Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ባንክ ‹‹ሲቢኢ ብር›› የተሰኘ የሞባይል ክፍያ አገልግሎት ጀመረ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ‹‹ሲቢኢ ብር›› በማለት የሰየመውንና የሞባይል ስልክን መሠረት በማድረግ የሚሰጠውን የባንክ አገልግሎት ማስጀመሩን አስታወቀ፡፡ ለዚህ አገልግሎት ከ2,600 በላይ ወኪሎችና ከ1,350 በላይ ተቋማትን እንደመለመለ ገልጿል፡፡

ባንኩ ስለአዲሱ አገልግሎት ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በቴክኖሎጂው አማካይነት በንግድ ባንክ በኩል አገልግሎት እንዲሰጡ ውክልናም ፈቃድም ከተሰጣቸው ተቋማት ጋር በመሆን፣ ለደንበኞች ሒሳብ መክፈት፣ ገንዘብ ማስተላለፍ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም የቅድመ ክፍያ የስልክ የአየር ሰዓት ክፍያ በመፈጸም ለደንበኛው የካርድ ሒሳብ መሙላትና ሌሎች የባንክ አገልግሎቶች በሲቢኢ ብር አማካይነት የሚቀርቡ አገልግሎቶች ናቸው፡፡

በመሆኑም ባንኩ ‹‹ሲቢኢ ብር›› በተሰኘው አገልግሎት አማካይት ደንበኞቹ በቅርንጫፍ ባንኮች የሚሰጡ አገልግሎቶችን በሞባይል ስልካቸው በመጠቀም አማራጭ  የባንክ አገልግሎት እንዲያገኙ ይረዳቸዋል ተብሏል፡፡ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ፣ በሱማሌኛ፣ በአፋርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችል አገልግሎት ሆኖ እንደቀረበ ታውቋል፡፡

ንግድ ባንክ ይህን አገልግሎት መስጠት የሚችሉ የንግድ ድርጅቶችን በመመልመልና ተገቢውን ሥልጠና እንዲሁም ፈቃድ በመስጠት የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማስፋፋት አዲሱ አገልግሎት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብሏል፡፡

‹‹ሲቢኢ ብር›› የሞባይል ስልክን መሠረት በማድረግ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የሚችልበት ሙከራ ግንቦት 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ተጀምሮ ነበር፡፡ ሙከራው በመሳካቱና የተዘረጋው ቴክኖሎጂም የሚፈለገውን አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል በመረጋገጡ በአሁኑ ወቅት ወደ ሙሉ ትግበራ ተሸጋግሯል፡፡ እስካሁንም አገልግሎቱን በሚሰጡ ወኪሎች፣ ላከናወኑት የዕቃ ሽያጭ ክፍያ በ‹‹ሲቢኢ ብር›› በኩል የሚቀበሉ የንግድ ተቋማት 225,980 ተጠቃሚዎችን ማሰባሰብ እንደቻሉ ባንኩ ገልጿል፡፡ የወኪሎቹን፣ የንግድ ተቋማትንና የደንበኞቹን ቁጥር ለማሳደግ መጠነ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ባንኩ አስታውቋል፡፡

‹‹ሲቢኢ ብር›› በቦታና በጊዜ ሳይገደብ የፋይናንስ አገልግሎትን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ፣ ከዚህ ቀደም በርቀት፣ በሚያንቀሳቅሱት አነስተኛ ገንዘብ መጠንና በሌሎችም ምክንያቶች የተነሳ፣ ወደ ባንኮች መሄድ ለማይችሉ ወይም የባንክ አገልግሎት ማግኘት ላልጀመሩ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ተብሏል፡፡

የሲቢኢ ብር ደንበኞች ከሚያገኟቸው አገልግሎቶች ውስጥ በዋናነት ከተጠቀሱት ውስጥ ገንዘብ ማስተላለፍ ሲሆን፣ ደንበኞች በሞባይል ስልክ ቁጥራቸው አማካይነት ከተከፈተው የሲቢኢ ብር አካውንት በኩል ገንዘብ ወደ ሌላ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መላክ የሚችሉበት ሥርዓት ነው፡፡  በአገልግሎቱ ተጠቃሚ ያልሆኑ ሰዎችም ቢሆኑ፣ የሞባይል ስልካቸውን ብቻ በመጠቀም ገንዘብ ማስተላለፍ የሚችሉበት አገልግሎት እንደሆነ ንግድ ባንክ አስታውቋል፡፡

ደንበኞች የሞባይል ስልካቸውን በመጠቀም የአገልግሎት ወይም ለዕቃ ግዥ ክፍያ ለመፈጸም በአካል በመቅረብ ወይም ባሉበት አካባቢ ሆነው ክፍያ ማስተላለፍ የሚችሉበትን አሠራር ያካተተው ይህ የክፍያ ዘዴ፣ ገንዘብ ወደ ሒሳብ ማጠራቀሚያ ለማስገባትም ተገልጋዮች የ‹‹ሲቢኢ ብር›› የአገልግሎት ወኪሎች ዘንድ በመሄድ ገንዘብ ማስገባትና ማስወጣት የሚችሉበትን አሠራር አስተዋውቋል፡፡   

በዚህ ‹‹የሲቢኢ ብር›› አገልግሎት አማካይነት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በተደረገ ስምምነት መሠረት፣ የአየር መንገዱን የጉዞ ትኬት መግዛት የሚቻልበት ዘዴም ተመሥርቷል፡፡

ይህም ሆኖ ደንበኞቹ በተለይ በኢንተርኔትና በሞባይል ስልክ አገልግሎቱ መቆራረጥ ላይ ቅሬታ ሲያሰሙ ይደመጣል፡፡ በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ከተሞች የተተከሉ የኤቲኤም ማሽኖች እንዲሁም የኢንተርኔትና የሞባይል አገልግሎት መስተጓጎል እንደሚታይ ቢገለጽም፣ በአብዛኛው የኔትወርክ መቆራረጥ የፈጠረው ችግር ስለመሆኑ ንግድ ባንክን ጨምሮ ሌሎችም ባንኮች የሚሰጡት ምላሽ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሁኑ ወቅት ከ1,250 በላይ ቅርንጫፎችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመክፈት የፋይናንስ አገልግሎቶችን እያቀረበ ይገኛል፡፡ 1,660 የኤቲኤም ማሽኖችንና 7,241 የሽያጭ መዳረሻ (ፖስ) የክፍያ ማሽኖችን ለአገልግሎት በማዋል ከአገሪቱ ባንኮች ቀዳሚው ሆኖ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች