Sunday, September 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የዳያስፖራው ተሳትፎ በመተማን መንፈስ ላይ ይመሥረት!

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን (ዳያስፖራ) በአገራቸው ልማት ተሳታፊ መሆናቸው በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የዳያስፖራው ተሳትፎ በዓይነትም በመጠንም ይጨምር ዘንድ በመተማመን ላይ መመሥረት ይኖርበታል፡፡ ዳያስፖራው በምልዓት ተንቀሳቅሶ በአገሩ የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳትፎ እንዳያደርግ ከሚገድቡት ችግሮች መካከል አንዱ፣ የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት የፈጠረው ግራ መጋባት ነው፡፡ በፖለቲካ አመለካከት መለያየት ያለ፣ የነበረና ወደፊትም የሚኖር ቢሆንም፣ ችግሩ ሥር የደሰደደና ጽንፈኝነት የተፀናወተው በመሆኑ የዳያስፖራውን ሙሉ ተሳትፎ እየገደበው ነው፡፡ በልዩነት ውስጥ  አንድነት መኖሩን ፈጽሞ የዘነጋው የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር፣ አቅም ያለውንም ሆነ የሌለውን ዳያስፖራ በመከፋፈል ለአገር ዕድገት የሚበጀውን ሀብትና ዕውቀት እያባከነ ነው፡፡ ይህንን መሠረታዊ ችግር በማስወገድ አገርንና ቡድናዊ ጥቅምን የሚለይ ከባቢ መፈጠር አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ መተማመን መፈጠር አለበት፡፡ ጠቃሚ ነጥቦች እናንሳ፡፡

  1. የአገሪቱና የዳያስፖራው ትስስር ይጠናከር

በዳያስፖራ የአገር ጠቃሚነት በዓለም ላይ ስማቸው ጎልቶ የሚነሳው ቻይናና ህንድ፣ በዳያስፖራዎቻቸው አማካይነት የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ልማታቸውን በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ላይ ናቸው፡፡ ከ55 ሚሊዮን በላይ ቻይናውያን ከአገራቸው ጠቅላላ  የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከ60 በመቶ በላይ ሲሸፍኑ፣ ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ህንዳውያን ደግሞ ከ15 በመቶ በላይ እንደሚሸፍኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከገንዘባቸው በተጨማሪ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስለሚያደርጉም ሁለቱ አገሮች በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ምንም እንኳ ቻይና በአንድ ዓይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ የምትመራ አገር ብትሆንምና በህንድ ደግሞ ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት የተከበሩ ቢሆኑም፣ በዳያስፖራውና በመንግሥታት መካከል አገርን ማዕከል ያደረገ መተማመን መፈጠሩ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

በአገራችን እንዲህ ዓይነቶቹን ልምዶች በመቀመር ልዩነቶችን አቻችሎ መቀራረብ መፍጠር ከተቻለ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ልማት ብቻ ሳይሆን፣ በፖለቲካው መስክም በተለይ ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት ጠቃሚ የሆኑ አስተዋጽኦዎችን ማበርከት ይቻላል፡፡ እያደር እያባሰበት የሚሄደው የፖለቲካ ራስ ምታት ለአገራቸው ተገቢውን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ዳያስፖራዎችን እያሸማቀቀ ነው፡፡ ለይቶላቸው አመፃ ውስጥ የገቡ ኃይሎችና የእነሱ ደጋፊዎች የተቆጣጠሩዋቸው ማኅበራዊና መደበኛ ሚዲያዎች በሚያሳድሩት ተፅዕኖ አንገታቸውን የደፉ ብዙ ናቸው፡፡ እንዲሁም መንግሥት በአገር ውስጥ በሚወስዳቸው ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች የሚከፉም አሉ፡፡ በእነዚህ ተፅዕኖዎች ምክንያት ሥጋት ውስጥ ሆነው ከአገራቸው ጋር የተለያዩ በርካቶች ናቸው፡፡

የፖለቲካው ልዩነት በሠለጠነ መንገድ ተይዞ ዳያስፖራው የአገሩ የልማት አጋር ይሆን ዘንድ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ሊፈጠር ይገባል፡፡ ዳያስፖራው ከአገሩ ጋር የነበረው ግንኙነት በጠንካራ መሠረት ላይ ይገነባ ዘንድ የፖለቲካው አጥር እንቅፋት መሆን የለበትም፡፡ ማንም ሰው በአመለካከቱ ምክንያት መገለል ወይም ጉዳት እንደማይደርስበት ማረጋገጫ ተሰጥቶ ዳያስፖራው የአገሩ የልማት ተሳታፊነቱ ይጠናከር፡፡ እዚህ ላይ በብርታታቸውና በአርዓያነታቸው የሚጠቀሱ የዳያስፖራ አባላት መወደስ አለባቸው፡፡ በትምህርት፣ በጤና፣ በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንትና በመሳሰሉት መስኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ዝነኛ የሆኑ ዳያስፖራዎች በምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡ የፖለቲካ አመለካከትም ሆነ የተለያዩ ልዩነቶች ሳይገድቧቸው ለእናት አገራቸው ተጠቃሽ የሆኑ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የዳያስፖራውና የአገሩ ትስስርም በዚህ መንፈስ እንዲጠናከር ያበረታታል፡፡ መተማመን ይፈጠር፡፡

  1. ዳያስፖራው ሀብቱንና ዕውቁትን የሚያውልባቸው መስኮች ይታወቁ

በዚህ ዘመን በመላው ዓለም ከተበተኑ ዳያስፖራዎች አገሪቱ በኃዋላ የሚላክ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ በዓመት ታገኛለች፡፡ እንዲሁም ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ያደረጉ ዳያስፖራዎችም በሥራ ላይ ናቸው፡፡ በኢንቨስትመንት መስክ የፈሰሰው የዳያስፖራው ገንዘብ አገሪቱ ከቱርክና ከቻይና ካገኘችው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ቀጥሎ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ አገሪቱ አንደኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አጠናቃ ሁለተኛውን በምትጀምርበት ወቅት ላይ ናት፡፡ በዚህ ጊዜ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በመሆኑ ዳያስፖራው ገንዘቡን፣ ዕውቀቱንና ልምዱን ይዞ ሊገባበት የሚገባው ትልቅ መስክ ነው፡፡ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ከተለያዩ አገሮች ለመምጣት ባሰፈሰፈበት በዚህ ጊዜ በተለይ አቅም ያለው ዳያስፖራ ማመንታት የለበትም፡፡ በግለሰብ ደረጃ አቅም ባይኖር እንኳ ተደራጅቶ መምጣት ተገቢ ነው፡፡ ይህ ፈጽሞ ሊታለፍ የማይገባው አጋጣሚ ነው፡፡

ኢትዮጵያ እጅግ በጣም ለም የሆነ መሬት፣ በጣም ትልቅ የውኃ ሀብት፣ ጥሩ የአየር ንብረት፣ ከምንም ነገር በላይ ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል ያለባት አገር ናት፡፡ ይህች አገር ለዘመናት የሚፈታተናት የምግብ እጥረት የተወሰኑ መሻሻሎች ቢታዩበትም አሁንም ትልቅ ሥራ ይጠብቃል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንደኛ የሆነ የእንስሳት ሀብት ይዛ ሥጋና የሥጋ ውጤቶች አሁንም ብርቅ ናቸው፡፡ ወተትና የወተት ውጤቶች ውድ ናቸው፡፡ ዶሮና ዓሳ ለአብዛኛው ሕዝብ የቅንጦት ያህል ናቸው፡፡ አትክልትና ፍራፍሬም እንዲሁ፡፡ በአግሮ ኢንዱስትሪው ዘርፍ በስፋት ተገብቶ ቢሠራበት ከአገሪቱ አልፎ ከኤክስፖርት ከፍተኛ ገቢ ይገኝበታል፡፡ የዳያስፖራው ሀብትና ዕውቀት እዚህ ላይ ቢፈስ ከፍተኛ ውጤት ይገኛል፡፡ በጠንካራ መሠረት ላይ የተቋቋሙ የአክሲዮን ማኅበራት ቢመሠረቱ ለማመን የሚቸግር ሀብት ይገኝበታል፡፡ መንግሥትና ዳያስፖራው በመተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ቢፈጥሩ በአጭር ጊዜ አገሪቱ ትለወጣለች፡፡ ዳያስፖራውም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ይህ በአጽንኦት ይታሰብበት፡፡

  1. ጠንካራ ሕጎችና አሠራሮች ይኑሩ 

በአሁኑ ጊዜ የአገሪቱን የኢንቨስትመንት ከባቢ ከሚያስቸግሩ ዋና ተግዳሮቶች መካከል፣ ለኢንቨስትመንት ምቹነት የሚረዱ ሕጎችና አሠራሮች በሚገባ አለመቀረፃቸው ነው፡፡ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትወቅስባቸው ቢዝነስ ለማከናወን የሚረዳ ከባቢ የላትም፣ ቢሮክራሲው አያላውስም፤ በፌዴራልና በክልሎች መካከል መናበብ የለም፣ ደንቦችና መመርያዎች ይጣረሳሉ፣ የአስፈጻሚዎች ብቃት ማነስና እያቆጠቆጠ የመጣው ሙስና ይጠቀሳሉ፡፡ በአገር ውስጥ ሀብታቸውን ያፈሰሱ ዳያስፖራዎችም የሚያማርሩት እነዚህን ችግሮች ነው፡፡ አሁን ደግሞ በየደረጃው የሚታዩት ዓይን ያወጣ ሙስናና ለሰሚ ግራ የሚያጋቡ አሠራሮች እንቅፋት እየሆኑ ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹን ኋላ ቀርና ከዘመኑ ጋር እኩል የማይራመዱ ተግባራትን በማራገፍ ጠንካራ ሕጎችና አሠራሮች እንዲሰፍኑ መደረግ አለበት፡፡ ጠንካራ የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፎች ወጥተው ሥራ ላይ  ይዋሉ፡፡ ዳያስፖራው ሀብቱንና ዕውቀቱን ይዞ የሚመጣው አስተማማኝ ሕጎችና አሠራሮች ሲኖሩ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም መንግሥት ቁርጠኛ ይሁን፡፡ መተማመን ይፍጠር፡፡

  1. ለዳያስፖራው ትጋት ዕውቅና ይሰጥ

መንግሥት የዳያስፖራ ፖሊሲ ቀርፆ ለዳያስፖራው ተሳትፎ የሚጠቅሙ አሠራሮች መፍጠሩ ጥሩ ነው፡፡ የዳያስፖራውንም ሳምንት ማክበርም ጀምሯል፡፡ ይኼም መቀጠል አለበት፡፡ የዳያስፖራው ንቁ ተሳትፎ አሁን ከሚታየው ደረጃ እጅግ በጣም በላቀ ሁኔታ መጨመር አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ኢንቨስትመንት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ላሉ የዳያስፖራው አባላትና ወደ አገር ውስጥ ኃዋላ ለሚልኩ ወገኖች ዕውቅና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ መሬት፣ ብድር፣ የታክስ እፎይታና ሌሎች ማበረታቻዎችን በመስጠት ጠንካራዎቹን መደገፍ ተገቢ ነው፡፡ የአገሪቱ የኤክስፖርት ምርቶች ከሚያስገኙት በላይ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ የሚያበረክቱ ዳያስፖራዎች ቁጥር እጥፍ በእጥፍ እንዲጨምር፣ ኢንቨስት የሚያደርጉም በከፍተኛ መጠን ቁጥራቸው እንዲያድግ፣ በብሔራዊ ደረጃ ዕውቅና መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ይህ ዕውቅና እጅግ የላቀ ውጤት ይኖረዋል፡፡ መተማመን ይፈጥራል፡፡

በአጠቃላይ ዳያስፖራው አገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እንድታደርግ፣ ጠንካራ፣ የበለፀገችና ዴሞራሲያዊት እንድትሆን፣ ዕድገቷም ጤነኛና አስተማማኝ ሆኖ እንዲቀጥል የሚፈልግ ከሆነ ከአዙሪት ውስጥ አልወጣ ካለው ጽንፈኛ ፖለቲካ መላቀቅ አለበት፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሰጥቶ የመቀበል መርህ ራሱን ያዘጋጅ፡፡ መንግሥትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው አሠራሮች በማስፈን፣ ልዩነቶችን የሚያስተናግድ ባህሪ ይላበስ፡፡ የዳያስፖራው ተሳትፎ በመተማመን መንፈስ ላይ እንዲመሠረት ሁሉም ወገን አስተዋጽኦ ያበርክት! በአስቸኳይ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...