Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልዝክረ ዓድዋ

ዝክረ ዓድዋ

ቀን:

ከውጫሌ እስከ ሶሎዳ ተራራ ቁጭትና ተቃርኖ

‹‹የዓድዋን ሥላሴ ጠላት አረከሰው

ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው››

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የዛሬ 122 ዓመት ጀግኖች የኢትዮጵያን መሬትና ሉዓላዊነት ለወራሪው የጣሊያን ጦር አሳልፈው ላለመስጠት ግንባራቸውን ለጥይት ሳይሰስቱ በታሪካዊው የዓድዋ ተራሮች የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ለማውለብለብ የቀራቸው ጥቂት ሰዓታት ብቻ ነበር፡፡ ከአምባላጌ ጀምሮ ጠላትን እየደመሰሱ የዓድዋ ተራራማ ሥፍራዎች በደረሱበት ወቅት አስቸጋሪውና ብዙ የሕይወት መስዋዕትነት ነበር ያስከፈላቸው፡፡

በዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን የጣሊያን ወራሪ ጦር በመፋለም በጀግንነት ድል ያደረጉና ሕይወታቸውን በዚያው ከሰዉት ውስጥ ፊታውራሪ ገበየሁ ስማቸው በደማቅ በታሪክ መዝገብ ከሰፈረላቸው ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡

የዓድዋ ድል በጀግኖቹ የኢትዮጵያ አርበኞች የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ከመጠናቀቁ ሦስት ሰዓት በፊት፣ መድፈኛው ፊታውራሪ ገበየሁ (አባ ጎራው) መንድብድብ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ ነበር በጥይት ግንባራቸውን ተመትተው ለአገራቸው በክብር የተሰዉት፡፡

የእሳቸውን መሰዋት ተከትሎም ነበር ሌላኛው አርበኛ ባልቻ አባነፍሶ መድፉን በማንሳት ታሪክ የማይዘነጋው ድልን የደገሙት፡፡ በተመሳሳይ ቦታ በተመሳሳይ ቀን፡፡ ይህ ሲሆን በሌላኛው ተራራማ ስፍራ እነ ራስ አሉላ አባነጋ፣ እነ ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ፈረሰኞች የማይደገም የሚመስሉ ጀብደኝነትን ያሳዩበት፣ እጅ በእጅ ተናንቀው የጣሊያን አንገት የቀጩበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ዳቦርሚዳ የተባለውን የጣሊያን ጄኔራል አንገት ቀጭተው በጋራ የተቀበሩበት ሥፍራ… ተጠቃሽ የታሪክ አሻራ የሰፈረበት መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ይህ ድል የመላው የኢትዮጵያውያን ድል ያደረገው ደግሞ ከደቂቅ እስከ ሊቅ፣ ሴት ወንድ ሳይል፣ ከሕፃን እስከ አዛውንት፣ ከተዋጊ አርበኛ እስከ ስንቅ አቀባይ፣ ከጦር አዛዥ አዋጊዎች እስከ ንጉሡ ነገሥቱ አፄ ምኒልክና ንግሥቲቱ እቴጌ ጣይቱ ሁሉም የየራሱን ድርሻ በመወጣት በአንድነት ተባብረው የኢትዮጵያን ኃያል ክንድ መሥርተው ወራሪውን ያደቀቁበት በመሆኑ ነው፡፡

ይህ ደማቅ ታሪክ ደግሞ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካና በመላው ዓለም ለሚገኙ የጥቁር ሕዝቦች ፈር ቀዳጅና የነፃነት ዓርማ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ይህ ታሪክ ዛሬም ድረስ ከሀገረ አሜሪካ እስከ ሩቅ ምሥራቆቹ ጃፓንና ኮሪያ፣ ከአውሮፓ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲሁም ከአውስትራሊያ እስከ ደቡብ አሜሪካ ድረስ በየትምህርት ቤቶቻቸውና ዩኒቨርሲቲዎቻቸው በዓለም ታሪክ ውስጥ ከሚማሩት የታሪክ ትምህርት ውስጥ ተካቶ ይማሩታል፡፡

ይህ የኢትዮጵያውያን ታሪክ ላለፉት 122 ዓመታት ሲዘከር ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ መጥቷል፡፡ ነገር ግን ዓመታዊ በዓሉ በተለያየ ጊዜያት አንዴ ደመቅ ሲል አንዳንዴም መደብዘዝ እየታየበት ቆይቷል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተለይም ከወጣቶች አካባቢ የዓድዋ በዓል ልዩ ትኩረት እየተሰጠው መምጣቱ በግልጽ ይታያል፡፡

ይኸውም ባለፈው ዓርብ የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በተለይ በአዲስ አበባ አራዳ ጊዮርጊስ ዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ሐውልት አካባቢ ሳቢ በሆነ መልኩ መከበሩ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ በዕለቱ የታሪኩ ዋነኛ ምልክት በሆነችው የዓድዋ ከተማም በደመቀ መልኩ ሲከበር በዕለቱም በርካታ አነጋጋሪ ክስተቶች ታይተውበት አልፏል፡፡

ከትንግርት ባለፈ የተዘነጋችው ውጫሌ

በቼክ ሪፐብሊክ መዲና ፕራግ ከሚገኙ በርካታ የቡና ሽያጭ ከሚያካሂዱ ካፍቴሪያዎች በስመጥርነቱ ካፌ ሉቭር የተባለውን የሚስተካከለው የለም፡፡ ይህ ካፍቴሪያ እ.ኤ.አ. በ1902 የተቋቋመ ሲሆን በመጀመርያውና ሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ጉዳት ደርሶበት ቢያልፍም እስካሁን ድረስ በዝነኝነቱና በርካታ ቱሪስቶች ቡና ከመጠጣት ባለፈ ለመጎብኘት ይተሙበታል፡፡ ምንም እንኳ በከተማዋ ፕራግ ከዚህ ካፍቴሪያ የበለጠ ዕድሜ ያላቸው ካፍቴሪያዎችና ሆቴሎች ቢኖሩም በቱሪስቶች ፍሰትና መጎብኘት ልዩ ሥፍራ ይሰጣል፡፡ ለዚህ ካፍቴሪያ ዝነኝነት ግን ምናልባትም በኢትዮጵያውያን ዕይታ ይህ ነው የተባለ ታሪክ አለው ለማለት ያስቸግር ይሆናል፡፡ ነገር ግን ካፌ ሉቭር ዝነኝነቱን ያጎናፀፈው ዋና ምስጢሩ በ1940ዎቹ በአንዲት ቀን ታዋቂው ሳይንቲስት አልበርት አንስታይን ለጥቂት ደቂቃዎች ተቀምጦ ቡና ስለጠጣበት ብቻ ነው፡፡

እንደ ፕራግ ሁሉ በሌሎችም የምዕራባውያን ከተሞች ከታዋቂ ግለሰቦችና መሪዎች መጎብኘት ጋር ዕድለኛ የሆኑ ካፍቴሪያዎች፣ ሆቴሎችና የሕዝብ ማዘውተሪያ ቦታዎች ዕውቅናቸው እየገዘፈ ከትውልድ ወደ ትውልድ በመሻገር ሙዚየም እስከመሆን የደረሱ በርካታ ሥፍራዎች ዛሬ ድረስ አሉ፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ሰፊ ታሪክና አስደማሚ ቅርሶች ባሉበት አገር ደግሞ በርካታ ታሪካዊ ሥፍራዎችና ሰፊ እሴቶች የሚገባቸውን ክብር ተነፍገው እንደተረሱ ይስተዋላል፡፡

ለዚህ ደግሞ ታሪካዊቷን የውጫሌዋን የይስማ ንጉሥ መንደር መመልከት ከበቂም በላይ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 460 ኪሎ ሜትር የምትገኘው ውጫሌ በኢትዮጵያ ውስጥ በታሪክ የገዘፈ ስም አላት፡፡ በተለይም ከከተማዋ አምስት ኪሎ ሜትር ያህል ርቀት በአምባሰል ወረዳ የምትገኘው የ03 ቀበሌዋ ‘ይስማ ንጉሥ’ ታሪክ ብዙ ተብሎላታል፤ ብዙም ተዚሞላታል፡፡ ብዙም ተገጥሞላታል፡፡ ይህች ሥፍራ ከኢትዮጵያም አልፋ ለአፍሪካውያን ኩራት የሆነው የዓድዋ ጦርነት መንስኤ የሆነው የውጫሌ ውል ስምምነት የተፈረመባት ነች ይስማ ንጉሥ፡፡

የአኩሪ ድል መነሻ የነበረችው ይስማ ንጉሥ ባትኖር ኖሮ ዛሬ ስለ ዓድዋ ድል በኩራት መናገር ባልተቻለ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎችም ሆኑ አመራሮች ይናገራሉ፡፡ ‹‹በዚች ሥፍራ የውል ስምምነቱ ሳይሳካ ቀርቶ ወደ ጦርነት ባይገባ ኖሮ ምናልባት ዛሬ የምንዘክራትን የዓድዋ በዓል ማሰብ አይቻልም ነበር›› ሲሉ የአምባሰል ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፀሐይ ወሌ ባለፈው ሳምንት በይስማ ንጉሥ ጉብኝት ያደረጉ ለነበሩ ጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡

የዚህ ታሪካዊ ሥፍራ በኢትዮጵያ የነፃነት ተጋድሎ ላይ የማይጠፋ አሻራ ቢኖረውም ሥፍራው በጎብኚዎች ብዙም ተደራሽ አለመሆኑ እሳቸውንም ሆነ የአካባቢውን ነዋሪ እንደሚያስቆጨው ገልጸዋል፡፡ ከቱሪስት ፍሰቱ ጋር በተያያዘም የአካባቢው ነዋሪም ሆነ አገሪቱም በኢኮኖሚ ረገድም ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም እያገኙ አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በ2000 ዓ.ም. የውጫሌ ስምምነት የተፈረመበትን ሥፍራ በማልማት የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እስከ 25 ሚሊዮን ብር የሚፈጅ የፕሮጀክት እንደሚገነባ ይፋ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም የመሠረት ድንጋይ ከመጣል ያለፈ ምንም ነገር አለመሠራቱን ሪፖርተተር በሥፍራው በተገኘበት ወቅት አረጋግጧል፡፡ ይህ ፕሮጀክትም ረጅም ርቀት መጓዝ አለመቻሉን ወ/ሮ ፀሐይም ያረጋገጡት ሐቅ ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት በሥፍራ አራት የሳር ጎጆዎችና የቦታውን ታሪካዊነት የሚገልጽ ከተተከለ ታፔላ በስተቀር ምንም ነገር አይታይበትም፡፡ ከዋናው መንገድ የሚያስገባ ተስማሚ መንገድ የሌለው በመሆኑ በብዛት እንደማይጎበኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ነገር ግን ከአሥር ዓመት በላይ የቆየውን ፕሮጀክት ዕውን ለማድረግ የፕሮጀክቱ ዲዛይን ተጠናቆ ወደ ግንባታ ለመግባት እንቅስቃሴ መጀመሩን የወረዳው የቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

እንደ ኃላፊዋ በ25 ሚሊዮን ብር የሚገነባው ፕሮጀክት ሙዚየምና ለቱሪስቶች መዝናኛ የሚሆን ሎጅ ሲኖረው የአፄ ምኒልክ፣ የደጃዝማች ዮሴፍና ለኢጣልያ ንጉሥ ወኪል ሆኖ ስምምነት ሲያደርግ የነበረው የኮንት አንቶኖሊ ሐውልት እንደሚቆም ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

ከፕሮጀክቱ ግንባታ ጎን ለጎን የታሪካዊ ሥፍራውን የበለጠ ለማግዘፍ እንዲረዳ በመንግሥት በኩል ይስማ ንጉሥን የዓድዋው የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ፕሮጀክት አካል እንዲሆን ጥረት እያደረጉ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ገና በመንግሥት ውሳኔ እንዳልተደረሰበት ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በእርግጥ ዘመን ተሻጋሪው የዓድዋ ጦርነት መንስኤ የሆነው የይስማ ንጉሥ በኢትዮጵያ ውስጥ አስታዋሽ ያጣ ብቸኛው ሥፍራ አይደለም፡፡ ይልቁንም በአካባቢው ያሉ አጎራባችና ራቅ ያሉ ሥፍራዎች በተመሳሳይ ትኩረት ተነፍጓቸው ያሉ ይገኛሉ፡፡ ለአብነትም አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን መስዋዕት አድርገው የወደቁበት የመቅደላ ተራራ (መቃብራቸው)፣ በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚባለው የጣና ሐይቅ ገዳም፣ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እንደነበረች የሚነገርላት የመቅደላ ከተማና ሌላ በርካታ ሥፍራዎች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

ታዋቂው የውጫሌ ውል ሚያዝያ 16 ቀን 1873 ዓ.ም. የተፈረመ ሲሆን 127ኛው ዓመቱ ነው፡፡ በዚህ ውል ውስጥ ከተጠቀሱ 20 አንቀጾች ውስጥ 17ኛው አንቀጽ ለጦርነቱ መነሻ መሆኑ በታሪክ ተዘግቧል፡፡ ይህንን ውል በኢጣልያ በኩል የተዋዋለው ኮንት አቶኒሊ ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል ራሳቸው አፄ ምኒልክ ነበሩ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱንም በትርጉም በኩል ሲያገለግሉ የነበሩት ግራዝማች ዮሴፍ ንጉሤ መሆናቸው ይነገራል፡፡

ድምቀትና ተቃርኖ በሶሎዳ ተራሮች

ከውጫሌ በተሻለ በየዓመቱ የኢትዮጵያውያን ተጋድሎ የሚበስስርባት የዓድዋ ከተማ የተሻለ ትኩረት የተሰጣትና በጎብኚዎችም ረገድ የተሻለ ዕይታ እንዳላት ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ከታሪካዊ ፋይዳነቷና ከነፃነት ምልክትነቷ አንጻር ዓድዋም ቢሆን የሚገባትን ክብር አግኝታለች ተብሎ በሙሉ ድፍረት መናገር ይከብዳል፡፡ ከጥቂት ጊዜ ወዲህ ግን ተስፋ ሰጪ የሚመስሉ እንቅስቃሴዎች መታየት ጀምሯል፡፡ ለማሳያም ያህል ከአንድ ወር በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ይፋ የሆነውና መንግሥት ለመነሻ 200 መቶ ሚሊዮን ብር የመደበለት የዓድዋ ፓን አፍሪካን ዩኒቨርሲቲን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ባለፈው ዓርብ የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. የተከበረውን የ122ኛውን የዓድዋ ድል ቀንን ተከትሎም የከተማዋ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር የራሱን ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል፡፡

ፕሮጀክቱ ከ260 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ተክለብርሃን ደረሰ ከበዓሉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ምንደብድብ (ማርያም ሸዊቶ) በተባለው ሥፍራ በነበረው ጉብኝት ወቅት ገልጸዋል፡፡

ከአዲስ አበባ 1066 ኪሎ ርቀት ላይ ታላቁ ጦርነት ድል የተገኘበት ሥፍራ ዓድዋ ከተማና በዙሪያዋ ባሉ ገመገሞች ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይ በየካቲት 23ቱ (1888 ዓ.ም.) ጦርነቱ የተካሄደባቸውና አርበኞቹ የአውሮፓውን ቀኝ ገዢ ድባቅ የመቱባቸው ሶሎዳ ተራራ፣ ማርያም ሸዊቶ፣ አዲተቡን፣ ረቢ አርእየኒ (እግዚሃር አሳየኝ) እና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ በእነዚህም ሥፍራዎች በላቀ ተጋድሎ ድል ያደረጉ አርበኞችንና የተማረኩ የጣሊያን የጦር አመራሮችን ጨምሮ የመታሰቢያ ሐውልት ከ100 ዓመታት በኋላ ለማቆም ዕቅድ ተይዞ ወደ ትግበራ እየተገባ መሆኑን የወረዳው አመራሮች በዘንድሮው ክብረ በዓል አከባበር ወቅት አሳውቀዋል፡፡ ከመታሰቢያ ሐውልቶች ጎን ለጎን ደግሞ ሙዚየምና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት ለመገንባት መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም ለፊታውራሪ ገበየሁ፣ ለራስ አሉላ አአባነጋ፣ ለባሻ አውአሎምና ለመሳሰሉ አርበኞች ሐውልት ሲቆሙ በመጨረሻዋ የጦርነቱ ፍጻሜ ላይ ለተገደለው ኢጣልያዊው ጄኔራል ዳቦሚዳም የመታሰቢያ ሐውልት እንደሚቆምም ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ለአፄ ምኒልክም ሆነ በጦርነቱ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ታሪክ በደማቁ የሚገልጽላቸው እቴጌ ጣይቱም በሥፍራው ሐውልት እንዲቆምላቸው በፕሮጀክቱ አለመካተቱ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ተስተውሏል፡፡ የፕሮጀክቱ ኃላፊዎችም በዚህ ጉዳይ ለምን ንጉሡና ንግሥቲቱ ሊካተቱ እንዳልቻሉ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

ምንም እንኳ የፕሮጀክቱ መገንባት ለዓድዋ ከተማም ሆነ ለአገሪቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም የጦርነቱ ድል ዋና አካላት የሆኑትን (አፄ ምኒልክንና ባለቤታቸውን እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ) ወደ ጎን መተው እንደ ታሪክ ሽሚያ ወይም ማፍለስ ተደርጎ የተመለከቱት አሉ፡፡

ዝክረ ዓድዋ

ለዚህ ዕይታ ደግሞ ተጨማሪ ጥርጣሬ ያጫረው በዓድዋ ከተማ ሶሎዳ ሆቴል ውስጥ ከበዓሉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በተከፈተው የፎቶ ዐውደ ርዕይ የታየው ክስተት ነው፡፡ ዐውደ ርዕዩ የድል ቀኑን የሚዘክር ሲሆን በርካታ ኢትዮጵያውያን አርበኞች በዓድዋ ድል ያደረጉትን ተጋድሎና አርበኝነት የሚዘክር ሲሆን ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች መሳተፋቸውን የሚያሳይ ነበር፡፡ ነገር ግን በግልጽ ይታይ የነበረው ተቃርኖ የድሉ መሪ የሆኑት የንጉሠ ነገሥቱ አፄ ምኒልክ ፎቶ አንድም አለመኖሩ ነው፡፡ እቴጌ ጣይቱም ቢሆኑ ለብቻቸው ጎላ ብሎ የሚታይ ፎቶ የሌላቸው ሲሆን አንድ ፎቶ ብቻ ከሌሎች አርበኞች ጋር በጋራ ውስጥ ነበር የሚታዩት፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ ‹‹የዓድዋ ድል በዓል ያለ ምኒልክና ጣይቱ›› የሚያስብሉ ሆነው ታይተዋል፡፡ በዕለቱ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) እና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ሒሩት ወልደማርያም (ዶ/ር) በተገኙበት ዋናው በዓልም ቢሆን የአፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ስም በቀጥታ ላለመጥራት ሲሞክሩ በአዘጋጆቹ ላይ ተስተውሏል፡፡ ይልቁንም ንጉሡና ንግሥቲቱ በማለት መጥራትን መምረጣቸው ተስተውሏል፡፡

ምናልባትም ንጉሡንና ንግሥቲቱን በሙሉ ስም በመጥራት ሲያወድሱ የታዩት ከአዲስ አበባ እስከ ዓድዋ ከ1000 ኪሎ ሜትር በላይ በእግር የተጓዙት ‹‹የጉዞ ዓድዋ ተካፋይ አባላት ብቻ ነበሩ የተስተዋሉት፡፡ በነ ያሬድ ሹመቴ የተመራው የተጓዥ ቡድን ‹‹ዳግማዊ ምኒልክ፣ ምኒልክ…›› በማለት እያወደሱ ለቅፅበት በበዓሉ ሥፍራ ተገኝተው በዓሉን በዘከሩበት ወቅት ነበር፡፡

የእግር ተጓዦቹ በክብረ በዓሉ አዘጋጆች ብዙም ቦታ ያልተሰጣቸው ቢሆንም ከከተማው ነዋሪዎች ግን ደመቅ ያለ አቀባበል ተደርጎላቸው ነበር፡፡ በሶሎዳ ተራራ ስር በዓሉ ለተከበረበት ሥፍራ በፕሬዚዳንቱ ፊት አጭር ዝማሬን አሰምተው ተጓዦቹ በሚያልፉበት ወቅት በርካታ ታዳሚዎች አጅበዋቸው ወደ አክሱም ኤርፖርት ሸኝተዋቸዋል፡፡

ከተጓዦቹ ሽኝት በኋላ ፕሬዚዳንቱና ሚኒስትሯ ባደረጉት ንግግር የበዓሉ ፍጻሜ ሆኖ ተደምድሟል፡፡፡ ነገር ግን በበዓሉ የተስተዋሉ የሚያተጉና ብዙ ውይይትና ግልጽነት የሚጠይቁ ጉዳዮችን ጥሎም አልፏል፡፡

ዝክረ ዓድዋ

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...