Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለደቡብ ሱዳን ቀውስ ዕልባት ያስገኛል የተባለው ድርድር እክል ገጠመው

ለደቡብ ሱዳን ቀውስ ዕልባት ያስገኛል የተባለው ድርድር እክል ገጠመው

ቀን:

ዕልባት ሳያኝ ለ19 ወራት የዘለቀውን የደቡብ ሱዳናውያን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም በአዲስ አበባ የመጨረሻ መፍትሔ እንዲደረግበት የተጀመረው ድርድር አሁንም ችግር እየገጠመው መሆኑ ተጠቆመ፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት በተደረገው የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጉብኝት የአሜሪካ መንግሥት ጠንከር ያለ ማዕቀብ በሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች እንደሚጥል ካስታወቀ በኋላ፣ የአሁኑ ድርድር የተሻለ መፍትሔ እንደሚያመጣ ቢጠበቅም የደቡብ ሱዳን መንግሥት ተቃዋሚ ወኪሎች በአዲስ አበባ ተገኝተው ውይይቱን እንዳይካፈሉ፣ የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር መንግሥት ከጉዞ እንዳገዳቸው ቀደም ሲል ገልጸው ነበር፡፡

የጉዞ ዕገዳውን ተከትሎም ውይይቱን በማደራደር የሚመራው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ጉዳዩ እንዳሳሰበውና በተደራዳሪዎቹ ላይ የተደረገው የጉዞ ማዕቀብ እንዲቆም፣ የደቡብ ሱዳንን መንግሥት አሳስቦ ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ድርድሩ ሐምሌ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. በሸራተን ሆቴል ተጀምሯል፡፡ በማግሥቱ ነሐሴ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ኢጋድ በሳልቫ ኪር መንግሥት የተደረገውን የጉዞ ዕገዳ አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡

በተለይም በድርድሩ ከሚጠበቁት ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆኑት ላም ኦኮል ሐምሌ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ጁባ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ፣ ከፕሬዚዳንቱ በተላለፈ ትዕዛዝ ወደ አዲስ አበባ እንዳይጓዙ መከልከላቸውን መግለጫው ጠቁሟል፡፡

በአዲሲቷ አገር የተከሰተውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም በኢጋድ የሚመራው አደራዳሪ ቡድን ብዙ ጥረት ቢያደርግም ያለምንም ውጤት እዚህ መዝለቁ ይታወቃል፡፡ ሁለቱም ተፋላሚ ቡድኖች ለሰላም ጥረቱ አለመሳካት እርስ በርሳቸው ሲወቃቀሱ ቆይተዋል፡፡

በኢጋድ ሲመራ የቆየው የሰላም ድርድር ባለመሳካቱ አሜሪካ፣ ቻይና፣ የአውሮፓ ኅብረትና የአፍሪካ ኅብረትና ሌሎች አገሮች ተጨምረውበት ድርድሩ ‹ኢጋድ ፕላስ› በሚል ስያሜ እንዲቀጥል መደረጉ ይታወቃል፡፡

በአሁኑ የኢጋድ ፕላስ ድርድርም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት እስከ ነሐሴ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ሁለቱ ወገኖች ስምምነት ላይ ደርሰው ጦርነቱን ሙሉ ለሙሉ እንዲያቆሙ የሚያስገድድ ነው ተብሏል፡፡ በዚሁም ውይይት መጠነ ሰፊ ክርክር እንደሚደረግበትና በሥልጣን መጋራትና በሽግግር ምሥረታ ላይ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ዋነኛው ግብ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በተለይም የአሜሪካ ግፊት እንዳለው የተነገረውን የእርቅ ሰነድ (Compromise Document) ላይ ድርድሩ የቀጠለ ሲሆን፣ ሰነዱ የሥልጣን ክፍፍልን በአግባቡ የሚመራ አስፈጻሚ አካልን መሰየምን ያካትታል፡፡ በሰነዱ መሠረት የአስፈጻሚው አካል 53 በመቶ የሚሆነውን የሥልጣን ድርሻ ለገዢው ፓርቲ (የሳልቫ ኪር መንግሥት) የሚሰጥ ሲሆን፣ 33 በመቶውን ለሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመስጠት የመፍትሔ ሐሳብ ያቀርባል፡፡ እንዲሁም 14 በመቶ የሚሆነውን ሥልጣን ለቀድሞ ታሳሪ ባለሥልጣናት እንዲሆን ሐሳብ አለው፡፡

ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በአዲስ አበባው ጉብኝታቸው ወቅት ከኢጋድ መሪዎችና ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በጋራ ሲመክሩ፣ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች በፍጥነት የኢጋድን አደራዳሪነት አክብረው ወደ መፍትሔ ካልገቡ አሜሪካ ‹‹አማራጭ መንገድ›› ለመከተል እንደምትገደድ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፡፡

የኢጋድ ዋና ልዩ መልዕክተኛና አደራዳሪው አምባሳደር ሥዩም መስፍን ድርድሩን በይፋ በከፈቱበት ወቅት፣ ‹‹አሁን ወሳኝ መንገድ ላይ ደርሰናል፡፡ እያንዳንዱ ተደራዳሪ የደቡብ ሱዳንን መፃኢ ዕጣ ፈንታ የሚወስን ተግባር የሚወሰኑበት ሰዓት ላይ ነን፤›› በማለት የድርድሩን ውጤት አስፈላጊነት ገልጸዋል፡፡

ዋና አደራዳሪው ይህን ቢሉም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በድርድሩ ላይ መሳተፍ እንዳይችሉ የሳልቫ ኪር መንግሥት ማደናቀፉ፣ አሁንም የሚጠበቀውን ተስፋ እንዳያደበዝዘው ሥጋት አጥልቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...