– በ2007 የተቀማጭ ገንዘባቸው ከ360 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ዕድገት እየታየበት የመጣው የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ በ2007 በጀት ዓመትም በከፍተኛ ደረጃ ጭማሪ በማሳየት ከ360 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ የዕድገቱ መጠን አሁን ባለው ደረጃ ከቀጠለም በቀጣዩ በጀት ዓመት ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
የ16ቱ የግል ባንኮችና የሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች የ2007 በጀት ዓመት ግርድፍ መረጃ እንደሚያሳየው፣ የሁሉም ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ25 በመቶ በላይ እየጨመረ ነው፡፡ የአንዳንድ ባንኮች ጭማሪም ከ35 በመቶ በላይ ሆኗል፡፡
በተለይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተቀማጭ ገንዘብ ከዚህ ቀደም ባልታየ መጠን እያገ በመምጣት በ2007 መጨረሻ ላይ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘቡ ከ242 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ 16ቱ የግል ባንኮችም በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ የተቀማጭ ገንዘባቸው 118 ቢሊዮን ብር በላይ ሊደርስ ችሏል፡፡
ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ውጭ ያሉት 18ቱ ባንኮች በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ከ360 ቢሊዮን ብር በላይ መድረስ የቻሉት የተቀማጭ ገንዘባቸው ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻውን በበጀት ዓመቱ ከ49 ቢሊዮን ብር በላይ አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ እንደቻለም ባንኩ ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተቀማጭ ገንዘቡ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣት አንዱ ምክንያት ‹‹ይቆጥቡ ይሸለሙ›› የሚለው ሽልማት አንድ ምክንያት መሆኑንም ሰሞኑን ገልጿል፡፡
እንደ ባንኩ መረጃ ባለፉት አምስት ዓመታት የተቀማጭ ገንዘቡ መጠን በየዓመቱ በአማካይ ወደ 35 በመቶ ዕድገት እያሳየ ነው፡፡ በ2007 በጀት ዓመት ብቻ ከ500 ሺሕ በላይ አዳዲስ አስቀማጮችን ማፍራት የቻለ በመሆኑም፣ የቆጣቢ ደንበኞቹ ቁጥር በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 10.5 ሚሊዮን ሊደርስ ችሏል፡፡ በቆጣቢዎች መጠንም ሆነ በቁጠባ የተቀመጠው ገንዘብ መጠን በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱን ከሚያመለክቱ መረጃዎች ውስጥ ባንኩ በ2004 ዓ.ም. 3.9 ሚሊዮን ደንበኞች የነበሩ መሆኑ ነው፡፡ የአገሪቱን ባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በጥቅል ሲታይም በ2000 ዓ.ም. የሁሉም ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ 62.9 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በ2001 ዓ.ም. ደግሞ 78.15 ቢሊዮን ብር እንደነበር የሚያሳይ በመሆኑ፣ የአገሪቱ የተቀማጭ ገንዘብ በምን ያህል ደረጃ እንዳደገ አመላካች ሆኗል፡፡
የግል ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ መጠን እያደገ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ሲነፃፀር ሰፊ ልዩነት ያለው እንዳለው እየታየ ነው፡፡ የግል ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ መጠናቸው ለመጀመርያ ጊዜ ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ መዝለል የቻለው በ2007 ዓ.ም. ግማሽ በጀት ዓመት ላይ ነው፡፡ በታኅሳስ 2007 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የሁሉም የግል ባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ 101 ቢሊዮን ብር መድረሱ ትልቅ እመርታ ስለመሆኑ መገለጹ ይታወሳል፡፡ በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ላይ 18ቱም ባንኮች 316.2 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ የነበራቸው ሲሆን፣ ከነዚህም 209.2 ቢሊዮን ብሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ ነው፡፡ ይህም ሰፊ ልዩነት እንዳለ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተቀማጭ ገንዘቡን ከመቶ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ የቻለው በ2004 በጀት ዓመት የመጨረሻዎቹ ወሮች ላይ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በ2004 ዓ.ም. 85 ቢሊዮን ብር የነበረውን ተቀማጭ ገንዘብ የ2005 ሪፖርትን ይፋ ሲያደርግ ከቀደመው ዓመት 39.7 በመቶ ብልጫ በማሳየት 122 ቢሊዮን ብር መድረሱን ይፋ ማድረጉም ይታወሳል፡፡
ባንኮቹ አሁን ለደረሱበት የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት በዋናነት እየተጠቀሰ ያለው ሁሉም ባንኮች በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት የቅርንጫፍና የደንበኞቻቸውን ቁጥር በማሳደጋቸው ነው፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ አወት ተክሌ እንደገለጹትም፣ የአገሪቱ የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት ከኢኮኖሚ ዕድገቱ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከብሔራዊ ባንክ ጀምሮ የፋይናንስ ተቋማት የቁጠባ ባህል እንዲያድግ የተሠራው ሥራ ከፍተኛ በመሆኑ የተገኘ ውጤት ተደርጐ ይቆጠራል፡፡ ባንኮች ተደራሽነታቸውን ማስፋታቸውም ለቁጠባ ዕድገቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ያስታወሱት አቶ አወት፣ ባንኮቹ ወደ ኅብረተሰቡ እየተጠጉ በሄዱ ቁጥር ቆጣቢዎች እየጨመሩ መሄዳቸው የሚጠበቅም ነው ብለዋል፡፡
በአንፃሩ ግን የባንኮች ተቀማጭ ገንዘቡ መጠን በዚህን ያህል ማደጉ ብቻውን ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን አንደሚያሳይ የሚገልጹ አሉ፡፡ አቶ አወትም በተቀማጭ ገንዘባቸውና በሚሰጡት ብድር መካከል ያለው ልዩነት የሚታይበት መሆኑን ገልጸው፣ ጉዳዩ በደንብ መጠናት አለበት ይላሉ፡፡
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመልክቱት ባንኮች ከነበራቸው ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ ለብድር ያዋሉት ከ20 እስከ 30 በመቶውን ብቻ በመሆኑ ተቀማጭ ገንዘባቸውን በአግባቡ እየተጠቀሙበት ነው ማለት እንደማይቻል ነው፡፡
አቶ አወት እንደገለጹት ደግሞ በአሁኑ ጊዜ የተቀማጭ ገንዝብ እያደገ ቢሆንም ባንኮች እየሰጡ ያሉት የብድር መጠን አነስተኛ የሆነበት ምክንያት በተለያየ መንገድ የሚታይ ነው፡፡ አንዱ ምክንያት የሚሆነው ብድር ለመስጠት የሚጠየቁት ማስያዣ ከፍተኛ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡
የዓለም ባንክ ጥናት እንደሚያሳየው አንድ ብር ለማበደር የሁለት ብር ከአርባ ማስያዣ የሚፈለግ በመሆኑ ይህንን አሟልቶ ለመቅረብ ያለው ክፍተት በተቀማጭ ገንዝባቸው ልክ ብድር እንዳይሰጡ አድርጓቸዋል ማለት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
በአንፃሩ ግን ብድር የሚፈልጉት በርካታ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ አወት፣ የዓለም ባንክ ባለፈው ዓመት ባካሄደው ጥናት ከ1,000 ብድር ፈላጊ አመልካቾች ውስጥ ብድር ማግኘት የቻሉት ከሁለት እስከ ሦስት አመልካቾች ብቻ በመሆናቸው እንዲህ ዓይነቱ ክፍተት ሊደፈን የሚችልበት አሠራር መኖር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡