Saturday, March 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ባለህበት እርገጥ?

እነሆ ከወሎ ሠፈር ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። መንገድ አልቆ መንገድ ልንጀምር፣ ዕድሜ ጨርሰን ዕድሜ ልንቀጥል እንራመዳለን። ወያላው፣ ‹‹የሞላ ሁለት ሰው! ከእነ ሠርተፊኬቱ፤›› ብሎ ይጮሃል። ‹‹የምን ‘ሠርተፊኬት’ ነው የሚያወራው?›› ሰው ግራ ገብቶት ይደናበራል። ‹‹ምነው እነ እንቶኔ ብቻ ናቸው ለጥቅም ብለው ለሚሰበሰቡላቸው ታዳሚዎች ‘ሠርተፊኬት’ መስጠት ያለባቸው? እኛስ ከማን እናንሳለን?›› ወያላው የሰውን መደናገር ግልጽ አደርጋለሁ እያለ ነገር ያወሳስባል። ‹‹አብዷል እንዴ ይኼ?›› ከመሀላችን አንዱ ይጠይቃል። ‹‹መቼ እሱ ሆነና? የትንኙን መራባት፣ የዝንቡን ቁጥር መጨመር ሳይቀር ከሕዝብ አስተዳደር ጋር ካላዛመዱ የማይሆንላቸውን እያየ እኮ ነው የሚቀባጥረው፤›› ይመልሳል ሌላው። እንዲህ ውጥንቅጡ በወጣ የእንካ ሰላንትያ ቅብብሎሽ ወጪ ወራጁ በነገር ይተጋተጋል፡፡ የሆነውን ሁሉ በመልካምና በክፉ ትውስታ ጉያ አሽቀንጥረን ጥለን በዘመን መለዋወጥ የምናምን ሁሉ፣ ራሳችንን ከዘመኑ ጋር ማላመድ አቅቶን ስንታይ ልዩ ፍጥረት እንመስላለን፡፡

‹‹ሐበሻ ብዙ ነገር ረስቶ በነገር ጉሽሚያ ወዲያና ወዲህ ተከፍሎ ያሳለፈውን ዘመን ዘንግቶ፣ በአንድ እንቅብ ተሰፍሮ አንድ ዓይነት ይመስላል፤›› የሚለው ወያላችን ነው፡፡ ‹‹በአሮጌ በሬ እያረሱ የኑሮን ሩጫ በትዕግሥት መሮጥ ስለማይቻል፣ ባለመሆን ጥላሸት የከሰለን ዕድል በብርሃን እንዶድ ለማጠብ ተስፋ ስለሚያሻ ሁሉም ጥቂት ማንነቱን ረስቶ፣ ጥቂት ኑሮውን ችላ ብሎ ከአቅሙ ይልቅ አምሮቱን አስቀድሞ ባልተጨበጠ ሐሳብ ይንደፋደፋል፤›› ብሎ ይመልሳል ሌላው። ‹‹ዓለም አሮጌ ጆንያዋን እንደ ወትሮው ሁሉ አራግፋ በአዲስ ጅማሮ ልታስሮጠን ፍቅረኛዋን እንደምታማልል ኮረዳ የዓመት ግብሯን ታገባለች። ከዕውቀት ሐዘን፣ ከጥበብም ብዛት ተስፋ ቢስነትን ያተረፈ መስሎ በማስመለስ የመኖር ዘይቤ ይህችን አታላይ ዓለም የናቃት ይመስላል። የመሆንና ያለመሆን መንገድ እንዲህ ቅዠት ባየለበት ስሜት ይጀመራል፤›› የሚሉት አዛውንት ተሳፋሪ ናቸው። እነሆ መንገድ!

‹‹ስማ አንተ! ምን ለማለት ፈልገህ ነው?›› አንድ አፉን ያዝ የሚያደርገው ኮስታራ ጎልማሳ ወያላው ላይ አፈጠጠበት። ‹‹ምን አልኩ ጋሼ?›› ወያላው ጎልማሳው ስለምን እየጠየቀው እንደሆነ ስላወቀ ከሸረኛ ሳቅ ጋር መለሰለት። ‹‹ያልሰማሁ መስሎህ እንዳይሆን! እንኳን ይኼንን የዝንብ ጠንጋራም እናውቃለን፤›› አለ ጎልማሳው። ወያላው ቀነጣጥቦ ካቋጠረው ጫት ጥቂት ቆንጠር አድርጎ ሲያበቃ፣ ‹‹ጉድ እኮ ነው! ‘የፌስቡኩን’ አደን ሳትጨርሱ ደግሞ ታክሲ ተራ ገባችሁ?›› ብሎ ያስነሳውን አቧራ የባህር ማዕበል አስመስሎት አረፈ። ‹‹ስለሠርተፊኬቱ እየጠየቅከኝ ከሆነ ግን ላንተ በቃ ሁለት እናደርግልሃለን!›› አለ። ‹‹ታዲያ ይኼንንም በጉልበት ከምትወስዱት በፀባይ፣ በመልካምነት፣ ከሰው ጋር በማደርና አገርን በቅንነት በማስተዳደር ቢሆን ይመረጣል፤›› አለው። ‘የመረቀነ ማንን ይፈራል?’ የሚል ይመስላል ወያላችን።

ጎልማሳው ተንቆራጠጠ። ‹‹በማን ላይ ሆነሽ ማንን ታሚያለሽ’ አሉ! አሁን አንተ በማን ላይ ሆነህ ነው እኛ እናንተ እያልክ የምትዘባርቀው?›› ብሎ ጎልማሳው ሲያፈጥ ወያላው፣ ‹‹ስንፈልግ ችላ በምንለው ስንፈልገው በምንዘክረው ሕገ መንግሥታችን ላይ ቆሜ ነዋ። ዛሬ እኮ መሬቱም የሕዝብ አልሆነ፤›› ብሎ ከራሱ ከጎልማሳው ጎን የተቀመጠ ተሳፋሪ ወያላውን በይፋ በመደገፍ መለሰ። ‹‹አቦ በቃህ ነገር አብርድ! ይኼ ያለንበት የከፋ ጊዜ በምጥ ደርሶ በምጥ እየሸኘን ሌላ ጣር ልታመጣ ነው?›› በጎርናና ድምፁ ሾፌራችን በገላጋይነት መሀል ገባ። ‘ምጥ’ ሲባል የነቁት አዛውንቱ ተሳፋሪ ጮክ ብለው፣ ‹‹እህ በይ ግድ የለም ግፊው ይወለዳል፣ ሽል ይፀነስ እንጂ አጥንት ሆኖ ያድጋል’ ይባላል ይኼውልህ፤›› ብለው ፈገግ አሉ። ገና ጉዞው ከመጀመሩ ከወዲህ ወዲያ የተነሳውን አለመግባባት ስናስተውል የተወሰንነው በግርምት ፈዘናል። እስከ መቼ በማንግባባበት ጎዳና ፈዘንና ግራ ተጋብተን እንደምንኖር ብቻ እንጃ!

ጉዟችን ቀጥሏል። በታክሲያችን የሬዲዮ ድምፅ ማጉያ በኩል አፍሬም ታምሩ፣ ‘አንቺ ልጅ አንቺ ልጅ’ ይላል። መጨረሻ ወንበር ላይ ከተቀመጥነው ተሳፋሪዎች ሁለቱ ስለመጪው ቅዳሜ ምሽት ሲጨዋወቱ ይሰማሉ። ‹‹እኔ ድሮም አንድ ገዴ አይደለችም እኮ፤›› ይላል አንደኛው። ‹‹እንዴት?›› ይለዋል ወዳጁ። ‹‹ሰባትን ትቼ አንድ ቁጥር ማልያ ለብሼ መጫወት እንደጀመርኩ እኮ ነው ያኔ እግሬ የተሰበረው። ይኼው የዝሆን ሎተሪ በመጨረሻዋ ቅዳሜ ሲወጣ ባዶ ሆኖ አረፈው…›› አለ በቁጭት። ከቁጥር ተጣልቶ በቁጥር ተስፋ አድርጎ። ‹‹እንዲያው ሰውን ግን አይተኸዋል? ለመስከርና ለመዝለል ቋምጦ ሎተሪ ፊቱን ሲያዞርበት ቅዳሜን የዓመቱ የመጨረሻዋ ብሎ ሰይሞ እንዳይሆን ሲሆን ይደር?›› ጠየም አጠር የሚለው ነው የሚገረመው።

‹‹ታዲያስ! ‘ሰበቡ ነጠላ ለብሼ’ የሚል ዘፈን የተዘፈነው ለምን ይመስልሃል? ‘ሳታማኸኝ ብላ’ የተባለውስ ያለምክንያት ይመስልሃል? የእኛ ሰው ዘመኑን በሙሉ ሰበብ አስባብ እየፈለገ መሠረት ለሌለው ነገር ለመጥፋትና ለመጠፋፋት የሚያክለው ስለሌለ እኮ ነው፤›› አለ ነገሩን የጀመረው ወጣት። ‹‹ኤድያ ጀመረህ ደግሞ እዚህ የፈረደበት ሕዝብ ላይ እንደ ሐምሌ ዶፍ መውረድ። ይልቅ ምናለበት ሁሉንም በአንድ መውቃት ትተህ ስለዚያች ቆንጅዬ ልጅ መጨረሻ ብትነግረኝ?›› ይላል የወዲያኛው። ይኼው ልጅ በአደባባይ ሙግት ነፍሱ የዛለች በኩሽና ጨዋታ ቀልቡ የተመሰጠ ግዴለሽ እንደሆነ ያስታውቃል። መሰልቸት ስንቱን ከሚጠበቅበት ሥራውና ኃላፊነቱ አዘግይቶት ይሆን?

‹‹ልጅቱማ ምን አደረገች መሰለህ?›› ቀጥሏል። ‹‹እንዴት ልንገናኝ ነው ታዲያ? ባይሆን ልብሽን ዛሬ ባትሰጪኝ ስልክሽን ስጪኝ አልኳት። ምን ብትለኝ ጥሩ ነው ይኼኔ? ‘ከምርጫ በኋላ!’ አትለኝ መሰለህ? ‘ከምርጫ በፊትስ?’ እላታለሁ ‘ቅስቀሳ ላይ ስለምሆን ቢዚ ነኝ!’ ብላኝ በኮንትራት ታክሲ ተሳፍራ ገትራኝ ሄደች። አይ የዘመኑ ሴቶች! አይ እኛ!›› ብሎ ራሱን ነቀነቀ። ‹‹ሐሳብን በነፃነት በየጎዳናው መግለጽ ላይ ቁጥጥር ከተጀመረ እንደ ቀልድ መጀንጀን ተረት ሆኖ ሊቀር ነው በለኛ!›› ብሎ ተራውን ጓደኛው ከት ብሎ ሳቀ። ‘በተለያየን ቀን በተጣላን ዘመን ብተክዝም ነፍሴ፣ ፎቶግራፍሽን ሳይ ፈገግ ይላል ጥርሴ’ ሆኖ ነው መሰል ነገሩ ሳቁ ወደ ሌሎቻችን ተጋባ፡፡

ወያላው ሒሳብ ይሰበስባል። ከድምፅ ማጉያው በኩል የአገራችን እግር ኳስ እንደ ጉድ ይወቀጣል። (የማይወቀጥ ምን ብሔራዊ ነገር አለን አትሉም?) የጋዜጠኞቹ ልክ የሌለው ትችት አልበቃ ብሎ ደግሞ አድማጩ በስልክ እየደወለ ያ ቢሆን ያ ባይሆን ይላል። አንዱ ‹‹አሠልጣኝ ካልተለወጠ አበቃልን፤›› ሲል ሌላው ቀበል አድርጎ፣ (በአንድ ፓርቲ የበላይነት ስለምንጨቆን ነው ዴሞክራሲ የማያድገው ሲል በከረመበት አፉ) ‹‹ከአንድ ክለብ ብቻ በርካታ ተጫዋቾች ስለተመረጡ ነው የተሸነፍነው፤›› ይላል። የማይታየውን በድምፅ የሚሠራ ድራማ ሳናገባድድ ታክሲያችን ውስጥ ተመሳሳይ እሰጥ አገባ ተነሳ። ‹‹የቀደመው አሠልጣኝ ይሻለን ነበር!›› አለ አንዱ። ‹‹እግዚኦ! ፖለቲካው ላይ እንደለመደብን በትንሽ ትልቁ ያለፈን ስንመኝ፣ ያላየነው ነገና ያልተቀበልነው ዘመን ገና ከፊታችን እያለ ያለፈው ይሻላል ማለት ምን ይሉታል? ኧረ ተው ጎበዝ እያስተዋልን?›› ትላለች መልከ መልካም ወጣት።

‹‹እንጃ! ንገሪልኝ እስኪ። ‘ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም’ ብለን መተረት የጀመርነው ድሮ በንጉሡ ጊዜ ነበር። ጭራሽ ዛሬ ካለፈው መማር አቅቶን ፍሬ ያለው ነገር መሥራት ቀርቶና መናገር ጠፍቶብን ይረፈው? አያድርስ እኮ ነው!›› ሲል ኮስታራውና ብስጩው ጎልማሳ አገዛት። ‹‹ታዲያ ዝም እንበልና ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ሌላ 31 ዓመት እንጠብቅ?›› አለ ጋቢና የተሰየመ ትንንሽ ዓይኖች ያሉት ወጣት። ‹‹አይ የለም በየመንገዱ እየቆመን ጎማ ስንቀይር ነዋ የተሻለ የምንፈጥነው? እንዴ ምነው ሰው እንዲህ ትዕግሥት አላውቅ አለ?›› ወጣቷ ጦፈች። ውዝግቡም ተጧጧፈ፡፡ አለመደማመጥ እንደተለመደው ታክሲያችን ውስጥ ሲነግሥ፣ ‹‹አይ እኛ ተቧድኖ ከመናቆር ወጥተን ተባብረን የምንሠራው መቼ ይሆን?›› አሉ አዛውንቱ! በእንጥልጥል የቀረ ጥያቄ!

በተከፋፈለ አስተሳሰብ በተቃረነ መንፈስ የተጠመደው መንገዳችን ወደ መገባደዱ ነው። ወያላው ውረዱልኝ እስኪለን ቸኩሎ፣ ‹‹አሁን ለራሳችን ዕረፍት ሳንሰጥ የምናርፍ መሰልን፤›› ይላል። በምርቃና ተንሳፎ አጠገቡ ያለውን ሁሉ ከሰው ሳይቆጥር ይጨፈጭፈናል። ‹‹ፍሬንድ! የምንጨቃጨቀው በዕውቀት የሚጨቃጨቅልን ስለጠፋ መሰለኝ፤›› ስትል በሞባይል ስልኳ አሥር ጊዜ ራሷን ፎቶ ስትቀጨቅጭ የነበረች ወጣት፣ ‹‹ራሳችን ይላል እንዴ! እኛም ሁሌም ዝግ የሆንን መስሎኝ?›› ብላ መልከ መልካሟ የዕድሜ አቻዋ ትደረብለታለች። ‹‹አቤት! የሴቶች የውይይት ተሳትፎ እንዲህ ከቀጠለ ታየኝ ይህች አገር የት እንደምትደርስ?›› የሚለው ደግሞ በዓመቱ የመጨረሻ ቅዳሜ ዓይኔ ባረፈባት ልጅ ልቤ ተሰበረ ባዩ ነው።

‹‹እናንተ ልጆች እውነት በዚህ አያያዛችሁ ትንሽ ገፋ የምታደርጉ ይመስላችኋል ግን?›› ሲሉ አዛውንቱ ድንገተኛ ጥያቄ ሰነቀሩ። ‹‹ምኑን ፋዘር?›› አላቸው መልኬ በቃኙ ፎቶግራፈር። ‹‹ሁሉን ነገር! ኑሯችሁን፣ ዴሞክራሲውን፣ ስፖርቱን? በዚህ የአለመደማመጥ ጭፍን ጥላቻና ትችት ዘዬያችሁ ከቀጠላችሁ የምትራመዱ አይመስልም፤›› አሉ ግርማ ሞገሳቸውን እንደተላበሱ በእርጋታ። ‹‹የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች ስትባሉ እንዳላደጋችሁ የዛሬ አበባዎች የነገ ጠውላጐች ተብላችሁ ያደጋችሁ ይመስል፣ ባህልና ሃይማኖት እንዲሁም ሥርዓት የሚያኮላሽ እንካ ሰላንትያ መልመድ ምን ይሉታል? ዘመንና ዕድሜ እላያችን ላይ እየቆጠረ እኛ እያደርን እዚያው ስንገኝ ትንሽ በራሳችን አናፍርም?›› ብለው ተሳፋሪውን ቃኙት። ወያላው፣ ‹‹መጨረሻ›› ብሎ በሩን ከፈተው። አዛውንቱ ከዘራቸውን ተደግፈው እየወረዱ መንገዳቸውን ሲጀምሩ ወጣቱ ጠጋ ብሎ፣ ‹‹ምኑ ነው የጠፋብን?›› ሲላቸው፣ ‹‹የጠፋብንን ከምትጠይቀኝ የቀረንን አትጠይቀኝም? የጠፋብንማ ተቆጥሮም አያልቅም፡፡ ስንደምርና ስንቀንስ ብንውል ባለንበት ነው ስንረግጥ የምንገኘው፤›› ብለው እብስ አሉ፡፡ መልካም ጉዞ!      

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት