Tuesday, February 27, 2024

የትብብር መንፈስ እየሰፈነበት የሚገኘው የዓባይ ፖለቲካ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኤፍራተስ ወንዝ ታሪካዊና ቱርክን እንደ እትብት ከሶሪያና ኢራቅ ጋር ያገናኘ የተፈጥሮ ገፀ በረከት ነው፡፡

የኤፍራተስ ወንዝ ዓመታዊ የውኃ መጠን 32 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የዚህ የውኃ መጠን 90 በመቶ የሚገኘው ከቱርክ ሲሆን፣ የቱርክን ግዛት ለቆ ወደ ሶሪያ ግዛት ይዘልቃል፡፡ በሶሪያ ሌሎች ገባሪዎችን አቀላቅሎ ማሳረጊያውን በኢራቅ የሚያደርግ ወንዝ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. እስከ 1946 ድረስ በሦስቱ አገሮች መካከል የወንዙን ውኃ አጠቃቀም የተመለከተ ስምምነት አልነበረም፡፡ በ1946 ስምምነት የተፈፀመው በዘመኑ ልዕለ ኃይል በነበረችው ኢራቅ ግፊት ሲሆን፣ የኤፍራተስ ወንዝ ምንጭ የሆነችው ቱርክ የቀድሞዋን ኃያል ኢራቅ ሳታማክር የወንዙ አቅጣጫን እንዳትቀይር ተገዳ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በዓመታት ሒደት የቱርክ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አቅም እየተቀየረ መምጣቱ አልቀረም፡፡

በመሆኑም የቱርክ የኢኮኖሚ ዕድገት የአካባቢው የኃይል ሚዛንና የፖለቲካ ተፅዕኖን እየለወጠው እንደመጣ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የቱርክ የተፈጥሮ በረከት የሆነውን የኤፍራታ ወንዝን ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመቀየር እ.ኤ.አ. በ1966 ከባን የተለየ የግድብ ፕሮጀክቷን ጀምራለች፡፡ ፕሮጀክቱ የቱርክን የኢንጂነሪንግ አቅም ያንፀባረቀ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ፕሮጀክቱ 13 የመስኖ ልማቶችን በመጀመሪያነት ወጥኖ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ 22 ግድቦችንና 19 የኃይል ማመንጫዎችን ያካተተ መሆኑን መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ስትራትፎር የስለላ ድርጅት መረጃ ያመለክታል፡፡

ከኃይል ማመንጫዎቹ መካከል አታቱርክ የተሰኘው የኃይል ማመንጫ ግድብ የመጀመሪያ ግንባታ የተጠናቀቀው በ1990 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይሁን እንጂ የአታቱርክ ኃይል ማመንጫን ሥራ ለማስጀመር ግድቡ በውኃ መሙላትን ይጠይቃል፡፡ በዚህ የተነሳ እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ ወር 1990 የአታቱርክ ግድብን ለመሙላት በሚል ምክንያት የቱርክ መንግሥት የኤፍራተስ ወንዝን ለአንድ ወር ያህል መገደቡን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ቱርክ የአታቱርክ ግድብን በመጠቀም የኤፍራተስን ፍሰት ከማቆሟ አንድ ዓመት ቀድማ ለሶሪያና ኢራቅ ዕቅዷን ዘርዝራ አሳውቃለች፡፡ ቢሆንም ድርጊቱ በሁለቱ የግርጌ አገሮች እንደ ድፍረት ተቆጠረ፡፡ ይሁን እንጂ ወቅቱ ያመጣው የሚዛን ለውጥ ቱርክን ያፈረጠመ በመሆኑ ድርጊቱን ከማውገዝ ያለፈ የወጣ ነገር የለም፡፡ ከዚህ ባለፈም አሁን ላይ የኤፍራተስ ወንዝ ቱርክ በኢራቅና በሶሪያ ኩርዶች ላይ ትልቁ የፖለቲካ መሣሪያዋ አድርጋ እየተጠቀመችበት ትገኛለች፡፡

የግብፅ የውኃና መስኖ ሚኒስትር የነበሩት ሞሐመድ አብዱል ሙታሊብ ከላይ የተገለጸውን የቱርክና የአካባቢው አገሮች የውኃ ፖለቲካ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ በመሳብ የፖለቲካ ውጥረትን በኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን ለመፍጠር ከሞከሩ የግብፅ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ሚኒስትሩ ሞሐመድ አብዱል ሙታሊብ እ.ኤ.አ. በፌብርዋሪ 2014 በታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ በሰጡት አስተያየት ‹‹ቱርክ የአታቱርክ ኃይል ማመንጫ ግድብን በገነባችበት ወቅት የሶሪያና የኢራቅ ሕዝቦችን በውኃ ጥም አሰቃይታለች፡፡ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ጥሳለች፡፡ አሁን አጠንክሬ ማለት የምፈልገው ግብፅ ሶሪያንና ኢራቅን አይደለችም፡፡ ኢትዮጵያም ቱርክን አይደለችም፤›› በማለት ፀብ አጫሪ ንግግር አድርገዋል፡፡

ሚኒስትሩ ይህንን ንግግር ያደረጉት የቱርክ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያን እየጐበኙ በነበረበት ወቅት ነው፡፡

የህዳሴው ግድብ የጫረው ፖለቲካ

የቀድሞው ጠቅላይ መለስ ዜናዊ በ2003 ዓ.ም. የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ይፋ ካደረጉ በኋላ በዚያው ዓመት የሚያዚያ ወር ላይ የመሠረት ድንጋዩን በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ጉባ ወረዳ በተራሮች በተከበበው ሸለቆ ውስጥ አኑረዋል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ያነቃነቀው ይህ የኃይል ማመንጫ ግድብ ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ 6,000 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል፡፡ የግድቡ ይፋ መሆንና የግንባታው መጀመር በኅብረተሰቡ ወጪውን ለመሸፈን በሚያደርገው መዋጮ ወዲያውኑ ታጅቧል፡፡

የግድቡ ግንባታ የተጀመረበት ወቅት በግብፅ ከተቀጣጠለው የዓረብ አብዮት ጋር የተገጣጠመ በመሆኑ ከግብፅ በኩል በግድቡ ላይ የተሰነዘረው ተቃውሞ የገዘፈ አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ የዓረብ አብዮት በግብፅ በተሳካ ሁኔታ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ሥልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ሙርሲ የህዳሴው ግድብ ግንባታን በጨለምተኛ ስሜት የተመለከቱ የሚል ትችት አስከትሎባቸዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ የዓባይ ወንዝ ተፈጥሯዊ መስመርን ለግንባታው ሲባል መቀየሱ ከፕሬዚዳንት ሙርሲ አስተዳደር ውስጥና በሌሎች የግብፅ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ ቁጣን መቀስቀሱ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ የግብፅ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችንና ታዋቂ ግለሰቦችን በጉዳዩ ላይ ፕሬዚዳንት ሙርሲ ባወያዩበት ወቅት በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት እስከ መክፈት የዘለቀ ውይይት አድርገዋል፡፡

‹‹ከግብፅ የውኃ ድርሻ አንድ ጠብታ እንኳን ቢቀር አማራጩ ደም ነው›› ማለታቸው በአካባቢው የፖለቲካ ውጥረትን ቀስቅሶ የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በግብፅ በኩል ተፈጥሮ ከነበረው የከረረ ጫፍ ፍፁም ተቃራኒ የሆነ የሰከነ አመለካከት በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል መንፀባረቁ የፖለቲካ ፍጥጫው እንዳይባባስ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ ምንም እንኳን የፕሬዚዳንት ሙርሲ አስተዳደር ለሁለተኛ ጊዜ በተቀሰቀሰው የዓረብ አብዮት መመታቱና አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኙት ፊልድ ማርሻል አብደል ፈታህ ኤልሲሲ ወደ ሥልጣን መምጣት ዋነኛው ምክንያት ቢሆንም፡፡

በትብብር መንፈስ የተጋረደው ውጥረት

የግብፅ ጦር የቀድሞ አዛዥ የነበሩት ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ ኤልሲሲ በ23ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመሳተፍ በኢኳቶሪያል ጊኒ ማላቡ እ.ኤ.አ. በጁን ወር 2014 ተገኝተዋል፡፡

ከዚህ ጉባዔ ጐን ለጐን ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሣለኝ ጋር በመገናኘት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡ ሁለቱ መሪዎች በማላቡ ከተወያዩ በኋላ ባወጡት መግለጫ ‹‹በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ሁለቱ አገሮች ውይይትና ትብብርን መሠረት አድርገው ለጋራ ጥቅማቸው ይሠራሉ›› በሚል መርህ ላይ መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል በፕሬዚዳንት ሙርሲ ዘመን ተመሥርቶ ብዙም መጓዝ ያልቻለው የኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን በግድቡ ዙሪያ ለመወያየት መሥርተውት የነበረ ኮሚቴ ውይይት ዳግም እንዲያንሰራራ እንዲሁም ቀደም ሲል ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን በግድቡ ግንባታ ዙሪያ በተጨማሪነት እንዲጠኑ ያቀረባቸው ሁለት ምክረ ሀሳቦች የሚተገብሩበት መንገድ እንዲፋጠን ሁለቱ መሪዎች በማላቡ ወስነዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች የትብብር ውይይትና የሦስትዮሽ የቴክኒክ ጉባዔው በሦስት ወራት ውስጥ ወደ ሥራው እንዲገቡ በተስማሙት መሠረት ከየአንዳንዱ አገር አራት ባለሙያዎች የተወከሉበት የሦስትዮሽ የቴክኒክ ኮሚቴ እ.ኤ.አ. በሴፕቴምበር ወር 2014 በአዲስ አበባ ተመሥርቶ በቀጥታ ወደ ሥራው ገብቷል፡፡

በወቅቱ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው ‹‹አሁን በግብፅ በኩል የፖለቲካ ለውጥ ያለ ይመስላል፡፡ ከዚህ ቀደም በአንድ ነጥብ ላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ ረዥም ጊዜን ይፈጃል፡፡ በሦስት ቀናት ውይይት ግን በግድቡ ላይ በተጨማሪነት እንዲጠኑ የተባሉ ሁለት ምክረ ሐሳቦችን ተግባራዊ የምናደርግበት መስፈርትን፣ የሦስትዮሽ የቴክኒክ ኮሚቴው የሚመራበትን ደንብ በስምምነት አጽድቀናል፤›› ብለው ነበር፡፡

የሦስትዮሽ የቴክኒክ ኮሚቴው ባወጣው መስፈርት መሠረት በዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን የቀረቡትን ሁለት ምክረ ሐሳቦች ለመተግበር እያንዳንዱ አገር ሦስት ኩባንያ በራሱ መርጦ እንዲያቀርብ በተስማሙት መሠረት በኦክቶበር 2014 በካይሮ ግብፅ ተገናኝተዋል፡፡ በዚሁ መሠረት የቀረቡ አምስት ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅቶች የጨረታ ዶክመንቶቻቸውን እንዲያቀርቡ ደብዳቤ እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኩባንያዎቹን ለመምረጥ ከተጠቀሙባቸው መስፈርቶች መካከል የዓለም ባንክ የጨረታ መስፈርት አንዱ ሲሆን፣ ሊመረጥ የሚችለው ኩባንያ ቢያንስ ለ20 ዓመታት የሚፈለገው የሥራ ልምድ ያለው፣ ለዚህም የሰነድ ማስረጃ ማቅረብ የሚችልና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

ኩባንያዎቹን ለመምረጥ የወሰደው ጊዜ በጣም ረጅም ቢሆንም እ.ኤ.አ. በአፕሪል 2015 አዲስ አበባ ላይ ሁለት ኩባንያዎች ጥናቱን እንዲያከናውኑ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

ሁለት ቀናትን በፈጀው የአዲስ አበባው ውይይት በኢትዮጵያና በሱዳን በኩል የቀረበው ቢአርኤል ኢንጂነርስ የተባለው ኩባንያ በዋና አጥኚነት እንዲሁም በግብፅ በኩል የቀረበው የኔዘርላንዱ ዴልታ ፌዝ ኩባንያ በተባባሪነት ተመርጠዋል፡፡

ኩባንያዎቹ ቢመረጡም ለተወሰነ ጊዜ በሦስትዮሽ የቴክኒክ ኮሚቴው መካከል መግባባት ላይ መድረስ ባለመቻሉ ወደ ጥናቱ ሥራ መግባት አልተቻለም፡፡

የኩባንያ ቅጥሩ ጊዜ የፈጀበት ምክንያት ምን እንደሆነ እንዲያብራሩ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ የወሰን ተሻጋሪ ተፋሰሶች አማካሪ አቶ ተፈራ በየነ ‹‹የተመረጡት ኩባንያዎች ከአንድ አገር ጋር በተደጋጋሚ በመሥራታቸው ሊሆን ይችላል›› ብለዋል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ጥናቱ በዚህ መልኩ ማለትም በሁለት ኩባንያዎች ጥምረት ማከናወን ያልተለመደ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ በሐምሌ ወር መጨረሻ አካባቢ በሱዳን ካርቱም በተደረገ የሦስትዮሽ የቴክኒክ ኮሚቴው ስብሰባ ልዩነቶችን ማጥበብ ተችሏል፡፡ በዚህ ስብሰባ ቢአርኤል ኢንጂነርስ የተባለው ኩባንያ ዋና የፕሮጀክቱ ተጠሪ ማለትም ሕጋዊ ኃላፊነቶችና የቴክኒክ ጉዳዮች የሚመለከቱት ሆኖ መመረጡን አቶ ተፈራ ገልጸዋል፡፡ የኔዘርላንዱ ኩባንያ 30 በመቶ የሚሆነውን ሥራ ለመሸፈን የሚያስችሉ ባለሙያዎችን በመመደብ ከቢአርኤል ኩባንያ ጋር በጋራ ያጠናል፡፡

ቢአርኤል ኢንጂነርስ የተባለው ኩባንያ በተያዘው ነሐሴ ወር አጋማሽ የባለሙያዎችን ስብጥርና የቴክኒክ ሠነድ ለሦስቱም አገሮች በማቅረብ ሦስቱ አገሮች በድጋሚ አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተው ኩባንያው ባቀረበው ሠነድ ላይ በድጋሚ ይደራደራሉ፡፡ በስምምነት ከተጠናቀቀም ከኩባንያው ጋር የፕሮጀክት ኮንትራት ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ነገር ግን ቢአርኤል የተባለው ኩባንያ ላይ ግብፅ ጥርጣሬ እንዳላት ይነገራል፡፡ ይህም የሚመነጨው ኩባንያው በርካታ ሥራዎችን በኢትዮጵያ በመከናወኑ እንደሆነ ያገኘናቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ይህ ሀቅ በኢትዮጵያ በኩልም በውይይቱ ወቅት ያልተካደ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ኩባንያው በኢትዮጵያ ያከናወናቸው የተለያዩ ጥናቶችና የማማከር ሥራዎችን ያከናወነው በዓለም ባንክ ተቀጥሮ መሆኑን ነው፡፡ የሦስትዮሽ የቴክኒክ ኮሚቴው ኰባንያ ለመምረጥ ከተጠቀመባቸው መስፈርቶች አንዱ የዓለም ባንክ የጨረታ መሰፈርት አንዱ በመሆኑ ኩባንያው በመጨረሻ በሦስቱም አገሮች ይሁንታ አግኝቶ ዋና አማካሪ ሊሆን በቅቷል፡፡

ይሁን እንጂ በግብፅ በኩል አሁንም ጥርጣሬ በመኖሩ የኔዘርላንዱ ኩባንያ ተሳትፎ ላይ ጫና በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ በአዲስ አበባ በሚካሄደው የሦስትዮሽ የቴክኒክ ኮሚቴ ጉባዔ ላይ የዴል ታሬዝ ኩባንያ ባለሙያዎች በጥናቱ ላይ የሚኖራቸው ድርሻ አሁንም አከራካሪ ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡ በተለይ ደግሞ የዴልታሬዝ ኩባንያ ባለሙያዎች በኃይድሮ ሲሙሌሽን ሞዴል ጥናቱ ላይ እንዲሳተፉ እንደሚፈለግ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ይህ የጥናት ዓይነት ታላቁ የህዳሴ ግድብ በዓባይ ተፋሰስ ማሃል መገንባቱ በወንዞች ፍሰት ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ በተለያዩ የዝናብ ወቅቶች ይኖረዋል የሚለውን የሚያሳይ በመሆኑ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን የነጋገርናቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

በመሆኑም ግብፅ የምትሻቸው ባለሙያዎች በዚህ ጥናት መሳተፍ በግብፅ በኩል ያለውን የውኃ ፍሰቱ ይቀንሳል የሚል ሥጋት ለማጥራት አልያም ለማጉላት የሚጠቀም በመሆኑ ነው፡፡

በኩባንያው አመራረጥ ሒደቱና የጥናቱ ውጤት አተገባበር ላይ ያነጋገርናቸው የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ተፈራ የጥናቱ ውጤት የግድቡን ግንባታ ሊያስተጓጉል ወይም የግድቡን ውኃ የመያዝ አቅም ሊቀንሰው አይችልም በማለት ይከራከራሉ፡፡

በግብፅ በኩል የነበረው የበላይነት መለወጥ

ኢራቅ በቀድሞው ዘመን በነበራት የበላይነት ቱርክ የኤፍራተስ ወንዝን አቅጣጫ ለመቀየር ከመምከሯ በፊት ለኢራቅ የማሳወቅ ግዴታን እ.ኤ.አ. በ1946 አስፈርማት ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ተቀይሮ በ1990 ቱርክ ሙሉ በሙሉ የኤፍራተስ ወንዝን ፍሰት ለአንድ ወር ገትታለች፡፡

የግብፅ የበላይነት ለዘመናት በዓባይ ተፋሰስ አገሮች ላይ ፀንቶ የቆየ ቢሆንም ዛሬ ላይ ይህ ተለውጧል፡፡

ኢትዮጵያ የዓባይ ተፋሰስን በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የማልማት አቋሟ ለዘመናት የነበረና መንግሥታት በተለዋወጡ ቁጥር ያልተቀየረ ነው ሲሉ አቶ ተፈራ ይገልጻሉ፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን የቆየ እምነቷን ወደ መሬት ማውረዷና የህዳሴውን ግድብ መጀመሯ የቆየውን የግብፅ የበላይነት ከመለወጥ ባለፈ የመተባበር መንፈስ እንዲመጣም ጉልህ ሚና አለው ብለዋል፡፡                  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -