Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየኢትዮጵያ አዝራሮች

የኢትዮጵያ አዝራሮች

ቀን:

መሰንበቻውን ‹‹ንባብ ለሕይወት›› በሚል መሪ ቃል ለአራት ቀናት በተካሄደው የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይና ባዛር ከተከናወኑት ልዩ ልዩ ትዕይንቶች መካከል አንዱ ስለክብር አልባሳት አዝራር (ቁልፎች) የሚያወሳው ነው፡፡

በዐውደ ርዕይና ባዛሩ መዝጊያ ሐምሌ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ያገኘነው ጋዜጠኛና ደራሲ ብርሃነ ሰሙ ‹‹የአዝራር ዲዛይንና ፋሽን በኢትዮጵያ›› በሚል ርእስ ቀደም ሲል በመጽሐፍ መልክ አውጥቶት የነበረውን ታሪካዊ ገጽታ በፎቶግራፍ፣ በሰነድና በቁልፍ ስብስብ አጅቦት አቅርቦታል፡፡  

‹‹በልብሶቻችን ላይ ያሉት ቁልፎች በአትኩሮት ብንመለከታቸው በላያቸው ላይ ታሪክ ታትሞ ወይም ማስታወቂያ ተነግሮባቸው እናገኛቸዋለን፡፡ ታሪክና ማስታወቂያ ባይተላለፍባቸው እንኳን በፈጠራና በዲዛይን ሥራቸው የሚያስገርሙን ሆነው ይገኛሉ፡፡ በዚህ ዓላማና ምክንያት የልብስ ቁልፎች በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ጥናትና ምርምር ይካሄድባቸዋል፤›› የሚለው አቶ ብርሃኑ፣ በኢትዮጵያ በልብስ ቁልፎች ላይ ጥናት ለመሥራት ግን ብዙ አልተሞከረም ይላል፡፡ በአገሪቱ የአልባሳት ቁልፎች አጠቃቀም ምን እንደሚመስል የሚያሳዩ መረጃዎች ግን በርካታ መሆናቸው፣ በምሳሌነትም በአዲስ አበባ ከተማ ሙዚየሞች የቀድሞ ዘመን ነገሥታትና ሹማምንት ይጠቀሙባቸው የነበሩ አልባሳት በቅርስነት መመዝገባቸውን በአልባሳቱም ላይ እንደ ምስር ደቃቅ የሆኑና በብረት የተሠሩ የልብስ ቁልፎችን እንዳሉባቸው ያነሳል፡፡

እነዚህ የልብስ ቁልፎች የት ተሠሩ? በማን ተሠሩ? መቼ ተሠሩ? እንዴት ተሠሩ? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚገኝበት ጥናት ጎልቶ ባይታይም የአልባሳቱ ቁልፎች በአገር ውስጥ አንጥረኞች ስለመሠራታቸው ግን ይገመታል፡፡ በዘመኑ ለአንጥረኞች ዕውቅና ክብር ስለማይሰጥ፤ የአልባሳቱ ቁልፍ በማንና የት እንደተሠሩ መረጃው እንዳይዘገብ ምክንያት ሆኗል የሚሉ ግምታዊ ምላሾች መኖራቸውን አቅራቢው ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡

ከ1940ዎቹ በኋላ ግን በአገራችን ኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት ስለቻሉት የክብር አልባሳት ቁልፎች ዝርዝር መረጃ ብቻ ሳይሆን፤ የትኛው የልብስ ቁልፍ ለየትኛው መኮንን እና የጦር ክፍል አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ማሳያ ምርትና ሰነዶች አሉ፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ክብር ዘበኛ፣ ጦር ሠራዊት (ምድር ጦር)፣ ፊናንስ ፖሊስ፣ የወህኒ ቤት ጥበቃ፣ ባሕር ኃይል፣ አየር ኃይል… የመሳሰሉ የጦር ክፍሎች ይለብሷቸው በነበሩ የክብር አልባሳት ላይ ግልጋሎት የሰጡት ቁልፎች የእያንዳንዱን የጦር ክፍል አርማ የያዙ እንደነበሩ አቶ ብርሃኑ በማብራሪያው ገልጿል፡፡

እነዚህ የክብር አልባሳት ቁልፎች፤ በአገር ውስጥ በቀድሞ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጥይት ፋብሪካና ፒያሳ ይገኝ በነበረው በአርመናዊው አንጥረኛ ሳቫጂያን ድርጅት የተመረቱ ሲሆን፣ ከአገር ውጭ ደግሞ በእንግሊዝ ከተሞች በለንደን፣ በካኒንግሃም፣ በብሪንግሃም፣ እንዲሁም በኮርያና በሌሎችም ተመርተው ወደ አገር ውስጥ መምጣታቸውን በአልባሳቱ ቁልፎች ጀርባ ላይ ከታተሙት መረጃዎች መረዳት ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ የልብስ ቁልፍን በተመለከተ እስከ ጥግ ድረስ አስባ እነዚህ የክብር ልብስ ቁልፎችን ለማምረትና ለመጠቀም ምን ዕውቀት ነበራት? በምን ሒደትስ እዚህ ላይ ተደረሰ? ሥራው የተመራበት ሕጋዊ ማዕቀፍስ ምን ይመስላል? ለሚለው ጥያቄ ምላሹ የሚገኘው ይህንኑ ርእሰ ጉዳይ ማዕከል አድርጎ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በ1941 ዓ.ም. ከወጣው አዋጅ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ያወሳል፡፡ ‹‹የጦር መኮንኖችና የሹማምንት የወታደሮችም በልባሳቸው ላይ ስለሚያደርጉት መለዮ የተሰጠ ድንጋጌ፤ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ›› በሚል ርእስ የወጣው አዋጅ፤ ስለወታደራዊ የክብር አልባሳት ቁልፎች አጠቃቀምም ደንብና ሥርዓት አስቀምጧል፡፡

በ1944 ዓ.ም. ይህንኑ ርእሰ ጉዳይ ያደረገ የሕግ መጽሐፍ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተዘጋጅቶ መታተሙ ይታወሳል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የጦር ሠራዊት መለዮ ልብስ ደንብ›› መጽሐፍም በርካታ ዝርዝር ነገሮችን ይዟል፡፡ አንዱ ምዕራፍ የክብር ልብስ ቁልፍ አጠቃቀምን የሚመለከት ነው፡፡ ጄነራል መኰንኖች፣ እግረኛ ጦር፣ ክብር ዘበኛ፣ ፈረሰኛ፣ መድፈኛ፣ መሐንዲስ፣ ሬዲዮ፣ ሕክምና፣ ሙዚቀኛ፣ ታንከኛ… የጦር ክፍሎች ምን ዓይነት የክብር አልባሳት ቁልፍ መጠቀም እንዳለባቸው ዝርዝር መመሪያና የቁልፎቹን ዲዛይን በሥዕል ጭምር ያቀረበ መጽሐፍ ነው፡፡

ከ1940ዎቹ ጀምሮ የሕግ ማዕቀፍ ተቀርፆላቸው በሕጋዊ ጥበቃና ከለላ አገልግሎት መስጠት የጀመሩት የክብር አልባሳት ቁልፎች፤ በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ብቻ ሳይሆን በደርግና በሪፐብሊኩ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ)፣ እነዲሁም በዘመነ ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዲሪ) መንግሥታት ዘመንም አገልግሎት መስጠታቸውን ቀጥለዋል፡፡ መንግሥታቱ ሲለዋወጡ ግን በክብር አልባሳት ቁልፎች ላይ የሚታተሙት የጦር ክፍሎቹ ዓርማ ግን ተለዋውጧል፡፡

‹‹የአገራችን የልብስ ቁልፍ ምርት ኢንዱስትሪ የዛሬ 50 እና 60 ዓመት ባሳየው ምልክት መጠን እያደገ መጥቷል ማለት አይቻልም፤›› የሚለው አቶ ብርሃኑ፣ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ “ኤልናኤል” እና “በላይነህ ቤካ” የሚባሉ የልብስ ቁልፍ ፋብሪካዎች መኖራቸውና  ይህንኑ ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ የፈጠራ ሥራዎችን እየሠሩ ያሉ ግለሰቦችም እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡ በቴምር ፍሬ፣ በእንጨት፣ በዳንቴል (ኪሮሽ ሥራ)፣ በቃጫ፣ በመሶብ ስፌት፣ በላስቲክ ቁልፍና የአልባሳት ጌጣጌጥ የሠሩ እንዳሉና የተለያዩ አርቲስቶችና የልብስ ቁልፍ አድናቂዎችም በቁልፍ የተለያዩ ጥበባዊ ሥራዎችን በመሞከር ላይ መገኘታቸውንም አውስቷል፡፡ እነዚህን አስተባብሮ በአንድነት መሥራት ከተቻለ የአገሪቱን የልብስ ቁልፍ ምርት ኢንዱስትሪ ከፍ ማድረግ እንደሚቻልም ሳያመለክት አላለፈም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...