Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበልዩ ሊዝ ጨረታ ለቀረበ 83 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ዝቅተኛ የመጫረቻ ዋጋ...

በልዩ ሊዝ ጨረታ ለቀረበ 83 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ዝቅተኛ የመጫረቻ ዋጋ ቀረበ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባወጣው ሁለተኛው ልዩ ሊዝ ጨረታ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለሪል ስቴት ልማት የቀረበው 83,069 ካሬ ሜትር ቦታ ያልተጠበቀ ዝቅተኛ ዋጋ ሲሰጠው፣ በየካ ክፍለ ከተማ ለጨረታ የቀረቡ ሁለት ቦታዎች ከፍተኛ ዋጋ ቀረበላቸው፡፡

አስተዳደሩ በልዩ ጨረታ ካወጣቸው ቦታዎች እጅግ ሰፊ የሆነው ይህ ቦታ ሳራ ይመር የተባሉ ባለሀብት በካሬ ሜትር 315 ብር በማቅረብ ባልተጠበቀ ዝቅተኛ ዋጋ ከፍተኛ ተወዳዳሪ ሆነዋል፡፡ በዚህ ቦታ ይለማል ተብሎ የሚጠበቀው ሪል ስቴት ሲሆን፣ አስተዳደሩ እስካሁን ለሪል ስቴት ልማት ካቀረበው መሬት ሁሉ ይህ መሬት ሰፊ ነው ተብሏል፡፡

በዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ይመራ የነበረው የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር ለሪል ስቴት አልሚዎች በድርድር ይሰጥ የነበረው 50 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ እንደነበር ይታወሳል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከዚህ ቦታ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ባወጣው ልዩ ጨረታ በቦሌ አራት፣ በየካ ሁለት፣ በኮልፌ ቀራኒዮ አንድ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ አንድ፣ በአቃቂ ቃሊቲ አራት፣ በድምሩ በአምስቱ ክፍላተ ከተሞች 12 ቦታዎች በልዩ ጨረታ አቅርቧል፡፡

የቀረቡት ቦታዎች ከመደበኛው ሊዝ ጨረታ በተለየ ሰፋፊ የሚባሉ ሲሆኑ፣ ቦታዎቹ ለሪል ስቴት ልማትና ለባለአምስት ኮከብ ሆቴሎች የሚውሉ ናቸው፡፡ ለጨረታ ካቀረቡት ቦታዎች ሁለቱ ቦታዎች ብቻ ናቸው ለሆቴል አገልግሎት የሚውሉት፡፡

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ለባለአምስት ኮከብ ሆቴል የወጣው 5,014 ካሬ ሜትር ቦታ፣ በካሬ ሜትር 4,152 ብር ቀርቦለታል፡፡ ይህንን የመጫረቻ ዋጋ ያቀረበው አሜስኮ ኩባንያ ነው፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ ለባለአምስት ኮከብ ሆቴል 8,999 ካሬ ሜትር የቀረበ ሲሆን፣ ተስፋ ማርያም ገብረ ማርያም የተባሉ ባለሀብት በካሬ ሜትር 4,693.50 ብር አቅርበዋል፡፡ ለዚህ ቦታ ተወዳድሮ ሁለተኛ የወጣው አሊያብ ቢዝነስ ኩባንያ 4,100 ብር አቅርቧል፡፡ ይህ ቦታ ከፀሐይ ሪል ስቴት ጀርባ ተራራው አናት ላይ ይገኛል፡፡ የተቀሩት ቦታዎች ለሪል ስቴት ልማት የሚውሉ ናቸው፡፡ በኮልፌ ክፍለ ከተማ ለጨረታ የቀረበው 57,752 ካሬ ሜትር ቦታ ፋይሰል አባ ሜጫ የተባሉ ባለሀብት በካሬ ሜትር 3,260 ብር አቅርበዋል፡፡ ይህ ዋጋ በቦሌ ክፍለ ከተማ ከቀረቡት የሊዝ መጫረቻ ዋጋዎች የሚበልጥ ነው፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ ለጨረታ የቀረበ 44,970 ካሬ ሜትር ቦታ ቦክራ ኩባንያ በካሬ ሜትር 1,500 ብር አቅርቧል፡፡ በዚሁ ክፍለ ከተማ ለወጣው 23,751 ካሬ ሜትር ቦታ ፊሊንትስቶን ሆምስ በካሬ ሜትር 3,150 ብር አቅርቧል፡፡ ለሦስተኛው 14,890 ካሬ ሜትር ቦታ ዋልሜስ ኮንስትራክሽን በካሬ ሜትር 2,110 ብር አቅርቧል፡፡

አራተኛው በቦሌ ክፍለ ከተማ የቀረበው 55,386 ካሬ ሜትር ቦታ ሰባት ተወዳዳሪዎች ቢቀርቡም፣ በመጨረሻው ሰዓት ጨረታው መሰረዙ ተገልጿል፡፡ ተጫራቾች ተቃውሟቸውን በወቅቱ ቢያቀርቡም የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊዎች ጨረታውን በሙሉም ሆነ በከፊል የመሰረዝ መብት አለን በማለት ተቃውሞውን አልፈውታል፡፡

ለውድድር የቀረቡት ተጫራቾች፣ ‹‹አንድ ተወዳዳሪ በአንድ ቦታ እንዲወዳደር የሚገደድ በመሆኑ፣ ቀደም ብሎ አስተዳደሩ የቦታው ጨረታ መሰረዙን ቢያሳውቅ በሌሎች ቦታዎች ላይ ልንወዳደር እንችል ነበር፤›› በማለት አሠራሩን ተችተዋል፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ከፀሐይ ሪል ስቴት ጀርባ ለጨረታ የቀረበው የሪል ስቴት መሬት 16 ተወዳዳሪዎች ቀርበውለታል፡፡ የቦታው ስፋት 23,813 ካሬ ሜትር ሲሆን፣ ዕልልታ ኮንስትራክሽን በካሬ ሜትር 7,055 ብር አቅርቧል፡፡ ይህ ቦታ ለሪል ስቴት ልማት አመቺ በመሆኑ የብዙዎችን ትኩረት ከመሳቡም በላይ፣ የሁለተኛው ልዩ ጨረታ ከፍተኛ ገንዘብ የቀረበለት ቦታ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ሁለቱም የየካ ክፍለ ከተማ ቦታዎች በልዩ ጨረታው ከፍተኛ የመጫረቻ ዋጋ የቀረበላቸው ሆነው ተመዝግበዋል፡፡ ባለሙያዎች እንደተናገሩት ለሰፋፊ ቦታዎች ይህንን ያህል ዋጋ በየካ ክፍለ ከተማ ሊቀርብ የቻለው በተራራው ላይ የቀረቡት የመጨረሻዎቹ ቦታዎች በመሆናቸው ነው፡፡

የጨረታ ውጤቱ በቅርቡ ፀድቆ ይፋ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ፣ አሸናፊዎቹ የሚያካሂዱት ግንባታ ዝቅተኛው ከስድስት ወለል በላይ መሆኑን አስተዳደሩ ሐምሌ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ባወጣው ማስታወቂያ ገልጿል፡፡ በጨረታ ሰነዱ ላይ ስድስት ወለል የአካባቢው ከፍተኛ የወለል መጠን ተደርጎ መገለጹም ስህተት እንደነበር አስተዳደሩ በማስታወቂያው ላይ ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...