Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ማሽኖች አስገጠመ

ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ማሽኖች አስገጠመ

ቀን:

ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የኤምአርአይና የሲቲ ስካን (MRI and CT Scan) የሕክምና መሣሪያዎች አስገጠመ፡፡ ማሽኖቹ በሆስፒታሉ መገጠማቸው የሕክምና ሒደቱን እንደሚያቀላጥፍና ታካሚዎችንም ካልተፈለገ እንግልት እንደሚያድን፣ ዓርብ ነሐሴ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በቅጥር ግቢው በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ ሆስፒታሉ አስታውቋል፡፡

ማሽኖቹን ለማስመጣት ረዘም ያለ ጊዜ እንደፈጀ የተናገሩት የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር መሐመድ፣ ላለፉት አምስት ዓመታት ማሽኖቹ የሚገጠሙበትን ሕንፃ ከመገንባት ጀምሮ በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ማሽኖች ባለመኖራቸው በርካታ ታካሚዎች ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት ይዳረጉ ነበር፡፡

በአንድ የግል ሆስፒታል ምርመራውን ለማግኘት እስከ 2,000 ብር እንደሚያስከፍል፣ አቅሙ የሌላቸው የነፃ ታካሚዎች ደግሞ ሆስፒታሎቹ በሚጠይቁት ዋጋ ተስፋ ቆርጠው ይቀሩ እንደነበር ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ ‹‹በሆስፒታላችን ከሚስተናገዱ 85 በመቶ የሚሆኑት የነፃ ታካሚዎች ናቸው፡፡ የሲቲ ስካን ምርመራ ሲያስፈልጋቸውም በሆስፒታሉ ባለመኖሩ የግድ ወደ ግል ሕክምና ተቋማት ይሄዳሉ፡፡ ነገር ግን የብዙዎች አቅም ስለማይፈቅድ ሳይታከሙ ይቀራሉ፤›› ብለዋል፡፡

- Advertisement -

በሌላ በኩል አቅሙ ኖሯቸው የሚመረመሩ ታካሚዎች የምርመራ ውጤታቸው በቶሎ ስለማይደርስ፣ አስፈላጊውን ሕክምና ሳያገኙ በሽታቸው ሥር እንደሚሰድ ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶ/ር አብዱልቃድር ገለጻ፣ ሆስፒታሉ አገልግሎቶቹን መጀመሩ ችግሮቹን ያቃልላል፡፡ በግል ሆስፒታሎች እስከ 2,000 ብር የሚያስከፍል ምርመራ በ500 ብር ያልቃል፡፡ ይህም የመክፈል አቅሙ ላላቸው ሰዎች የወጣ ዋጋ ሲሆን፣ መክፈል የማይችሉ ሕክምናውን በነፃ ያገኛሉ፡፡

ከዚህ ቀደም ሆስፒታሉ ይጠቀምበት የነበረው ሲቲ ስካን ስምንት ስላይስ (የመመርመር አቅም) እንደነበረው የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ አገልግሎት መስጠት ካቆመ ዓመታት መቆጠራቸውን፣ በአንፃሩ ደግሞ አዲሱ ሲቲ ስካን 128 ስላይስ አቅም እንዳለው፣ በአንድ ጊዜም በርካታ ምርመራዎችን ማድረግ የሚችል የደም ሥር፣ የልብ፣ የአንጐልና ሌሎችም የምርመራ ዓይነቶችን እንደሚያከናውን አስረድተዋል፡፡

የሲቲ ስካን ማሽኖች በሌሎች የሕክምና ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ቢሆንም፣ የአገሪቱ ሪፈራል ሆስፒታል በሆነው በጥቁር አንበሳ አለመኖሩ ግን የአሠራር ችግር መሆኑን፣ ማሽኖቹንም ለማስገጠም የወሰደው ረዘም ያለ ጊዜም አግባብነት እንደሌለው ተነግሯል፡፡

‹‹ማሽኖቹ ጥቂት በማይባሉ የጤና ሳይንስ ኮሌጆችና ሆስፒታሎች ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን በሕክምናው ስፔሻላይዝድ አድርገው የሚወጡ ባለሙያዎችን የሚያፈራው ኮሌጅ ማሽኑ አልነበረውም፡፡ ይህም የሚፀፅት ነው፤›› ያሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ፣ ሆስፒታሉ ማሽኖቹን ለማስተከል የበጀት ችግር የነበረበት ቢሆንም ጉዳዩን ለውይይት አቅርቦት እንደማይታወቅ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በየዓመቱ ትርፍ በጀት ይመልሳል፡፡ ነገር ግን በሆስፒታሉ ያለውን የበጀት እጥረት አውቀን ቢሆን ኖሮ ይመለስ የነበረውን ትርፍ በጀት ወደ ሆስፒታሉ ማዞር እንችል ነበር፤›› በማለት የነበረውን ክፍተት ኮንነዋል፡፡ አክለውም የሆስፒታሉን የአገልግሎት ጥራት የማሳደግ ኃላፊነቱ የሁሉም ባለድርሻ አካላት መሆኑን ጠቁመው፣ የአሠራር ሥርዓቱን ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ ክትትል ሊደረግበት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜም የሲቲ ስካን ማሽኑ አገልግሎት የጀመረ ሲሆን፣ በቀጣይ የኤምአርአይ ማሽኑ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ሜዲካል ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...