Wednesday, February 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአገራዊ አገልግሎት የተንፀባረቀበት የወርቅ ኢዮቤልዩ

አገራዊ አገልግሎት የተንፀባረቀበት የወርቅ ኢዮቤልዩ

ቀን:

ከሒልተን አዲስ ፊት ለፊት ያለው መንገድ በሠርገኞች ተጨናንቋል፡፡ የአፍሪካ ፓርክን ጥግ ይዘው ፎቶግራፍ የሚነሱ ጥንዶችም ብዙ ናቸው፡፡ ሙሽሮች በተናጠል እንዲሁም ከሚዜዎቻቸው ጋር ማስታወሻ ፎቶ ሲነሱ ይስተዋላል፡፡ በአካባቢው በሠርግ ወቅት ተመሳሳይ ትዕይንቶችን መመልከት አዲስ አይደለም፡፡ ቦታውን ፎቶግራፍ ለመነሳት የሚጠቀሙ ሙሽሮች በተለያየ ሁናቴ እየቆሙ እየተቀመጡም የሠርጋቸውን ዕለት ትውስታ በካሜራ ያስቀራሉ፡፡

ከጥቂት ቀናት በፊትም በተመሳሳይ መልኩ አካባቢው በሙሽሮችና በሠርገኞች ተከቦ ነበር፡፡ ሒልተን አዲስ ደግሞ የሠርግ ሥነ ሥርዓታቸውን የሚያከብሩ ጥንዶችን በማስተናገድ ተጠምዶ ነበር፡፡ ከሆቴሉ አዳራሾች በአንዱ የነበሩ ታዳሚዎች እርስ በእርሳቸው እየተጨዋወቱ ጥንዶችን ይጠባበቁ ነበር፡፡ ጥንዶቹን መንገድ ላይ ፎቶግራፍ ከሚነሱና በሆቴሉ አዳራሽ ከተገኙት ሙሽሮች ለየት የሚያደርጋቸው የጋብቻቸውን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ የሚያከብሩ መሆናቸው ነው፡፡ የጋብቻ የወርቅ ኢዮቤልዩአቸው በበርካታ አዳዲስ ሙሽሮች የተከበበ ይመስላል፡፡

ጥንዶቹ ዶ/ር አግደው ረዴና ወ/ሮ ቆንጂት ታደሰ ናቸው፡፡ ቤተ ዘመዶቻቸውና ወዳጆቻቸው ይጠብቋቸው ወደነበረበት የሆቴሉ አዳራሽ ሲዘልቁ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ በጥበብ ልብስ ያሸበረቁትን ጥንዶች 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ  ያሰናዱት ልጆቻቸው ነበሩ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዕለቱም ከቅርብ ወዳጆቻውና ከሚዜዎቻቸው መሀከል ጥቂቱ እንኳን ለዚህ አበቃችሁ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ለአምስት አሠርታት በትዳር መዝለቅ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠውና አዳዲስ ሙሽሮች ረዥም ዓመታትን በአብሮነት ካሳለፉ ጥንዶች ብዙ እንደሚማሩ የተናገሩ ነበሩ፡፡

ሐምሌ 24 ቀን 1957 ዓ.ም. በጋብቻ አንድ የሆኑት ጥንዶቹ አምስት ልጆች አፍርተዋል፡፡ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ጥንዶቹ ያሳለፉትን ሕይወት የሚያንፀባርቁ ፎቶግራፎችን አሰባስበው ‹‹የፍቅር ታሪክ›› በሚል ርእስ ለታዳሚዎች አጭር ቪዲዮ አሳይተዋል፡፡ ከጥንዶቹ የቅርብ ወዳጆች አንዱ የሆኑት አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ጥንዶቹ ከተዋወቁበት ጊዜ አንስቶ ልጅ እስካፈሩበት ጊዜ ያሳለፏቸውን ትውስታዎች ለታዳሚዎች አካፍለው ፈገግ አሰኝተዋል፡፡

‹‹እኔና ባለቤቴ በሥጋ እስከምንለያይ ድረስ አብረን ለመኖር ቃል የገባንበትን ቀን የማክበር ሐሳብን ያመጡት ልጆቻችን ናቸው፤›› የሚሉት ዶ/ር አግደው፣ ልጆቻቸው ዝግጅቱን በምስጢር እንዳዘጋጁትና ስለ ሥነ ሥርዓቱ ሲያውቁ በጣም እንደተደሰቱ ይናገራሉ፡፡ ልጆቻቸው የሳቸውንና የባለቤታቸውን ውለታ ለመመለስ ትልቅ ዝግጅት በማሰናዳታቸው እንዳደነቋቸውም ያክላሉ፡፡ ‹‹በሕይወታችን ያሉ ቤተ ዘመዶችን ብቻ ሳይሆን ያኔ ለሠርግ ያልጠራናቸው ስዎችም በዕለቱ ተገኝተዋል፤›› ይላሉ ኢዮቤልዮው ብዙዎችን ስለማሰባሰቡ ሲገልጹ፡፡

ዶ/ር አግደው የተወለዱት ምሥራቅ ጎጃም፣ ደጀን ውስጥ ነው፡፡ የአራት ዓመት ልጅ ሆነው ነበር ወደ አዲስ አበባ የመጡት፡፡ አባታቸው በጣልያን ሠራዊት እጅ ሰማዕት ከመሆናቸው በፊት አርበኛ ነበሩ፡፡ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ አዳሪ ትምህርት ቤት ገብተው መማር ጀመሩ፡፡ በወቅቱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ይጎበኙ እንደነበረ ያስታውሳሉ፡፡

አዳሪ ትምህርት ቤት የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ እንግሊዝ ወደሚገኘው ኖቲንግሀም ዩኒቨርሲቲ አመሩ፡፡ በሥነ ትምህርት (ኤጁኬሽን) ሥር ሳይኮሎጂ አጥንተው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡ ከባለቤታቸው ወ/ሮ ቆንጂት ጋር የተዋወቁትም በዛ ወቅት ነበር፡፡

በወቅቱ ውጪ አገር ሄደው ተምረው የመጡ ተማሪዎች እቴጌ ጣይቱ ሆቴል ያርፉ ነበር፡፡ መንግሥትም ለመቋቋሚያ 2,000 ብር ይሰጣቸዋል፡፡ ዶ/ር አግደው ቤት ከተከራዩ በኋላ ለመቋቋሚያ በተሰጣቸው ገንዘብ መኪና ገዙ፡፡ ወ/ሮ ቆንጂት የተከራዩበት ቤት ይሄዱ ነበር፡፡ ዶ/ር አግደውም በመኪናቸው ይሸኟቸው ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ተላምደውም ትዳር መሠረቱ፡፡

ከውጭ መጥተው ትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ውስጥ ከሠሩ በኋላ ወደ ኮተቤ መምህራን ማሠልጠኛ ተቋም ተዘዋወሩ፡፡ ከዛም የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሆኑ፡፡ በዘውዳዊው ሥርዓት ‹‹የትምህርትን ፍቱን መድኃኒትነት በሥራ መግለጽ ነው›› የሚል መሪ ቃል የነበረውና በርካታ አገራዊ አገልግሎት ያበረከተው፣‹‹የኢትዮጵያ ወጣቶች አገልግሎት›› (Ethiopian Youth Service) ከመሠረቱት ታዋቂ ባለሙያዎች  አንዱ ናቸው፡፡ በሁለገብ አገልግሎታቸው መካከልም  አሜሪካ ያለው ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ነፃ የትምህርት እድል በማግኘታቸው፣ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሠሩት በኤጁኬሽን ሳይኮሎጂ ሲሆን በዚያው ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ኦፍ ኤጁኬሽን ዶክትሬታቸውን አግኝተዋል፡፡  ወደ አገራቸው ሲመለሱም በትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር የፕላን ቺፍ ኤክስፐርት ሆነው የሚኒስትሩ አማካሪ በመሆን የሠሩ ሲሆን፤ ከዛም ወደ ከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን ተዘዋውረው በዋነኛነት በዩኒቨርሲቲዎች ማስፋፊያ ላይ ሠርተዋል፡፡ ዶ/ር አግደው በተለይ በትምህርት ዘርፍ ለዓመታት ሠርተዋል፡፡ የአምቦ፣ የጅማ፣ የዓለማያ፣ የጎንደር፣ የመቐለ፣ የድሬዳዋና ሌሎችም ዩኒቨርሲቲ ማስፋፊያዎች ላይ የነበራቸው አስተዋፅኦ ተጠቃሽ ነው፡፡ ዶክተሩ ጂቲዜድ ውስጥ የሠሩ ሲሆን፣አሁን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር ናቸው፡፡

ከ23 ዓመት በፊት የተቋቋመውና የአገሪቱን ጥንታዊ ቅርሶች ለመጠበቅና ከአደጋ ለመታደግ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ከመሥራች አባልነት ባሻገር ባሁን ጊዜ የቦርድ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው እየሠሩ ነው፡፡

ከ40 ዓመታት በላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመምህርነት ያገለገሉት የትምህርት ባለሙያው በትዳር ውስጥ ላሉ እንዲሁም ለወደፊት ለሚገቡ ወጣቶች ከተሞክሯቸው አካፍለውናል፡፡

እንደ እሳቸው ዓይነት የጋብቻ መታሰቢያ ክብረ በዓሎች በትዳር ውስጥ ላሉ እንዲሁም ላላገቡ ወጣቶች መማሪያ እንደሚሆኑ ይናገራሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ሰው በተለያየ አጋጣሚ ይገናኛልና ጋብቻ ሁሌ በስሌት አይሆንም፡፡ ጥንዶች ተግባብተውና አንድ ዓላማ ይዘውም ወደ ጋብቻ መግባት አለባቸው፡፡ እሳቸውና ባለቤታቸው ለአምስት አሠርታት በትዳር የዘለቁት ተመሳሳይ  ስሜት ይዘው በመጋባታቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ምን ያህል ዘመን በትዳር እንደሚኖሩ ሳያውቁ ቢጋቡም እንኳን መዋደዳቸው ዓመታትን እንዳዘለቃቸው ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ቤተሰብ የማኅበረሰብ መሠረት ነው፤ ትዳር ሁለት ሰዎች ተግባብተው ለራሳቸውም ለአገራቸውም የሚሠሩበት ነው፤›› የሚሉት ዶክተሩ፣ ጥንዶች ሁልጊዜም ኃላፊነት የሚሰማቸው መሆን እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ ቤተሰብ ከተመሠረተ በኋላ እርስ በእርስ መተሳሰብ ሲኖር ትዳር ይሰምራል ብለው ያምናሉ፡፡

በእርግጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ በትዳር የሚገጥሙ መሰናክሎች በርካታ እንደሆኑ ሳይናገሩ አላለፉም፡፡ አንዱ ጥንዶች በየፊናቸው ያላቸው ዓላማ ነው፡፡ የየግል ዓላማቸው አንዳቸው ለሌላቸው ማድረግ የሚጠበቅባቸውን እንዳያሟሉ መሰናክል ሊሆን ቢችልም እርስ በእርሳቸው ከተሳሰቡ መፍትሔ ይገኛል ይላሉ፡፡

ከ50 ዓመታትም በላይ በትዳር የኖሩ ጥንዶች እንዳሉ በማጣቀስ፣ ቤተሰብ ለመመሥረት የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ የትዳርን አስፈላጊነት በአግባቡ መገንዘብ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ሌላው አቅምን አውቆ በእቅድ መኖር ነው፡፡ የጥንዶች ሕይወት ያላቸውን አቅም ያገናዘበ መሆን አለበት የሚሉት ዶክተሩ፣ ‹‹ዋነኛው የትዳር መሠረት አብሮ መኖርን መማር ነው፤›› ይላሉ፡፡ በእሳቸው እምነት፣ ጥንዶች ወደ ትዳር ከገቡ በኋላ እንደቀደመ ሕይወታቸው ሳይሆን በኅብረት መኖር አለባቸው፡፡  ‹‹ከተጋቡ በኋላ እንደ ሕፃን መሆን አይቻልም፤ የሕይወት ዓላማቸውን ሰፋ አድርገው ማሰብ ይኖርባቸዋል፤›› ይላሉ፡፡  

ባልና ሚስት ከመፋቀር በተጨማሪ መተማመን ያስፈልጋቸዋል በማለት ሌላው የሚያነሱት ነጥብ፣ ማንኛውም ሰው ዕድሜው በሚፈቅደው መንገድ ሕይወቱን መምራት እንዳለበት ነው፡፡ በየሰው ዕድሜ እርከን ከሚከናወኑ አንዱ ጋብቻ ነው፡፡ በወጣትነት ቤተሰብ መመሥረት ተመራጭ ቢሆንም ዕድሜ ከገፋ በኋላ የማይገባበት ተደርጎ መወሰድ የለበትም ይላሉ፡፡ ወደ ትዳር ለመግባት ከሚቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች መሀከል ገንዘብና ቁሳቁስን የመሰሉቱ ተገቢ እንዳልሆኑ ያምናሉ፡፡ ‹‹ትዳር የሚመሠረተው ኑሮ ከተደላደለ በኋላ ብቻ ሳይሆን በችግር ጊዜም አጋር ያስፈልጋል፡፡ ችግርን አብሮ ለመወጣት ትዳር አስፈላጊ ነው፤›› ይላሉ፡፡

ከተሞክሯቸው በመነሳት ከባለቤታቸው ጋር አብዛኛውን ሕይወታቸውን መጋራታቸውን በደስታ ይገልጻሉ፡፡ ወደ ትዳር ከገቡ በኋላ እሳቸውም ባለቤታቸውም ሥራ መሥራታቸውን ይናገራሉ፡፡ ሁለተኛ ዲግሪያቸውንና ፒኤችዲያቸውን ያገኙት በትዳር ሳሉ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ስንጋባ ቤት አልነበረንም፤ የምንኖረው ተከራይተን ነበር፡፡ የእኔ ደሞዝ ብቻ ነበረን፡፡ ከዛ በኋላም እሷም ሥራ ያዘች፤ ቤታችንም ረድኤት ኖረው፤›› ይላሉ ሕይወታቸውን በጋራ ማሳለፋቸውን ሲገልጹ፡፡

የጥንዶችን ሕይወት ከሚያስተካከሉ መሀከል በሃይማኖታቸው አልያም በግላቸው የሚይዟቸውን የሕይወት መመሪያዎችን ይጠቅሳሉ፡፡ የጥንዶች ሕይወት በአንዳች መርሕ የማይመራ ከሆነ በማኅበረሰቡ ተቀባይነት ላያገኙ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ደስተኛ እንዳይሆኑ ሊያደርጋቸው ይችላል፤ ይላሉ፡፡

ትዳር ሁልጊዜም አልጋ በአልጋ እንዳልሆነና ጥንዶችም ብዙ ፈተና እንደሚገጥሟቸው እሙን ነው፡፡ ዶ/ር አግደው በትዳር ሕይወት ገጥሞኛል የሚሉት ፈተና በትምህርትና በሥራ ምክንያት ከቤተሰብ ርቆ መሄድን ነው፡፡ የኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ዲን ከሆኑ በኋላ ነበር ወደ ትዳር የገቡት፡፡ ከዛ በኋላ የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር በሆኑበት ወቅት አብዮቱ ይፈነዳል፡፡

በወቅቱ የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ ውጪ አገር ለመሄድ ዝግጅት እያደረጉ ነበር፡፡ ቢሆንም ‹‹ሚስትና ልጅ ኢምፔሪያሊስት አገር አይሄዱም›› ይባላሉ፡፡ ባለቤታቸውንና አራት ልጆቻቸውን ትቶ መሄድ አስቸጋሪ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ለሦስት ዓመታት በቆዩበት ወቅት ቀይ ሽብርን በማሰብ ለቤተሰባቸው ሕይወት ይሠጉ ነበር፡፡

ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ቦትስዋና ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎችና አካዴሚክ ጉዳዮች ዲን እንዲሆኑ ይጠየቃሉ፡፡ ተስማምተው ዕቃቸውን ወደ ቦትስዋና ቢልኩም ወደ ቦትስዋና የሚወስዳቸውን አውሮፕላን ለመሳፈር ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀራቸው ሆዳቸው መሸበር ጀመረ፡፡

ቤተሰባቸውን ጥለው ቦትስዋና መኖር እንደማይችሉ ወሰኑ፡፡ ከአሜሪካ ለንደን ከሄዱ በኋላ ወደ ደቡብ አፍሪካ ከዛም ቦትስዋና የሚወስዳቸውን አውሮፕላን ሆን ብለው አሳለፉ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የትኬት ቢሮ አቀኑና ትኬት ቆርጠው አዲስ አበባ መጡ፡፡

ከባለቤታቸው ጋር ካሳለፉት ዓመታት ከሚደሰቱባቸው ሁነቶች አንዱ ቤተሰቦቻቸው ተሰባስበው ማየት ነው፡፡ ችግርንም ደስታንም አንድ ላይ ማሳለፋቸው ያስደስታቸዋል፡፡ አሁን ልጆቻቸው ራሳቸውን ችለው ከቤተሰባቸው ቤት ቢወጡም በአንድ ላይ ተሰባስበው የሚያሳልፉትን ጊዜ በሐሴት ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹እኔና ባለቤቴ በስሜት ሳይሆን በምክንያታዊነት ተነጋግረን የምንወስናቸው ነገሮች ያስደስቱናል፤›› ይላሉ፡፡

በትዳር መሀከል ግጭቶች ሲከሰቱ አንዳንዴም ወደ ፍቺ ሲያመሩ ይታያል፡፡ በዶ/ር አግደው እይታ፣ ስለቤተሰብ አመራር ትምህርት ቢሰጥ ለውጥ ይመጣል፡፡ ‹‹በአብዛኛው የሴሰከድና ደቂቃዎች ጉዳይ ነው ሰውን የሚያጋጨው፤ ጥንዶች ድንበራቸውን አውቀው መቻቻል አለባቸው፣ እኛ 50ኛ ዓመታችንን ስናከብር በጣም ደስታ ተሰምቶናል፤ ሌሎችም ወጣቶች ቤተሰብ ካላቸው በአግባቡ እንዲመሩ፣ ከሌላቸው እንዲመሠርቱና በደስታ እንዲኖሩ እመኛለሁ፤›› ይላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የካቲት አብዮት – ጥያቄዎችሽ ዛሬም እየወዘወዙን ነው!

በበቀለ ሹሜ አጭር መግቢያ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከ1960ዎች ወጣቶች ርዝራዦች አንዱ...

የሰሞኑ የ“መኖሪያ ቤቶች” የጨረታ ሽያጭ ምን ዓይነት ሕጋዊ መሠረት አለው?   

በዳዊት ዮሐንስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አየር ላይ ከሚንሸረሸሩ ዜናዎች...

ሁለቱ ወጎች፡ ከሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! እስከ በዓሉ ቤርሙዳ

በተክለ ጻድቅ በላቸው ሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! ከሁለት ሦስት ዓመት...

ለትግራይ ክልል ድርቅ ተፈናቃዮች አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ...