በምዕራብ ወለጋ ዞን ቱሉ ካፒ በተሰኘ ሥፍራ ከፍተኛ የወርቅ ማምረቻ ለመገንባት አራት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እየተጫረቱ ነው፡፡
ከፊ ሚኒራልስ የተሰኘው የእንግሊዝ ኩባንያ በቱሉ ካፒ አካባቢ የወርቅ ፍለጋና የአዋጪነት ጥናት ሲያካሂድ ቆይቶ የፕሮጀክቱን አዋጪነት ካረጋገጠ በኋላ፣ ከማዕድን ሚኒስቴር ከፍተኛ የወርቅና የብር ምርት ፈቃድ ወስዷል፡፡
ከፊ ሚኒራልስ በቱሉ ካፒ ግዙፍ የወርቅ ማምረቻ ለመገንባት አቅዶ የወርቅ ማምረቻ ማሽኑን የሚያቀርብ፣ የሚተክልና ሥራውን የሚያስጀምር ኩባንያ ለመቅጠር ዓለም አቀፍ ጨረታ አውጥቷል፡፡ የጨረታውን መውጣት ተከትሎ በርካታ ዓለም አቀፍ ኮንትራክተሮች የጨረታ ሰነድ አስገብተዋል፡፡
ታማኝ የዜና ምንጮች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከፊ ሚኒራልስ የጨረታ ሰነድ ካስገቡት ኩባንያዎች መካከል አራቱን በመምረጥ ኩባንያዎቹ ያቀረቡትን የቴክኒክና የፋይናንስ ዕቅድ በዝርዝር እየገመገመ ይገኛል፡፡ በኮንትራክተሮቹ የቀረቡትን ሰነዶች የሚመረምሩት የከፊ ሚኒራልስ ማኔጅመንትና ኩባንያው የቀጠራቸው አማካሪ ድርጅቶች መሆናቸውን የጠቀሱት ምንጮች፣ የጨረታው ውጤት በመጪው መስከረም ወር ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የወርቅ ማምረቻው በዓመት 1.2 ሚሊዮን ቶን የወርቅ አፈር በማጣራት ከ2,650 እስከ 2,800 ኪሎ ግራም ወርቅ የማምረት አቅም ይኖረዋል፡፡ የወርቅ ማምረቻውን ለመገንባት በአጠቃላይ 120 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተመድቧል፡፡ የመሠረት ድንጋይ በጥቅምት 2008 ዓ.ም. እንደሚጣልና ግንባታው 18 ወራት እንደሚፈጅ የገለጹት ምንጮች፣ የወርቅ ምርት በ2009 ዓ.ም. ለመጀመር መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ገንጂ ወረዳ፣ ቱሉ ካፒ አካባቢ የሚገኘው የከፊ ሚኒራልስ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ይዞታ ሰባት ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ የኩባንያው የምርት ፈቃድ ለ20 ዓመታት የፀና ይሆናል፡፡ ኩባንያው 151.6 ሚሊዮን ዶላር የመነሻ ካፒታል መድቧል፡፡ ለ700 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይታመናል፡፡
ከማዕድን ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ፣ ከፊ ሚኒራልስ በመጪው አሥር ዓመታት 28,875 ኪሎ ግራም ወርቅ በማምረት 1.2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ፣ ለመንግሥት በግብርና በባለቤትነት ክፍያ (Royalty Fee) 130 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፍል ይጠቁማል፡፡
ወርቅ ለወጪ ንግድ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው ወርቅ በዓመት ከ450 እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ባህላዊ ወርቅ አምራቾች ቀዳሚውን ሚና ይጫወታሉ፡፡ በአምስት ክልሎች የሚገኙ ባህላዊ ማዕድን አምራቾች በዓመት ከሰባት እስከ ስምንት ቶን ወርቅ በማምረት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያቀርባሉ፡፡
እስካሁን በከፍተኛ ወርቅ ምርት ላይ የተሰማራው ብቸኛ ኩባንያ ሚድሮክ ጐልድ ሲሆን፣ የከፊ ሚኒራልስ ትልም ከተሳካ ወርቅን በዘመናዊ መንገድ በማምረት ሁለተኛው ኩባንያ ይሆናል፡፡ የማዕድን ሚኒስቴር በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ኢዛና ማይኒንግ፣ ኦስኮም ማይኒንግና ናሽናል ማይኒንግ ኮርፖሬሽን የተሰኙት ኩባንያዎች በከፍተኛ ወርቅ ምርት ላይ ይሰማራሉ ብሎ ተስፋ ጥሎባቸዋል፡፡