Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የባንኮች ማኀበር ፕሬዚዳንቱንና ምክትሉን መረጠ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሁሉንም የግልና የመንግሥት ባንኮች በአባልነት የያዘው የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር፣ የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሃባን ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመት በፕሬዚዳንትነት እንዲያገለግሉት መረጣቸው፡፡

ማኅበሩ በቅርቡ ባደረገው ምርጫ በምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲያገለግሉ የተመረጡት ደግሞ፣ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ ናቸው፡፡ ከአቶ አቤ ቀደም ብሎ ማኅበሩ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ ነበሩ፡፡ የማኅበሩ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት የተመረጡት፣ በዕጩነት የቀረቡ ተመራጮች ባገኙት ከፍተኛ ድምፅ መሠረት ነው፡፡ በማኅበሩ ደንብ መሠረት ከፍተኛ ድምፅ ያገኘው ፕሬዚዳንት፣ ሁለተኛውን ከፍተኛ ድምፅ ያገኘው ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ይሆናሉ፡፡

ከዚህ የፕሬዚዳንትና የምክትል ፕሬዚዳንትነት ምርጫ ቀደም ብሎ ማኅበሩ ለ12 የቦርድ አባላት ምርጫ ማካሄዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአዲሱ የቦርድ አባላት ምርጫ የተመረጡት የኢትየጵያ ንግድ ባንክ፣ የአዋሽ ባንክ፣ የዳሸን ባንክ፣ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ የኅብረት ባንክ፣ የንብ ባንክ፣ የደቡብ ግሎባል ባንክ፣ የዘመን ባንክ፣ የብርሃን ባንክ፣ የአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ የአዲስ ኢንተርናሽናል ባንክና የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንቶች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር በ1994 ዓ.ም. ሲቋቋም የመጀመርያው የማኅበሩ ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገሉት፣ በወቅቱ የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ላይከን ብርሃኑ ናቸው፡፡ ከእሳቸው ቀጥሎ የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ የተረከቡት ደግሞ የአሁኑ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሃባ ነበሩ፡፡ አቶ አዲሱ ሁለተኛው የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት የኮንስትራክሽን ቢዝነስ ባንክ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት ነው፡፡ ከአቶ አዲሱ ቀጥሎ የማኅበሩ ሦስተኛው ፕሬዚዳንት የኅብረት ባንክ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ብርሃኑ ጌታነህ ናቸው፡፡ አቶ ብርሃኑ የኃላፊነት ዘመናቸው ሳያጠናቅቁ በፈቃዳቸው በመልቀቃቸው በእርሳቸው ምትክ አቶ አዲሱ ሃባ ቦታውን እንዲይዙ ተደርጎ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

በሰሞኑ የማኅበሩ ምርጫ አቶ አዲሱ በድጋሚ መመረጣቸው በሦስት የተለዩ ባንኮች ፕሬዚዳንትነት ለሦስት የምርጫ ዘመኖች ማኅበሩን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት የመጀመርያው ያደርጋቸዋል፡፡ አቶ አዲሱ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ40 ዓመታት በላይ ያገለገሉ ሲሆን፣ በ1969 ዓ.ም. የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ በሚባል ይታወቅ የነበረውንና አሁን ከንግድ ባንክ ጋር የተቀላቀለውን ከክለርክት እስከ ፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል፡፡

የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክን ከለቀቁ በኋላ የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው ሠርተዋል፡፡ ከአቢሲኒያ ባንክ በኋላ ደግሞ በአሁኑ ወቅት የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን በማገልገል ላይ ናቸው፡፡  

የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ የተመረጡት አቶ አቤ ሳኖ ደግሞ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ወደ 20 ዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም ከወጡ በኋላ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የተቀላቀሉት አቶ አቤ፣ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ በወጣትነታቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት መሆን የቻሉ ናቸው፡፡ አቶ አቤ ባልተለመደ ሁኔታ የኢትየጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲሾሙ በወቅቱ የ31 ዓመት ወጣት ነበሩ፡፡ ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው ቀደም ብሎ ባንኩ ውስጥ ለአጭር ጊዜ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉ ሲሆን፣ ንግድ ባንክን ከለቀቁ በኋላ ደግሞ ከምሥረታው ጀምሮ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ዋነኛ ዓላማው አድርጎ ያስቀመጠው በባንኮች መካከል የእርስ በርስ ግንኙነት ማዳበርና መረጃ እንዲለዋወጡ ማድረግ የሚለው ይገኝበታል፡፡ በጋራ በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ ተባብሮ ለመሥራት አመቺ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ሌላው ዓላማው ነው፡፡ የባንክ ዘርፉን ለማስፋፋት ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት፣ በባንክ ኢንዱስትሪው ላይ ጥናት ማካሄድ፣ ባንክን የሚመለከቱ የሚወጡ መመርያዎችና ደንቦችን በማስጠናት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር አመቺ ሁኔታዎች እንዲኖሩ ማስቻልና የባንክ ባለሙያዎች ማሠልኛ ተቋማትን የመገንባት ዕቅድ አለው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች