Saturday, September 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ግብፅ በ8.5 ቢሊዮን ዶላር አዲሱን የስዊዝ ካናል ማስፋፊያ ገነባች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግብፅ በ8.5 ቢሊዮን ዶላር የገነባችውን አዲስ የስዊዝ ካናል የማስፋፊያ ፕሮጀክት ሐምሌ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. መርቃ ክፍት አደረገች፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ በርካታ የዓለም መሪዎች በተገኙበት ደማቅ ሥነ ሥርዓት ተመርቆ ለሥራ ክፍት የሆነው ይኼው አዲስ ካናል ሜዲትራንያን ባህርንና ቀይ ባህርን የሚያገናኝ ሁለተኛው ክፍል ነው፡፡

ሥራውን እ.ኤ.አ. በ1961 ዓ.ም. ተጀምሮ በ1969 የተጠናቀቀውና ሁለቱን የውኃ አካላት ያገናኘው የመጀመርያው ስዊዝ ካናል፣ የዓለምን ፖለቲካ ከቀየሩት መካከል አንዱ ታሪካዊ ክስተት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ አዲሱ የውኃ መተላለፊያ መስመር የዚሁ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል መሆኑን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡

የግብፅ ባለሥልጣናት አዲሱ የውኃ መስመር የግብፅ ሕዝብ ኩራት መገለጫ እንደሆነ እየተናገሩ ሲሆን፣ ‹‹የዓለምን ካርታ እንደ አዲስ የሚቀይር ስጦታ›› ተብሎለታል፡፡

በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ተገኝተው የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ፣ ‹‹ግብፃውያንን ይኼ ፕሮጀክት ዕውን እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፤›› ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በተጨማሪ፣ ‹‹የዚህ ፕሮጀክት መሠረት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግብ ከማሳካት የላቀ ስኬት የሚያሳይ በመሆኑ ለግብፃውያን ክብርን፣ መረጋጋትንና ፍትሕን ያጎናፅፋል፤›› ብለዋል፡፡

በአገሪቱ ከቱሪዝም ቀጥሎ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኘው ነባሩ የስዊዝ ካናል አገልግሎት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻውን አምስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የአሁኑ የማስፋፊያ ፕሮጀክት የግብፅ መንግሥት ስዊዝ ካናልን የዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስና የንግድ መነሃሪያ ለማድረግ ያለው ዕቅድ አካል መሆኑ እየተነገረ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2023 በዓመት ከ13 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስገኛል ተብሎ ተገምቷል፡፡

በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ላይ በርካታ የዓረብና የአፍሪካ መሪዎች ታድመዋል፡፡ ከአውሮፓ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ኦላንድና የግሪክ ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሲስ ሲፕረስ ተገኝተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽርም ከተጋባዥ እንግዶች መካከል ናቸው፡፡

የአዲሱን የስዊዝ ካናል ምርቃት ሥነ ሥርዓት ከኢትዮጵያውያንና ከዲፕሎማቶች ጋር በመሆን አዲስ አበባ በሚገኘው የግብፅ ኤምባሲ በቀጥታ የተከታተሉት በኢትዮጵያ የግብፅ ተሰናባች አምባሳደር ሙሐመድ ኢድሪስ፣ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሥነ ሥርዓቱ በመገኘታቸው ከፍተኛ ደስታ የተሰማቸው መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹የሁለቱ እህትማማችን አገሮች ግንኙነት አመላካች ነው፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች