Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክእየተንከባለሉ የመጡት የፍርድ ቤቶች የቤት ሥራዎች

እየተንከባለሉ የመጡት የፍርድ ቤቶች የቤት ሥራዎች

ቀን:

ከሦስቱ የመንግሥት አካላት ዓመቱን ሙሉ በሙሉ አቅሙ ሳያቋርጥ የሚሠራው አስፈጻሚው አካል ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚከሰቱ ጉዳዮችን በየሴክተሩ አቅዶ የሚፈጽም በመሆኑ ዓመቱን ሙሉ እየሠራ ይቆያል፡፡ አሰፈጻሚው ለሕዝቡ የቀረበ፣ መሠረታዊ ኅብረተሰባዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት የሚሠራና የመንግሥትን የዕለት ተዕለት መርሃ ግብሮች አቅዶ የሚፈጽም ስለሆነ ዕረፍት ከወሰደ አገርም ታርፋለች፡፡ በአገራችን ዓውድ ከአስፈጻሚው በተለየ/በተቃራኒ ክረምቱን የሚያርፉት የሕግ አውጭውና የሕግ ተርጓሚው ናቸው፡፡ የሕግ አውጭው በሕገ መንግሥቱ በግልጽ በሰፈረው መልኩ በዓመቱ መጀመሪያ መስከረም የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ ሥራውን ጀምሮ ሰኔ 30 ለዕረፍት ይወጣል፤ በመካከሉም ለአንድ ወር ሊርፍ ይችላል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ‹58›ን ይመለከቷል፡፡ የዘንድሮው ምክር ቤት የሥራ ዘመኑን ስላጠናቀቀ የሚመለስ ባይሆንም በሥራ ዘመኑ ምክር ቤቱ የሚያርፈው ከመረጠው ሕዝብ ጋር በመገናኘት የሕዝቡን ችግር በቅርብ ለመረዳት፣ በምክር ቤቱ የተወሰኑትን ዐቢይ አገራዊ ጉዳዮች ሕዝቡ እንዲያውቀው ለማድረግና በምክር ቤቱ የተሰጡ የቤት ሥራዎችን አባላቱ እንዲወጡ ለማስቻል ነው፡፡ የዳኝነት አካሉ የሚያርፍበትን ጊዜ በተመለከተ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በሌላ ሕግ በግልጽ የተመለከተ ነገር ባይኖርም፣ ከሐምሌ 30 ጀምሮ ለሁለት ወራት ያህል መደበኛ ሥራውን አይሠራም፡፡ በእነዚህ ጊዜያት አዲስ መዝገብ መክፈት፣ አስቸኳይ ጉዳዮች በሚመደቡ የተወሰኑ ዳኞች ከሚመረመሩ ውጭ መደበኛ ቀጠሮዎች አይስተናገዱም፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ዳኞች የክረምት እረፍቱ ሁሉንም የሚመለከት እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ በተጨባጭ በክረምት ፍርድ ቤቶችን ለጎበኘ ግን ክረምት ዕረፍት ዕረፍት ይሸታል፡፡

ፍርድ ቤቶች በክረምቱ የሚያርፉበት ጊዜ የሕግ መሠረት ሳይሆን የልማድ መሠረት ያለው ይመስላል፡፡ ጸሐፊው በዕድሜ ከጠገቡ የሕግ ባለሙያዎች ለመረዳት እንደቻለው የፍርድ ቤቶች በክረምት ማረፍ የተጀመረው በአፄዎቹ ዘመን ነው፡፡ ዘመኑ በኃይለ ሥላሴ ዘመን ሳይሆን አልቀረም፡፡ በዚያ ጊዜ ዳኝነቱ ማዕከላዊ ነበር፡፡ ነገሥታቱና ሹማምንቱ ዳኝነት የሚሰጡት ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ረዥም መንገድ አቋርጠው ለሚመጡ ዜጎች ነበር፡፡ ፍትሕና ፍርድ ቤት በአብዛኛው በዋና ከተማዎች የሚሰጥ ሲሆን፣ እንዳሁን ትራንስፖርት ባለመኖሩ ሕዝቡም በእግሩ፣ በበቅሎና በፈረስ ሙግት ለማቅረብ ወደ ከተማ ይመጣ ነበር፡፡ እናም ይህ ለሙግት ወደ ከተማ የመምጣት ጉዞ በክረምት ውኃ ስለሚሞላ፣ ተራራው ስለሚናድ፣ መንገዱም ስለማይመች የዳኝነት ሥርዓቱ እንዲቋረጥ ተደርጎ ክረምቱ ሲጠናቀቅ እንደሚቀጥል ይናገራሉ፡፡ ይህ በአፈ ታሪክ የሚነገር ጸሐፊው በተጻፈ ዋቢ ጽሑፍ ያላገኘው ነው፡፡ ስለዚህ ክረምት ያለመሥራት የፍርድ ቤቶች ልማድ በንጉሳውያኑ የተጀመረና ከክረምቱ መግባት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የአሁኑን ትክክለኛ ምክንያት ለማግኘት ባያስቸግርም ይሄው ልማድ በመቀጠሉ መሆኑን መናገር አሳማኝ ነው፡፡ አንዳንዶች ዳኞች ዕረፍት ጊዜያቸውን የሚጠቀሙበት ወቅት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ የአሁኑ ዘመን ከአፄዎቹ ዘመን ይለያል፡፡ አሁን ፍርድ ቤቶች በየአካባቢው ተሠርተዋል፣ ዳኞች በስፋት ተሹመዋል፣ መንገድና ሌሎች መሠረተ ልማቶችም በመሠራታቸው ክረምቱ የዳኝነቱን ሥራ አያስተጓጉለውም፡፡ በዚህ ዘመን ያሉት የመዛግብት ብዛት እንኳን ታርፎ ሳይታረፍም በጊዜው የሚስተናገዱ አልሆነም፡፡ ዳኞች ማረፍ አይኖርባቸውም ወይ ከተባለም እንደ አስፈጻሚው አካል ሁሉ ግለሰባዊ የዓመት ዕረፍትን ማመቻቸት ይቻላል እንጂ ተቋማዊ ዕረፍት መፍትሔ መሆኑ በአግባቡ ሊፈተሽ ይገባል፡፡ የንግድ ግብይት ባልቆመበት፣ ከሕዝቡ ጋር በዕለት ተዕለት ጉዳይ የሚገናኘው አስፈጻሚው በሚሠራበት የክረምት ወቅት ፍርድ ቤቶች በራቸውን መዝጋታቸው ፍትኃዊ አይመስልም፡፡

የጽሑፋችን ማጠንጠኛ የፍርድ ቤቶቹ የቤት ሥራ ላይ እንጂ ተቋማዊ ዕረፍቱ ላይ ባለመሆኑ በዓመቱ ፍርድ ቤቶች ሲያስችሉ ከታዘብናቸው ጉዳዮች በመነሳት የፍርድ ቤቶች አመራርና ሠራተኞች በክረምቱ ሊሠሯቸው የሚገቡ አንዳንድ ነጥቦችን ለማንሳት እንሞክር፡፡ እነዚህ ነጥቦች ከተለያዩ የሕግ ባለሙያዎች የተወሰዱና ግላዊ ምልከታዎች እንጂ የምርምር ጥናት አካል ባለመሆናቸው የሚመለከተው አካል በፍርድ ቤቶች ላይ የሕዝቡን አመለካከት ለመቃኛ መነሻ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ይታመናል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የፍትሕ መዘግየት ጉዳይ

የዘገየ ፍትሕ እንደተነፈገ ይቆጠራል የሚለው ብሒልን ለማስቀረት ፍርድ ቤቶቻችን ብዙ ጥረት ቢያደርጉም የተሳካላቸው አይመስልም፡፡ የፍርድ ቤቶች የማሻሻያ መርሃ ግብር መነሻም አንዱ ይሄው ነበር፡፡ ፍትሕ የሚዘገየው ከዳኞች ቁጥር ማነስ፣ መዛግብትና የዳኞች ቁጥር አለመመጣጠን፣ የችሎታ ማነስ፣ የልዩ ችሎቶች አለመቋቋም፣ የመዛግብት አስተዳደር ችግር ወዘተ. እንደሆነ በግልጽ ታውቆ መፍትሔ መወሰድ ከጀመረ ቢቆይም፣ የተጠበቀውን ያህል ለውጡን ማምጣት አልተቻለም፡፡ ብዙ ዳኞች ተሹመዋል፣ መዛግብት በሰዓት መቅጠር ተጀምሯል፣ ልዩ ችሎቶች (የፍቺ፣ የሕፃናት፣ የፀረ ሙስና፣ የፀረ ሽብርተኝነት፣ የእጅ ከፍንጅ፣ የንግድ፣ የጉዲፈቻ፣ የውል ወዘተ. ችሎቶች) ተቋቁመዋል፡፡ ተስፋፍተዋል፡፡ ተከታታይ ሥልጠናዎችም ተሰጥተዋል፡፡ ግን መዛግብት አሁንም ያለምርመራ ይቀጠራሉ፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ሳይቀር የዘንድሮን ቀጠሮዎች እስከ ጥር 2008 ዓ.ም. ድረስ ቀጥሯል፣ የቼክ ጉዳይ ከዓመት በላይ ይራዘማል፣ ዳኞች ሥልጠና ላይ ናቸው እየተባለ ቀጠሮዎች በማስታወቂያ በተከታታይ ተላልፈዋል፡፡ አንዳንድ ጠበቃዎች ስለ ሥልጠናው ጉዳይ ሲገልጹ ‹‹ሌላ ጊዜ ክረምት ላይ ይሰጥ የነበረው ሥልጠና ዘንድሮ በበጋው ወቅት ሲሰጥ በመቆየቱ ዳኞች ችሎታቸውን ትተው ለሥልጠና መትጋታቸው አልቀረም፡፡›› በሥልጠና ወቅት ዳኞች ሲቀሩ መዛግብት በማስታወቂያ ይቀጠራሉ፤ ካልሆነም ሌሎች ዳኞች ቀጠሮ የሚለውጡ ይሆናል፡፡ ሁለቱም አሠራር ዳኞች የራሳቸውን ጉዳይ እንዳይመረምሩ፣ በቀጠሮ ላይ ቀጠሮ እንዲደረብና ፍትሕ እንዲዘገይ ማድረጉን አንዳንዶች ይገልጻሉ፡፡ ሥልጠናዎች ስለመጡ ብቻ የሚሰጡ ከሆነ የፍትሕ መዘግየቱ የሚቀጥል በመሆኑ፣ የፍርድ ቤቶች አስተዳደር ሥልጠናው በዳኞች የዕረፍት ወቅት ተቀናጅቶ እንዲሰጥ ከሚመለከተው ክፍል ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አቶ መንበረ ፀሐይ ታደሰ ጉዳዮችን ለመወሰን ረዥም ጊዜ ከወሰደና የሚወስነው ውሳኔም ፍጥነት የሌለው ከሆነ ዜጎች የኢኮኖሚ ግንኙነትን ለመፍጠር አይፈልጉም፣ አገሪቱም ኢንቨስትመንትን ለመሳብ አትችልም፣ የአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴም እንዳይጠናከር መሰናከል ይሆናል ይላሉ፡፡ አቶ መንበረ ፀሐይ ፍትሕ መዘግየት ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል እንደሚጎዳ ሲገልጹ ‹‹ንግድ ይስተጓጐላል፣ ወንጀል ሊበረከት ይችላል፣ በኅብረተሰብ ውስጥ የሚኖር ግንኙነት ሊሻክር ይችላል፣ ይህ ሁኔታ በቤተሰብ ውስጥ ሳይቀር ይንፀባረቃል፡፡ የተቀላጠፈ የፍርድ ሒደት ካልኖረ በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጠር ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት አግኝቶ ሰዎች መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ ማድረግ አይቻልም፤›› ይላሉ፡፡

አቶ ዮሴፍ አዕምሮም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጆርናል ላይ ባሳተሙት ጽሑፍ የፍትሕ መዘግየት መነሻው የተለያየ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ጸሐፊው ካነሷቸው ምክንያቶች ውስጥ የጉዳዩ ብዛትና የዳኞች ቁጥር አለመመጣጠን፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያወጣውን የቀጠሮ ፖሊሲ አለመቆጣጠሩ፣ ዳኞች የሚያስፈልጓቸው ቁሶች (ለምሳሌ የድምፅ መቅረጫ) አለመሟላት፣ የአቅም ማነስ፣ ተገቢ ያልሆኑ የጠበቆች ጉዳይ የማዘግያ ዘዴዎች መብዛት እንደሆነ ይጠቀሳሉ፡፡ የፍትሕ መዘግየት ምክንያቶች በየዐውዱ የሚነሱና ፍርድ ቤትን ጨምሮ ለባለድርሻ አካላት የተገለጡ ከሆነ ፍርድ ቤቱ ፍትሕ እንዳይዘገይ የሚያስችሉ ጠንካራ የቁጥጥር ዘዴዎችን ለመጪው ዓመት ካልተገበረ ‹‹የዘገየ ፍትሕ እንደተነፈገ ይቆጠራል›› የሚለው መርህ የመድረክ ማድመቂያ ብቻ ይሆናል፡፡

የውሳኔዎች የጥራት ጉድለት

የጠንካራ የፍትሕ አስተዳደር መገለጫ ጉዳዮችን በተቀላጠፈ ሁኔታ ማስተናገድ ብቻ ሳይሆን ዳኞች ተገቢውን ሒደት አልፈውም የሚሰጡት ፍርድ ሕጉን በአግባቡ የተከተለ፣ ማስረጃዎችን በምልዓትና በጥንቃቄ የመረመረ፣ አሳማኝና ወጥነት ያለው ፍርድ የሚሰጥበት ሲሆን ነው፡፡ ውሳኔዎች ጥራት ከጎደላቸው ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቢወጡ እንኳን የይግባኝ ፍርድ ቤቶችን ማጨናነቃቸው አይቀርም፡፡ ጸሐፊው ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ፍርድ ቤቶች ዳኞችን በብዛት እየሾሙ ቢሆንም፣ ዳኝነት የመሾሚያው መንገድ በፈተናና በውድድርም ቢሆንም የውሳኔዎችን ጥራት ማምጣት እንዳልተቻለ ያምናሉ፡፡ በሕግ ዕውቀታቸው የተመሰከረላቸው፣ ሁልጊዜ የሚያነቡና የሚማሩ፣ በጥንቃቄ ውሳኔ የሚሰጡ ዳኞች ያሉትን ያህል ተገቢውን ጭብጥ የማይመሠርቱ፣ የፍሬ ነገር፣ የማስረጃና የሕግ ትንተናን የማይሠሩ፣ ተገቢ የሆነውን የሕግና የሰበር አስገዳጅ የሕግ ትርጉምን የማይከተሉ መኖራቸውን አንዳንዶች ይናገራሉ፡፡ አቶ ዮሴፍ አዕምሮ ባሳተሙት ጽሑፍ የፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች ተመሳሳይ ፍሬ ነገርና ሁኔታን ይዘው በቀረቡ ጉዳዮች ላይ ወጥና ተገማች መሆን ቢጠበቅባቸውም፣ በተግባር ግን ከብቃት ማነስና ተገቢ ባልሆነ ግንኙነት መነሻነት ውሳኔዎች እንደሚወስኑ ዋቢ ያደረጉዋቸውን የሕግ ባለሙያዎች በመጥቀስ ይናገራሉ፡፡ ዳኞች የሚወስኗቸው ውሳኔዎች ጠበቆች በፍርድ ቤት ችሎት ሲጠብቁ በጎና መጥፎ ጎናቸውን በዝርዝር እንደሚመረምሩ ባወቁ ኖሮ እንዴት ጠንከር ያለ ጥንቃቄ በወሰዱ ነበር፡፡ ውሳኔ እንደማንኛውም የመንግሥት ሰነድ የሕዝብ ሰነድ በመሆኑ ጥንቃቄ ተደርጎበት ካልተሠራ የባለሙያን ሙያ መመስከሩ አይቀርም፡፡ የጥራት ጉድለቱ በሥር ፍርድ ቤቶች ብቻ ሳይሆን በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶችና በሰበር ሰሚ ችሎት ላይም አልፎ አልፎ የሚንፀባረቅ መሆኑን ከአንዳንድ ውሳኔዎች እርስ በእርስ መጣረስና ወጥ አለመሆን መረዳት ይቻላል፡፡ ጸሐፊው የዳኞች የውሳኔ ጥራት መጓደል ባለሙያዎቹን ከሚያሠለጥኑ ትምህርት ቤቶች የመነጨ ሊሆን እንደሚችል ያምናል፡፡ ትምህርት ቤቶቹ የጥራት ችግር እንዳለባቸው በአደባባይ ሲተች የምንሰማው ጉዳይ ነው፡፡ የሕግ ትምህርት ቤቶቹ የሚሰጡት ትምህርት ዳኛ የሚሆኑትን ባለሙያዎች የሕግ ዕውቀትና የዳኝነት ክህሎት ብቁ የሚያደርግ መሆኑን በድፍረት መናገር ያስቸግራል፡፡ የማሠልጠኛዎቹ ጅማሬም ጥሩ ቢሆንም የተወሰኑ ውስንነቶች አለባቸው፡፡ ፍርድ ቤቶች በዳኞች የሚሰጡትን ውሳኔዎች ይዘት በመመርመር፤ ያለባቸውን ክፍተት በመለየት ዳኞች የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንዲያገኙና በዝርዝር የውሳኔ አሰጣጥ መመርያ እንዲመሩ ካላደረጉ ክረምቱም ካለፈ በኋላ ለውጥ ለማየታችን ዋስትና አይኖረንም፡፡

 

የዳኞች የሥነ ምግባር ጥያቄዎች

ዳኞች እንደማንኛውም የመንግሥት ሹም ከሕግ ውጭ ከሠሩ ወይም የአፈጻጸም ጉድለት ካሳዩ በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የሕግ አተረጓጎም ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ ከሕግ ውጭ በዘፈቀደ የሚሠራ ዳኛ በሥነ ምግባር ሊጠየቅ እንደሚገባ የሕግ መሠረት ተጥሏል፡፡ በአገራችን ሕገ መንግሥቱና የዳኞች የሥነ ምግባር ደንብ የዳኞችን የሥነ ምግባር ሁኔታ በግልጽ በመደንገግ የዳኞችን ተጠያቂነት ዋስትና ሰጥተዋል፡፡ የዳኝነት አካሉ በሙስና መበራከት ከሚጠቀሱት ተቋማት አንዱ መሆኑ በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ መረጃዎች ከማሳየታቸውም በላይ በኅብረተሰቡ የታመነ ሃቅ እየሆነ ነው፡፡ ጸሐፊው በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው አመለካከት ሙሉ በሙሉ ፍርድ ቤቶችን የሚገልጽ ባይሆንም፣ ሙስና እንደ አስፈጻሚው ሁሉ የዳኝነት አካሉም ችግር መሆኑን ይቀበላል፡፡ በ1997 ዓ.ም. የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር ባስጠናው አጠቃላይ የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም ጥናት መሠረት የኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ካሉበት ዋና ዋና ችግሮች ውስጥ አንዱ የፍትሕ አስተዳደሩ ሙስና፣ በሥልጣን አላግባብ መገልገልና ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት መሆኑ በግልጽ ተመልክቷል፡፡ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ባስጠናው ጥናት የኅብረተሰቡን አመኔታ ካጡ አምስት የመንግሥት ተቋማት መካከል አንዱ ፍርድ ቤቶች ናቸው በሚል መዘገቡንም እናስታውሳለን፡፡ ፀረ ሙስና ያጠናው ጥናት የተሠራው የ6,500 ሰዎችን አስተያየት መሠረት አድርጎ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቶች በኅብረተሰቡ አመኔታ ካጡ ተቋማት ተርታ መፈረጃቸው የሙስናና የሥነ ምግባር ብልሽት ለመኖሩ አመላካች ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ፍርድ ቤቶች ከሙስና የፀዱ መሆናቸውን ደፍሮ የሚናገር የለም፡፡ እንዲያውም በቅርቡ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት የሥነ ምግባር ችግር በዳኞች እንደሚታይ በመግለጽ ችግሩን ለመቅረፍ ከኅብረተሰቡ ጋር እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አሁንም ክረምቱን የሚሻገር የፍርድ ቤቶች ትልቁ ፈተና ሙስናን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን የዳኞችን ሥነ ምግባር ካላሻሻሉ፣ የሚወሰዱ የሥነ ምግባር ዕርምጃዎችን ካልገለጹ ችግሩ ሊቀረፍ አይችልም፡፡ እንደሚታወቀው ሙስና በገሃድ የማይፈጸም በምስጢርና በኔትዎርክ የሚፈጸም በመሆኑ ከመንግሥት ሰፊ ሥራ ይጠበቃል፡፡

በመጪው ዓመት ምን እንጠብቅ?

የዳኝነት አካሉ ከተወሰኑ ዓመታት ጀምሮ በለውጥ ላይ ቢሆንም ጉዳዮች በቅልጥፍና እንዲያልቁ፣ የውሳኔ ጥረት እንዲኖርና የዳኞች ሥነ ምግባር እንዲስተካከል የተደረጉ ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ተሳክተዋል ማለት አይቻልም፡፡ ዘንድሮ በየችሎቶቹ የቀረበ ባለጉዳይ፣ ጠበቃ፣ ነገረ ፈጅ ወዘተ. ሊመሰክር እንደሚችለው ፍርድ ቤቶች ጉዳዮች በቅልጥፍና የሚስተናገዱባቸው ተቋማት አልሆኑም፡፡ ዳኞች መዛግብትን ለምርመራ በማለት በተደጋጋሚ መቅጠር፣ በማስታወቂያ ቀጠሮ መለወጥ፣ ያለምክንያት ቀጠሮ መለወጥ ያለማንም ጠያቂነት ተንሰራፍቶ ያለ አስመስሎታል፡፡ የውሳኔ ጥራትም ቢሆን ከቀድሞዎቹም የቀነሰበት ሁኔታ አልፎ አልፎ ይስተዋላል፡፡ በሰበር ችሎት ፍርዶች ላይ የሚሰጡ ትችቶች፣ በየጋዜጦችና ጆርናሎች ላይ የሚጻፉ ትንተናዎች ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ የሥነ ምግባር ጥያቄዎች የሚነሱም አይመስልም፡፡ ያጠፉ ዳኛ ስለመኖሩ፣ ስለመገሰጹ፣ ወይም በማስጠንቀቂያ ስለመታለፉም ሆነ ጠንካራ ዕርምጃ የተወሰደበት ስለመኖሩ ዜና ከሰማን ከረምረም ብለናል፡፡ ቀጣዮቹ ጊዜያት እንዳለፉት እንዳይሆኑ የሕዝብን አመለካከት ለመለወጥ የሚያስችሉ ሥራዎች ከፍርድ ቤቶቻችን እንጠብቃለን፡፡ ፍርድ ቤቶች ለጉዳዮች መጠናቀቂያ ጊዜ ያስቀመጡዋቸው መመርያዎች ከወረቀት ባለፈ እንዲተገበሩ ግልጽ አቅጣጫ ሊያስቀምጡ ይገባል፡፡ 3 ሰዓት የተቀጠረ ባለጉዳይ 7 ሰዓት ሊጠራ አይገባም፤ ጊዜውንና ገንዘቡን ልንቆጥብለት ይገባል፡፡ ፍርድ ቤቶች የሰጡዋቸውን ውሳኔዎች በዝርዝርና በምልዓት በማጥናት የጥራት ችግሩ ምንጭ ሊለይ ይገባል፡፡ የአጻጻፍ፣ የይዘት፣ የትንታኔ፣ የዕውቀት፣ የሥራ ብዛት፣ የክህሎት ወዘተ. ችግር መኖሩ በጥናት ከተረጋገጠ ችግሮችን በየመልካቸው ለይቶ ተፈጻሚ የሚሆኑ መፍትሔዎች ማስቀመጥ ይገባል፡፡ የተወሰኑትን ማስተማር፣ የተወሰኑትን ማሠልጠን፣ የተወሰኑትን (በተለይ የዳኝነት ፀጋው የሌላቸውን) ማግለል መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ ከሁሉ በላይ የመንግሥትን ቁርጠኝነት የሚፈልገው ግን የዳኞችን ሥነ ምግባር የመቆጣጠር ሥራ ነው፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽንና መሰል ተቋማት የሚያወጡት ሪፖርት የፍርድ ቤቶች የሙስና ደረጃ ከፍተኛ፣ የሕዝቡም አመኔታ ዝቅተኛ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ችግር የመጣው ደግሞ በዳኞችና በድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች የሥነ ምግባር ጉድለት በመሆኑ ዝርዝር መመርያ በማውጣት፣ የቁጥጥር ኔትወርክ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር በመዘርጋትና የተወሰዱ ዕርምጃዎችን ለሕዝቡ በማሳወቅ መንግሥት የሕዝቡን መተማመን ሊመልስ ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

                              

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...