Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርምሳሌና ዓርአያ የነበሩት ባለሥልጣን

ምሳሌና ዓርአያ የነበሩት ባለሥልጣን

ቀን:

በቅድሚያ በአቶ ዓሊ ሲራጅ ድንገተኛ ሕልፈተ ሕይወት የተሰማኝን ሐዘን እየገለጽኩ ቸሩ አላህ ለቤተሰባቸው መጽናናትን እንዲሰጣቸው እመኛለሁ፡፡

የአቶ ዓሊን ሕልፈተ ሕይወት ያነበብኩት ሐምሌ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. በወጣው የሪፖርተር ጋዜጣ ከቀረበው የሕይወት ታሪካቸው ነው፡፡ ታሪካቸውን ሳነብ በጣም ያስደነቀኝ እኝህ ሚኒስትር ዴኤታ አሮጌ ቤቶች በበዙበት በደጃች ውቤ ሠፈር፣ በወር 180 ብር የቤት ኪራይ በሚከፈልበት አነስተኛ መኖሪያ ቤት መኖራቸው፣ ባላቸው ሥልጣን የተሻለ ቤት ማግኘት ሲችሉ ቤት ይሰጠኝ ብለው እንዳልጠየቁ፣ ለግል ሕይወታቸው ብዙም እንደማይጨነቁ፣ ለቀብራቸው ማስፈጸሚያ በቤታቸው የተፈለገው መጠን ገንዘብ አለመገኘቱ ማንበቤ ነው፡፡

ይህን አጭር ታሪካቸውን አንብቤ አቶ ዓሊን ያነፃፀርኩት ከሌሎች የአገሪቷ ሚኒስትሮች ጋር ነው፡፡ እነዚህ ሚኒስትሮች እጅግ ውድ በሆኑና ምቾታቸው በጣም ከፍተኛ በሆኑ የመንግሥት ቤቶች ውስጥ እንደሚኖሩ የታወቀ ነው፡፡ የትኛው ሚኒስትር ነው 180 ብር የሚከፈልበት ቤት ውስጥ የሚኖረው? ማን የሚባለው ሚኒስትር ይሆን ችምችም ያለ ሠፈር ውስጥ ከተራ ሰዎች ጋር አብሮ የሚኖረው? እርግጥ ጥቂቶች እንደማይጠፉ አቶ ዓሊ ማስረጃ ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እኝህ ባለሥልጣን ለሌሎቹ ሚኒስትሮች ምሳሌና ዓርአያ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ በሕይወት ያሉት ሚኒስትሮችና ፖለቲከኞች ከሟቹ ትምህርት ሊቀስሙ ይገባቸዋል፡፡

በነገነራችን ላይ አቶ ዓሊን በፍፁም እንደማላውቃቸውና ምንም ግንኙነት እንደሌለኝ ለአንባብያን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡

ይህቺን አጭር ማስታወሻ እንድጽፍ የገፋፋኝ ግን በጋዜጣው የሰፈረው የሕይወት ታሪካቸውና በጎረቤቶቻቸውና በወዳጆቻቸው የተሰጠው አስተያየት ነው፡፡ የአቶ ዓሊ የአኗኗር ሁኔታ ሲገለጽ ነፃ መንፈስ ያላቸው፣ በራሳቸው የሚተማመኑና ምንም የሚፈሩት ወይም የሚጨነቁበት ጉዳይ እንደሌለ በግልጽ ያሳያል፡፡ አንድም ቢሆን እንዲህ ያለ ሰው አገሪቱን ከሚመሩት ባለሥልጣናት መካከል መገኘቱ በጣም አስደንቆኛል፡፡

ሥልጣን አደራ ነው! ልዩ ጥቅም ማግኛ አይደለም!!

(ከሕዝባዊነት)

*******

ለመሥራት ትጋት ስብዕናና ሀቅ ይኑረን

እሑድ ሐምሌ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. በይድረስ ለሪፖርተር ዐምድ ላይ ‹‹ያልገባቸው ያልገባንን ግራ ሲያጋቡ፤›› በሚል ርዕስ የተጻፈ አስተያየት አይሉት ዘለፋ፣ ሐሜት (ራሳቸው ስላሉት) አይሉት ግምገማ፣ ከግለሰቦች ጀምሮ እስከ ድርጅቶች ቂም የቋጠሩ ያልገባቸውና ግራ የተጋቡ ጸሐፊ የሰጡትን አስተያየት ስንመለከት አብዛኞቻችን የኮርሱ ተሳታፊዎች በስልክም በአካልም ተገናኝተን ተወያይተንበታል፡፡ በስማችን የተጻፈ አስተያየት ስለሆነም መልስ እንድንሰጥበት ተስማምተን ጽፈናል፡፡

ጸሐፊው የኮርሱ ተሳታፊ ይሁኑ አይሁኑ እርግጠኛ መሆን ባንችልም የኮርሱ ይዘት በካፍ የተዘጋጀ፣ ለሁሉም ተታፊዎች አንድ ዓይነት ሲለበስ፣ (Syllabus) ሲሆን የመቐለው ሥልጠናም በንድፈ ሐሳብ፣ በተግባር፣ በቪዲዮ እርስ በርስ በመማማር፣ የግልና የቡድን ሥራ በመሥራት ከማሳተፍ በተጨማሪ፣ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ከሚጎኙና በዘርፉ ጥልቅ ዕውቅት ባላቸው መምህራን አማካይነት የሚሰጥ ነው፡፡ ህንዳዊውን ፊዚዮቴራፒስትና የፒኤች ዲግሪ ትምህርታቸውን በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ከሚከታተሉት አንዱን በማሳተፍ የተሰጠ ኮርስ እንደነበረ አስተያየት ሰጪው የኮርሱ ተሳታፊ ከነበሩ ይዘነጉታል ብለን አናምንም፡፡ አብዛኞቻችን የኮርሱ ተሳታፊዎች ግን በኮርሱ ኢንስትራክተሮች ደስተኞች ነበርን፡፡ በሙያቸውም አንቱ ስለመባላቸው ካፍም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም የመሰከረላቸው፣ በብዙ የስፖርት ቤተሰቦች ከበሬታን ያገኙ ናቸው፡፡ ለዚህም ነበር በኮርሱ ደስተኞች ስለነበርን አድናቆታችንን ለመግለጽ ትንሽ ስጦታ በመስጠትና ግብዣ በማድረግ (ከኮርሱ ተሳታፊዎች በተዋጣ ገንዘብ) የገለጽነው፡፡

ይሁን አንጂ አስተያየት ሰጪው ራሳቸውን በላቀ ትምህርት፣ ተሞክሮ፣ ሥነ ምግባርና በቤተሰብ አስተዳዳሪነት ሲያስቀምጥና ሲገልጹ፣ ኮርሱን የሰጡን ባለሙያተኞች ግን ከትምህርት፣ ከተሞክሮ፣ ከሥነ ምግባርና አስተዳደሪነት ውጭ ከማድረጋቸውም በላይ አስተያየታቸውን በኮርሱ ተሳታፊዎች ስም ማድረጋቸው ትልቅ ስህተት ነበር፡፡

በዚህ መሠረት አብዛኞቻችን ይህን መልስ እንድንጽፍ የተስማማን የኮርሱ ተሳታፊዎች ያልገባቸውና ግራ የተጋቡትን አስተያየት ሰጪ በስማችን መጠቀማቸው ለማደናገር የዘየዱት ዘዴ መሆኑን አንባቢያን እንዲረዱልን ስንጠይቅ፣ የክልላችንና የአገራችን እግር ኳስ ማሳደግ የሚቻለው በተሰጠን ኮርስ ዕውቀት ተጠቅመን ሕፃናትን እያሠለጠንን ስናሳድግ፣ በየተሰማራንበት የእግር ኳስ ተግባር ተግተን ስንሠራ፣ የወሬ ሳይሆን የተግባር አሠልጣኞች ስንሆን ብቻ ስለሆነ፣ ቀጥል ወደ ሥራ ቀጥል ወደ ተግባር የሚል መርህ ይኑረን፡፡ እኛም እንድንሠራ የሙያ ሥነ ምግባሩ ስለሚያስገድደነና የዜግነት ኃላፊነት ስላለብን፣ የተሰጠንን ኮርስ ወደ ተግባር እንደምንለውጠው በመግለጽ ነው፡፡ ለመሥራት ስንተችም ስብዕናና ሀቅ ይኑረን፡፡ ገንቢ ትችት ለዕድገት ጠቃሚ ነውና፡፡

(የኮርሱ ተሳታፊዎች፣ ከመቐለ)

********

የሐዋሳ ከተማ ግድፈቶች

አንድ ከተማ አደገ ወይም ተሻሻለ የሚባለው ለነዋሪው ሕዝብ ምቹና የተሟሉ መሠረተ ልማቶች ሲኖሩ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ መንገድና መናፈሻ ቦታዎች (አረንጓዴ ቦታዎች) ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ስለሆነም የዛሬ አስተያየቴ የሐዋሳ ከተማ የመንገዶች አቀያየስ ላይ ስለሚታዩ የማስተር ፕላን አተገባበር ግድፈቶች ላይ ይሆናል፡፡

ከዚህ አንፃር የሐዋሳ ከተማ ምንም እንኳን በወረቀት ላይ ያተኮረ የተቀመጠው የከተማዋ ማስተር ፕላን ከበርካታ የኢትዮጵያ ከተሞች የተሻለችና ዘመናዊ ከተማ የሚያደርጋት ቢሆንም፣ የማስተር ፕላኑ አተገባበር ላይ ግን በርካታ ግድፈቶች እየታዩ በመሆኑ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከተማዋ እንደ አዲስ አበባ ወደ መልሶ መገንባት (አፍርሶ መገንባት) ሥራ ውስጥ ሊያስገባት እንደሚችል በግልጽ የሚያሳዩ ጉድለቶችን መመልከቱ አስፈላጊ ነው፡፡

በዚህ መሠረት በከተማዋ ውስጥ በርካታ አካባቢዎች የንግድ ድርጅቶች ማለትም ካፍቴሪያዎች፣ ሱፐር ማርኬቶችና መደብሮች ከሕጋዊ ይዞታቸው ውጭ ከአሥርና አሥራ አምስት ሜትር በላይ ወደፊት እስከ እግረኛ መንገድ ተስፋፍተው ቦታ ይዘው ይገኛሉ፡፡

ለምሳሌ መጥቀስ ካስፈለገም ካፌ አሊያንስ ሕንፃ ሥር የሚገኘው የሚገኙት ቤቶች ከሚጠቀሱ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እንዲሁም በከተማዋ አንዳንድ ካፌዎች ለተሽከርካሪ ማቆሚያነት በተዘጋጀ ሥፍራ ላይ ተከፍተዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በማስተር ፕላኑ መሠረት ለተሽከርካሪዎች ፓርኪንግ የተተወ ክፍት ቦታ ሁሉ በንግድ ድርጀቶች ሕገወጥ መስፋፋት ሳቢያ እየተያዘ፣ ከቀጠለ የከተማዋን ገጽታ ያበላሸዋል፡፡ ከዚህም አልፎ አሁን እየታየ ባለው ሁኔታ ተሽከርካሪዎች የፓርኪንግ ቦታ በማጣት ዋናውን መንገድ ለፓርኪንግ መጠቀም በመጀመራቸው የከተማዋ ጎዳናዎች መጣበብ ጀምረዋል፡፡ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ከአምስትና ስድስት ዓመታት በኋላ የሐዋሳ ከተማ በመንገዶች መጣበብ የተነሳ የተጨናነቀችና ለነዋሪው የማትመች ከተማ ሊያደርጋት እንደሚችል መገመት አያስቸግርም፡፡

በዚህ ላይ ሠፈረ ሰላም ትሩፋት በሚባለው በኩል የሚያልፈው የወልደ አማኑኤል ጎዳና በማስተር ፕላኑ መሠረት ስፋቱ 42 ሜትር መሆን ሲገባው፣ የመሐንዲሶች የብቃት ችግር ሊሆንም ይችላል በሃያ አምስት ሜትር እንዲቀየስ በመደረጉ ይህ መንገድ ለእግረኛውም ሆነ ለተሽከርካሪዎች የተጨናነቀ መንገድ ሆኗል፡፡ በተለይ ትሩፋት በሚባለው መስቀለኛ መንገድ ላይ በማስተር ፕላን መሠረት አደባባይ ሊኖረው ሲገባ የትራፊክ መብራት እንዲገባለት በመደረጉ የትራፊክ መጨናነቅ አስከትሏል፡፡

ሌላው ከዚሁ ጋር የሚነሳው ከዋርካ አደባባይ በአራት አቅጣጫ ከሚወጡት መንገዶች ውስጥ ወደ መናኸሪያና ወደ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የሚወስደው መንገድ ነው፡፡ በማስተር ፕላኑ መሠረት የተቀየሰ ሲሆን፣ ወደ ዓረብ ሠፈርና ወደ ጎድጓዳ ሠፈር የሚወስዱት ሁለቱ መንገዶች ግን በማስተር ፕላኑ መሠረት ባለመቀየሳቸው በተለይ አንደኛው በሳውዝ ስታር ሆቴል በኩል የሚያልፈው የእግረኛ መንገድ እንኳ የሌለው በመሆኑ፣ መንገዱን ማስፋት ቢያስፈልግ የሆቴሉን ሕንፃ በከፊል ማፍረስ ይጠይቃል፡፡ ለመሆኑ ለሆቴሉ የግንባታ ቦታ ሲፈቀድ የመንገዱን ማስተር ፕላን እንዴት ማገናዘብ አልተቻለም?

ጉዳዩ በአጠቃላይ ሲታይ የማስተር ፕላኑን አተገባበር ግድፈቶች በሚመለከት በርካታ ማስረጃዎችን መጥቀስ የሚቻል ቢሆንም፣ ለጊዜው ከላይ የቀረበውን አስተያየት የከተማው አስተዳደርና ማዘጋጃ ቤቱ እንደገንቢ አስተያየት በመውሰድ ከፍተኛ የሀብትና የጊዜ ብክነት ወደሚያስከትል የመልሶ ግንባታ ሥራ ውስጥ እንዳያስገባ ሳይረፍድ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል እላለሁ፡፡ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርም ባለሙያዎችን በመላክ የከተማዋን የማስተር ፕላን አተገባበር ኦዲት በማድረግ ለከተማው አስተዳደር አስፈላጊውን የቴክኒክ እገዛ ቢያደርግ መልካም ይመስለኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ውስጥ ባሉ ዋና ዋና መንገዶች ዳርቻና በአደባባዮች ዙሪያ እየተሠሩ ያሉ የጀበና ቡና መነገጃ የሳር ጎጆዎች ዘመናትን ያልተላበሱና ቁጥራቸውም ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ በመሆኑ፣ የከተማዋንም ገጽታ ከማበላሸት በላይ ለእሳት አደጋም የተጋለጡ ስለሆኑ ይህ ሊታረም ይገባዋል፡፡

በመጨረሻም ይህ ከዚህ በላይ የተሰጠው አስተያየት በገንቢነቱ ተወስዶ የሐዋሳን ከተማ በንድፍ ላይ በተቀመጠውና ከተማዋን ዘመናዊ ሊያደርጋት በሚችለው ማስተር ፕላን መሠረት እንድትገነባና ለነዋሪዎቿም ሆነ ሊሚጎበኟት እንግዶች የተመቸች ከተማ እንድትሆን የሚመለከታቸው ሁሉ አፋጣኝ ዕርምጃ ሊወስዱ ይገባል እላለሁ፡፡

 (ማቴዎስ ሽመሌ፣ ከሐዋሳ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...