የጥቃቅንና አነስተኛ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ራሱን ችሎ በፌዴሬሽን ደረጃ የተቋቋመው አምና 2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ በመላው አገሪቱ በጥቃቅን፣ ታዳጊና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በተደራጁ 2000 ማኅበራት አማካይነት የተመሠረተ ነው፡፡ ራሱን ችሎ የተቋቋመበት ምክንያት ኢንተርፕራይዞችን የሚወክሉ ማኅበራት በመበራከታቸውና በሥራቸው የሚያቅፏቸው ሠራተኞችም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ በመምጣታቸው የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት ሰላማዊ ለማድረግ ከወዲሁ ማኅበራትን ወደ ፌዴሬሽን ደረጃ ማሳደግ አስፈላጊ በመሆኑ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ2,500 በላይ አባላት ያፈራው የኢትዮጵያ ጥቃቅንና አነስተኛ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ምን እየሠራና ወደፊት ሊሠራ ያቀዳቸውን ነገሮች በተመለከት የፌዴሬሽኑን ፕሬዚዳንትና የትንሣኤ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ኃይሌን ታምራት ጌታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- አባሎቻችሁ በምን ዓይነት መስክ የተሠማሩ ናቸው? ፌዴሬሽኑ ምን ያህል አባላትስ አሉት?
አቶ ጌታቸው፡- በኢትዮጵያ በጠቅላላው ወደ 600ሺ ኢንተርፕራይዞች (ማኅበሮች) አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ በኛ ሥር ያሉት 2,500ዎቹ ናቸው፡፡ ይኼ ብቻ የሆነው ጥቃቅንና አነስተኛ ሲደራጁ በየክልሉ ሆኖ መሠረታዊ ማኅበሮች በመሆናቸው ነው፡፡ እነዚህን ማኅበራት በቅርቡ በክልል ደረጃ በማሳደግ በክልሉ የኢትዮጵያ ጥቃቅንና አነስተኛ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይ በሌሎችም ክልሎች እንደዚህ ዓይነት አደረጃጀቶች እየፈጠርን ነው፡፡ እንግዲህ ስሙ ራሱ እንደሚያመለክተው ጥቃቅንና አነስተኛ ሆነው ለምሳሌ እንጀራ በመጋገር ተነስተው ወደ ባለ ሆቴልነት የተቀየሩት፣ ከቀን ሥራ ጀምረው ትልልቅ ኮንስትራክሽን ሥራ የሚሠሩ በተለያዩ የሙያ ዘርፍ ያሉትን ያጠቃልላል፡፡ አሠሪ እነዚህ 2,500 ማኅበሮች በትንሹ እያንዳንዳቸው ከ10 እስከ 30 የሚደርሱ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኛ ቀጥረው የሚያስተዳድሩ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?
አቶ ጌታቸው፡- መጀመሪያ እኛን ያቋቋመን ራሱ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ነው፡፡ ሌሎች በአገሪቱ ካሉ አምስት አሠሪ ፌዴሬሽኖች ጋር በጋራ ለመሥራት በወሰነው መሠረትም እየሠራን እንገኛለን፡፡ ለኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽንም አብረን ለመሥራት ጥያቄ አቅርበን መልስ እየጠበቅን እንገኛለን፡፡
ሪፖርተር፡- ራሳችሁን ለማደራጀት በየክልሉ እየተንቀሳቀሳችሁ ነው፡፡ በሥራችሁ የገጠማችሁ ችግር ካለ?
አቶ ጌታቸው፡- ማደራጀቱ ገና ቀጣይ ሥራ ነው፡፡ በቅርቡም በደቡብ ክልል በአምስት ዞኖች ላይ በወልቂጤ፣ በወላይታ ሶዶ፣ በአርባ ምንጭ በተጨማሪም ለማደራጀት ዝግጅት የጨረስን ነው፡፡ እንደዚሁ ደግሞ በትግራይ ክልል በምሥራቃዊ ዞን አዲግራትን ጨምሮ ዘጠኝ ወረዳዎችን ለማደራጀት ወደዚያው የምናቀና ይሆናል፡፡ በመቐለም በተመሳሳይ ሁኔታ የምናጠናክር ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በጅማ፣ በአዳማ፣ በቢሾፍቱ ያደራጀን ሲሆን፣ በቀጣይ በነቀምቴ፣ በአምቦና በሌሎች ከተሞች ለማደራጀት እንቅስቃሴ ላይ ነን፡፡ እነዚህን ሥራ ስንሠራ እየገጠሙን ያሉ ችግሮች በዋናነት የገንዘብ እጥረት ነው፡፡ ሁለተኛ ከኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ጋር ልዩነታችሁ ምንድነው በሚል የሚገጥመን ሙግት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አባሎቻችሁን ለማብቃት ምን እያከናወናችሁ ነው?
አቶ ጌታቸው፡- መንግሥት እነዚህ ኢንተርፕራይዞች ወደፊት የአገርን ፍላጎት አሟልተው ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ያመጣሉ ብሎ የሚያምንባቸው የወደፊት ኢንዱስትሪውን ይረከባሉ ተብለው የሚጠበቁ ናቸው፡፡ ስለዚህ ዛሬ ራሳቸውን አዘጋጅተው መጠበቅ ስላለባቸው የመደራጀት ጥቅሙ ምንድን ነው፣ በመደራጀት ችግሮች እንዴት ተፈቱ የሚለው አንዱ ሲሆን፣ ዛሬም የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ሕጉን ባለማወቅ እሰጥ አገባ ውስጥ በመግባት የገንዘብ፣ የጊዜና የንብረት ብክነት እየመጣ በመሆኑ አዋጁን በማስተማር ምልከታ መስጠት፣ ሌላው ደግሞ የሥራ ፈጠራን በሚመለከት ነው፡፡ አንዱ ገንዘብ ይዞ ምን እንደሚሠራ ግራ ይገባዋል፡፡ አንዱ እውቀት ይዞ የት እንደሚሠራ ፈጠራውን የት መሸጥ እንዳለበት ባለማወቅ እየተላለፈ ይኖራል፡፡ እነዚህን እንዴት ማገናኘት እንደሚቻል የጠለቀ እውቀት የሚገኝበት መድረክን በየጊዜው እያዘጋጀን ነው፡፡ ተሳታፊዎችም ያገኙትን እውቀት በቀላሉ ለሌሎች እንዲያካፍሉ ይደረጋል፡፡ እኛም ይኼንን መሳይ ትምህርት በማዘጋጀት ወደፊት በስፋት የምንሄድበት ይሆናል፡፡ ይኼም የኢንዱስትሪውን ሰላም ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ያሉበት ችግሮች ምንድናቸው? ወደፊትስ ምን ሊሠራ አስቧል?
አቶ ጌታቸው፡- ለጊዜው ያለብን የገንዘብ ችግር ነው፡፡ አባላት መዋጮዋቸውን በጊዜው ስለማይከፍሉ ለሠራተኞችና ለቤት ኪራይ ከመክፈል ውጪ ባለፈ የሚተርፍ አይደለም፡፡ ሌላውና ትልቁ ችግር ፌዴሬሽኑ የራሱ ሕንፃ የለውም፡፡ አሁን ያለው በኪራይ ቤት ነው፡፡ ቋሚ የሆነ ቢሮ ስለሌለው ቋሚ አድራሻም የለውም፡፡ ከየትኛውም የመንግሥት አካል ድጋፍ እያገኘንም አይደለም፡፡ በራሳችን ነው የምንንቀሳቀሰው፡፡ ፌዴሬሽኑ ግን እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም፡፡ ከሁለት ወር በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚገኙበት የእውቅናና የምስጋና ፕሮግራም ከከተማው የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ጋር በመሆን አገር አቀፍ ንቅናቄን ለመፍጠር እየተዘጋጀን ነው፡፡ በዚሁ ፕሮግራም ላይ መንግሥት ለጥቃቅንና አነስተኛው ዘርፍ ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ ሳይሰለች ላደረገልን ድጋፍ ምስጋና የምናቀርብ ይሆናል፡፡ ሌላው ፌዴሬሽኑ ከማኅበሩ ምሥረታው ጀምሮ ነገ ምን መድረስ አለበት በሚል ጥናታዊ ጽሑፍ በማቅረብ በዚያው የሠራቸውን ሥራዎች የሚገመገምበት፣ ያሉበትን ችግሮችም ዘለቄታዊ መፍትሔ የሚያገኙበት ይሆናል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ሌላው የረዥም ጊዜ ዕቅዶቻችን ከእነዚህ ከ600ሺ በላይ የሆኑትን ማኅበሮችን በማሰባሰብ ባንክ ማቋቋም ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ለኢንተርፕራይዙ ትልቅ ችግር እየሆነ ያለው የብድር አቅርቦት ነው፡፡ የሚቋቋመው ባንክም ያለውን ችግር መቅረፍ የሚችል እንዲሆን ታቅዷል፡፡ ለጊዜው በዚህ በኩል ያለብንን ችግር ለመፍታት ከልማት ባንክ ጋር እየተነጋገርን እንገኛለን፡፡