የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውጭ አገር ተጨዋቾችን አስመልክቶ ቀደም ሲል ለፕሪሚየር ሊግና ብሔራዊ ሊግ ክለቦች ያስተላለፈውን ውሳኔ ማሻሻሉን አስታወቀ፡፡ አንድ ክለብ የሚያስፈርማቸው የውጪ አገር ተጨዋቾች ቁጥር ከሦስት ወደ አምስት ከፍ እንዲል ማድረጉንም በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡
በአገሪቱ በሁሉም ክለቦች የውጪ አገር ተጨዋቾች እየተበራከተ መምጣቱ ለስፖርቱ ውድቀት እንደ አንድ ምክንያት ተደርጎ በመውሰድ የፕሪሚየር ሉጉም ሆነ የብሔራዊ ሊጉ ክለቦች ከ2008 የውድድር ዓመት ጀምሮ እያንዳንዳቸው ማስመዝገብ የሚችሉት የውጪ አገር ተጨዋች ቁጥር ከሦስት መብለጥ እንደሌለበት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ቀደም ሲል መመርያ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡
ይሁንና መመርያው ለአገሪቱ የእግር ኳስ ዕድገት እንደማይበጅ፣ ይልቁንም ውድቀቱን እንደሚያፋጥነው በመጥቀስ አንዳንድ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የፌዴሬሽኑን ውሳኔ በጽኑ ሲቃወሙት መቆየታቸውም ይታወሳል፡፡ ጉዳዩም የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን ለሁለት ከፍሎ እያወዛገበ መቆየቱ የሪፖርተር ምንጮች ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡
በመጨረሻም ፌዴሬሽኑ በነሐሴ መጀመርያ ለፕሪሚየርና ለብሔራዊ ሊግ ክለቦች ባስተላለፈው አዲስ መመርያ፣ ‹‹በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 14 በተራ ቁጥር 1.1 መሠረት አንድ ክለብ ሦስት የውጪ ተጨዋቾችን ለክለቡ ማስመዝገብ ይችላል፤›› በሚለው ዙሪያ የፌዴሬሽኑ ኢመርጀንሲ ኮሚቴ ጉዳዩን በጥልቀት በመመርመር በአገሪቱ የእግር ኳስ ስፖርትን ለማሳደግ የሚችሉ አካዴሚዎች ባለመስፋፋታቸው፣ በቂ የሆነ ቁጥር ያላቸው ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች በአገሪቱ ባለመኖሩ፣ አንዳንድ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በሚኖራቸው አህጉራዊ ውድድሮች አጥጋቢ ውጤት ባለማስመዝገባቸው ውሳኔው እንደገና እንዲታይ በመጠየቃቸው የተነሳ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የቀድሞውን ውሳኔ በመሻር አንድ ክለብ አምስት የውጭ አገር ተጨዋቾችን ማስመዝገብ የሚችል መሆኑን በመግለጽ ማሻሻያውን ይፋ አድርጓል፡፡