- የዋልድባ ገዳም መነኮሳትም ክሳቸው ተቋርጦ ይፈታሉ ተብሏል
መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋትና አገራዊ መግባባት ለመፍጠር በማለት ታኅሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት፣ ተጠርጣሪዎችንና ፍርደኞችን በሁለት ወራት ውስጥ እንደሚፈታ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ ቀናት ቢቀሩትም እንደሚቀጥል ተጠቆመ፡፡
የክስ ጉዳያቸው በፍርድ ቤቶች በመታየት ላይ ያሉ ተጠርጣሪዎችና ወንጀል መፈጸማቸው ተረጋግጦባቸው የቅጣት ውሳኔ የተላለፉባቸው ፍርደኞች መንግሥት ያወጣውን መሥፈርት የሚያሟሉ ሆነው ከተገኙ፣ እስከ መጋቢት ወር መጀመርያ ድረስ እየተጣራ እንደሚለቀቁ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በዚህም መሠረት በመላው አገሪቱ ማረሚያ ቤቶች ከሚገኙ ተጠርጣሪዎችና ፍርደኞች መካከል ከሰባት ሺሕ በላይ የሚሆኑት ክሳቸው መቋረጡና በይቅርታ መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡
ነገር ግን በቀጣይም የክስ ሒደታቸው እየታየ የሚቋረጥላቸውና በይቅርታ የሚፈቱ እንዳሉ የሪፖርተር ምንጮች አረጋግጠው፣ ምንም እንኳን በመንግሥት በኩል የተነገረው የመፍቻ የሁለት ወራት ጊዜ ሊጠናቀቅ ቀናት የቀሩት ቢሆንም፣ ሊቀጥል እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ በሽብር ተግባር ወንጀል ክስ የተመሠረተባቸው የዋልድባ ገዳም ሁለት መነኮሳትን ጨምሮ ሌሎች ተከሳሾችም ክስ እንደሚቋረጥና ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የሚገኙም በይቅርታ እንደሚፈቱ አስረድተዋል፡፡
መንግሥት የሰጠው የጊዜ ገደብ ግን ቅዳሜ መጋቢት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደሚያበቃ ታውቋል፡፡