Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ዳያስፖራ እሹሩሩ!

እነሆ ከወሎ ሠፈር ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። መንጋቱ ነው። በጋ የመሰለው የነሐሴ ደመና መጣሁ ቀረሁ የሚለውን ዝናብ እያጓጓ ቢሆንም፣ ፍጥረት ኩርምት አድርጎ ያሳደረውን እግሩን እያፍታታ ይጓዛል። ፈጣሪን የሚማፀኑ ዓይኖች ወደ ላይ ተተክለዋል፡፡ ያው የጎዳና ጫጫታ አለ። ጎልቶ የሚደመጠው ግን ገበሩ ነው። ጥልቅ የኩርፊያ ዝምታው። መኪናው ያጓራል፣ የትራፊክ ፖሊስ ፊሽካ ‘ፋውል’ እንደበዛበት የእግር ኳስ ጨዋታ በላይ በላይ ‘ሲር ሲር’ ይላል። ወያሎች ይጮሃሉ፣ ወራጆች ከወያላ ጋር በ10 በ15 ሳንቲም አንገት ላንገት ሲተናነቁ እሪታቸው ተቆርቋሪና ሃይ ባይ እንዳጡት የመካከለኛው ምሥራቅ ሕዝቦች ይመስላል። ምናልባት አንዳንዱ አጨንቋሪ በእነዚህ እሪታዎች ጎሬ በማስተዋል ቢሽሎከለክ፣ ከቁም ዘጠኝ ሞት ያው የማይቀረውን ሞት የሚመርጡት ለምን ዘለዓለም እንደሚወደሱ ይገባዋል። በተስፋ ቀን መግፋት ራስን ከማጥፋት በምን ይለያል ብሎ ከተከዘ ግን ታክሲ ሊያመልጠው ይችላል።

እየተራመዱ የሚያንቀላፉ የበዙት ለዚህ ሳይሆን ይቀራል? ስንት ዙር ሮጥን? ማን ነው ዙራችንን በኃላፊነት የሚቆጥረው? ከመቃብር በፊት ሩጫችንን ማጠናቀቅ አይቻልም? እውን ሕይወት ማስተንፈሻ ያልተበጀላት ድፍን ማንቆርቆሪያ ናት? ዕውን ዕጣችን ነው ተንተክትኮ ማለቅ?  . . . ማብቂያ በሌለው የሐሳብ ሕመም የተጎሳቆለ ጎዳና ላይ ጥርሳችንን ነክሰን እንንጎማለላለን። ለስሙ ነጋ ብለን ጠባ እያል አበባዬ ሆይን ከመዘመራችን፣ ‘ቡሔ ከወጣ የለም ክረምት’ ከመባባላችን በፊት ያደባ ዶፍ ይወርድብናል። ልክ ትናንት ዙፋን ተገነደሰ፣ ነፃ ወጣን ብለን ችቦ ስንለኳኮስ ጎጆውን እንዳነደድነው። አንድደን ስንጨርስ ዛሬ ለአዲስ ቤት ግንባታ የዘመናት ወግና ታሪክ በአጭር ጊዜ ለመገልበጥ ከጣሪያው እንጀምር ብለን እንደምጣደፈው። ዝንት ዓለም እውነት አርነት ታወጣን ዘንድ እንደመፅናት ከብርሃን ገጽ መጥፋት፣ ሙቀት ተባብረን ማዳፈን፣  አመድ ለአመድ መንከባለል የሚለቀን አንመስልም። መጥኔ ለዚህ መንገድ!

ጉዟችን ተጀምሯል። ጎልማሳው ሾፌራችን ጋቢ ለበስክ ተብሎ ዓይን በዝቶበታል። በተቃራኒው ወያላችን የተቀዳደች ሸሚዝ ደርቦ ሲንጎማለል መተሐራ የሚጓዝ የአውቶቡስ ረዳት ይመስላል። “አንተ እንዲያው ይህቺን ብጥቆ ለብሰህ አይበርድህም?” ይሉታል ከሾፌሩ ጀርባ ከጎኔ የተቀመጡ አዛውንት። “ብደርብስ ይሞቀኛል ብለው ነው? ዘንድሮ እኮ ብርዱ የበረታው በደራረቡት ነው፤” ብሎ ይመልሳል። ብልህና አስተዋይነት ጎልቶ የሚነበብባቸው እናት “ነገረኛ” ብለው ፈገግ አሉ። ጆሮዬ ከፊል እዚህ ከፊል ጋቢና ወደ ተቀመጡት ወጣቶች ነው። ሾፌሩ ቆየት ያለ ሙዚቃ ስብስቦቹን እያጫወተ መንገዱንም ተሳፋሪውንም የረሳ ይመስላል። “እንቅልፌን ደርበህ ተኛልኝ እባክህ!” ትላለች በዛወርቅ አስፋው። “እስኪ ትንሽ ድምፁን ከፍ አድርገው፤” ይላል አንደኛው። “ሰምቼው አላውቅም እባክህ፤” ሲል መልሶ “መስማት ሲፈጥርብን አይደል?” ይለዋል ከጎኑ የተቀመጠው።

የፊተኛው ግጥሙን አጣርቶ ሰምቶ ሲያበቃ ከት ብሎ እየሳቀ፣ “እንኳን እንቅልፍ ደርበን ሳንደርብም ቅዠቱን አልቻልነው፤” ብሎ ሳቁን ቀጠለ። “ምን ማለትህ ነው ዘፈኑ እኮ የፍቅር ነው። ተኙልኝ አላለች? ያለችው ተኛልኝ ነው። በሰው አደራ ምን አገባን እኛ?” ብሎ አጠገቡ ያለው ተሳፋሪ ነጀሰው። ነገር ቆስቋሹ ተሳፋሪ ንጀሳውን ችላ ያለ መስሎ፣ “ብቻ ሥልጣንና ፍቅር የማያሳብደው የለም። የሁለቱ አንድነት ታዲያ በእብደታው መሀል ደርብ የሚሉህ ነገር ብዛት ነው። ከእንቅልፍ እስከ ችጋር አምጥተው አንተ ላይ መቆለል ነው። አስተኝተው ማሸት ሲችሉበት ብሎ፤” አብሮ ማዜም ጀመረ። “በቃ ሰው በሰበብ አስባቡ በመንግሥት ካልተነጫነጨ አይሆንለትም?” ስትል ከኋላዬ አንዷን ደርባባ አዳምጣለሁ። “ከእንቅልፉ ሲቀሰቀስ የማይነጫነጭ ሰው አለ ብለሽ ነው?” የሚላት ደግሞ አጠገቧ ‘ፌስቡክ’ ላይ ‘ሎግ ኢን’ ብሎ ያቀረቀረ ተሳፋሪ ነው። የሱሳችን ብዛትና ተለዋዋጭነት አይገርምም ግን?

ወያላው ሒሳብ መቀበል ጀምሯል። አዛውንቷ የሙዚቃው ድምፅ እየረበሻቸው ነው። “ልጄ እባክህ ትንሽ ቀነስ አድርገው። ሲሆን በፆሙ መዝሙር በከፈትክ፤” አሉት አዋዝተው። ሾፌሩም መሪውን በአንድ እጁ ይዞ ጋቢውን እያጣፋ፣ “ሃይማኖትና ታክሲ ለየብቻ ነው ሲባል አልሰሙም፤” አለ ለጨዋታ። “ታዲያ ለምንድነው ሃይማኖተኞች ካልተፈናጠጥን እያሉ የሚያስቸግሩ?” ብሎ ‘ፌስቡክ’ ጎርጓሪው ጣልቃ ገባ። “መንገዱ ነዋ ተጠያቂው። ለስንት ሺሕ ዘመናት ሲሠራበት የኖረ ነገር ገና ለገና 21ኛው ክፍለ ዘመን የሥልጣኔን ሻማ ለኮሰ ተብሎ በአንዴ ይተዋል እንዴ?” ብላ መጨረሻ ወንበር የተቀመጠች ቁንድፍት ገባችበት። ከጀርባዬ ደርባቢት፣ “ሥልጣኔ ምንድነው? ምንድነው መሠልጠን?” እያለች ጎኗ የተቀመጠውን ስትጨቀጭቀው እየሰማሁ መጨረሻ ወንበር ደግሞ፣ “ኧረ እባካችሁ መንገድ መንገድ እያላችሁ በመንገድ የማይታማን መንግሥት አንጀት አትቁረጡ፤” ብሎ የሚመልስላትን ወጣት አዳምጣለሁ።

“እንደ ጋሪ ፈረስ ቀጥታ እያዩ ቀጥታ የሚመለሱ እኮ አላስቀምጠን አሉ፤” የሚባባሉት ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየሙት ጎልማሶች ናቸው። ጎልማሶቹ ከኅብረቱ ተነጥለው ብቻቸውን ዘልቀዋል። “መቼ ለት ፆም መያዣ ተብሎ አይተሃል የሆነውን?” ሲል አንደኛው፣ “አብረን አልነበርን? መጠጡ፣ ስካሩ፣ ድሪያው፣ ዳንኪራው፣ ሙዚቃው ሲቀልጥ ያመሸን ቀን? ነገር ግን ሰበብ አግኝተን መብላቱን እንብላ። ለመጠጥ፣ ለድሪያና ለዳንኪራ ግን ቀን ጠፍቶ ነው ሃይማኖታዊ በዓላት፣ ፆም መያዣና መፍቻ ቀናት የሚመረጡት?” ይላል የወዲያኛው። “ምን ታደርገዋለህ? ውርደት ክብር የሆነበት ቀን መጣ። አባቶቻችን ስምንተኛው ሺሕ የሚሉህ ይኼን ነው እኮ!” ብሎ አንደኛው በረጂሙ ተነፈሰ። ተሳፋሪው በቅፅበት በጭውውት ጠኔ ተመታ። የታሰረ አንጀቱ ሳይፈታ ደግሞ ሌላ የቤት ሥራ፣ ሌላ እንቆቅልሽ መፍታት ያዘ። ይዘን መልቀቅ ባይቀናን ይኼኔ ስንት መንገድ አጥርተን መጥተናል?!

ጉዟችን ቀጥሏል። ጎልማሶቹ ወደ ግል ጨዋታቸው ዞረዋል። “አንተ ባለፈው ያን ጉዳይህን ጨረስክ ወይስ እስካሁን እያመላለሱህ ነው?” ይጠይቃል አንደኛው። “ኧረ ተወኝ። ሳምንት ሲቀጥሩኝ፣ ወር ስመላለስ ቆይቼ፣ ይኼው አሁን ደግሞ የዛሬ ሁለት ሳምንት ያልቃል ብለውኝ ተቀምጫለሁ፤” ይመልሳል በብስጭት። “አይ ቢሮክራሲና የባለጉዳይ አበሳ፤” አለች ሳታስበው ከኋላቸው የተቀመጠች እንስት። “ቢሮክራሲ ብቻውን ቢሆን እስካሁን በመልካም አስተዳደር እጦት የምንሰቃይ ይመስልሻል? አይ ሞኝት። ዋናው ቢሮክራሲ እኮ የሚያስተናግዱሽ ሰዎች ቀናነት ማጣት፣ ለሥራ ያላቸው የተነሳሽነት ስሜት መቀዛቀዝ፣ የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው ስለሚበዙ ጭምር እኮ ነው፤” አለና መስኮቱ ጥግ የተቀመጠ ወጣት ተሳፋሪ ቀጠለ።

“ለምሳሌ ባለፈው ሰሞን አንድ ስም አይጠሬ መሥሪያ ቤት ለሆነ ጉዳይ ሄጄ አንዱ ቁም ስቅሌን አሳየኝ። እዛ ቢሮ ግባ ይለኛል። ስገባ የለም እዚህ አይደለም እዚያ ነው ስባል፣ ብቻ ምን አለፋችሁ እሄዳለሁ ቀኑ ይመሻል። ማልጄ እሄዳለሁ ሲመሽ እመለሳለሁ። ሲመረኝ፣ መቼም ሲመረን ሁላችን አለን ቀን አይደል? ሄድኩና አንዱ ላይ ስጮህ እየሳቀ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ‘አንተ ማን ስለሆንክ ነው እኔ ተቀምጨ አንተ ቆመህ አዘኸኝ የማስተናግድህ? ገና እንደመጣህ እዚህ ተቀምጬ ስታየኝ ዝቅ እንዳደረግከኝ ገብቶኛል’ አለኝ። ይታያችሁ እስኪ። ‘ተቀምጨ፣ አንተ ቆመህ ቁልቁል እያየኸኝ ጉዳይህ እንዴት ቶሎ ሊያልቅ ትፈልጋለህ?’ ብሎ ነገር አለ?” ብሎ ገጠመኙን ሲነግረን ፈጠራ እንጂ እውነት ያጋጠመው አልመስለን ብሎ እርስ በርስ ተያየን። በመፋጠጥ የአፈጻጸምና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የምንቀርፍ ይመስል። ጉድ አሉ የባሰባቸው!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ወያላው መልሳችንን እያቀበለ ከሙዚቃው እኩል ያቀነቅናል። በመልካም አስተዳደርና ችግሮች ዙሪያ ባለጉዳዩች ገጠመኞቻቸውን እያወሩ ትውውቁ ሰፍቷል። ይኼን ጊዜ ታዲያ ደርባቢት፣ “እኛስ እኛ ነን። ግን መንግሥት እንዴት ነው ስንት የቀና የሠለጠነ አገር የኖሩ ዳያስፖራዎችን ‘ኑ!’ እያለ ድግስ የሚደግሰው? ቋንጣ ሳያደርቁ የሸኙትን ዘመድ ቢያንስ መደብ አበጃጅቶ መቀበል አይገባም?” ብላ አቧራውን አጨሰችው። “መምጣቱን ይምጡ። እነሱስ ማን አላቸው? ወገን ናቸው። የሰው አገር ኑሮ አይሞላ። ግን ስንት አለ ደግሞ በአገሩ ያልሞላለት። ስንት ሥራ አጥ፣ ልጅነታቸውን በቅጡ ሳያዩ ጎዳና የወደቁም አሉ። የሚብሰውን ማየት የባሰ እንዳይመጣ ያደርጋል በሚለው እንያዘውና እንኳን ደህና መጣችሁ ብለን ዳያስፖራ ወገኖቻችንን መቀበል ነው፤” አሉ አዛውንቷ።

“መቼስ እርስዎ እናት ስለሆኑ ነው እማማ። ግን እንዲያው ሲያስቡት ድግስ መደገስ ምን ያስፈልጋል? ስንቱ እዚህ አገሩ ወገኑ መሀል ከበሽታው ብሶ ሐኪም እየገደለው፣ በመድኃኒት እጥረትና እጦት ያለ ዕድሜው እየተቀጨ፣ መደገስ ‘ከልጅ ልጅ ቢያዳሉ ዓመትም አይቆዩ’ ብሎ አያስተርትም?” አንደኛው ጎልማሳ አዛውንቷን ጠየቃቸው። “ምን ታደርገዋለህ? አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት ይሰማል ብለህ ነው? ይልቅ አሁን ‘ፌስቡክ’ ላይ ያየኋትን ‘ጆክ’ ልንገራችሁ። አባት ልጁን ይጠይቃል። ‘ወደፊት ስታድግ ምን መሆን ትፈልጋለህ?’ ሲለው ልጁ ምን ቢል ጥሩ ነው?” ብሎ ሳይጨርስ ተሳፋሪው ከአፉ ነጥቆ “ዳያስፖራ?!” አለና አውካካ። ‘ፌስቡክ’ ጎርጓሪው ያልተጠላለፈ እንደሌለ ሲታየው ‘ሎግ አውት’ አለ መሰል ዝም አለ። ወያላው “መጨረሻ” ብሎ በሩን ሲከፍተው አዛውንቷ ወደኔ ዞረው “የት እንደበቅ? ወሬ ሰለቸን እኮ!” ብለውኝ ወረዱ። እውነታቸውን እኮ ነው። ግን መደበቅ የሚቻለው እኮ መደበቂያ ሲገኝ ነው፡፡ ‘ግመል ሰርቆ አጎንብሶ’ እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ “የሆነስ ሆነና ዳያስፖራዎቻችን እንዴት ሰንብተዋል?” አለ አንዱ ተሳፋሪ ከአጠገቤ ሆኖ እየተራመደ፡፡ አዛውንቷ ሳቅ ብለው እያዩት፣ “ዳያስፖራማ እሽሩሩ በዝቶበት እየተሞላቀቀ ነው…” እያሉ ሲያሾምሩ በቁማችን በሳቅ ፈረስን፡፡ እኛም ‘እሹሩሩ’ እያልን ቀሪውን ጉዞአችንን ቀጠልን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት