Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ሥዕልን ያን ያህል የተገነዘበ ማኅበረሰብ አለን ለማለት ያስቸግራል››

ሠዓሊት ስናፍቅሽ ዘለቀ፣ የሴት ሠዓልያን ማኅበር ሊቀመንበር

የሴት ሠዓልያን ማኅበር የተመሠረተው በ2004 ዓ.ም. ሲሆን፣ ከዚያ ቀደም ‹‹ፍሬንድሺፕ ኦፍ ውሜን አርቲስትስ›› በሚል መጠሪያ ለዓመታት ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ ማኅበሩ እንደ አዲስ ከተቋቋመ በኋላ ዋነኛ ትኩረቱን በሴት ሠዓልያን ላይ በማድረግ በሥነ ጥበብ ዘርፍ የተለያዩ ክንዋኔዎችን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ስለማኅበሩ እንቅስቃሴ የማኅበሩ ሊቀ መንበር ሠዓሊት ወ/ሮ ስናፍቅሽ ዘለቀን ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡‑ የሴት ሠዓልያን ማኅበር የተመሠረተበት ዓላማ ምን ነበር?

ወ/ሮ ስናፍቅሽ፡‑ የሴት ሠዓልያን ማኅበር በጣም ብዙ ዓላማ አለው፡፡ ሴት ሠዓሊዎች ተበረታትተው እንዲሠሩ ማድረግ አንዱ ነው፡፡ በተለያየ ቦታ ላይ ሴቶች በእርግጠኝነት ይህን ሥራ ለተመልካች አቀርባለሁ የሚል ስሜት እንዲኖራቸው ማድረግና ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር አብሮ መሥራትም ይጠቀሳሉ፡፡ በተጨማሪ ሴቶች በተለያየ ጊዜ ከወንድ የተለየ ጉዳት ያጋጥማቸዋል፡፡ ያንን ስሜታቸውን ትተው ወደ ሥራቸው እንዲያተኩሩ ማድረግ ይገኝበታል፡፡ የአገራችንን ባህልና እሴት በሴቶች የማሳወቅ ዓላማ አለን፡፡ በአገር ውስጥም ይሁን ከአገር ውጪ ዐውደ ርዕዮች እናሳያለን፡፡ ይህን ስናደርግ የአገራችንን ባህል፣ እሴትና ቋንቋ ማስተዋወቅ ትልቁና ዋነኛው ዓላማችን ነው፡፡ ከሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ወይም ሌላ ማዕከል የሚመረቁ ሴቶች በአንድነት በሚሆኑበት ጊዜ የራሳቸውን ስሜት ነፃ ሆነው ይነጋገራሉ፡፡ ይህ አጋጣሚ ትልቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡‑ ማኅበሩ በ2004 ዓ.ም. እንደ አዲስ ከተቋቋመ በኋላ ለአባላቱ ምን አገልግሎት እየሰጠ ነው?

ወ/ሮ ስናፍቅሽ፡‑ ዐውደ ርዕይ ማሳያ ቦታ ማግኘት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ከሠሩ በኋላ ሥዕላቸውን አጠራቅመው ወደ ዐውደ ርዕይ ለማምጣት የሚቸገሩ አሉ፡፡ ለምሳሌ አንዲት ሠዓሊት በዓመት ሁለት ወይም ሦስት ሥዕል ብትሠራ ያንን ከሌሎች ጋር በጋራ እንድታቀርብ አጋጣሚ መፍጠር ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ጠፍታ የነበረች ወይም ስሟ የማይታወቅ ሠዓሊት በዚህ አጋጣሚ በሥራዎቿ ከሕዝብ ጋር ግንኙነት ትፈጥራለች፡፡ ይኼኔ ማንነቷ ታውቆ እንዲህ እየሠራች ነው ያስብላል፡፡ በእኛ ማኅበር አባላት መካከል መነሳሳት ያልነበረበት ሁኔታ ነበር፡፡ ዐውደ ርዕይ በሚኖር ጊዜ ግን ሁሉም መሳተፍ አለበት፡፡ አልችልም የሚባል ነገር የለም፡፡ እርስ በርሳችን እንተጋገዛለን፡፡ እንዲህ ብታደርጊው፣ እኔ ያደረግኩት እንዲህ ነው እንባባላለን፡፡ ከዚያ ሁሉም ወደ ሥራ ይመጣል፡፡ ሲሥሉ ደግሞ በጣም ይሠራሉ፡፡ ከሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ከወጡ በኋላ የተወሰነ ድረስ ሄደው ይሠሩና ያቆማሉ፡፡ መጀመሪያ ላይ የኑሮ ጫና ይኖርና ይተውታል፡፡ በመረዳዳት እንዲሠሩ ይደረግና በጋራ ዐውደ ርዕይ እናደርጋለን፡፡ ኅብረተሰቡ መጥቶ አንድ ሠዓሊት ምን ዓይነት ደረጃ ላይ እንዳለች ካየ በኋላ ማንም አይገፋትም፡፡ የሴቶች የሚለው ነገር ትልቁ ጥቅሙ ይሄ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ አባላት ከአዲስ አበባ ወጥተን አንዳንድ ቦታዎችን እንጐበኛለን፡፡ ወጥተን በምናይበት ጊዜ መዝናናት ብቻ አይደለም፡፡ የሥነ ጥበብ ሰው ማየት አለበት፡፡ በተደጋጋሚ የምናየው የከተማ ሰው እንቅስቃሴ ድግግሞሽ ሊሆን ይችላል፡፡ ወጣ ስንል ግን አዳዲስ ነገሮችን ይዘን ነው የምንመለሰው፡፡ እየተዝናናንም ስለማኅበራችን የምንወያይበት ጊዜ አለ፡፡ ምን ሠራን በቀጣይስ ምን እናደርጋለን? የሚለውንም ሠርተን ነው የምንመለሰው፡፡ ይኼ የማኅበሩ ቆንጆ ጐን ነው፡፡ ማኅበሩ እንዲወደድም አድርጐታል፡፡

ሪፖርተር፡‑ አዳዲስ አባላትን የምትመለምሉት በምን መንገድ ነው?

ወ/ሮ ስናፍቅሽ፡‑ ሴት ሆና የማኅበሩን ሕግና ደንብ የምታሟላ ማንኛዋም ሠዓሊት አባል መሆን ትችላለች፡፡ በአማተርነት የሚሠሩ ልጆች አሉ፡፡ እነሱን አባል ማድረግ ሳይሆን ትምህርት የሚሰጥበት መንገድ አለ፡፡ እነሱ ሲመረቁ ወደ አባልነት ይመጣሉ፡፡ አባሎቻችን እንዲበዙ እንፈልጋለን፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ሳይሆን ሌሎችንም ማቀፍ እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡‑ ሥነ ጥበባዊ ክንውኖቻችሁን ከአዲስ አበባ ውጪ በማካሄድ ከከተማው ውጪ ያሉ ሠዓልያንን ለማሳተፍ ያደረጋችሁ እንቅስቃሴ አለ?

ወ/ሮ ስናፍቅሽ፡‑ ያ ሰፊ ነገር ይፈልጋል፡፡ ከከተማ ሲወጣ ሥዕሎች ተይዘው ነው፡፡ የትራንስፖርትና የምግብ ወጪ ደግሞ ከፍተኛ ነው፡፡ ለሥዕሎች ጥንቃቄም ያስፈልጋል፡፡ ማኅበራችን ያንን ማድረግ አይችልም፡፡ ለወደፊት ልናደርገው እንችላለን፡፡ እዚህ አዲስ አበባ ላይ ለምናደርገው እንቅስቃሴ ራሱ ቦታ ለማግኘት መሯሯጡ ቀላል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም የቤተሰብ ኃላፊ ነው፡፡ እያንዳንዳችን ሥራ ተከፋፍለን ተሯሩጠን ነው የምንሠራው፡፡ ተቀጣሪ የለንም፡፡ የሚደግፉን ተቋሞች ብናገኝ መልካም ነው፡፡ ከ2004 ዓ.ም. በፊት እንቅስቃሴ ቢኖርም ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ያለውን ነው ሰው በበለጠ የሚያዳምጠው፡፡ ለምሳሌ ሥራዎቻችንን ይዘን ወደ ቦንጋ ሄደን ነበር፡፡ ቦንጋ በአገራችን የመጀመሪያው ብሔራዊ የቡና ሙዚየም አለ፡፡ እዛ ዐውደ ርዕይ አድርገናል፡፡ ቦንጋ ከመሄዳችን በፊት 2006 ዓ.ም. ላይ በብሔራዊ ሙዚየም ዐውደ ርዕይ አሳይተን ነበር፡፡ ያን ያደረግንበት ምክንያት እኔ የቦንጋውን ሙዚየም ልጐበኝ ሄጄ ነበር፡፡ የሙዚየሞች ቀን ሲከበር ሁኔታውን ካየሁ በኋላ ስለሁኔታው ለአባላቱ ተናገርኩ፡፡ ከሥራዎቻችን 50 በመቶ ሽያጩን ለሙዚየሙ ለማድረግም ተስማማን፡፡ ርእሱ ቡና ላይ ነበር፡፡ ብሔራዊ ሙዚየም ከታየ በኋላ ለብሔራዊ የቡና ሙዚየሙ ምርቃት ወደ ቦንጋ ሄደ፡፡ ዐውደ ርዕዩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ተገኝተው ነበር፡፡ በዐውደ ርዕዩ ስለነበሩት ሥራዎቻችን አስረድቻቸዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡‑ ማኅበሩ በተሳተፈበት ዓመታዊው የሥነ ጥበብ ፌስቲቫል ላይ ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሥዕል መምህራን የሰጣችሁን ሥልጠና ምን ይመስል ነበር?

ወ/ሮ ስናፍቅሽ፡‑ ‹‹ጥበብ ለሁሉም›› ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር የተዘጋጀ ትልቅ ፌስቲቫል ነበር፡፡ 2006 ዓ.ም. ላይ የመጀመሪያው ሲቀርብ ብሔራዊ ቴአትር ጋለሪ የራሳችንን ሥራዎች አሳይተን ነበር፡፡ የመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ ሸራ ዘርግተን ማንኛውም በዛ መንገድ የሚያልፍ ሰው ሥዕል እንዲሥል አደረግን፡፡ ብሩሽና ቀለም ነክቶ የማያውቅ ሰው ሁሉ ሲሠራ በጣም ደስ ይል ነበር፡፡ ዐውደ ርዕዩን የዘጋነው ለምን አይቀጥልም እየተባልን ነበር፡፡ 2007 ዓ.ም. ላይ መምህራንን ለማሠልጠን አሰብን፡፡ መሠረታዊ የሆኑትን መምህራን ካሠለጠንን ተማሪዎችን አገኘን ማለት ነው፡፡ ተማሪዎችን አገኘን ማለት ደግሞ ትውልዱን አገኘን ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ቀኑ አጭር ነበር፡፡ መጀመሪያ መጥሪያ አዘጋጅተን ለየትምህርት ቤቱ በተንን፡፡ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ከአንድ በላይ መምህር መላክ ቢፈልጉም ያለን አቅም ከየትምህርት ቤቱ አንድ አንድ መምህር የማሠልጠን ነበር፡፡ ወቅቱ ሰኔ ወር ላይ ነበር፡፡ ስለጉዳዩ ባለመገንዘብ ወይም የፈተና ጊዜ ስለነበረ ሊሆን ይችላል አንዳንድ ትምህርት ቤቶች መምህር አላኩም፡፡ የመጡትን መምህራን ለስድስት ቀን አሠለጠንን፡፡ ሥልጠናው በጣም ስኬታማ ሆኖ ነው የተጠናቀቀው፡፡ መምህራን ተማሪዎቻቸውን ሊያስተምሩ የሚችሉትን ያህል አሠልጥነናል፡፡ ሥዕል ምንድነው? ሥዕል ለምን እንሠራለን? ከሚለው መሠረታዊ ነገር ነው ሥልጠናው የተጀመረው፡፡ ሁሉም የየራሱን ሐሳብ በሻይ ሰዓት ጭምር ይሰነዝር ነበር፡፡ በቆየንባቸው ቀናት ከመምህራኑ ጋር ተቀራርበን እንደ እህትና ወንድም ሆነን ነበር፡፡ ካለው ሁኔታ አኳያ ተቋረጠ እንጂ እንዲቆምም አልፈለጉም ነበር፡፡ ከእያንዳንዳቸው ሥራዎችን መርጠን ወደእኛ አስቀርተናል፡፡ የተቀረውን ሌላ ጊዜም ጥናት እንዲያደርጉበት ለራሳቸው ወስደዋል፡፡ ከድሮዊንግ፣ ከመለጠፍ፣ ከቀለም ጥናትና ከሌሎችም መርጠን እኛ ጋ የቀረውን ሰዎች እንዲመለከቱት አድርገናል፡፡ ይኼ ነገር ኅብረተሰባችን ለሥዕል ያለውን አመለካከት ያሰፋል ብዬ አስባለሁ፡፡ እኔ እንደምረዳው ሥዕልን ያን ያህል የተገነዘበ ማኅበረሰብ አለን ለማለት ያስቸግራል፡፡ ስለጥበቡ ከማንበብና ከማየት ተነስቶ ብዙ የሚያውቅ አለ፡፡ አንዳንዴ በሌላ ሙያ ዘርፍ በጣም የተማሩ ግለሰቦች ሥዕል ምን ያደርጋል ሊሉም ይችላሉ፡፡ ሥዕል ምንድነው? ለምንስ ይሠራል ተብሎ ቢጠየቅ የሚመልሰው ጥቂት ሰው ነው፡፡ በአገራችን ሥዕል እንደ ጊዜ ማሳለፊያ ይታያል፡፡ በትምህርት ቤት ራሱ ለተማሪዎች የሚመደበው መምህር በጣም ደካማ የሚባል ነው፡፡ ትምህርቱ ግን በጣም ከባድ ነው፡፡ ሥዕል የአእምሮም የጉልበትም ሥራ ነው፡፡ ወደ ሥልጠናው ከመጡት መካከልም ያለሙያቸው ሥዕል አስተምሩ ተብሎ የተሰጣቸው ይገኙበታል፡፡ እዚህ ጥበብ ላይ ገና ያልታየ ብዙ ነገር አለ፡፡ እንዲታይ ማድረግ ያለብን እኛ ባለሙያዎች ነን ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡‑ በሥነ ጥበቡ ካሉ የሙያ ማኅበራት መካከል የሠዓልያንና ቀራጽያን ማኅበር ይጠቀሳል፡፡ የሴት ሠዓልያን ማኅበር ከሌሎች ማኅበራት በተለየ ሴቶችን የሚያበረታታው በምን መንገድ ነው?

ወ/ሮ ስናፍቅሽ፡‑ ሴት ሠዓልያንን የምናበረታታው ወደኛ ሲመጡ ነው፡፡ እኛ ወደነሱ መሄድ አንችልም፡፡ ዐውደ ርዕያችን ላይና ሌሎችም ዝግጅቶች ላይ ሴት ሠዓልያን ወደኛ እንዲመጡ ሁልጊዜ እናስባለን፡፡ የሚመጡም የሚቀሩም አሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ከመሥፈርቱ የማያሟሉት ነገር አለ፡፡ መጥተው ምክር የሚጠይቁም አሉ፡፡ የምንረዳዳው ሙያዊ በሆነ ነገር ነው፡፡ የሠዓልያንና ቀራጽያን ማኅበር የራሱ ነገር አለው፡፡ የእኛ ማኅበርም እንደዛው የራሱ ነገር አለው፡፡ ሙያው ግን አንድ ያደርገናል፡፡ እኛ በምንሠራበት ጊዜ እንደ እህትማማች መሆናችን ስለችግሮቻችንም ለመነጋገር ያስችለናል፡፡ በሩቁ ቢሆን ስለችግር መነጋገር አይቻልም፡፡ በስሜት የመመሳሰልም ነገር አለ፡፡ እኛ ሴቶችን የምናግዛቸው አንድም ሥራቸውን በርትተው እንዲሠሩ ነው፡፡ በርትተው ከሠሩ እንደማንኛውም ሰው አልፈው መሄድ ይችላሉ፡፡ በቁሳቁሶችም እርስ በርስ እንደጋገፋለን፡፡ የማኅበሩ ሕግና ደንብ ሆኖ ሳይሆን በየግላችን እንደጋገፋለን፡፡ አንድ መርሐ ግብር ስናዘጋጅ ሁላችንም እንነጋገርበታለን፡፡ ሥራ አመራር ብቻ ቢነጋገርበት ሊጠብ ይችላል፡፡ ስንነጋገር አዲስ ሐሳብም ይመጣል፡፡ እንዲህ እንድንሆን ያደረገው የአባላቱ ቁጥር ማነስ ሊሆንም ይችላል፡፡ 400 ወይም 500 በሚገባበት ጊዜ የሚሆነው አይታወቅም፡፡ ሌላ መንገድ እንፈጥር ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡‑ ሴት ሠዓልያን ከሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ከወጡ በኋላ በሙያው ብዙ ፈተናዎች ሲገጥሟቸው ይስተዋላል፡፡ ከተሞክሮዎ እንዴት መውጣት ይቻላል ብለው ያስባሉ?

ወ/ሮ ስናፍቅሽ፡‑ ጉዳዩን እንደ ሴት ሠዓሊ ስመለከተው ከባድ ነው፡፡ ቢሆንም ከባድ ነው ተብሎ መታለፍ የለበትም፡፡ እንደኔ በትግል የሚታለፍ ሕይወት ይጣፍጣል፡፡ በእንቅፋቶች ተደናቅፎ መቅረት ሳይሆን ተነስቶ መራመድ የግድ ነው፡፡ ካለፈው ስህተት መማርም ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች ባለማወቅ ለሴት የሚሰጡት የተሳሳተ ግምት አለ፡፡ ባለማወቅ በመሆኑ ይህን አልፎ ወደፊት መራመድ ያስፈልጋል፡፡ ሴት ልጅ የቤተሰብ ኃላፊ ከሆነች እንደ እናትም ብዙ ኃላፊነት አለባት፡፡ የልጆቿን ስሜት ማዳመጥ አለባት፡፡ አባት አያዳምጥም ማለት ሳይሆን እናት በተፈጥሮ የተሰጣት ነገር አለ፡፡ ይህ ደግሞ ጊዜን ይሻማል፡፡ አርቲስቷ ቤተሰብ ከመመሥረቷ በፊት ይኼን ማወቅ አለባት፡፡ ካወቀችው እንዴት እንደሚታለፍ ትዘጋጅበታለች፡፡ ልጅ ሲወለድ ብሩሽና ሸራ መቀመጥ የለበትም፡፡ ወንድ ሠዓሊም በቤተሰብ ውስጥ ብዙ ችግር ሊገጥመው ይችላል፡፡ ሥዕል ለምን ትሠራለህ ለእኔ ትኩረት ስጠኝ የምትል ሚስትም ትኖራለች፡፡ የእኛ ሙያ ደግሞ በጣም ትኩረት ይፈልጋል፡፡ አንዳንዴ ከባለቤቴ ጋር ማውራት ላልፈልግ እችላለሁ፡፡ ማውራት የምፈልገው ስለሥዕሌ ሲሆን እንዲረዳኝ ማድረግ አለብኝ፡፡ ይኼ በጓደኝነት ጊዜ ቢሆን ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በጓደኝነት ጊዜ የተቀረጸ ሰው በኋላ ላይ አዲስ አይሆንበትም፡፡ የግድ ሠዓሊ ይሁን ማለት ሳይሆን ፍላጐትን እንዲያውቅ ማድረግ ነው፡፡ ሠዓሊነት ማለት ኃላፊነት መውሰድ ነው፡፡ ሥዕል የማንነትን መገለጫ፣ ማስተማሪያም ነው፡፡ ስለዚህ ሠዓሊው ሠርቶ ለኅብረተሰቡ ማሳየት አለበት፡፡ ገንዘብ ማግኘት ብቻ አይደለም፡፡ ጥበቡ የሚሞትለት ነው፡፡ ሴት ልጅ ዓላማዋን ካወቀችና የሚያግዛት ካለ ወደፊት መውጣቱን ታውቅበታለች፡፡ ሁሉም ነገር ያለፈተና አይሆንምና መጋፈጥ አለብን፡፡ መጀመሪያ ለሥዕሉ የሚያስፈልጉ ነገሮች መሟላት አለባቸው፡፡ የግድ የምሠራበት የራሴ ስቱዲዮ ይኑረኝ ከተባለ ጊዜው ያልፋል፡፡ ይህን ስንጠየቅ ጥበቡን እየረሳንና እየራቅን እንሄዳለን፡፡ ጥበቡን እንደ መርሳትና መጣል ያህል ማንሳቱ ቀላል አይሆንም፡፡ አሁን ላይ ያሉ ወጣቶች የተሻለ ግንዛቤ ያላቸው ይመስለኛል፡፡ እኔ የገጠሙኝ ፈተናዎች ያህል በቀጣይ የሚመጡ ወጣት ሠዓልያን ላይገጥማቸው ይችላል፡፡ አሁን ያለነው ሠዓሊዎች የበለጠ ስንጣጣር ነገሩን እናቀለዋለን፡፡

ሪፖርተር፡‑ ማኅበሩ ምን ዓይነት ችግሮች ገጥመውታል?

ወ/ሮ ስናፍቅሽ፡‑ የማኅበራችን ቢሮ የሚገኘው በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ውስጥ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ የሚጠቀምበት የራሱ ክፍል ነው፡፡ እኛ ቢሮ አልነበረንም፡፡ የምንሰበሰበው ካፌ ውስጥ ነበር፡፡ ብሔራዊ ሙዚየም ግቢ ውስጥም እንሰበሰብ ነበር፡፡ ችግራችንን ዳይሬክተሩ አቶ ብርሃኑ ሽብሩ ተመልክቶ ይህን ክፍል አገኘን፡፡ አንድ ወቅት ላይ ክፍሉን ቢፈልጉት ቢሮ የለንም ማለት ነው፡፡ ድጋፍ ካገኘ በጣም ብዙ ነገር የሚሠራ ማኅበር ነው፡፡ ብዙ ሐሳብ እያለን የምንቆምበት ጊዜ አለ፡፡ የሴት ሠዓልያን ማኅበር ይህን አድርጓል ተብሎ ቢደገፍ ጥሩ ነው፡፡ ካፒታላችንም ማደግ ይችላል፡፡ አሁን ያለን ካፒታል ግን በጣም ዝቅ ያለ ነው፡፡ ማኅበሩ ኮምፒዩተር እንኳን የለውም፡፡ የራሳችን ዌብ ሳይት [ድረ ገጽ] የለንም፡፡ ካለብን ሸክም ጋር ሲደራረብ መስዋዕትነት የሚጠይቅ ነው፡፡ ቢሮ ያስፈልገናል፡፡ ዐውደ ርዕይ የምናቀርብበት አንድ ማዕከል ያስፈልገናል፡፡ ያንን እንደ ቢሮም እንደ ጋለሪም ልንገለገልበት እንችላለን፡፡ በአንድ ወቅት ጥያቄ ያቀረብን ቢሆንም ልናገኝ አልቻልንም፡፡ በቅርስነት የሚቀመጡ ቤቶች ቅርስነታቸው እንዳለ ሆኖ ማኅበሩ ኃላፊነቱን ወስዶ የዐውደ ርዕይ ቦታ ቢያደርጋቸው ሴቶች ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሠዓሊዎችም እንዲያሳዩ ማድረግ ይቻላል፡፡ ቦታው ስቱድዮ መሆንም ይችላል፡፡ ብዙ የሚጐድሉን ነገሮች አሉ፡፡ ባለመገናኘት እንጂ ሥራችንን ሊደግፉ የሚችሉ ብዙ ድርጅቶች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡‑ ማኅበሩ በመጪው ዓመት የሚያከናውናቸውን ዕቅድ እያወጣ ይገኛል፡፡ ዕቅዳችሁ ምን ምን ያካትታል?

ወ/ሮ ስናፍቅሽ፡‑ በ2007 ዓ.ም. በጊዜ ማጠርና በተለያዩ ምክንያቶች ያላከናወናቸውንና አዳዲስ ሐሳቦችን ጨምረን ዕቅድ አውጥተናል፡፡ የመንገድ ላይ የሥዕል ትርኢት ማቅረብ አንዱ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ በሚንቀሳቀስበት አካባቢ በቀላሉ ሥዕል እንዲያገኝ ለማድረግ አቅደናል፡፡ ማኅበሩ በስሙ ጋለሪ እንዲኖረው ማድረግ ሌላው ዕቅድ ነው፡፡ ጋለሪው ስቱድዮ የሚሆን ሲሆን፣ ሌሎችንም ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ ይኼ ለሥዕሎች ደኅንነትም ሲባል ነው፡፡ አሁን ዐውደ ርዕዮች ላይ የታዩ ሥዕሎችን የምናስቀምጥበት ቦታ ስለሌለን ወደየቤታችን እንወስዳቸዋለን፡፡ ‹‹ማርች 8 የሴቶች ቀን›› ማክበር ሌላው ዕቅድ ነው፡፡ ባለፈው ዓመትም ያከበርን ሲሆን፣ በቀጣይ ዓመት ለየት ባለ መልኩ የምናከብር ይሆናል፡፡ ሌላው ተጨማሪ አባላት እንዲኖሩን ማድረግ ነው፡፡ ሌላው ከተለያዩ ሀገሮች ጋር ሙያዊ ግንኙነት እንዲኖረን ማድረግ ነው፡፡ በኤምባሲዎች በኩል ሥራዎቻችንን መላክና እነሱም እንዲመጡ ማድረግ ማለት ነው፡፡ የአገራችን ታሪክ በሥነ ሥዕል ምን ይመስላል የሚለውን ማሳወቅ እንፈልጋለን፡፡ ኢትዮጵያ ቀድሞ የነበራት ገጽታ እንደዚህ አልነበረም፡፡ የሚወራው ስለረሃብ ነበር፡፡ አሁን ተመስገን የሚያሰኝ ነው፡፡ እኛ ሴት ሠዓሊዎች ያለውን ለውጥና ልማት ማሳየት እንፈልጋለን፡፡ ለእኛ ለሠዓሊዎች ብቻ ሳይሆን አገራዊ ለውጥም ያመጣል፡፡ በቀጣዩ ዓመት ፓናል ውይይቶች እናዘጋጃለን፡፡ የእርስ በርስ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ያስችላል፡፡ ትምህርታዊ ጉዞ በማድረግ አባላት አዳዲስ ነገር እንዲያውቁ ማድረግ ሌላው ዕቅድ ነው፡፡ የአገራችንን መልክዓ ምድርና የሕዝቦቿን አኗኗር ለማየት ይረዳል፡፡ ሁላችንም መሠረታችን ያለው ገጠር ነው፡፡ የዋሁ የገጠር ሰው አለባበሱ፣ መልክዓ ምድሩ ምን ይመስላል የሚለውን ይዘን ነው የምንመጣው፡፡ ከአባሎቻችን ጥንካሬ አንፃር ዕቅዶቻችን ስኬታማ እንደሚሆኑ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡‑ ማኅበሩ አሁን ካለበት ደረጃ የማስፋት ምናልባትም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የመክፈት ዕቅድ አላችሁ?

ወ/ሮ ስናፍቅሽ፡‑ አሁን የበጐ አድራጐትና ማኅበራት ኤጀንሲው ፈቃድ ሰጥቶናል፡፡ ማኅበሩን አስፍቶ የኢትዮጵያ የማድረግ ዕቅድ አለን፡፡ የኢትዮጵያ በሚባልበት ጊዜ ሁሉንም ያካትታል፡፡ በየክልሉ የራሳችን ቅርንጫፍ ይኖረናል ማለት ነው፡፡ ሴቶች የግድ ወደዚህ ይምጡ ማለት ሳይሆን እዛው ሆነው ተሰባስበው እንዲሠሩ ማድረግና መቆጣጠር ነው፡፡ ሁሉም ፕሮፌሽናል ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዱ አንዱን ተጠግቶ እንዲደጋገፍና ክንዳቸው እንዲጠነክር ማድረግ ነው፡፡ የበለጠ እንዲሠሩ ተሞክሮን ማካፈል ነው፡፡ ሙያው እዚህ አዲስ አበባ ብቻ እንዲቀር ላለማድረግም ነው፡፡ በየክልሉ ተወካዮች ያስፈልጉናል፡፡ 2008 ዓ.ም. ላይ ከበጐ አድራጐት ማኅበራት ጋር እንመካከርበታለን፡፡ ካልሆነ እንኳን በጀት መድቦ ወይ ከኪስም ቢሆን ወጪ አውጥቶ በየክልሉ ሄዶ ቅርንጫፍ መመሥረት አለበት የሚል ስሜት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡‑ ማኅበሩ ሠዓልያትን በማበረታታት እንዲሁም ኅብረተሰቡ ስለ ሥዕል ያለውን ግንዛቤ በማዳበር ረገድ ምን አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለው ያምናሉ?

ወ/ሮ ስናፍቅሽ፡‑ እናንተ እንደዚህ መሥራታችሁ እኔንም እንድጠነክር ያደርገኛል የሚሉ አስተያየቶችን እሰማለሁ፡፡ ዐውደ ርዕዮች ስናቀርብ ሰዎች እናገኛለን፡፡ ሰዎች ፍላጐታቸውን ይገልጹልናል፡፡ ወደእኛ እንዲመጡም አድራሻ እንለዋወጣለን፡፡ መኖራችንና የእኛ እንቅስቃሴዎች መደጋገም የሌሎችንም መምጣት ያጠናክራል፡፡ ሴት ሠዓሊዎች ያሉ የማይመስላቸውም አሉ፡፡ ይኼን ስናይ በጣም እንድንሠራ ያደርገናል፡፡ ከገጠር መጥቶ ደግሞ ስለእናንተ በሬዲዮ ሰምቼ ነበር፣ እንኳን አገኘኋችሁ የሚል አለ፡፡ ዐውደ ርዕይ መኖሩን አውቀው የሚመጡም አሉ፡፡ ማኅበሩን ብንተወው ብዙ የሚጠይቀን አለ፡፡ መተውም የለብንም፡፡ የሴት ሠዓልያን ማኅበር መጠናችን ይነስ እንጂ ዓላማችን በጣም ብዙ ነው፡፡ ሐሳብ እርስ በርስ እንለዋወጣለን፡፡ ለመተግበር ግን የገንዘብ አቅም ይጠይቃል፡፡ የእኛ መሥራት ኅብረተሰቡ ስለሥዕል ያለው ግንዛቤ ሰፊ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ የሴት ሠዓልያን ማኅበር ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሠዓልያንም እየሠሩ ነው፡፡ ዐውደ ርዕዮችም ያቀርባሉ፡፡ የሴት ሠዓልያን ማኅበር መኖሩ ጠንካራ መሆናችንንም ጭምር ነው የሚያሳየው፡፡    

                         

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የቆመው የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ፋውንዴሽን

የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት አባላት ለአገራቸው የሕይወት መስዋዕትን ለመክፈል የወደዱ፣ ለአገራቸው ክብር ዘብ የቆሙና ውለታን የዋሉ ናቸው፡፡ እነኚህ የአገር ጌጦች በአገሪቱ በተከሰተው የሥርዓት ለውጥ...

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...