Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሳተላይት የማምጠቅ ጅማሮ

ሳተላይት የማምጠቅ ጅማሮ

ቀን:

ሳተላይት ለማምጠቅ አገሮች ሊከተሉት የሚገባ ራሱን የቻለ ፖሊሲና መመዘኛዎች አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የሳተላይት ዓይነቶች የሚገኙ ሲሆን፣ የመገናኛ የመሬት ቅኝት፣ የአየር ፀባይ መመርመርያ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከፈር ቀዳጇ የሩሲያ ሳተላይት ከስፑትኒክ በኋላ ወደ ሕዋ ከተላኩት መካከል 2,500 ሳተላይቶች በሥራ ላይ መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡ አንድ ሳተላይት በሕዋ ላይ የሚቆይበት ዕድሜ ከ10 እስከ 15 ዓመት ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ግን ፈርሶና ተበትኖ ይሞታል፡፡ በምትኩ ሌላ ሳተላይት ይመጥቃል፡፡

በፖሊሲና መመዘኛዎቹ መሠረት ከአፍሪካ ሳተላይት ያላቸው ደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያ ናቸው፡፡ አገሮች አንድን ሳተላይት በ20 ሚሊዮን ዶላር ይገዛሉ፣ ይሸጣሉ፡፡ ነገር ግን ሳተላይት እንደማንኛውም ሸቀጥ ተገዝቶ የሚሰቀል አይደለም፡፡ ሳተላይት ለማምጠቅ በቅድሚያ ከአውታር ስፔስ ሳተላይት ፈቃድ ማግኘት ግድ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ እስካሁን የራሷ ሳተላይት ባይኖራትም ይህን ፈቃድ ካገኘች ሰነባብታለች፡፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብነት እዝራ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ለኮሙዩኒኬሽን ሳተላይት በየዓመቱ እስከ 8 ሚሊዮን ዶላር ታወጣለች፡፡ የሳተላይት ዕገዛ ከሚያስፈልጋቸው ትልልቅ የአገር ውስጥ ፕሮጀክቶች መካከል ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አንዱ ነው፡፡ ግድቡ ለሦስት ዓመታት ያህል በሳተላይት መጠናቱን፣ የአፈር ምርመራ ሐደቱ ሳይቀር የተካሄደው በሳተላይት ነው፡፡

ከሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ የራሷ ሳተላይት ይኖራታል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ለዚህ ሐሳብ ዕውን መሆን ሶሳይቲው ምን አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል ‹‹ኢትዮጵያ በአምስት ዓመት ውስጥ በሦስት የሳተላይት ዘርፎች ራሷን መቻል አለባት የሚል አቅጣጫ በመጠቆም የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ 12ኛ ጠቅላላ ጉባኤን አስመልክቶ ዋና ሥራ አስኪያጁ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳብራሩት፣ ሶሳይቲው ላሊበላ ላይ አቋቁሞ ለመንግሥት ያስረከበው ኦብዘርባቶሪ የሥልጠናና ምርምር ማዕከል አገሪቱ የራሷን ሳተላይት እንዲኖራት በማነሳሳት ረገድ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል፡፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ባለፉት 13 ዓመታት እመርታ ሊባሉ የሚችሉ በርካታ እንቅስቃሴዎች በማከናወን ኢትዮጵያ ከምንም ተነስታ በዘርፉ አሁን ለደረሰችበት ደረጃ መድረስ እንድትችል፣ ቢያንስ ጉዳዩ ለውይይት እንዲበቃ እንዳደረጋት ነው የተናገሩት፡፡

አገሪቱ ዕድገት፣ ልማትና ብልፅግና ለመጎናፀፍ የምትችለው ሳይንስና ቴክኖሎጂ በኅብረተሰቡ ሁለንተናዊ ሕይወት ላይ በተሟላና በብቃት መተግበር ሲቻል ነው፡፡ የመልማት አቅምና ባህልን መገንባት በማስቻል የበለፀገና የሠለጠነ ኅብረተሰብ፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ዕድገት የተረጋገጠባትን አገር መፍጠር የሚያስችል ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ሶሳይቲው ያምናል፡፡

በኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በናይጄሪያና በደቡብ አፍሪካ ሳተላይት መር (ሳተላይት ቤዝድ) የሆነ ትምህርት ለመምህራንና ለተማሪዎች በሳተላይት ለማስተላለፍ የሚረዳ ፕሮግራም ለመጀመር የሚያስችል እንቅስቃሴ በመካሄድ ላይ እንደሆነ፣ ለተግባራዊነቱም ቴክኖሎጂና ኢንፎርሜሽን አርቲክቴክቸር እንደተፈጠረ በሳተላይት ቴክኖሎጂው ዙሪያ የሚሠራ የያዝሚ ኢትዮጵያ ድርጅት መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኖህ ሳማራ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ፋይበር ኦፕቲክስ መስመር በፍጥነት በመዘርጋት በዓለም ውስጥ ግንባር ቀደም መሆኗን ኖህ ሳሞራ ጠቁመው፣ በዚህም የተነሳ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 4,000 ኪሎ ሜትር ፋይበር ኦፕቲክስ ለመዘርጋት እንደቻለች አስረድተዋል፡፡

‹‹ይህንንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ልታከናውን የቻለችው መስመሩ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች በሥራው እንዲሳተፉ በማድረጓ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አምስት ኪሎ ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ የስብሰባ አዳራሽ የካቲት 24 እና የካቲት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በተካሄደው በዚሁ ጉባኤ የሶሳይቲው ያለፈው ዓመት የሥራ አፈጻጸምና የዚህ ዓመት ዕቅድ ቀርቦ በስብሰባው ታዳሚዎች ሰፋ ያለ ውይይትና የሐሳብ መለዋወጥ ከተከናወነ በኋላ ዕቅዱ ሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምፅ ፀድቋል፡፡

ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት እንደተቻለው ሶሳይቲው በዓለም አቀፍ ደረጃ ከትምህርት፣ ሥልጠና፣ ምርምርና የዕውቀት ሥርጭት ተቋማት ጋር በኢትዮጵያ የሕዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ከዘመኑ ጋር በሚመጥን ደረጃ የማራመድና ጥቅም ላይ የማዋል እንቅስቃሴውን በተጠናከረ መልኩ እየሠራ ይገኛል፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታትም ሕዝቡ ለሳይንስ ያለውን ፍላጎት እንዲያጠናክርና የሕዋ ሳይንስን አስፈላጊነት ለመገንዘብ እንዲችል የተለያዩ ፕሮግራሞች መካሄዱንና፣ ከእነዚህም አንዱ ወርኃዊ የሆነው የኮከብ ምልከታ ፕሮግራም መሆኑን አመልክቷል፡፡

ወርኃዊ የኮከብ ምልከታው የተለያዩ የኅብረ ከዋክብት ፕላኔቶች፣ ጨረቃን ጨምሮ የተለያዩ የሕዋ አካላትን በቴሌስኮፖች በማሳየት ትምህርታዊ የሆኑ ትንታኔዎችና ገለጻዎች ያካተተ ነው፡፡ በዚህም ማኅበረሰቡ የሕዋ ሳይንስ ጥናትና ምርምር ለአገሪቱ ያለውን ቀጥተኛና ተዛማጅ ጥቅሞች እንዲረዳ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በዚህ ዓመት ይተገበራሉ ተብለው በዕቅድ ከተያዙት ተግባራት መካከል ለሕዋ ምርምር ጣቢያነት ተስፋ አላቸው የሚባሉ የአገሪቱን ቦታዎች ማጥናት፣ የእንጦጦን አብዘርባቶሪ ዕቅዶች ማሳኪያ ድጋፍ መስጠት፣ ኅብረተሰቡ ስለ ሕዋ ሳይንስ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ፣ አገሪቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንድትሆን ማስቻል የሚሉና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...