የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የሃይማኖቶች ነፃነት ኮሚሽን በእነ አቡበከር አህመድ መዝገብ የተከሰሱ ግለሰቦች ላይ የተሰጠው የጥፋተኝነት ብይንና ቅጣት ተገቢነት የለውም አለ፡፡
ሐምሌ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት በተከሳሾቹ ላይ ከሰባት እስከ 22 ዓመታት ፅኑ እስራት መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
‹‹ተከሳሾቹ ወንጀለኞች ሳይሆኑ ሰላማዊ የሃይማኖት ነፃነት አቀንቃኞች ናቸው፤›› ያሉት የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ዶ/ር ሮበርት ጆርጅ፣ ‹‹የክስ ሒደቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችንና ተቃዋሚዎችን ፀጥ ለማድረግ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን መጠቀም መቀጠሉን ያሳያል፤›› ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ የአሜሪካ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ተቃውሞውን እንዲያቀርብ ጥሪ አድርጓል፡፡ የኮሚሽኑ አባላት እ.ኤ.አ. በ2012 ኢትዮጵያን ሲጎበኙ የተከሳሾቹ የፍርድ ሒደት ችግሮች እንደነበሩበት መረዳታቸውን፣ ከእነዚህም መካከል አንዱ የእስር አያያዛቸው በሕግ መሠረት የማይከናወን እንደነበር አስታውሷል፡፡
በኮሚሽኑ መግለጫ ላይ መንግሥት አስተያየት እንዲሰጥ ጥረት ቢደረግም፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት መግለጫውን እንዳላዩት ገልጸዋል፡፡