Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በህዳሴው ግድብ ላይ የሚደረጉት ጥናቶች የግንባታውን ሒደትና የግድቡን መጠን ሊለውጡ አይችሉም››

አቶ ተፈራ በየነ፣ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ የወሰን ተሻጋሪ ወንዞች አማካሪ

በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ ሁለት ተጨማሪ ጥናቶች ቢጠኑ በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል መግባባትንና መተማመንን መፍጠር ይቻላል ተብሎ በዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን የቀረበውን ምክረ ሐሳብ እውን ለማድረግ፣ ሦስቱ አገሮች የመሠረቱት የሦስትዮሽ ቴክኒክ ቡድን ጥናቱ መካሄድ የሚችልበትን መንገድ እያመቻቸ ይገኛል፡፡ ጥናቱን ለማጥናት በወጣው የተወሰነ ጨረታ ቢአርኤር ኢንጂነርስ የተባለ የፈረንሣይ ኩባንያና ዴልታ ሬዝ የተባለ ሌላ ኩባንያ በሚያዝያ ወር 2007 ዓ.ም. ተመርጠዋል፡፡ የእነዚህ ኩባንያዎች የሥራ ድርሻና ኃላፊነትን የተመለከተ ስምምነት በሐምሌ ወር መጨረሻ አካባቢ በሱዳን ተደርጓል፡፡ ጥናቶቹን ለማካሄድ በተወሰነው መሠረት ሦስቱ አገሮች አማካሪ ኩባንያ ለመምረጥ ያለፉበትን ሒደት በተመለከተ፣ የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አማካሪ የሆኑት አቶ ተፈራ በየነን ዮሐንስ አንበርብር አነጋግሯቸዋል፡፡ አቶ ተፈራ ከዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ድርድር ወቅት አንስቶ፣ እስካሁን ያለውን የተፋሰሱን ሦስት አገሮች ፖለቲካዊ ግንኙነትን በቅርበት ተከታትለዋል፡፡ ዝርዝር ቃለ መጠይቁ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡   

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ በዓለም አቀፍ አጥኚ ቡድን ከቀረቡ ሁለት ምክረ ሐሳቦች መካከል አንዱ ኃይድሮ ሲሙሌሽን ሞዴል የተሰኘ ነው፡፡ በአጠቃላይ የቀረቡት ምክረ ሐሳቦች ምን ማለት እንደሆኑ ቢያብራሩልን?

አቶ ተፈራ፡- የኢትዮጵያ መንግሥት የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በሁለቱ የግርጌ አገሮች (ግብፅና ሱዳን) ላይ የሚኖረውን ጠቀሜታ፣ እንዲሁም አሉታዊ ተፅዕኖ የሚኖረው ከሆነ ማየት እንዲቻል አገሮቹና ሌሎች ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች የተወከሉበት ዓለም አቀፍ ፓናል እንዲቋቋም አድርጐ ነበር፡፡ ይህ ቡድን ግድቡን የተመለከቱ መረጃዎችንና ሰነዶችን ተመልክቶ፣ ግንባታው በሚካሄድበት ቦታ ጭምር በመገኘት ጥናት አድርጐ ተጨማሪ ክትትል ቢደረግባቸው በማለት ያቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ጥናቶች አንዱ ኃይድሮ ሲሙሌሽን ሞዴል ነው፡፡ ከውኃ አጠቃቀም አኳያ ግድቡ በግርጌ አገሮች ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል የሚለውን የሚዳስስ ነው፡፡ በአጠቃላይ የግድቡ ዕውን መሆን በውኃ ሥሌቱ ላይ ምን ተፅዕኖ ያመጣል የሚለውን የሚመለከት ነው፡፡ ይህንን ለማጥናት በኃይድሮሎጂ ሲሙሌሽን ሞዴል የታገዘ ጥናት በማድረግ አጠቃላይ በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ ያለውን ውኃ የሚዳስስ ጥናት ነው አንደኛው ምክረ ሐሳብ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በአካባቢና ማኅበራዊ ጉዳዮች ረገድ የሚኖረውን ተፅዕኖ የሚገመግም ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ፓናሉ ያቀረባቸውን እነዚህን ሁለት ተጨማሪ ጥናቶች ተግባራዊ ለማድረግ ነፃ በሆኑ አማካሪ ኩባንያዎች እንዲጠና ነው በዝግጅት ላይ ያለው፡፡ በጥናቶቹ የሥራ ቢጋር (ይዘት) ላይ በሦስቱ አገሮች መካከል ስምምነት ተደርሶ፣ ጥናቱን የሚከታተል ሦስትዮሽ ብሔራዊ ኮሚቴ ከእያንዳንዱ አገር አራት ባለሙያዎች የሚወከሉበት ኮሚቴ ተደራጅቶ ሥራውን ጀምሯል፡፡

ኮሚቴው የሥራ ቢጋሩን፣ ከዚያም ኩባንያዎቹን ለመጋበዝ የጨረታ ዶክመንቱን አዘጋጅቷል፡፡ በዚህ መሠረት በአገሮቹ መካከል ንግግር ተደርጐ የተወሰኑ ዓለም አቀፍ ትልልቅ ኩባንያዎች በውስን ጨረታ ተመርጠው፣ ፕሮፖዛላቸውን ወይም የጨረታ ዶክመንታቸውን እንዲያስገቡ ተጠይቋል፡፡ በዚህ መሠረት አምስት ኩባንያዎች ጥናቱን ለማከናወን ፍላጐታቸውን በመግለጽ የጨረታ ዶክመንታቸውን አስገብተዋል፡፡ በዚህ በሦስትዮሽ ኮሚቴው በተቀመጠ የአሠራር ሥነ ሥርዓት ደንብ መሠረት የጨረታ ዶክመንቱን ገምግመው የተሻለውን ኩባንያ መርጠዋል፡፡

በመረጣው ሒደት ወቅት የተወሰኑ ችግሮች ነበሩ፡፡ ይህ ሥራ በአገሮች መካከል መተማመንን ለመፍጠር የሚሠራ ነው፡፡ በመረጣው ሒደት የተወሰኑ ልዩነቶች ቢኖሩም በመጨረሻ በሚያዚያ ወር 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተካሄደ የሦስቱ አገሮች የውኃ ሚኒስትሮች ባሉበት ስብሰባ አንድ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ስለዚህም በሦስቱ አገሮች ግምገማ የተሻለ የሆነው ኩባንያ የጥናቱ ዋና አማካሪ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ሌላኛው ኩባንያ ደግሞ ከዋና አማካሪው የተወሰኑ ሥራዎችን ወስዶ አብረው በጋራ እንዲሠሩ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡    

ሪፖርተር፡- ዋና አማካሪ ሲባል ምን ማለት ነው? በጥናቱ ላይ የሚኖረው ድርሻና የኃላፊነት መጠኑ ምን ያህል ነው?

አቶ ተፈራ፡- እንግዲህ በጨረታ ሒደት መሠረት ዋና አማካሪ ተብሎ የተመረጠ ኩባንያ አጠቃላይ ኃላፊነቱን የሚወስድ ነው የሚሆነው፡፡ ሕጋዊ ኃላፊነቱ የሚወድቀውና በቴክኒክም ተጠያቂ የሚሆነው መሪ ኩባንያ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ዋና መሪ የተባለው [የፈረንሳዩ ቢአርኤል ኢንጂነርስ] ኩባንያ ከ30 በመቶ ያልበለጠውን የጥናት ሥራ ለሁለተኛው [ዴልታ ሬዝ የተባለ የኔዘርላንድ] ኩባንያ በመስጠት በጋራ ይሠራሉ በማለት ነው የተስማማነው፡፡ ይህ ጉዳይ ወደ አፈጻጸም ሲሄድ አሁንም ልዩነቶች በተወሰነ ሁኔታ ተከስተዋል፡፡ የእያንዳንዱ የጥናት ድርሻ ምን ይሆናል? ከጥናት ውጤቱ አኳያ ኃላፊነቱ የማን ይሆናል? በአጠቃላይ የፕሮጀክቱ ተጠሪና የአስተዳደር ጉዳይ የማን ኃላፊነት ይሆናል? በሚሉት ጉዳዮች ላይ የተወሰኑ ልዩነቶች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ በቅርቡ በሱዳን ካርቱም በተካሄደው ስብሰባ ልዩነቱ ተወግዶ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ሁሉም አገሮች የአንዱን ኩባንያ መሪነት ተቀብለው ኩባንያው በሕግም በቴክኒክም ኃላፊነቱን የሚወስድ፣ እንዲሁም የፕሮጀክት ውሉ የሚፈጸመውም ከዋና መሪ ኩባንያው ጋር ነው በሚል ሐሳብ ቀርቦ በዚህ ላይ መግባባት ተችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- ሁለቱ ኩባንያዎች በጥናቱ ውስጥ የሚኖራቸው ድርሻስ?

አቶ ተፈራ፡- ድርሻውን በተመለከተ በመጠን ዋናው አማካሪ 70 በመቶ የሚሆነውን ሥራ ለማከናወን የሚያስችሉ ባለሙያዎችን ይመድባል፡፡ በአንፃሩ ሁለተኛው ኩባንያ ደግመ ከ30 በመቶ የማይበልጥ ጥናት ለማከናወን የሚያስችል ባለሙያ በመመደብ ሁለቱ ኩባንያዎች በጋራ ይሠራሉ፡፡ በዚህ መሠረት ዋና አማካሪ ኩባንያው የተጠቀሰውን ለመፈጸም የባለሙያ ስብጥር ከሁለቱ ኩባንያዎች ምን ያህል ይሆናሉ የሚለውንና አጠቃላይ ቴክኒካል ፕሮፖዛሉን በቀጣዩ ስብሰባ ያቀርባል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በቅርቡ ተካሂዶ የነበረው የካርቱሙ ስብሰባ በዚህ ረገድ ጥሩ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በመሠረቱ ስምምነቱ የተደረሰው በአዲስ አበባ ቢሆንም፣ ከላይ የተገለጹትን ይዘቶች በመፍታት ረገድ ውጤት የተገኘው በካርቱሙ ስብሰባ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የልዩነቱ መሠረታዊ ምንጭ ምንድነው? በኩባንያዎቹ ላይ የገለልተኝነት ጥያቄ ተነስቶ ነው?

አቶ ተፈራ፡- የተለያዩ አመለካከቶች በአገሮች መካከል ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ምናልባትም ኩባንያዎቹን የማወቅና ያለማወቅ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዶቹ ኩባንያዎች ከአንድ አገር ጋር ተደጋጋሚ ሥራ ሠርተው ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ከዚያ አኳያ የእነዚህ ኩባንያዎች መኖር የተሻለ መተማመን ይሰጠናል ከሚል እምነት ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ግን ምናልባት በዚህ መልኩ ጥናቱ ሲሠራ ያልተለመደ በመሆኑም ሊሆን ይችላል፡፡ ዋና አማካሪና ከዋናው አማካሪ ሥራ የሚወስድ ሌላ አማካሪ መቅጠር የተለመደ አሠራር ቢሆንም፣ ብዙ ጊዜ ሁለተኛው አማካሪ የሚቀጠረው በዋናው አማካሪ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ጥናት ላይ ሁለቱንም አማካሪዎች የመረጡት አገሮች ናቸው፡፡ ስለዚህ ለአገሮች የኩባንያዎቹን ማንነት የማጥራት ሥራን ይጠይቃል፡፡   

ሪፖርተር፡- ግልጽ ለመሆን ያህል አሁን የደረሳችሁበት ስምምነት አንድ ኩባንያ ዋና አማካሪ ወይም ሙሉ ኃላፊነት የሚጣልበት ይሆናል፡፡ ሥራው የሚሠራው ግን በሁለቱ ኩባንያዎች በጋራ ነው ማለት ነው? ዋናው አማካሪ የጥናቱን የተወሰነ ክፍል ለሌላ የመስጠት (Outsource) አሠራር ቀርቷል ማለት ነው?

አቶ ተፈራ፡- ትክክል ነው፡፡ በጋራ ነው የሚሠሩት፡፡ በዋና መሪ ኩባንያው ኃላፊነትና መሪነት ማለት ነው፡፡ በድርሻ ረገድ በፊትም ብዙ ልዩነት የለም፡፡ ነገር ግን አሁን የበለጠ ግልጽነት ተገኝቷል፡፡ ከጥናቱ አኳያና ከማኔጅመንት የማን ኃላፊነት ምን ይሆናል የሚለው ነበር ወሳኙ ልዩነት፡፡ አሁን ይህ ተፈቷል፡፡

ሪፖርተር፡- በነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ በአዲስ አበባ የሦስትዮሽ ኮሚቴው ለመሰብሰብ ቀጠሮ ይዟል፡፡ የዚህ ስብሰባ አጀንዳ ምንድነው?

አቶ ተፈራ፡- የሁለቱ ኩባንያዎች የሙያተኞች ስብጥር ያካተተው ፕሮፖዛል በዚህ ስብሰባ ላይ ይቀርባል፡፡ አገሮቹ ይህንን ፕሮፖዛል ገምግመው እንደማንኛውም የጨረታ ሒደት ፕሮፖዛሉ ላይ ያላቸውን አስተያየት አካተው ከአማካሪ ኩባንያው ጋር ለድርድር የሚቀመጡበት ስብሰባ ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በአሁኑ ወቅት ከ40 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡ በሌላ በኩል የቀረቡት ሁለት ምክረ ሐሳቦች እስካሁን ጥናታቸው አልተጀመረም፡፡ የጥናቱ መዘግየት ከጊዜ አንፃር እንዴት ነው የተገመገመው? ጥናቱ በግንባታው ላይ ማስተካከያ ቢጠይቅ ከግንባታው ፍጥነት ጋር ችግር አይፈጥርም?

አቶ ተፈራ፡- በማንኛውም አመለካከትና ዕይታ የግድቡ ዲዛይን ተጠናቋል፡፡ በዚያ ዲዛይን መሠረት ግንባታው ተጀምሮ እየተሠራ ነው ያለው፡፡ እናም ይህ ጥናት የግንባታውን ሒደት እንዲሁም የግድቡን መጠን የመሳሰሉትን ሊለውጥ የሚችል አይደለም፡፡ ስለዚህ በማንኛውም ጊዜ ጥናቱ ቢመጣ ችግር የለውም፡፡ ዋናው ነገር ይህ ግድብ ለማንኛውም አገር ጠቀሜታ አለው፡፡ ማንንም አገር በጉልህ አይጐዳም የሚል እምነት ነው ያለን፡፡ በተወሰነ ደረጃ ጥናቱ የሚያመላክተው ጉዳት ሊኖር ቢችል እንኳ ያንን የመቀነስ ወይም ማረሚያ መንገድ የመፍጠር ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ብዙ የሚያመጣው ልዩነት አይኖርም፡፡ ይኼ ግድብ ሲጠና እና ዲዛይን ሲደረግ በወሰን ተሻጋሪ ወንዝ ላይ የሚገነባ እንደሆነ ይታወቃልና በግርጌ በኩል ሌላ የውኃው ተጠቃሚ መኖሩን ከግንዛቤ ያስገባ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን እንዲጠኑ የሚፈለጉት ሁለት ጥናቶች ከግንባታው በፊት በኢትዮጵያ በኩል ጥናት የተደረገባቸው ናቸው ማለት ነው?

አቶ ተፈራ፡- በሁለቱም የጥናት ዓይነቶች ላይ በኢትዮጵያ በኩል የተሠራ ሥራ አለ፡፡ ለማንኛውም በአገሮቹ መካከል መተማመንን ለመፍጠር ተጨማሪ ሥራ ቢሠራ ጉዳት አይኖረውም፡፡

ሪፖርተር፡- የጥናት ውጤቱ ተግባራዊነት አስገዳጅ ነው?

አቶ ተፈራ፡- ጥናቱ እንዴት ተቀባይ እንደሚሆን በሦስትዮሽ የቴክኒክ ኮሚቴ አማካይነት የተቀመጡ አካሄዶች አሉ፡፡ በአጠቃላይ በሁሉም አባላት ይሁንታ (Consensus) የሚሠራ ነው የሚሆነው፡፡ ጥናቱ አስገዳጅ ነው የሚል ስምምነት የለም፡፡ ትልቁ ነገር ጥናቱን አጠናቆ ተፅዕኖ የሚኖረው ከሆነ ተፅዕኖው የሚቀንስበትን መንገድ ማመቻቸት ነው፡፡ አጥኚዎቹ በቀጥታ ይህንን አድርግ ይህንን አታድርግ የሚሉበት ጥናት አይደለም፡፡ የጥናቱን ውጤት አገሮቹ በጋራ ይመረምሩታል፡፡ እናም አካሄዱ የሚሆነው ሁሉም አገሮች የተስማሙበት ነው ወደ ድርጊት የሚሄደው፡፡ ስለዚህ የየራሱ ደረጃ አለው፡፡ በሦስትዮሽ የጋራ ኮሚቴው ይታያል፣ ወደ ሚኒስቴሮች ይሄዳል፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ በገለልተኛ ባለሙያዎች ውጠቱ እንዲገመገም ይደረጋል፡፡   

ሪፖርተር፡- የሱዳን መንግሥት በህዳሴው ግድብ ጠቀሜታ ላይ አምኖ ለኢትዮጵያ አጋርነቱን እያሳየ ነው፡፡ በዚህ የአማካሪ ድርጅት መረጣና ቅጥር ላይ የነበረውን ሚና እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ተፈራ፡- የአማካሪ ድርጅት መረጣው ላይ በሱዳን በኩል እየታየ ያለው አቋም ከሞላ ጐደል ከኢትዮጵያ ጋር የሚጣጣም ነው፡፡ አገሮች በአንድ ነገር አንድ ዓይነት አቋም ሊኖራቸው ይችላል፣ በተወሰነ ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ ሁሉም የየራሱ አመለካከት አለው፡፡ ይህም ከብሔራዊ ጥቅም የሚመነጭ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ መግባባት ሊኖር ይችላል ወይም ልዩነት ሊኖር ይችላል፡፡ ጥናቱን የሚያካሂዱ ኩባንያዎች መረጣን በተመለከተ ሱዳን በአብዛኛው ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ አቋም ብታራምድም በአንዳንድ ጉዳዮች ደግሞ የተለየ አቋም ታራምድ ነበር፡፡ የሆነ ሆኖ በመጨረሻ ላይ ሦስቱም አገሮች የጋራ መግባባት ላይ ነው የደረሱት፡፡ ከዚህ አኳያ ይህ የእከሌ አቋም ነው፣ ያኛው የእከሌ ነው የሚያሰኝ ልዩነት የለም፡፡ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ በአንዳንድ ሁኔታዎች ልዩነቶች ነበሩን፣ አሁን ግን ይህ ሁኔታ የለም፡፡ አለመግባባቱ ቢኖር ነው ይህ የእከሌ አቋም ነው፣ ይኼኛው የኢትዮጵያ ነው የሚል ነገር ሊመጣ የሚችለው፡፡  

ሪፖርተር፡- በዓባይ ተፋሰስ ፖለቲካ ውስጥ ረጅም ጊዜ የፈጀ ተሳትፎ ያደረጉ ከመሆንዎ አንፃር፣ ኢትዮጵያ ካፀደቀችው የዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ድርድር ጀምሮ እስካሁን እየተሳተፉ መሆንዎን መነሻ በማድረግ አሁን ያለው የአማካሪ ኩባንያ የመምረጥ ሒደት እንዴት ይጠናቀቃል ብለው ይገምታሉ? ኢትዮጵያ የምትሻው ትብብር በመተማመን ሊፈጠር ይችላል?

አቶ ተፈራ፡- የቀደሙ ልምዶች የሚያሳዩት እንደዚያ ተስፈኛ እንድትሆን ነው፡፡ በቀላል የሚደረግ አይደለም፡፡ እልህ አስጨራሽ፣ እንቅልፍ የሚያሳጣ፣ ረዥም ጊዜ የሚቆዩ ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ እስካሁን ያለው ሁኔታ ጥሩ ነው፡፡ የትብብር ማዕቀፉን ጉዳይ ስናነሳ እጅግ በጣም በብዙ ነገሮች ላይ ተስማምተናል፡፡ እርግጥ መጨረሻ ላይ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ልዩነት እንዳለን ይታወቃል፡፡ ልዩነታችን በመሠረታዊ ጉዳይ ላይ ነው፡፡ አሁን እየሆነ ያለው የተሻለ ይመስላል፡፡ ምናልባት ሁኔታዎች የፈጠሩት ሊሆን ይችላል፡፡ ሁኔታዎች ስል ምን ማለቴ ነው? ለምሳሌ በኢትዮጵያ በኩል በወሰን ተሻጋሪ ወንዞች ላይ ያለው የቆየ እምነት በተግባር የማሳየት ጉዳይ መፈጠር አንዱ ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? የጋራ ሀብት ነው፡፡ የጋራ ሀብትን ሁሉም ተጋሪ አገር ተጠቃሚ በሚሆንበት መንገድ ማልማት፣ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ ሁኔታ በፍትሐዊነት ሊጠቀምበት ይገባል የሚል የቆየ እምነት በኢትዮጵያ በኩል አለ፡፡ መንግሥታት ሲቀያየሩ ያልተቀየረ አቋም ነው፡፡ ይህንን ወደ መሬት ማውረድ መጀመሩ ነው ፖለቲካውን መቀየር የጀመረው፡፡ ትብብሩን ያፋጠነውም ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ እኔ እላለሁ፡፡ በምሥራቅ ዓባይ ተፋሰስ አገሮች የድርጊት መርሐ ግብር በጋራ የሚሠሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ወደ ተግባር ለመቀየር ትልቅ ምኞት ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም የተግባር እንቅስቃሴ ሳይኖር ረዥም ጊዜ ነው የፈጀው፡፡ በመሆኑም በተናጠል ነገር ግን በመርህ ላይ የተመሠረተ የተግባር እንቅስቃሴን አስከትሏል፡፡

ይህ የተናጠል እንቅስቃሴ ሲመጣ አንዳንዶች ምን ማለት ነው ሲሉ ተቃውመዋል፡፡ የትብብር እንቅስቃሴውን ይጐዳዋል የሚል ሥጋት ተፈጥሮባቸው ነበር፡፡ የእኔ እምነት ግን ትብብሩን ያፋጥነዋል የሚል ነበር፡፡ አሁን ትብብሩ እየመጣ ይመስለኛል፡፡ መጀመሪያ በፍትሐዊ አጠቃቀም መርህ ላይ ስንነጋገር በአንዳንድ አገሮች በሩቅ የሚተገበር ነው ብሎ የማሰብ ሁኔታ ነበር፡፡ አሁን ግን ቀርቦ እየመጣ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን በትብብር ማዕቀፉ ላይ ያሉ መብቶችና ግዴታዎችን ወደ መሬት የማውረድ ሥራ እየተሠራ ያለ ነው የሚመስለኝ፡፡ ኢትዮጵያ የትብብር ማዕቀፉን ፊርማ በሕግ አውጪው አካል አፅድቃዋለች፡፡ ግብፅና ሱዳን የትብብር ማዕቀፉን አልፈረሙም፣ አላፀደቁትም፡፡ ነገር ግን የትብብር ማዕቀፉን ድንጋጌዎች በተወሰነ ሁኔታ እየተተገበረ ነው ያለው፡፡ ጨለምተኛ አይደለሁም፡፡ ትብብሩ የግድ እያለ፣ ሁኔታዎች ትብብርን የግድ እያሉ ይሄዳሉ የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ አሁን ይህ እየመጣ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ ቀደም ብሎም ቢሆን በዚህ ተፋሰስ ውስጥ ልማት ነበር፡፡ ነገር ግን የተናጠል ልማት ነው፡፡ አሁን እየመጣ ያለው ከቀድሞው የተለየ ነው፡፡

የቀድሞው አመለካከት የውኃውን የበላይ ተጠቃሚነት በማንኛውም መስዋዕትነት ማረጋገጥ ነበር፡፡ ይህ አሁን የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ስለዚህ መተባበር ነው የሚያዋጣው፡፡ በትብብር የእያንዳንዱ አገር የጥቅም ድርሻ እየጨመረ ሊሄድ ይችላል፡፡ በዚያው ልክ ጉዳት ሊቀንስ ይችላል፡፡ ለማንኛውም ኢትዮጵያ የምትከተለው መርህ እናም የተፈጥሮ ሀብቷን ለማልማትና ዜጐቿን ከዚህ ተጠቃሚ ለማድረግ በወሰደችው ዕርምጃ፣ ትብብሩን እንዲመጣ ጉልህ ድርሻ እየተጫወተ ነው ያለው፡፡  

ሪፖርተር፡- እንዳሉት የኢትዮጵያ የቆየ እምነት ወደ ተግባር በተለወጠበት በአሁኑ ወቅት አንዳንድ አገሮች የኢትዮጵያን እግር ተከትለዋል፡፡ ለምሳሌ ሱዳንን ማንሳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከግብፅ በኩል የታየ የትብብር ፍላጐት አለ ወይ? በተለይ በአገሪቱ ከተደረገው የሥልጣን ሽግግር በኋላ? 

አቶ ተፈራ፡- ይመስለኛል፡፡ ለረጅም ጊዜ አብረን መሥራታችን፣ በናይል ቤዚን በኩልም ውይይቱን አብረን መቀጠላችን፣ ብዙ ጥናቶች መደረጋቸውና የጥናቶቹ ውጤት ደግሞ በትብብር ወንዙ ቢለማ ጠቃሚ መሆኑን የሚጠቁሙ በመኖራቸው፣ ሁኔታዎች እንዲቀየሩ ያደረገ ይመስለኛል፡፡ ከሱዳን አኳያ ስንመለከተው አንድ አገር በአንድ ጉዳይ ላይ ወደ ስምምነት ሊመጣ የሚችለው ከራሱ ብሔራዊ ጥቅም አኳያ ነው፡፡ በግብፅም በኩል ቢሆንም በእኔ እምነት የተለወጡ ነገሮች አሉ፡፡ በዋናነት ይህንን ለውጥ አምጥቷል ብዬ የማምነው ኢትዮጵያ የቆየ እምነቷን ወደ ተግባር ማውረድ መጀመሯ ይመስለኛል፡፡ ተወደደም ተጠላ ለረዥም ጊዜ የነበረ ውኃውን በብቸኝነት የመጠቀም ልማድ ሊቆይ አይችልም፡፡ አለመተባበር የሆነ እንደሆነ ከተፋሰሱ አገሮች ፍላጐት ጋር የሚጋጭ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ ማለት ምንድነው? የተፋሰሱ አገሮች የወደፊት ፍላጐት በተፋሰሱ ውስጥ ካለው የውኃ መጠን በላይ ነው የሚሆነው፡፡ ፍላጐቱን አጣጥሞ ለመሄድ የግድ መተባበርን ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ የመሬት አቀማመጥ የዓባይ ተፋሰስ ለኃይል ማመንጫ ትልቅ ጥቅም ሲኖረው በሱዳን በኩል ደግሞ ለመስኖ ልማት ይመቻል፡፡ ስለዚህ እነዚህን አጣጥሞ መሥራት ነው በተፋሰሱ ዘላቂ ልማት ሊያመጣ የሚችለው፡፡ ይህ አሁን እየሆነ ይመስለኛል፡፡    

ሪፖርተር፡- የዓባይ ተፋሰስ በኢትዮጵያ ኃይል ከማመንጨት ውጪ ለመስኖ ጥቅም እንዳይውል ከጥቂት ወራት በፊት የሦስቱ አገሮች መሪዎች የፈረሙት የመርህ መገለጫ ሰነድ፣ ኢትዮጵያ በግድቡ የሚያጠራቅመውን ውኃ ለኃይል ማመንጫ ‹‹ብቻ›› እንድትጠቀም ያስገድዳታል የሚሉ አስተያየቶች አሉ፡፡ በዚህ ላይ ምን ምላሽ ይኖርዎታል?

አቶ ተፈራ፡- ‹‹ብቻ›› አይልም፡፡ የህዳሴው ግድብ በዋናነት ለኃይል ማመንጫ ይውላል ነው የሚለው፡፡ በዚህ ላይ ክርክር የለም፡፡ በኢትዮጵያ በኩልም ግድቡ እየተገነባ ያለው በዋናነት ኃይል ለማመንጨት ነው፡፡ ‹‹ኃይል ለማመንጨት ብቻ›› በሚለውና ‹‹በዋናነት ኃይል ለማመንጨት›› በሚሉት ሐረጐች መካከል ልዩነት አለ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን እንዲጠኑ የሚፈለጉት ሁለት ጥናቶች እውነተኛ መረጃዎችን ከሦስቱም አገሮች ማግኘትን ይጠይቃሉ፡፡ በዚህ ረገድ ለጥናቶቹ ወሳኝ የሆኑ ትክክለኛ መረጃዎችን አገሮች በታማኝነት ያቀርባሉ ተብሎ ይታሰባል? ይህ ራሱን የቻለ ያለመግባባት ምንጭ ሊሆን አይችልም?

አቶ ተፈራ፡- አገሮች በታማኝነት መረጃዎችን እንዲያቀርቡ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነገር ግን አገሮች የሚያቀርቡት መረጃ በሦስትዮሽ የቴክኒክ ኮሚቴው ማረጋገጫ ማግኘት የሚችልበት አሠራር ተቀምጧል፡፡ መረጃዎቹ በጋራ ተፈትሸውና ተተንትነው ነው ተዓማኒነታቸው የሚረጋገጠው፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ ተነስቶ ድንበር የሚሻገር ተፋሰስ ዓባይ ብቻ አይደለም፣ ሌሎች ተፋሰሶችም አሉ፡፡ ኢትዮጵያ በእነዚህ ተፋሰሶች ላይ ያላት ፖሊሲ ምንድነው?

አቶ ተፈራ፡- በድንበር ተሻጋሪ ተፋሰሶች ላይ የተለያዩ ፖሊሲዎች የሉንም፡፡ ኢትዮጵያ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞቿ ላይ ያላት ፖሊሲ አንድ ወጥ ነው፡፡ የውኃ አስተዳደር ፖሊሲ አለ፡፡ ከዚያ በተጨማሪ በእያንዳንዱ ተፋሰስ ላይ ያለውን የሀብት መጠን መለየትና መጠቀም ነው፡፡ ከ1950ዎቹ ጀምሮ የመጀመሪያው የዓባይ የአፈርና የውኃ ጥናት ከተሠራ ጀምሮ ምን ሀብት አለ? መቼ ሊለማ ይችላል? የሚሉ ጥናቶች ተከናውነዋል፡፡

በመጀመሪያ የናይል ተፋሰስ ገባር የሆኑ ሦስቱ ወንዞች ማለትም የዓባይ፣ የተከዜ መረብና የባሮ አኮቦ ማስተር ፕላን ተጠንቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሁሉም ድንበር ተሻጋሪ ተፋሰሶች ማስተር ፕላን ተጠንቷል፡፡ ይህ እንግዲህ ሐሳቡ ፕሮጀክቶችን ለመለየት ነው፡፡ እያንዳንዱ ማስተር ፕላን ውስጥ የዓሳ ልማት፣ የኃይል ማመንጫ፣ በአጠቃላይ የተቀናጀ ልማትን ለመፍጠር ነው፡፡

ከዚያ እንደገና እየተሸነሸኑ ዝርዝር ጥናቶች ይካሄድላቸዋል፡፡ ማስተር ፕላኖቹ ቅድሚያ መልማት ያለባቸው የሚባሉትን የሚተነትኑ በመሆናቸው፣ በአገሪቱ የአምስት ዓመት ዕቅድ ውስጥ እየገቡ ወደ ተግባር እየተለወጡ ነው፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...