Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየፕሬስ ነፃነት መከበር ያለበት ማንም እውነትን መፍራት ስለሌለበት ነው

የፕሬስ ነፃነት መከበር ያለበት ማንም እውነትን መፍራት ስለሌለበት ነው

ቀን:

በእስመለዓለም ቢተው

የሐሳብ ነፃነትና የመሰለንን አቋም ማራመድ የሰው ልጆች ሁሉ ያልተገደበ መብት በመሆኑ፣ ዓለም የጋራ ዕውቅና ከሰጠው ቢያንስ ከስድስት አሥርት ዓመታት (እ.ኤ.አ. በ1948 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች አንቀጽ 19 ጀምሮ) ሆኖታል፡፡ በዴሞክራሲዊና በሰብዓዊ መብቶች ልዕልና በተጎናፀፉት ምዕራባዊያን ዘንድ ግን መቶዎች ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

ወደ እኛ አገር ስንመጣ የሐሳብ ነፃነትን ብሎም የመናገር፣ የመጻፍ፣ ሐሳብን ተደራጅቶ የመግለጽ ዓይነት ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር ከፍተኛ ውጣ ውረድ ታልፏል፡፡ የሌላው ዓለም ሕዝብ ያገኘውን የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት እንጎናፀፍ፣ የብሔር እኩልነትና የጋራ ተጠቃሚነት ይከበር፣ ወዘተ ብለው የታገሉና ደማቸው በየሜዳው የፈሰሱ ብዙ ናቸው፡፡ አጥንታቸው ተከስክሶ ለአካል መጉደል የተዳረጉትም ቁጥራቸው በርካታ ነው፡፡ ከዚያም አልፈው የሌሎች መስዋዕነት ያስገኘውን ፍሬ ጭላንጭል ማየት የቻሉ የቀደመው ትውልድ አባላትም አሉ፡፡

የዜጎች ሐሳብን የመግለጽ (የፕሬስ ነፃነት) ነጥለን ስንመለከት በመጻፍና በመናገር ብቻ ሳይሆን፣ “በማሰቡ” የተቀጣ ትውልድ ያለፈባትን አገራችንን እንደ በዓሉ ግርማና አቤ ጉበኛ ያሉ የብዕር ፈርጦችን ደም ገብራለች፡፡ ለእስርና ለእንግልት የተዳረጉትም ብዙ ናቸው፡፡

ያ ሁሉ አልፎ በ1983 ዓ.ም. የሥርዓት ለውጥ ሲካሄድና ከዚያም በ1987 ዓ.ም. የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ሲፀድቅ የፕሬስ ነፃነትም ሆነ የዜጎች ሐሳብን የመግለጽ መብት መረጋገጡ ተበስሯል፡፡ በእርግጥም ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ በአገራችን የንባብ ገበያ ተወዳድረው ይፈለጉም ይውደቁም፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጣና መጽሔቶች ታይተዋል፡፡ በሙያው በጥልቀት ይሠልጥኑም አይሠልጥኑም ያንኑ ያህል ጋዜጠኞችም ታይተዋል፡፡

ከሃያ አራት ዓመታት በኋላ ግን ፕሬሱ ወደኋላ ተንሸራቷል፡፡ ዛሬ በመቶ ሺዎች ኮፒ ሊታተምባት በሚገባ አገር ውስጥ ከአሥር ሺሕ ኮፒ እምብዛም የማያልፉ ጋዜጦችና መጽሔቶችን ማግኘት አይቻልም፡፡ ከነችግራቸው ከፍተኛ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ብሎም ማኅበራዊና ባህላዊ ጉዳዮችን አንባቢያንን (አብዛኛው የጋዜጣ አንባቢ ልሂቁ መሆኑን ልብ ይሏል) የሚቀሰቅሱ የኅትመት ውጤቶች ድራሻቸው ጠፍቷል፡፡ ያሉት የግል የኅትመት መገናኛ ብዙኃንም ቢሆኑ በጣት የሚቆጠሩ ከመሆናቸው በላይ፣ ተጠናክረው መውጣት ላይ ፈተናው ከብዷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጋዜጠኞች ሲታሰሩ፣ ሲሰደዱና ሥራቸውን እርግፍ አድርገው ሲተው በሌላው ላይ መሸማቀቅ ተፈጥሯል፡፡

በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የተደራጁት ዕድሜ ጠገብ ጋዜጦች ዕድገትና ጥንካሬ ላይ የምናየው ጅምር እንኳን የለውም፡፡ እንዲያውም የጎላ የአመራር ችግር ያለባቸው፣ ሙያተኛው በገፍ የሚለቅባቸው፣ በራሳቸው ገቢ የማይተዳደሩ፣ ከመንግሥት ምንዳ ጠባቂነት ያልውጡ ናቸው፡፡ በዚህና ተያያዥ ምክንያቶችም የሕዝቡን እሮሮና ፍላጎት ከማዳመጥ ይልቅ የጎደለውን በመላምት እየሞሉ መንግሥትን ከሠራው በላይ የሚያሞግሱ ናቸው፡፡ ሙያተኛውም በብዛት ለመኖር የሚሠራ እንጂ መርምሮና ፈልፍሎ ለውጥ ለማሳየት የሚነሳ መሆን አልቻለም፡፡

በኤሌክትሮኒክ መገናኛ ብዙኃን መስክ ያለው እውነታም ፀሐይ የሞቀው ነው፡፡ በአንድ በኩል መንግሥት የአየር ሞገድና ቻናሎችን ከማከራየት ባለፈ ለግሉ ዘርፍ ሊለቀው ያልደፈረው “ከባድ” መስክ አድርጎታል፡፡ በሌላ በኩል ያሉት የግልም ሆኑ የመንግሥት ሬዲዮና ቴሌቪዥኖች ነፃነት የሚሰማቸው ስፖርት፣ መዝናኛና ሙዚቃ ላይ ብቻ ነው፡፡ የማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መድረኮችን ለማዘጋጀትና ለማከራከር ገና አንደበታቸው ሊከፈትም አልቻለም፡፡ ጉዳዬ ብለው በተጠቀሱት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ዘገባ ቢሠሩም ለሚዛናዊነት፣ ሀቀኝነት፣ ነፃ ሐሳብና አሳታፊነት የሚሰጡት ዋጋ ዝቅተኛ ነው፡፡

“የልማት ጋዜጠኝነት” ጎብጦ እየበቀለ በመሆኑ ከላይ (ከመንግሥት ኃላፊዎች) ወደ ሕዝቡ የሚንቆረቆር፣ ከታች ያለውን ሀቅ የሚያሳይ የመገናኛ ብዙኃን አዘጋገብ ተንሰራፍቷል፡፡ የሐሳብ አማራጮች ያለማስተናገድ፣ ከመንግሥት ወገን ያለውን ብቻ ማንበልበል የቀን ከሌት ሥራ መሆኑ ሊሸሸግ አይችልም፡፡

እንግዲህ የፕሬስ ነፃነትም ሆነ ሐሳብን የመግለጽ መብት በእንደዚህ ዓይነት ቅርቃር ውስጥ በገባበት ወቅት ነው በቅርቡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትን ተከትሎ አጀንዳው በስፋት እየተነሳ ያለው፡፡ እርሳቸው በኬንያ፣ በኢትዮጵያ (ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋርም ሆነ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ) የዜጎች ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ ያለገደብ መሳተፍና የመደራጀት መብት ሊከበር ይገባል ሲሉ በአፅንኦት ገልጸዋል፡፡ ጋዜጠኞች በነፃነት በመጻፋቸው ሊታሰሩ እንደማይገባ፣ የፕሬስ ነፃነትም በተግባር ሊረጋገጥ እንደሚገባ በውስጥም በውጭም አስታውሰዋል፡፡

ይህን ተከትሎ መንግሥትም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሰጡት ምላሽ ነው ዛሬ “ዕውን የፕሬስ ነፃነት አልተገደበምን?!” እንድል ያደረገኝ፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም “… ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙኃን እጅግ ያስፈልጉናል፡፡ የሠራናቸውን ውጤታማ ተግባራት በመግለጻቸው ብቻ ሳይሆን ድክመቶቻችንንም ቢያሳዩንም እንደምንጠቀም እናውቃለን፡፡ በእኛ ሁኔታ ግን አንዳንዶች በሽብር ድርጊትና በአፍራሽ መንገድ ተሰማርተዋል፡፡ እርግጥ ዋናው ክፍተታችን የአቅምና የልምድ ነው፡፡ ለዴሞክራሲ ባህል አዲስ እንደመሆናችን ከእናንተ የልምድ፣ የሥልጠናና የአሠራር ድጋፍ እንዲደረግ እንሻለን…” የሚል (ቃል በቃል የተወሰደ አይደለም) ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

“ዴሞክራሲያችን ለጋ በመሆኑ” ትችትን አንቀበልም?

በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ጥንት በሥልጣን ላይ የነበሩ ገዥዎችና ፀረ ዴሞክራሲያዊ የሕዝብ “መሪዎች” ከንቱ ሙገሳ፣ የአዝማሪና የተራ ፕሮፓጋንዳን ውዳሴን እንጂ ነቀፌታና ቅሬታንም ሆነ ገንቢ ሒስን መስማት አይሹም ነበር፡፡ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌላው ዓለም በቀጥተኛና በግልጽ ጸሐፊዎች፣ ደራሲዎችና ፈላስፋዎች ላይ ያረፈውን በትር ማስታወስ አባባሉን ያሳያል፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ላይ ኤዞፕን የመሰለ ጥንታዊ የግሪክ ጠቢብ ዴልፎስ በባለሥልጣናት ከኮረብታ ተጥሎ እንዲገደል የተደረገው በግልጽ ትችቱ ነበር፡፡ በ399 ዓመተ ዓለም ሰቅራጦስ መርዝ ጠጥቶ እንዲሞት የተበየነበትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ስቴዶስ የተባለ የግሪክ ባለቅኔ በምፀታዊ ግጥሞቹ ምክንያት ባህር ውስጥ ተጥሏል፡፡

ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ባለመኖሩ ምክንያት በኋለኛው ዘመንም እነ ቨርጅን ዳንቴ፣ ቤከን ሲዛሮ፣ ሚካኤል አንጀሎና ሌሎችም ዕውቅ የዓለም የጥበብ ሰዎች ብዙ ስቃይ አይተዋል፡፡ ዕውቁ ዊልያም ሸክስፔር በ”ንጉሥ ሊር”፣ “የቬኑሱ ነጋዴ” እና “ዳግማዊ ሪቻርድ” የመሳሰሉት ተውኔቶቹ ወድመዋል፡፡ እርሱም በእስር ተንገላቷል፡፡

እነዚህን የእኛ አገር ያልሆኑ ያውም የቀደሙ ታሪኮችን ያነሳሁት በሌሎች አገሮች ላይ የተከሰቱ የአፈና ክስተቶችም ቢሆኑ እኛንም ሊያስተምሩን እንደሚችሉ ለመጠቆም ነው፡፡ አገራችን ለ24 ዓመታት ገደማ በዴሞክራሲ እየተለማመደች በአጭር ጊዜ ውስጥ ታድጋለች እንጂ እንደ አሜሪካ፣ ስፔንና እንግሊዝ ሁለት መቶ ዓመት እንቆይ ልንል አንችልም፡፡ ይልቁንም ከሌላውም ከራሳችንም በመማር ገንቢ ትችቶችንና ችግሮችን ከነመፍትሔ የሚያሳዩ ሒሶችን የሚቀበል ትከሻ ልንፈጥር ግድ ይለናል፡፡

ከሁሉም በላይ ዜጎች ሐሳብን የመግለጽም ሆነ የመደመጥ መብት እንዳላቸው ተገንዝቦ እዝነ ህሊናን መክፈት የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ ተቃዋሚ ድርጅቶችም ሆኑ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ኢትዮጵያውያን እንደመሆናቸው በአገራቸው ጉዳይ እንደሚያገባቸው ዘንግቶ ችላ ማለትም አገሪቱን ወደኋላ የሚመልስ ነው፡፡ ዜጎች ለተጨነቁበት ጉዳይ ተገቢ ምላሽና መረጃ መስጠት እንጂ፣ “ለምን ተነፈስክ?” የሚል አካሄድ ከተጀመረ በዚህ ሥርዓት መቶ ዓመትም ቢቆይ ዕርምጃው ስለመለወጡ ዋስትና የለም፡፡

ጠቅላይ ኃይለ ማርያም ለፕሬዚዳንት ኦባማ “ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙኃን እጅጉን ያስፈልጉናል…” ሲሉ ከልብ መሆኑን በተግባር ማሳየት አለባቸው፡፡ አሁን በአንዳንዶቹ ሙያተኞች የሚታየው ከሚዛናዊነት የወጣና ኃላፊነት የጎደለው የጀብደኝነት አጻጻፍ (መንግሥት ነፃ አውጪዎች ይላቸዋል) እንዲስተካከልም መንግሥት በሩን መክፈት አለበት፡፡ በመረጃ ረገድ በየቦታው የተዘጉ የመረጃ ቋቶች፣ የኮሙዩኔኬሽን ሙያተኞችና የሥራ ኃላፊዎች ነፃ ሆነው ለሕዝብ መረጃ የመስጠት ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ጠንካራ መገናኛ ብዙኃን፣ ታታሪ ጸሐፊዎች (እንደ ፊልምና ሙዚቃ ያሉትም ጭምር) ሊበረታቱና ዕውቅና ሊያገኙም ይገባል፡፡

ከሁሉ በላይ የኅትመት ሚዲያውን እያኮሰሰው ያለው የማተሚያ ቤት ችግር፣ ሰው ሠራሽ የወረቀት ዋጋ ንረትና የታክስ ሥርዓቱ ሊፈተሽ የግድ ይላል፡፡ መንግሥት የፍርኃት ቆፈኑ አለቅህ ያለውን የአሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙኃን የግል ባለቤትነትም ቀስ በቀስ ሊጀምረው በተገባ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምዕራባውያንን በሥልጠናና በልምድ ደግፉን ማለታቸው ጥሩ ሆኖ፣ መንግሥትና ሙያተኛው ራሱ በጋራ ምን ያህል ተንቀሳቀሱ መባልም አለበት፡፡

ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች በልበ ሙሉነት የሚንቀሳቀሱበት፣ ከሥጋትና ከፍርኃት የሚላቀቁበት ምኅዳር መፈጠሩ ብቻ ሳይሆን ለብሔራዊ ጥቅም የሚጨነቁ በአገራዊ ጉዳይ ባለቤትነት ያላቸው ጋዜጠኞች እንዲሆኑ የማድረግ ድርሻም አለበት፡፡ ዘርፉን በሚመሩት (እንደ ኮሙዩኒኬሽን መሥሪያ ቤቶች ባሉት) አዕምሮና አሠራር ውስጥ የተፈጠረው የወዳጅ ጠላት ሙያተኛ ፍረጃ መነጽር ወድቆ ሊሰባበርም ይገባል፡፡ ሌላው ቀርቶ እንደ አገር ለሙያተኛው ሥልጠና ሲሰጥና አዲስ ፖሊሲ ሲወጣ መነጣጠሉ ካልቀረ የፕሬስ ነፃነት የሚባል እሴት ሊያንሰራራ አይችልም፡፡ “ከጭንጫ መሬት ላይ ማኛ እንደማፈስ” ይቆጠራል፡፡

በድምሩ ዴሞክራሲያችን ለጋ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ከደረሱበት የግንዛቤ ደረጃና ታሪካቸው፣ እንዲሁም ዓለም ከተጎናፀፈው ተራማጅ አስተሳሰብ አንፃር የፕሬስ ነፃነትን ያለ እንከን ማክበር ተገቢ ነው፡፡ ዜጎች በሐሳባቸው ሊታሰሩም ሆነ ሊወነጀሉም አይገባም፡፡ ቢያጠፉ እንኳ በሆደ ሰፊነት ሊገሩና ሊስተካከሉ ይገባል እንጂ፡፡

የምንኮራበት ሕግስ አለን? ለምን እንሸራርፋለን?

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት በያዛቸው የሰብዓዊ ዴሞክራሲ እሴቶች (Values) ዴሞክራሲያዊ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ከብዙዎቹ ሥልጡን አገሮች የተወሰዱና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ያከበሩ ድንጋጌዎችንም ይዟል፡፡ የአንቀጽ 29ም ሆነ ሌሎች የሰብዓዊ መብት አንቀጾች ችግር የለባቸውም፡፡ እንደ ብዙዎቹ የአገራችን ሕግጋት የፕሬስ ነፃነቱ ላይ የተጋረጠው ክስተት አፈጻጸም ላይ የሚታየው ድክመት ነው፡፡ እዚህ ላይ ችግሩ ከመንግሥት ወገን (አስፈጻሚው) ነው ብሎ ብቻ ማላከክ አይገባም፡፡ ከራሳቸው ከመገናኛ ብዙኃንና ከሙያተኞች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከፍርድ ቤቶችና እንዲሁም ከምሁራንና ከማኅበረሰቡ ጋር የሚያያዙ ድክመቶች ተዘርዝረው ሊለዩ ይገባል፡፡

ሕግን አስምሮ አውጠቶ ‹‹ለጌጥ›› ብቻ ይመስል ተግባር ላይ እንዳይደከም የመንግሥት ኃላፊነት ወሳኝ መሆኑን ግድ መካድ አይቻልም፡፡ ከሽብርተኝነት፣ ከስም ማጥፋትና ከሌሎች ጉዳዮች አንፃር የሚጣሉ ገደቦችና የሚወጡ ሕጎችም ቢሆኑ ትልቁን የዴሞክራሲያዊ መብት ከፍታ (የፕሬስ ነፃነትን) ገድበው እንዳይቀብሩት ማሰብና መጨነቅ ይገባል፡፡

“ነገሩን ወደ ጫፍ ለጠጥከው” እንዳትሉኝ እንጂ የለየላቸው አንዳንድ ጨፍጫፊ አምባገነኖችንም እኮ እንደማይተገብሩት አውቀው “የሚያምር” ሕግ ያወጣሉ፡፡ ለምሳሌ ሒትለር ቀደም ሲል በጀርመን ውስጥ የነበረውን “የፕሬስ ነፃነት” እንዳላገደ ይነገርለታል፡፡ ነገር ግን በበርሊን ከተማ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በተገኙበት 25 ሺሕ መጻሕፍትን አቃጥሏል፡፡ አብዛኛዎቹ በአይሁዳውያን ደራሲዎች የተጻፉና የበሳል ምሁራን የምርምር ሥራዎችን በተከታታይ ሲያወድም እንደነበር ታሪክ ያስረዳናል፡፡

ከዚያ በኋላም የፕሬስ ነፃነት በጽሑፍ ደረጃ አሸብርቆ በሰፈረበት ምሥራቅ ጀርመን አምስት ሚሊዮን የሶሻሊስት ሥርዓትን የሚያጥላሉ መጻሕፍት በአደባባይ ተቃጥለዋል፡፡ ስለካፒታሊዝም በጎ ነገር የሚያወሩ ጋዜጦችም ድራሻቸው ጠፍቷል፡፡ እነዚህ ለአብነት ቢጠቀሱም በአፍሪካም ሆነ በእስያ በርካታ ምሳሌዎችን ማስከተል እንደሚቻል መገንዘብ ይገባል፡፡ በአገራችንም እንዲሁ፡፡

በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት ጥልቅ የዴሞክራሲ ምሰሶ ውስጥ ያለው እንቅፋት የፀረ ሽብር ሕጉ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ አገራችን ሰላሟና ደኅንነቷ እንዲጠበቅ የዚህ ሕግ መኖር የግድ አስፈላጊ ቢሆንም፣ በራሱ ዜጎችን የሚያሸብርና የሚያስደነግጥ እንዳይሆን መመርመር ይገባል፡፡ በተመሳሳይ በአዋጅ በግልጽ መረጃ የመስጠት መንግሥታዊ ግዴታ ተቀምጦ ሲያበቃ በጥራት፣ በቅልጥፍናና በግልጽነት መረጃን ማግኘት አለመቻሉ እንደነውር ሊቆጠር ይገባዋል፡፡ መረጃን የሚከለክሉ፣ ቀንሰው ወይም አብዝተው የሚሰጡ መንግሥታዊ አካላትም መጠየቅ አለባቸው፡፡ የመልካም አስተዳደር መስፈን ፈተና በሆነበት አገር መገናኛ ብዙኃን ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ሊያግዙ ሲገባ “የሚስጥራዊነት አደጋዎች” ተብሎ በመንግሥት ደረጃ ከታሰበ፣ ሌላ በርካታ መቶ ዓመታት ቢመጡም ማረም የሚቻል አይመስለኝም፡፡

ዕውን የፕሬስ ነፃነት ጠበቃ የሆነ የሙያው ኃይል ተፈጥሯል?

ባገባደድነው በጀት ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ የፕሬስ ቀን ሲከበር አንድ ጽሑፍ አቅራቢ እንዲህ አሉ፡፡ “የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃንና ሙያተኞች ልዩ ባህሪ አንዱ ሌላውን ለማጥፋት የተሠለፉና የሚሠሩ መሆናቸው ነው፤” ከማለት አልፈው እንደ ቀይ ቀበሮ የአገር መገለጫ ሆኗል ያሉት ከአዕምሮዬ አይወጣም፡፡ እውነትም የግልም ይባል የመንግሥት ሚዲያው በተመጋጋቢነት የአገርና የሕዝብን ጥቅም የሚያስከብር ሳይሆን፣ አንዱ ተለጣፊ ሌላው ባላንጣ ሆኖ የበቀለ ነው፡፡ መሀል ላይ ያለ ቢኖርም የበዛና ጠንካራ አይደለም፡፡ ይህ አንድ መገርሰስ ያለበት በሽታ ነው፡፡

ሌላኛው ጋዜጠኛው ኅብረት ኖሮት ነፃ ሆኖ የተደራጀ፣ ጥቅሙን የሚያስከብር፣ ግዴታውንም የሚወጣ መሆን ያልቻለ ነው፡፡ በአገሪቱ በማኅበራት መሪዎች ስም እየተጠሩ ለምሽ እንደያዘው ሕፃን ባሉበት የሚድሁት “አደረጃጀቶችም” አንዱ ከሌላው ያላቸው ልዩነት የማይታወቅና አባላቱ እነማን እንደሆኑ በውል የማይለዩ ናቸው፡፡ የሙያ ማኅበራት ሕገ ደንብን ተከትሎ ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት ወቅቱን የጠበቀ የአመራር ምርጫም ሆነ የኦዲት ውጤት ማሳወቅ ስለመሥራታቸውም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ይልቁንም አንዳንዶቹ ማኅበራት የግለሰቦች መጠቀሚያና ሙያው እንዲሽመደመድ ታሪካዊ ስህተት እየፈጸሙ ስለመሆናቸው አለመናገር የፀያፍ ተግባር ተባባሪ መሆን ይመስለኛል፡፡

ይህን ተከትሎ ወደ ተጠናከረ “ፕሬስ ካውንስል” ለመሄድ እየተደረገ ያለው ጥረትም መቋጫ አላገኘም፡፡ እዚህ ላይ ጥቂት ባይሆንም ጉዳዩ ተጠናቆ መንግሥትና ጋዜጠኛው ከፖሊስና ከሌባ ዓይነት ድብብቆሽ ወጥተው፣ የፕሬስ ነፃነት በለም መሬት ላይ እንደበቀለ ዕፅዋት እንዲለመልም አለመረዳት ሁሉንም ወገን ሊያስጨንቅ ይገባል፡፡

በአገራችን ከነችግራቸው “አንቱ!” የተባሉ ደራስያን፣ ሙዚቀኞች፣ የፊልምና የቴአትር ባለሙያዎች አሉ፡፡ በሌላው ሙያም ከነጉድለቱ አይጠፋም፡፡ በተከበረው ጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥስ ማንን መጥራት እንችል ይሆን? በተለይ በዚህ ትውልድ ውስጥ ራሱን ለሙያው የሰጠ፣ ለሙያ ሥነ ምግባርና መርህ የተገዛ፣ በምርመራ ዘገባ ቁንጮ የሚባል ተግባርን የፈጸመ፣ በአጀንዳ ወይም በምርመራ ዘገባ የሚጨበጨብለት እየተፈጠረ ነውን? ነው ወይስ በውሸትም በግነትም ጀብደኝነት የተጠናወተው፣ ከሙያ ሥነ ምግባር አፈንግጦ ስድስብና ዘለፋ የሚቀናው፣ አድርባይነትና አስመሳይነትን ሙያ ያደረገ፣ ፈሪና ቁርጠኝነት የነጠፈበት፣ የኮክቴል ጋዜጠኝነትን የለመደ፣ ወዘተ እየበረከተ ነው የሚለውን መመርመር ያሻል፡፡

በአጠቃላይ የፕሬስ ነፃነትና የሐሳብ መንሸራሸር እንደቀደሙት ሥርዓቶች የማያስገድል ባይሆንም የሚያሳስር እየሆነ ነው፡፡ በሕግ ነፃነቱ መረጋገጡ ቢታይም በአፈጻጸም ፈተና እየገጠመው፣ “በዴሞክራሲው ለጋ ነው” ሒሳብ እየተጉላላ ነው፡፡ ባራክ ኦባማ መጥተው ስለዴሞክራሲም አወሩ ስለመረጃ ነፃነት ጉዳዩ የእኛው የኢትዮጵያውያን በመሆኑ በዘርፉ የተጋረጠብንን ፈተናና ሸክም ራሳችን አስተካክለን የነፃ ማኅበረሰብ ግንባታችንን ዕውን ልናደርግ ይገባል፡፡ እንግሊዛዊው ዳኛ፣ ጋዜጠኛና ፕሮፌሰር ዊሊያም ብላክስቶን እንዳለው፣ ‹‹The Liberty of the press is indeed essential to the naature of a free state. But this consists in laying no previous restraints upon publications and not in freedom from censure for criminal matter when published.›› (ነፃ ለሆነ መንግሥትና ማኅበረሰብ ግንባታ የፕሬስ ነፃነት መረጋገጥ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህም የተቃናና ነፃ ኅትመትን ለመተግበር ምቹ የሆነ መደላደል ማበጀትና ከቅድመ ምርምራም ሆነ ወንጀል ለመፈጸም የሚገፋን ሐሳብ ከማተም የሚቆጥብ ሥርዓት መገንባት ይገባል)፡፡

ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አንድ አካል የሆነው የፕሬስ ነፃነት እንዲከበር በጣም በትልቁ መንግሥት፣ ከዚያም ሕዝብ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ለሕዝብ ታዛዥ ነኝ የሚል መንግሥት የፕሬስ ነፃነትን ማክበር አለበት፡፡ ሕዝብ የመከታተል ኃላፊነት አለበት፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዴሞክራቱ ጆን ኤፍ ኬኔዲ፣ “ሕዝቡ እውነትንና ሐሰትን እንዲዳኝ የማይፈልግ መንግሥት የሐሳብ ገበያ እንዳይኖር የሚፈልግና ሕዝቡን የሚፈራ ነው፤” ብለው ነበር፡፡ እውነትን አንፍራ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...