Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምለፖል ካጋሜ የሥልጣን ማራዘሚያ ሕገ መንግሥቱ ሊሻሻል ነው

ለፖል ካጋሜ የሥልጣን ማራዘሚያ ሕገ መንግሥቱ ሊሻሻል ነው

ቀን:

‹‹የአፍሪካ መሪዎች ለምን በሥልጣን ረዥም ጊዜ መቆየት እንደሚፈልጉ አይገባኝም፡፡ በተለይ ብዙ ገንዘብ እያላቸው … አንዳንዶች ደግሞ በሥልጣን ለመቆየት ሲሉ በሥልጣን ዘመናቸው የሕግ ማሻሻያዎች ያደርጋሉ…›› የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ይህን የተናገሩት ሐምሌ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ለአፍሪካ አገሮች መሪዎች፣ ለተወካዮቻቸውና ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ባደረጉት ንግግር ነበር፡፡ በንግግራቸውም ብሩንዲን እንደ ምሳሌ ጠቅሰው ነበር፡፡

በብሩንዲን እ.ኤ.አ. ከ2005 ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ጊዜያት በፕሬዚዳንትነት የመሩት ፒዬር ንኩሩንዚዛ ለሦስተኛ ጊዜ የመወዳደርም ሆነ የመምራት መብት አለኝ በማለታቸው፣ በአገሪቱ ሰላም ከደፈረሰ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በሩዋንዳ ደግሞ አካሄዱ ከዚህ ለየት ያለ ነው፡፡

አንድ ፕሬዚዳንታዊ የሥልጣን ዘመን በሰባት ዓመት በሚለካባት ሩዋንዳ፣ እ.ኤ.አ. ከ2003 ጀምሮ የፕሬዚዳንትነት ሥልጣኑን የያዙት ፖል ካጋሜ ለሦስተኛ ዘመን ይወዳደሩ አይወዳደሩ የሚለውን ለመወሰን ዕድሉ የተሰጠው ለሕዝቡ ነው፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እንደዘገቡትም ካጋሜ ሥልጣኔ ይራዘም ብለው አልጠየቁም፣ ወይም ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን እወዳደራለሁ ሲሉ አልተሰሙም፡፡

እ.ኤ.አ. በ2017 የሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸው የሚያበቃው ካጋሜ፣ ‹‹የእኔን በሥልጣን መቆየትና አለመቆየት የሚወስነው የሩዋንዳ ሕዝብ ነው፤›› ማለታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ የመወሰን ዕድሉን ለሕዝባቸው ሰጥተዋል፡፡

የሩዋንዳ የፓርላማ አባላትና ዜጐች የሥልጣን ዘመናቸው እ.ኤ.አ. በ2017 የሚያበቃውን ፕሬዚዳንታቸውን ሥልጣን ለማስቀጠል የሚያስችል የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ለማድረግ መምከር ከጀመሩ ሰንብተዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 101 ላይ የተቀመጠውና የአገሪቱን የፕሬዚዳንት ሥልጣን ዘመን በሁለት ጊዜ የሚወስነውን ወደ ሦስት አሻሽሎ፣ የፕሬዚዳንት ካጋሜ የሥልጣን ዘመን ለማስቀጠል በፓርላማውና በሕዝቡ እንቅስቃሴ መጀመሩ ለሩዋንዳ ትኩስ አጀንዳ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ1994 በሁቱና በቱትሲ ጎሳዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት 800 ሺሕ ያህል ዜጐቿን ያጣችው ሩዋንዳ፣ ሰላሟን አግኝታ ወደ ዕድገት ጐዳና እያመራች የምትገኘው በፖል ካጋሜ ጥንካሬ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ፖል ካጋሜ ለአብዛኞቹ ከዘር ጭፍጨፋ ለተረፉ ሩዋንዳውያን እንደ መሲህ የሚቆጠሩም ናቸው፡፡ በመሆኑም የፖል ካጋሜ ከሥልጣን መሰናበት በሩዋንዳ ዳግም የዘር ጭፍጨፋን ያመጣል የሚል ሥጋት በሕዝቡ ሰፍኗል፡፡ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ይህ ጥያቄ አይደለም፡፡ የፕሬዚዳንቱ ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸውን የሥልጣን ዘመን ጨርሰው መሰናበት አለባቸው ብለው ያምናሉ፡፡ ሥልጣን ለማራዘም ሲባል የሚደረግ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሪፈረንደምንም ይቃወማሉ፡፡

አብዛኛው ሕዝብ ግን ተስፋ በቆረጡበት ዘመን ትልቅ ተስፋ የሆኗቸውን ካጋሜ ከሥልጣን ማጣት አይፈልግም ነው የሚባለው፡፡ የአንድነትና የሰላም ተምሳሌትም ናቸው ይላሉ፡፡ ስለሆነም የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ተደርጐ ካጋሜ በሥልጣን የሚቆዩበት ጊዜ እንዲራዘም ይፈልጋሉ፡፡ የአገሪቱ ፓርላማም የሕገ መንግሥት ማሻሻያውን አስመልክቶ የቀረበለትን ሞሽን በአብላጫ ድምፅ ካፀደቀው ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ ግን የካጋሜን መንግሥት ለሚቀናቀነው ለአረንጓዴው ዴሞክራቲክ ፓርቲ የሚዋጥ አይደለም፡፡

የፓርለማ አባላት ድምፅ በሚስጥር ቢሰጡም ሕገ መንግሥቱ አይሻሻል ከሚሉበትና ሐሳብን በነፃነት ከሚገልጹበት ደረጃ አይደሉም ብሎም ፓርቲው ይሞግታል፡፡ ጉዳዩንም ፍርድ ቤት አቀርባለሁ ብሏል፡፡  

የፓርላማ አባላት ለካጋሜ ለሦስተኛ ጊዜ መመረጥ መንገድ የሚጠርገውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሞሽን ቢደግፉም፣ ከፖል ካጋሜም ሆነ ከፓርቲያቸው የሥልጣን እፈልጋለሁ ድምፅ አልተሰማም፡፡ ሆኖም በሕገ መንግሥቱ ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት የተሰጠው የሁለት ጊዜ የሥራ ዘመን ቢቀየር ምርጫቸው እንደሆነ ካጋሜ አሳውቀዋል፡፡ የፕሬዚዳንት የሥራ ዘመን እንዲራዘምም 3.8 ሚሊዮን ሕዝብ የፊርማ ድጋፉን መስጠቱ ተሰምቷል፡፡

የአገሪቱ ፓርላማ ቃል አቀባይ ዶናቲሊ ሙካባሊሶ የፓርላማ አባላት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳቡን መደገፋቸውን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ በቀጣይ ሕዝቡ ሪፈረንደም እነደሚያካሂድ ተናግረዋል፡፡

በብሩንዲ፣ በቡርኪና ፋሶ እንዲሁም በሴኔጋል ከፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ማራዘም ጋር ተያይዞ እንደተፈጠሩ ግጭቶች በሩዋንዳ ይነሳል የሚል ሥጋት ቢኖርም፣ 11.7 ሚሊዮን የሚጠጉት ሩዋንዳውያን ሰላምን መርጠዋል፡፡ ‹‹አገሪቱ የጠንካራ ተቋም እንጂ የጠንካራ ሰው ችግር የለባትም፤›› የሚሉ ተቃዋሚዎች ቢኖሩም ጥያቄያቸውን ወደ ፍርድ ቤት መውሰድን ነው የመረጡት፡፡ ያለፈውን ክፉ የዘር ጭፍጨፋ ታሪካቸውን መድገምም አይፈልጉም፡፡

የሕገ መንግሥቱን ማሻሻያ ሐሳብ ሕዝቡ በሪፈረንደም እንዲያፀድቀው ወይም እንዲጥለው ለማድረግ የፊርማ ማሰባሰብ ሥራ ተከናውኗል፡፡ የአገሪቱ ሕግ አውጪዎች በአገሪቱ ባደረጉት ብሔራዊ ፊርማ የማሰባሰስ ሥራም አሥር በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ ብቻ ሐሳቡን እንዳጣጣለው አሳውቀዋል፡፡

ከ3.7 ሚሊዮን ወይም ከ60 በመቶ በላይ መራጮችም አንቀጽ 101 ይሻሻል ሲሉ ፈርመዋል፡፡ ከዚህ በኋላ የቀረው ሪፈረንደም ማካሄድ ሲሆን፣ አንቀጹ መሻሻል የሚችለውም ሕዝቡ በሪፈረንደም ውሳኔ ከሰጠ በኋላ ይሆናል፡፡

ሕዝቡ አንድ ፕሬዚዳንት ለሦስት ተከታታይ ምርጫ መወዳደርና መምራት ይችላል የሚለውን ካፀደቀ፣ በሩዋንዳ አንድ ፕሬዚዳንት እስከ 21 ዓመት ሊመራ ይችላል ማለት ነው፡፡

ሥልጣን ለረዥም ዘመን መያዝ ለአፍሪካውያን መሪዎች የተለመደ ቢሆንም ሁሌም ብጥብጥ፣ ግጭትና ሞትን ሲያስከትል ይስተዋላል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዶ አሸንፈናል የሚሉ የአፍሪካ መሪዎችም ሁሌም ከትችትና ከወቀሳ አምልጠው አያውቁም፡፡ አብዛኞቹም በአምባገነንነታቸውና በጨቋኝነታቸው በሕዝባቸው የሚተቹ ናቸው፡፡ በአፍሪካ ምርጫ በተካሄደ ቁጥርም ሆነ ለምርጫ ዝግጅት ሲደረግ ትልቁ ፈተናም ምርጫው ግጭት ያስከትል ይሆን የሚለው ሥጋት ነው፡፡ በሩዋንዳ የሚካሄደው ሪፈረንደም ሩዋንዳን ዳግም ለግጭት ይዳርጋት ይሆን? ወይስ እንደተባለው በሰላም ይቀጠላል?

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...