Tuesday, May 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቱርኩ ትራንስፎርመር አምራች በ150 ሚሊዮን ብር ማስፋፊያ አካሂዳለሁ አለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ምርት ከጀመረ አንድ ዓመት ተኩል ያስቆጠረው የቱርኩ ሰንራይዝ ኢንጂነሪንግ ኤንድ ማሽነሪስ ማኑፋክቸሪንግ ኩባንያ፣ የኃይል ማሠራጫና ማከፋፈያ ትራንስፎርመሮችን በማምረት ላይ ይገኛል፡፡ ያስመዘገበውን ኢንቨስትመንት ካፒታል በእጥፍ በማሳደግ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ከ100 እስከ 150 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ተጨማሪ ገንዘብ የማምረት አቅሙን ለማሳደግ መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

የኩባንያው መሥራች ባለድርሻና ዋና ሥራ አስኪያጅ ኤኒስ ዩርችጉ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ኩባንያቸው በገላን ከተማ በ20 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ይዞታው፣ በዓመት 3600 ኃይል ማሠራጫ ትራንስፎርመሮችን የማምረት አቅም ይዞ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ሆኖም በሚያጋጥመው ቢሮክራሲና በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት በሙሉ አቅሙ ለማምረት ሳይቻለው ቆይቷል፡፡ ይህም ሆኖ ተጨማሪ ማስፋፈያ በማካሄድና አቅሙን በማሳደግ ኃይል አስተላላፊ ትራንስፎርመሮችን ለማምረት ዝግጅት መጀመሩን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በሙሉ አቅሙ ሲያመርትና ማስፋፊያውን ሲገነባ አሁን ያሉትን 45 ሠራተኞች ወደ አንድ መቶ እንደሚያሳድግ ይፋ አድርገዋል፡፡

ኩባንያው ከአገር ውስጥ ገበያ ባሻገር ወደ ጎረቤት አገሮች ምርቶቹን ለመሸጥ ፍላጎት አለው፡፡ በኩባንያው ዕቅድ መሠረት ቀደም ብሎ ምርቶቹን ወደ ውጭ የመላክ ሐሳብ ቢኖርም በትራንስፖርትና በሎጂስቲክስ ወጪዎች መናር ሳቢያ በአገር ውስጥ ገበያ መገደቡን አስታውቋል፡፡ ሥራ አስኪያጁ እንደሚገልጹት፣ ከኢስታንቡል ከተማ ወደ ኒውዮርክ ምርት ለመላክ የሚጠይቀው የማጓጓዣ ወጪ ሁለት ሺሕ ዶላር ቢሆንም፣ ከኢስታንቡል እስከ ሞጆ ደረቅ ወደብ ድረስ ለማጓጓዝ ግን ከ6500 ዶላር በላይ ወጪ ይጠይቃል፡፡ ይህ በመሆኑ የውጭ ገበያውን ለጊዜው መተው እንዳስፈለገ ጠቅሰዋል፡፡

በአንፃሩ በአገር ውስጥ ያለው የትራንስፎርመር ፍላጎት መጠን ከፍተኛ መሆኑን ወደፊትም እየጨመረ እንደሚሄድ የገለጹት ዩርችጉ፣ የግልገል ጊቤ ሦስት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሥራ ሲጀምር በዓመት የሚኖረው የትራንስፎርመር ፍላጎት 20 ሺሕ ሊደርስ እንደሚችል ይታሰባል ያሉት ባለሀብቱ፣ የህዳሴው ግድብ ሥራ በሚጀምርበት ወቅት የሚኖረው ፍላጎት ከፍተኛ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ  ወቅት የግዥ ውል በመፈጸም ትራንስፎርመሮች እንዲመረቱለት ያዘዘው ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ የግል ድርጅቶች ትዕዛዝን እያስተናገደ የሚገኘው ሰንራይዝ ኩባንያ፣ አንድ መቶ ያህል የተመረቱ ትራንስፎርመሮች ክምችት እንዳለው አስታውቋል፡፡ ትራንስፎርመሮችን ከማምረት ባሻገር የጥገና አገልግሎት የሚሰጠው ሰንራይዝ፣ ለሚያመርታቸው ትራንስፎርመሮች የጥራት ማረጋገጫ ሪፖርትና የዋስትና ሰርቲፊኬት እንደሚሰጥ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትም የጥገናና የኃይል ማሠራጫ ትራስፎርመሮች አቅራቢነት ዕውቅና እንደሰጠው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከሰንራይዝ ባሻገር በኢትዮጵያ ውስጥ በቅርቡ ትራንስፎርመር ማምረት መጀመራቸውን ካስታቁ ድርጅቶች መካከል የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ታጠቅ ተብሎ በተሰየመው የትራንስፎርመር ማምረቻ ተቋም አማካይነት በዓመት አሥር ሺሕ ለማምረት መዘጋጀቱን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ በሪጅቴክ የተባለው አገር በቀል ኩባንያም በኤምሬቴሱ አል-ናስር ኢንዱስትሪ ኢንተርፕራይዝ ሥር ከሚገነው ፌደራል ትራንስፎርመር ኩባንያ ጋር በመጣመር በዓመት አራት ሺሕ ትራንስፎርመሮችን ለማምረት የሚያስችላቸውን ስምምነት እንዳደረጉ መዘገቡም አይዘነጋም፡፡

በአገሪቱ በተደጋጋሚ ለሚከሰተው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል የትራንስፎርመሮች ችግር አንዱ ሲሆን፣ በተለያዩ አካባቢዎችም ዋናው የኃይል ማሠራጫ ተተክሎ በትራንስፎርመር እጦት ሳቢያ ኤሌክትሪክ አጥተው የሚጠባበቁ በርካታ አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች