ጥራታቸው፣ ደኅንነታቸውና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ እንዲሁም የተጭበረበሩና ከደረጃ በታች የሆኑ መድኃኒቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፉና ሥጋት እየሆኑ ነው፡፡ በተለይም በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ችግሩ ገዝፏል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት በተጭበረበሩና ከደረጃ በታች በሆኑ መድኃኒቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ለሦስት ቀናት ያዘጋጀው የሥልጠና ዐውደ ጥናት በተከፈተበት ሥነ ሥርዓት፣ የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ አማካሪ አቶ አብርሃም ገብረ ጊዮርጊስ እንዳብራሩት፣ የቁጥጥር ሥርዓታቸው ጠንካራ በሆኑባቸው ባደጉት አገሮች ችግሩ ዝቅ ሲል በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ችግሩ የከፋ ነው፡፡
በአገራችን ያለበት ደረጃ እስካሁን በጥናት እንዳልታወቀ፤ ነገር ግን ባለፈው ዓመት ከገበያ በተሰበሰቡ የተወሰኑ መድኃኒቶች ላይ በተካሄደ ጥናት 7.8 በመቶ ያህሉ ከደረጃ በታች መሆናቸው እንደተረጋገጠና ይህም ዝቅተኛ ቁጥር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የተጭበረበሩና ከደረጃ በታች የሆኑ መድኃኒቶች በሕጋዊ መንገድ ተመርተው ከሚሰራጩ መድኃኒቶች ጋር ተመሳስለው የሚመረቱ በመሆናቸው በላብራቶሪ ካልሆነ የመድኃኒቶቹን እውነተኛነት ለመለየት አይቻልም፡፡
እንደ አቶ አብርሃም፣ አንዳንዱ መድኃኒት ሌብል ወይም መግለጫ አለው፡፡ ሌብሉም አንድ ትልቅ ስም ያለው ፋብሪካ ሊሆን ይችላል፡፡ በውስጡ ግን ለፈውስ የሚውል መድኃኒት የለውም፡፡ ዱቄት፣ ወይም ስኳር እንዲሁም ባዕድ ነገር ይይዛል፡፡ በዚህም የተነሳ ብዙ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ ሕጻናት የሞቱበትና የተለያዩ የጤና ጉዳቶች የደረሱበት አጋጣሚም አለ፡፡
ሕገወጥ መድኃኒቶች ሕጋዊ መስመር ውስጥ ገብተው ሲሸጡ ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ የሚዘዋወሩት በኮንትሮባንድ ወይም በሕገወጥ መንገድ ነው፡፡ በተለይም ከዋና ዋና ከተሞች ወጣ ባሉ ሥፍራዎች ከሌሎች ሸቀጦች ጋር ለፀሐይ ተጋልጠው እንደሚቸረቸሩ አቶ አብርሃም ይናገራሉ፡፡
መድኃኒቶች ወደ አንድ አገር ሲገቡ ወይም ሲመረቱ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣውን መስፈርት አሟልተው መገኘት አለባቸው፡፡ መስፈርቱም ደህንነት፣ ፈዋሽነትና ጥራት ሲሆን ይህም የሚረጋገጠው በላባራቶርና በዶክመንት ነው፡፡ ይህንን መሥፈርት አሟልተው የሚወጡት መድኃኒቶች ደግሞ ሕጋዊ የማሰራጫ ሥርዓት ሊበጅላቸው ይገባል፡፡ ሥርዓቱም ቁጥጥር የተሞላበት መሆን አለበት፡፡ ይህ ሁኔታ ከተስተካከለ ከደረጃ በታች የሆኑ መድኃኒቶችን የማሰራጨት ዕድል ይቀንሳል፡፡
አቶ ቢቂላ ባይሳ የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግሩ የከፋ አለመሆኑ የተረጋገጠው በተለያዩ ጊዜያት ገበያ ላይ የዋሉ መድኃኒቶችን ሰብስቦ በላባራቶሪ የጥራት ፍተሻ በማካሄድ፣ በተለያዩ የጤና ተቋማት ከሚገኙ ባለሙያዎች በሚቀርብ ሪፖርትና ከኅብረተሰቡ በሚደርስ ጥቆማ፣ ከዓለም ጤና ድርጅትና ዩኤስፒ ከሚባል አጋር ድርጅትና በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አቅም በተደረገ ጥናት ነው፡፡
ውድና የሚፈለጉ መድኃኒቶችን መንግሥት በበቂ መጠን ማቅረቡ፣ የቁጥጥር ሥርዓቱ ጠንካራ መሆንና የኅብረተሰቡ አጋርነት ደረጃቸውን ያልጠበቁ መድኃኒቶች ገበያ ላይ በአነስተኛ መጠን እንዲገኙ ለማድረግ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም ተናግረዋል፡፡ በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል እና በሞያሌ አካባቢ ይታይ የነበረው የሕገወጥ መድኃኒቶች ምንጭም በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱን አመላክተዋል፡፡
በካፒታል ሆቴል ከነሐሴ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በሚካሄደው የሥልጠና ዐውደ ጥናት ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከግብጽ፣ ከሱዳን፣ ከኬንያ፣ ከዩጋንዳ፣ ከብሩንዲ፣ ከናይጄሪያ፣ ከማላዊ፣ ከታንዛንያ፣ ከዛምቢያ፣ ከዚምባቡዌ የተውጣጡ ፋርማሲስቶች እየተሳተፉ ነው፡፡