችሉ ፈተናዎችን በማስረጃ በማስደገፍ ያቀርባል። በዘርፉ የበቃ ልምድ ያካበቱ ምሁራንና የውጭ ግንኙነት ባለሙያዎች የሚሰጧቸው ምልከታዎች ሰፊው ሕዝብ ስለአገሩ የሚኖረው መረዳትን በመቅረፅ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። በዚህ ወቅት በሚደረጉ ፈርጀ ብዙ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ከዕለት ዕለት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋን እያገኘ ያለው የኅብረተሰብ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ፣ በዚህ የመገናኛ ብዙኃን መስክ የሚተላለፈው ፕሮግራም ተደራሽነት መስፋት በዘርፉ ለሚደረጉ የለውጥ እንቅስቃሴዎች እንደ በጎ ጅምር ይታያል።

ከላይ የተጠቀሱት መልካም ጎኖች ቢኖሩም፣ ፕሮግራሙ ወጥነት ባለው ሁኔታ እንዳይተላለፍ የሚያደርጉ ክስተቶች መደራረብ፣ ኅብረተሰቡን በቀጥታ የማያሳትፍ መሆን፣ ከሁለትዮሽ መስተጋብር ይልቅ በአንድ መንገድ (One Way) የመረጃ ሰጪና ተቀባይ ተዋረድ የመፍጠሩ ዝንባሌ መጉላት፣ በተጨማሪም የአየር ሽፋኑ አነስተኛነት ፕሮግራሙ የታለመለትን ግብ እንዳይመታ ማነቆ ይሆናሉ። በእርግጥ ቀድሞ በኅብረተሰቡ ውስጥ የዲፕሎማሲ ተግባር ስስ የፖለቲካና ብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ ነው በሚል በዘርፉ ውስጥ ሰላሉ ባለሙያዎች ብቻ የተተወ ሥራ አድርጎ የመቁጠር ዝንባሌ ገዝፎ ይስተዋል ነበር። በዘርፉ ሰፊው ሕዝብ የራሱ ሚና እንዳለው በማሳየት ረገድ ፕሮግራሙ ረጅም ርቀት የተጓዘ ቢሆንም ቅሉ፣ መንግሥት ከካዝናው የሚያወጣውን አንጡራ ሀብት በሥራ ላይ እስካዋለ ድረስ ከላይ የተጠቀሱትን ውስንነቶች ማረቅ ቢቻል፣ የተጀመሩትን እንቅስቃሴዎች በማይናድ መሠረት ላይ ለመደልደል ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል።

  1. ባለድርሻ አካላትን የመለየት ሥራ

በሕዝብ ዲፕሎማሲ ዘርፍ የሚገኙ ዓበይት ልሂቃን ሀቲት መሠረት በዘርፉ አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ ከሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል የሕዝብ ዲፕሎማሲ አባላትን መለየትና እንዳስፈላጊነቱ በቅደም ተከተል የማስቀመጡ ጉዳይ ይገኝበታል። በዚህ ዙሪያ የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ ስንመለከት ጉዳዩን በባለቤትነት የሚከታተለው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ጅምር ሥራዎችን አከናውኗል፣ በማከናወንም ላይ ይገኛል። የዚሁ ጥረት መገለጫም በቅርቡ ወደ ግብፅና ሱዳን የተንቀሳቀሰው የሕዝብ ዲፕሎማሲ ቡድን ይሆናል። ምንም እንኳን የሕዝብ ዲፕሎማሲ ቡድኑ ከየትኛው የኅብረተሰብ ክፍል፣ የሙያ ማኅበር ወይም ዘርፍ ይመረጣል? በምን መመዘኛስ? የሚለው ግልጽ መመርያ የሌለው ቢሆንም፣ የተሳለጡ ጅምሮችን በማበረታታት በቀጣይ ሊወሰዱ የሚገቡ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ረገድ መሥሪያ ቤቱ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በሰፊው ሊሄድበት የሚገባው ጉዳይ መሆኑ አጽንኦት ሊሰጠው ያስፈልጋል።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አገራችን ውስጥ መንግሥትም ሆነ ሌሎች አካላት በሁሉም አቅጣጫ ጠንክረው እንዲሠሩ የሚገፋፋ ኅብረተሰብ (Demanding Society) መፍጠር ተችሏል። የዚህ ዓይነት ኅብረተሰብ በሚገኝበት ሥፍራ፣ መንግሥት የሥልጣን መንበርን እንደ ርስት ሳይሆን ቅቡልነትን (Popular Legitimacy) ለማግኘት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የኅብረተሰቡን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች በአግባቡ ለማሟላት የሚተጋበትን አመለካከት ይፈጥራል። ስለዚህ የኅብረተሰቡን ፈርጀ ብዙ ጥያቄዎችን ለመመለስ ንቃተ ህሊናን የማጎልበት ሥራ ሊሠራባቸው ከሚገቡ ዘርፎች መካከል የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ካስማ ሆኖ ይገኛል። እንደማሳያ በቅርቡ ከተደረጉ የሕዝብ ዲፕሎማሲ ትሩፋቶች መካከል የኢትዮ ግብፅ ግንኙነትን እንመለከታለን።

ኢትዮጵያና ግብፅ ለረዥም ጊዜ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው አገሮች ሲሆኑ፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የመሠረቱት እ.ኤ.አ. በ1924 ነው። የዓባይ ወንዝ ሁለቱን አገሮች የሚያስተሳስራቸውና በግንኙነታቸው ላይም በአሉታዊና በአዎንታዊ መንገድ ተፅዕኖ የሚያደርግ ታሪካዊና በእጅጉ ወሳኝ ሀብት ነው። ይህ ዕድሜ ጠገብ የሆነው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ቀደምቶቹም ሆኑ የዛሬዎቹ የግብፅ መንግሥታት ሁለቱን አገሮች በሚያስተሳስረው ዓባይ ወንዝ ዙሪያ በሚንፀባረቅ ለዘመናት የቆየ “የብቸኛ ባለቤትነት ስሜት” ኢትዮጵያን በጥርጣሬ ዓይን የተመለከቱበትና አልፎ ተርፎም ችግር በመፍጠር አገራችንን ለማዳከም የጣሩበት ታሪክ ነው ተብሎ ማስቀመጥ ይቻላል። ይህም የሁለቱን አገሮች ግንኙነት በአለመተማመን አጥሮ ከታሪካዊነት ባለፈ መድረስ ከሚገባው ደረጃ ላይ እንዳይደርስ አድርጎት የቆየ ቢሆንም፣ ሁለቱ አገሮች በተለያዩ መስኮች ለመተባበርና በመካከላቸው የመተማመን መንፈስ ለማጎልበት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ይህንንም ተከትሎ በተለይ በኢትዮጵያ በኩል የሁለቱን አገሮች የፖለቲካዊ ግንኙነት ዳራ፣ የኢኮኖሚ ትስስር፣ የማኅበራዊና የሃይማኖታዊ ግንኙነቶች ዕይታ ለማስተካከል (Paradigm Shift) መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ መዋዕለ ንዋይ አፍስሷል። እንደ ምሳሌ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠ በኋላ የተሠራው ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ብሎም ምክክር ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝን በተመለከተ ለረዥም ጊዜ ሰፍኖ የኖረውን የተዛነፈ ምልከታ ለመለወጥ ጥረት ማድረጓን መመልከት ይቻላል። በእርግጥ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በየዕለቱ እያደገ የመጣውን ኢኮኖሚና የሕዝብ ፍላጎት ማርካት የሚችል አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት የማረጋገጥ ቁርጠኝነት ቢኖረውም፣ ሌሎች የተፋሰሱን አገሮች በማይጎዳ መንገድ ራስን የማልማት የዘመናት የኢትየጵያ ሕዝብ ጥያቄ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ኩሩ ኢትዮጵያውን ንቅናቄን በመፍጠር “የአገር ልማት በአገር ልጅ” የሚል መፈክር በኅብረተሰቡ ልብ ውስጥ ከትቧል፡፡ ለድህነት በአልሸነፍ ባይነት ስሜት እጅግ የላቀ ጥያቄን በመንግሥት ላይ በማጫር መንግሥት ለእንቅስቃሴው በማያዳግም ሁኔታ ምላሽ እንዲሰጥ አድርጓል፡፡ ምንም እንኳን አገራችን ከሰማንያ አምስት በመቶ በላይ የጥቁር ዓባይ ወንዝ አመንጪ ብትሆንም ቅን የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የሚል ብሂልን ወደ ጐን በመተው፣ ለዘመናት የቆየውን በመቻቻልና በመተባበር ስሜት ለጋራ ተጠቃሚነት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሕዝባችን ልዩ መገለጫ መሆኑን አሳይቷል፡፡ ይህንን ከማሳየት ባሻገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መርህ ቀድሞ በሁለንተናው የሰረፀ ስለመሆኑ ለተቀረው የዓለም ማኅበረሰብ አስመስክሯል።

  1. የሴቶች ተሳትፎ

ከኢትዮጵያ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በተገኘ መረጃ የአገራችን ሕዝብ ብዛት በሐምሌ 2006 ዓ.ም. 87,952, 000 (ሰማንያ ሰባት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሃምሳ ሁለት ሺሕ) እንደነበር ገልጿል። ከዚህም ውስጥ አጠቃላይ የሴቶች ብዛት 43,748,000 (አርባ ሦስት ሚሊዮን ሰባት መቶ አርባ ስምንት ሺሕ) ይሸፍናል። እኚህን ግማሽ የኅብረተሰብ ክፍል በአግባቡ የማይወክል ማንኛውም እንቅስቃሴ ግቡን ሊመታ እንደማይችል ብቻ ሳይሆን፣ እንደማይታሰብም ሳይታለም የተፈታ ነው። ሴት ኅብረተሰቡን በማስተማር ቀዳሚ ነች፡፡ ሴት ኅብረተሰቡ ላይ የተጋረጡ ተግዳሮቶችን ለመጋፈጥ ምናልባትም የመጀመሪያዋ ነች፡፡ በአገሮች መካከል በሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭት የመጀመሪያውም የመጨረሻውም አሰቃቂ ድርጊቶች ከሚጋረጥባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ሴቶች ቀዳሚዎች ናቸው።

አገራችን በምታከናውነው የሕዝብ ዲፕሎማሲ ሥራ ላይ የዚህ ሁሉ ችግሮች ቀዳሚ ገፈት ቀማሽ የሆነች ሴት ልትጫወት በምትችለው ሚና ላይ ያተኮረ የተሳትፎ  ሽፋን በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን ቁመና ሊወክል አልቻለም። ለምሳሌ ወደ ግብፅ ከተጓዘው የሕዝብ ዲፕሎማሲ ቡድን ጠቅላላ አባላት የሴቶች ተሳትፎ በአሥር በመቶ ብቻ የተገደበ ነበር። በእርግጥ የቀደሙ ጭቆናዎች፣ ባህልና ሌሎች ጎታች አመለካከቶች ሴቶች በየዘርፉ ልቀው እንዳይወጡ አድርጓቸው ሊሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ ግን ሴቶችን በተለያዩ መስኮች ማሳተፍ የችሮታ ጉዳይ ሳይሆን የህላዌ አዝማሚያን ተላብሷል። ስለዚህ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዋናነት በሚያከናውነው የሕዝብ ዲፕሎማሲ ክንውኖች የሴቶችን ተሳትፎ በማጎልበት ረገድ ለወደፊቱ ከፍተኛ የማብቃት ሥራ እንደሚጠብቀው ከወዲሁ በመገንዘብ ዘርፈ ብዙ እገዛዎችን (የአቅም ግንባታ፣ የአመለካከትና የተደራሽነት አድማስን የማስፋት) እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ከወዲሁ መዘጋጀት ይጠበቅበታል።

በዓለም አቀፍ መድረክ ዜጎች አገሮቻቸውን በበጎ መልክ የሚያስተዋውቁበት (Branding) እንዲሁም በሰጥቶ መቀበል መርህ (Reciprocity) ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁበት አጋጣሚ በመፈጠሩ፣ ስለወቅታዊና አጠቃላይ የአገሪቱ ሁኔታ መረጃዎችን ለዜጎች ማስታጠቅ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው። ለዚህም ነው አብዛኞቹ የዓለማችን አገሮች የዜጎች ዲፕሎማሲ (Citizen Diplomacy) መርህን በመከተል ዜጎቻቸው የአገራቸውን ገጽታ ገንብተው፣ የተለያዩ የቢዝነስ አማራጮችን ወደ አገር እንዲያመጡ የሚያግዟቸው። በአገር ውስጥ የሚደረጉ የሕዝብ ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ሁሉን የኅብረተሰብ ክፍል ያካተተ ሆኖ በስፋት መከናወን አለበት የሚባለውም ለዚህ ነው።

ዴሞክራሲ በአገራችን እንደ ቅንጦት የሚታይበት ዘመን አክትሟል። አሁን ለሁሉም እንቅስቃሴዎች የዴሞክራሲ ጥያቄዎች መሠረታዊ ከመሆናቸው የተነሳ “ዳቦ ይቀድማል ዴሞክራሲ” የሚለውን የቆየ ክርክር ገሸሽ በማድረግ፣ ሁለቱም መሳ ለመሳ የሚሄዱበት አግባብ እየተፈጠረ ይገኛል። በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 12 ላይ እንደተደነገገው፣ መንግሥት የሚያከናውናቸው ሥራዎች ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነትን በተከተለ መንገድ መከናወን አለባቸው የሚለውን መርህ ወደ ተግባር መቀየር የግዴታ ውዴታ ሆኗል። ኅብረተሰቡ የሚያስፈልገውን የመጫሚያ ቁጥር መንግሥታት ለብቻቸው የሚወስኑበት ዘመን አብቅቷል፡፡ በምክክር ይሆናል እንጂ። የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ማረጋገጥና ማጎልበት፣ የሕዝብ ዲፕሎማሲን ጨምሮ በማናቸውም ዘርፍ  ከታለመለት ግብ ለመድረስ የማይተካ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው፣ የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች ከማናቸውም በተሻለ ማሳያ ይሆናሉ።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles